በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሳይቤሪያ ነብር ከመጥፋት ይተርፍ ይሆን?

የሳይቤሪያ ነብር ከመጥፋት ይተርፍ ይሆን?

የሳይቤሪያ ነብር ከመጥፋት ይተርፍ ይሆን?

በሩሲያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በሩሲያ ምሥራቃዊ ጫፍ፣ በአንድ ብሩሕ የክረምት ቀን ሄሊኮፕተር የሚያሳድደው አንድ ትልቅ ነብር በሚያንጸባርቀው በረዶ ላይ ይሮጣል። አነጣጣሪ ተኳሽ የሆነ ሰው ከሄሊኮፕተሩ ላይ ብቅ ሲል ነብሩ ዛፍ ላይ ዘሎ በመውጣት ሰውየውን ለመግጠም መዘጋጀቱን የሚጠቁም ድምፅ አሰማ። በዚህ ጊዜ ሰውየው ወደ ነብሩ ተኮሰ። ከዚያም ሄሊኮፕተሩ መሬት አረፈና በውስጡ የነበሩት ሰዎች ወደ ተመታው አውሬ በቀስታ ቀረቡ።

እነዚህ ሰዎች ሕገ ወጥ አዳኞች አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ እንስሳትን ማደንዘዣ በመውጋት ጥናት የሚያካሂዱ ተመራማሪዎች ነበሩ። ሰዎቹ የመጡት፣ ዝርያቸው ለመጥፋት ከተቃረቡ ብርቅዬ እንስሳት መካከል አንዱ የሆነውን የሳይቤሪያ ነብርን ለማጥናት ነው። *

እጅግ አስደናቂ ፍጡር

የሳይቤሪያ ነብሮች በአንድ ወቅት በኮሪያ፣ በሰሜናዊው ቻይና፣ በሞንጎሊያና በስተ ምዕራብ ሩሲያ ርቆ እስከሚገኘው የባይካል ሐይቅ ድረስ ባለው ቦታ ላይ ይኖሩ ነበር። ይሁንና ካለፈው መቶ ዘመን አንስቶ ቁጥራቸው እጅግ እያሽቆለቆለ መጥቷል። የመጨረሻው መሸሸጊያ ቦታቸው በሩሲያ ከቫላዳቮስታክ በስተ ሰሜን ጫፍ በጃፓን ባሕር ዳርቻ ላይ የሚገኘው የተራራ ሰንሰለት ነው።

ነብሮች በጠረናቸው እርስ በርስ በደንብ የሚተዋወቁ ሲሆን ይህ ደግሞ የመራቢያ ጊዜያቸው ሲደርስ ተባዕቶቹ እንስቶቹ ያሉበትን ቦታ ለማወቅ ይረዳቸዋል። ነብር የምትወልደው በአንድ ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት ግልገሎችን ነው። ግልገሎቹ ገና እንደተወለዱ ዓይናቸውን የማይገልጡ ሲሆን አርፈው መቀመጥ አይሆንላቸውም። የሳይቤሪያ ነብሮች ከድመት ግልገሎች በተለየ መልኩ ፈጽሞ አያንኮራፉም። በዚህ ፈንታ የማጉረምረም ድምፅ እያሰሙ ለአምስት ወይም ለስድስት ወራት የእናታቸውን ጡት ሲጠቡ ይቆዩና ከዚያ በኋላ ሥጋ መብላት ይጀምራሉ። መጀመሪያ ላይ ከእናታቸው ጋር ወደ አደን ቢሄዱም አንድ ዓመት ተኩል እስኪሆናቸው ድረስ ራሳቸውን ችለው ማደን አይችሉም። ነብሮች ዕድሜያቸው ሁለት ዓመት እስኪሞላ ድረስ ከእናታቸው ጋር ሊኖሩ ይችላሉ። ከዚያ በኋላ ግን ከእናታቸው ተለይተው በመሄድ የራሳቸውን የመኖሪያ ክልል ያበጃሉ።

በዱር ከሚኖሩት ከእነዚህ ነብሮች መካከል አንዳንዶቹ በጣም ግዙፍ ይሆናሉ። ተባዕቶቹ ነብሮች ክብደታቸው ከ270 ኪሎ ግራም፣ ርዝመታቸው ደግሞ ጅራታቸውን ጨምሮ ከሦስት ሜትር በላይ ሊደርስ ይችላል። ነብሮቹ ቀዝቃዛና በረዷማ ክረምቶችን በጥሩ ሁኔታ መቋቋም ይችላሉ። ሰውነታቸው ጥቅጥቅ ባለ ፀጉር የተሸፈነ ሲሆን ትልልቅ መዳፎቻቸውም በበረዶ ላይ ለመራመድ የሚያስችል የፀጉር ድብዳብ አላቸው።

የሳይቤሪያ ነብሮች፣ ብርቱካንማ ቀለም ያለው ቆዳቸው በጥቁር መሥመሮች ያጌጠ ነው። በእያንዳንዱ ነብር ላይ ያለው ጥቁር መሥመር ልክ እንደ ሰዎች የጣት አሻራ ፈጽሞ የተለያየ በመሆኑ አንዱን ነብር ከሌላው መለየት ይቻላል። ብዙውን ጊዜ ነብሩ ከደኑ ካልወጣ በስተቀር መልኩ ከአካባቢው ጋር ስለሚመሳሰል በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል። ሆኖም ነብሩ ከደኑ ከወጣ በረዶው በግልጽ እንዲታይ ያደርገዋል። ይህም የነብር ብቸኛ ጠላት ለሆነው ለሰው እይታ ያጋልጠዋል።

ለመጥፋት ተቃርቧል

የሳይቤሪያ ነብር በሕይወት ለመኖር እንደ አጋዘን፣ ኤልክ የተባለ ትልቅ የአጋዘን ዝርያና ከርከሮ ያሉ ትላልቅ እንስሳትን ማደን አለበት። ይሁን እንጂ በምሥራቃዊው ሳይቤሪያ ዱር ውስጥ የሚኖሩት እንደነዚህ ያሉት እንስሳት ቁጥር እየተመናመነ ነው። በ1,000 ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ላይ የሚኖሩት እንስሳት ለአራት ወይም ለአምስት ነብሮች ምግብ ከመሆን አያልፉም። ስለሆነም የሳይቤሪያ ነብሮች በዱር ውስጥ መኖራቸውን እንዲቀጥሉ ከተፈለገ በቂ የሆነ ክልል ሊኖራቸው ይገባል።

ሰፋፊ የሆኑትና ሰው የማይደርስባቸው የሳይቤሪያ ደኖች ለብዙ ዓመታት ለእነዚህ ድንቅዬ እንስሳት ተስማሚ መኖሪያ ሆነውላቸው ነበር። ለዚህ የድመት ዝርያ ብቸኛ ጠላት የሆኑት ሰዎች ወደ አካባቢው የሚሄዱት አልፎ አልፎ ነበር። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከውጭ አገር የመጡ ጣውላ አምራች ኩባንያዎች አብዛኛውን ደን መንጥረውታል።

ዛፎቹ እየተመናመኑ ሲሄዱ እንደ አጋዘን፣ ኤልክና ከርከሮ ያሉት እንስሶችም እየጠፉ ይሄዳሉ። ይህ ደግሞ የሳይቤሪያ ነብሮች ቁጥር እንዲመናመን ያደርጋል። የሩሲያ መንግሥት የእነዚህን እንስሳት ቁጥር ማሽቆልቆል ለመግታት ሲል ሲክአቴ አሊን ተብሎ የሚጠራውን የተፈጥሮ እንክብካቤ ተቋም የመሰሉ የዱር አራዊት ጥበቃ የሚያገኙባቸውን ሰፋፊ ቦታዎች ከልሏል። ይሁን እንጂ ነብሮቹ ከእነዚህ ክልሎች ሲወጡ፣ የስጦታ ዕቃዎችን ለሚሸጡ ሕገ ወጥ አዳኞች ራሳቸውን ያጋልጣሉ። የትንንሾቹን ግልገሎች ጨምሮ የነብር ጥርስ፣ ጥፍር፣ አጥንትና ቆዳ ከፍተኛ ዋጋ ያወጣል።

የሳይቤሪያ ነብሮችን ሕይወት መታደግ

የሳይቤሪያ ነብርን ለማዳን ትልቅ ጥረት እየተደረገ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎችም በዚህ ተግባር ላይ በግንባር ቀደምትነት እየተሳተፉ ይገኛሉ። በውጤቱም የሳይቤሪያ ነብሮች ቁጥር በመጠኑ ጨምሯል። በ2005 በተደረገው ቆጠራ መሠረት በሳይቤሪያ ከ430 እስከ 540 የሚደርሱ ነብሮች እንዳሉ ታውቋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በአራዊት ጥበቃ ተቋማት ውስጥ ያሉ የሳይቤሪያ ነብሮች በቀላሉ መራባት የሚችሉ ሲሆን በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ በጥሩ ይዞታ ላይ ይገኛሉ። በመላው ዓለም በሚገኙ የዱር አራዊት ጥበቃ ተቋማት ውስጥ ከ500 የሚበልጡ የሳይቤሪያ ነብሮች አሉ። ታዲያ ከእነዚህ ነብሮች ውስጥ የተወሰኑትን በመልቀቅ በዱር ያሉት ነብሮች እንዲበራከቱ የማይደረገው ለምንድን ነው? የሳይንስ ሊቃውንት ይህን ለማድረግ ያቅማማሉ። አንዲት ተመራማሪ እንደገለጹት “የወደፊት ደኅንነቱ አስተማማኝ እስካልሆነ ድረስ አንድን እንስሳ ወደ ዱር መልቀቅ ዋጋ የለውም።”

እነዚህን ትላልቅ የድመት ዝርያዎች ጨምሮ ሁሉም ሕያዋን ፍጥረታት የአምላክን ጥበብና ኃይል የሚያንጸባርቁ ሲሆኑ እሱም ትኩረትና እንክብካቤ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አድርጎ ይመለከታቸዋል። (መዝሙር 104:10, 11, 21, 22) የፈጣሪን ሥራዎች በጥልቅ የሚያደንቁ ብዙ ሰዎች የሳይቤሪያ ነብር የተደቀነበት የመጥፋት አደጋ የሚወገድበት ጊዜ እንደሚመጣ እርግጠኞች ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 የሳይቤሪያ ነብር አንዳንድ ጊዜ የአሙር ነብር በመባል ይጠራል። ምክንያቱም ይህ የነብር ዝርያ በአሁኑ ጊዜ በብዛት የሚገኘው በሩሲያ ምሥራቃዊ ጫፍ ባለው የአሙር ወንዝ አካባቢ ስለሆነ ነው።

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ትልቁ የድመት ዝርያ

ከተባዕት አንበሳና ከእንስት ነብር የሚወለደው ላይገር ተብሎ የሚጠራው የነብር ዝርያ በግዝፈቱ ከሳይቤሪያ ነብር ይበልጣል። ላይገር ርዝመቱ ከ3 ሜትር፣ ክብደቱ ደግሞ ከ500 ኪሎ ግራም ሊበልጥ ይችላል። ይህ እንስሳ የሚዳቀለው በዱር አራዊት ጥበቃ ተቋማት ውስጥ ሲሆን በደን ውስጥ ቢገኝም እንኳ ቁጥሩ እጅግ አናሳ ነው።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

ከላይ:- © photodisc/age fotostock; ከታች:- Hobbs, courtesy Sierra Safari Zoo, Reno, NV