የምስጥ ኩይሳ
ንድፍ አውጪ አለው?
የምስጥ ኩይሳ
▪ የምስጥ ኩይሳዎች ድንቅ የምህንድስና ውጤት እንደሆኑ የሚነገር ሲሆን እንዲህ የተባሉትም ያለ ምክንያት አይደለም። እነዚህ ከአፈርና ከምራቅ የተሠሩ አስደናቂ ሕንፃዎች እስከ 6 ሜትር ከፍታ ሊኖራቸው ይችላል። አርባ አምስት ሴንቲ ሜትር ውፍረት ሊኖረው የሚችለው ግድግዳ እንደ ሲሚንቶ እስኪጠነክር ድረስ በፀሐይ ይደርቃል። አንዳንድ ኩይሳዎች ቃል በቃል በአንድ ሌሊት ተሠርተው ያድራሉ።
በየቀኑ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ እንቁላሎችን መጣል የምትችለው ንግሥቲቷ ምስጥ የምትኖረው በኩይሳው ማዕከላዊ ክፍል ነው። ክንፍ የሌላቸውና ማየት የማይችሉት “ሠራተኛ ምስጦች” እንቁላሎቹን ተሸክመው ልዩ ወደሆኑ ክፍሎች ይወስዷቸዋል። እጮቹ በሚፈለፈሉበት ጊዜም ይንከባከቧቸዋል። ይሁንና ከኩይሳ አሠራር እጅግ አስደናቂ የሆነው አየር በውስጡ የሚዘዋወርበት መንገድ ሳይሆን አይቀርም።
የሚከተለውን እስቲ አስብ:- ከኩይሳው ውጪ ያለው የአየር ሁኔታ የሚለዋወጥ ቢሆንም በውስጡ የሚገኙት ተቀጣጥለው የተሠሩ በርካታ ክፍሎችና ክፍት ቦታዎች የማይለዋወጥ የሙቀት መጠን ይኖራቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በአፍሪካ ውስጥ በምትገኘው በዚምባብዌ ከኩይሳው ውጪ ያለው የሙቀት መጠን እጅግ ይለዋወጣል። በምሽት እስከ 2 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ፣ በቀን ደግሞ እስከ 38 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሊደርስ ይችላል። ሆኖም በኩይሳው ውስጥ ያለው የሙቀት መጠን ከ31 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ከፍ ወይም ዝቅ አይልም። ለምን?
በኩይሳው ግርጌ ላይ ያሉት ቀዳዳዎች ንጹሕ አየር ለማስገባትና የታመቀውን አየር ከላይ በኩል በሚገኙት ቀዳዳዎች በኩል ገፍቶ ለማስወጣት በሚያስችል ምቹ ቦታ ላይ የተቀመጡ ናቸው። ቀዝቃዛ አየር ከመሬት ሥር ባሉት ክፍሎች አማካኝነት ወደ ኩይሳው ከገባ በኋላ በመተላለፊያዎቹና በትንንሽ ክፍሎቹ ውስጥ ይዘዋወራል። ምስጦቹ ቀዳዳዎቹን በመክፈትና በመዝጋት ሙቀቱን እንደ አስፈላጊነቱ ይቆጣጠራሉ። ምስጦቹ ዋነኛ ምግባቸው የሆነውን ፈንገስ ለማሳደግ የማይለዋወጥ የሙቀት መጠን ያስፈልጋቸዋል።
የምስጥ ኩይሳ አሠራር እጅግ አስደናቂ ከመሆኑ የተነሳ በዚምባብዌ መሃንዲሶች ተመሳሳይ ዲዛይን በመጠቀም አንድ የመሥሪያ ቤት ሕንፃ ገንብተው ነበር። ሕንፃው ተስማሚ የአየር ሙቀት እንዲኖረው ለማድረግ የሚውለው የኃይል ፍጆታ በተለመደው መንገድ የተሠሩ ተመሳሳይ ሕንፃዎች ከሚጠቀሙት 10 በመቶ ብቻ ነው።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? ምስጦች በኩይሳው ውስጥ ያለውን የሙቀት መጠን የመቆጣጠር ችሎታ ያገኙት እንዲሁ በአጋጣሚ ነው? ወይስ ይህ ችሎታቸው ንድፍ አውጪ እንዳላቸው የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው?
[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
ከላይ:- Stockbyte/Getty Images; ከታች:- Scott Bauer/Agricultural Research Service, USDA