ይሖዋ የሚለውን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁበት ቦታ
ይሖዋ የሚለውን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁበት ቦታ
ፓቮል ኮቫር እንደተናገረው
ከባድ የቦምብ ድብደባ በነበረበት ወቅት እንደምንም ብለን ለመሸሸጊያነት ወደተሠራው ምሽግ ደረስን። የቦምብ ድብደባው እየጠነከረ ሲሄድና መጠለያችንን ሲንጠው አብሮኝ የታሰረ አንድ ሰው ጮክ ብሎ “ይሖዋ ሆይ፣ አድነን! ለቅዱስ ስምህ ስትል እባክህ አድነን!” በማለት ጸለየ።
ወቅቱ ጥር 8, 1945 ሲሆን ኦስትሪያ ውስጥ በሊንዝ ከተማ የጦር እስረኛ ነበርኩ። በዚያ ምሽግ ውስጥ 250 ያህል እስረኞች የነበርን ሲሆን ሁላችንም ከቦምብ ድብደባው በሕይወት መትረፍ ቻልን። ከምሽጉ ስንወጣ በዙሪያችን የሚታየው ነገር ሁሉ ወድሟል። ያን ከልብ የመነጨ ጸሎት የጸለየው ማን እንደሆነ ባላውቅም በአእምሮዬ ውስጥ ተቀርጾ ቀርቶ ነበር። የይሖዋን ማንነት የኋላ ኋላ ያወቅሁት እንዴት እንደሆነ ከመናገሬ በፊት ስለ አስተዳደጌ ጥቂት ላውጋችሁ።
የተወለድኩት በዚያን ጊዜ የቼኮዝሎቫኪያ ግዛት በነበረችው በምዕራባዊ ስሎቫኪያ በምትገኘው በክራይኔ መንደር አጠገብ ይኖር በነበረ አንድ ቤተሰብ ውስጥ ሲሆን ወቅቱ መስከረም 28, 1921 ነበር። ወላጆቼ አጥባቂ ፕሮቴስታንቶች ነበሩ። አባቴ ሁልጊዜ እሁድ ጠዋት መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነብልን እናቴና እኛ አራታችን ልጆች ደግሞ በትኩረት እናዳምጥ ነበር። ሆኖም አባቴ ይሖዋ የሚለውን ስም የተጠቀመበት ጊዜ ትዝ አይለኝም። በአካባቢያችን ቀለል ያለ ኑሮ መምራት የተለመደ ሲሆን እኛም ባለን ጥቂት ነገር ረክተን እንኖር ነበር።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1939 ሲጀምር የአካባቢው ሰዎች በጣም ተደናገጡ። ከ20 ዓመታት በፊት ተካሂዶ የነበረው አንደኛው የዓለም ጦርነት ያስከተለው መከራ ገና ከአእምሯቸው አልጠፋም ነበር። በ1942 በስሎቫኪያ ሠራዊት ውስጥ እንዳገለግል ተጠራሁ። በዚያን ወቅት ስሎቫኪያ ከጀርመን ጎን መሰለፏን ይፋ አድርጋ የነበረ ቢሆንም በነሐሴ 1944 ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን መልሶ ለማቋቋም ሙከራ ተደረገ። ሙከራው ሲከሽፍ እኔን ጨምሮ በሺህ የሚቆጠሩ የስሎቫኪያ ወታደሮች ተማርከን በጀርመን ቁጥጥር ሥር ወደነበሩ ክልሎች ተላክን። በመጨረሻም፣ በሊንዝ ከተማ አቅራቢያ በነበረው ማውትሃውሰን ተብሎ በሚጠራው አስከፊ ማጎሪያ ካምፕ አካባቢ በነበረው ጉዘን በሚባል መለስተኛ ካምፕ ውስጥ ገባሁ።
የጦር እስረኛ
ከሳንክት ጂኦርጀን አን ዴ ጉዘን መንደር ብዙም ሳይርቅ እየተገነባ በነበረው የአውሮፕላን ጣቢያ ውስጥ እንድንሠራ ተመደብን። በዚያም በእንጨት መሰንጠቂያ ላይ እሠራ ነበር። የሚሰጠን ምግብ ጥቂት ነበር፤ የናዚ ሠራዊት በተሰለፈበት ግምባር ሁሉ እየተሸነፈ በመምጣቱ በጥር 1945 የሚሰጠን ራሽን የባሰውን ተቀነሰ። የሚሰጠን ሞቅ ያለ ምግብ ትንሽ ሾርባ ብቻ ነበር። በየዕለቱ ጠዋት ከማውትሃውሰን ማጎሪያ ካምፕ ሠራተኞች ይመጡ ነበር። ብዙውን ጊዜ ዘቦቹ ለመሥራት በጣም አቅም ያነሳቸውን እስረኞች ደብድበው ይገድሏቸው ነበር። በኋላም እስረኞች አስከሬኑን በሠረገላ ላይ ጭነው አስከሬን ወደሚቃጠልበት ስፍራ ይወስዱት ነበር።
በከባድ ሥቃይ ውስጥ ያለን ብንሆንም እንኳ ጦርነቱ ቶሎ እንደሚያበቃ ተስፋ ነበረን። በመግቢያው ላይ የጠቀስኩት የቦምብ ድብደባ ከደረሰ ከአራት ወራት በኋላ ማለትም በግንቦት 5, 1945 ከፍተኛ ግርግር ከእንቅልፌ ቀሰቀሰኝ። ከዚያም ወደ ውጪ ሮጥኩ። ጠባቂዎቹ በስፍራው አይታዩም፣ ጠመንጃዎች ተከምረዋል እንዲሁም የግቢው በሮች ወለል ብለው ተከፍተዋል። ከመስኩ ወዲያ ባለው ካምፕም ውስጥ ምን እየተከናወነ እንዳለ በግልጽ ይታየን ነበር። ነፃ የወጡት እስረኞች ከካምፑ እየሮጡ ሲወጡ በእሳት ከተያያዘ ቀፎ የሚሸሹ ንቦች ይመስሉ ነበር። ነፃ መውጣታቸውን ተከትሎ እስረኞቹ ጭካኔ የተሞላበት የብቀላ ድርጊት መፈጸም ጀመሩ። የደረሰው እልቂት እስካሁን ድረስ ከአእምሮዬ አልጠፋም።
እስረኞች፣ ካፖ ተብለው የሚጠሩትን ከናዚ ወታደሮች ጋር ሲተባበሩ የቆዩ እስረኞች እየደበደቡ በመግደል የበቀል ድርጊት ይፈጽሙ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ፣ ካፖ ተብለው የሚጠሩት እስረኞች ከናዚ ዘቦች ይበልጥ ጨካኞች ነበሩ። አንድ እስረኛ “አባቴን ገድሎብኛል። ስንት መከራ አሳልፈን እዚህ ከደረስን በኋላ፣ ከሁለት ቀን በፊት ገደለው!” እያለ በመጮኽ አንዱን ካፖ ደብድቦ ሲገድለው ተመልክቻለሁ። ማምሻው ላይ መስኩ በመቶዎች በሚቆጠር የካፖዎችና የሌሎች እስረኞች አስከሬን ተሞላ። በኋላም አካባቢውን ለቀን ከመሄዳችን በፊት በካምፑ ውስጥ እየተዘዋወርን የመርዝ ጋዝ ክፍሎቹንና የእቶን ምድጃዎቹን ጨምሮ ሌሎች መግደያ መሣሪያዎችን ተመለከትን።
ስለ እውነተኛው አምላክ አወቅሁ
በግንቦት 1945 መጨረሻ ላይ ወደ ቤቴ ተመለስኩ። ወላጆቼ በመጠለያ ካምፑ ውስጥ የሰማሁትን የአምላክን ስም ከማወቅ አልፈው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው አገኘኋቸው። ቤት ከተመለስኩ ብዙም ሳይቆይ መንፈሳዊ አስተሳሰብ ካላት ኦልጋ የተባለች ልጅ ጋር ተዋወቅሁ፤ ከአንድ ዓመት በኋላም ተጋባን። ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የነበራት ቅንዓት እኔም ስለ ይሖዋ መማሬን እንድቀጥል ገፋፋኝ። አዲሱ የኮሚኒስት አገዛዝ በ1949 የስብከት ሥራችንን ከማገዱ በፊት አድርገናቸው ከነበሩት የመጨረሻ ስብሰባዎቻችን በአንዱ ላይ ኦልጋና እኔ 50 ከሚያህሉ ሌሎች ሰዎች ጋር ሆነን ፒየሽቲያን ከተማ በሚገኘው የቫህ ወንዝ ውስጥ ተጠመቅን። ከጊዜ በኋላም ኦልጋ እና ቭላስታ የሚባሉ ሁለት ሴቶች ልጆች ወለድን።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የስብከቱን ሥራ እንደ አዲስ በማደራጀቱ ሥራ ላይ ትልቅ እርዳታ ያበረከተው ወንድም ያን ሴቢን አዘውትሮ ወደ ቤታችን ይመጣ የነበረ ሲሆን የአገልግሎት ጓደኛዬም ነበር። ኮሚኒስቶች የሚያደርሱብን ስደት እያደር ቢጨምርም ከመስበክ ወደኋላ አላልንም። ለሰዎች ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንናገር ስለነበር ወዲያውኑ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አገኘን። ወንድም ያን አካባቢውን ለቅቆ ሲሄድ ባለቤቴና እኔ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹን ማስጠናት ቀጠልን። ከጊዜ በኋላም እነዚህን ውድ ወዳጆቻችንን ከልጆቻቸውና ከልጅ ልጆቻቸው ጋር በትልልቅ ስብሰባዎቻችን ላይ ብዙ ጊዜ እናገኛቸው ነበር። ይህ ትልቅ ደስታ አስገኝቶልናል!
ልዩ አገልግሎት
እስከ 1953 ድረስ የስብከቱን ሥራ በግንባር ቀደምትነት ሲመሩ የነበሩ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ታሰሩ። ስለዚህ ከምንኖርበት አካባቢ 150 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በሚገኝ አንድ ክልል ውስጥ በስብከቱ ሥራ እንድረዳ ተጠየቅሁ። በየሁለት ሳምንቱ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ሰብዓዊ ሥራዬን ስጨርስ ከኖቬ ሜስቶ ናድ ቫሆም ከተማ በባቡር ተሳፍሬ በሰሜን ማዕከላዊ ስሎቫኪያ ወደምትገኘው ወደ ማርቲን እጓዝ ነበር። እዚያም እስከ ሌሊት ድረስና እሁድ ሙሉ ቀን መጽሐፍ ቅዱስን ለሰዎች በማስተማር አሳልፍ ነበር። እሁድ አመሻሹ ላይ ወደ ኖቬ ሜስቶ ለመመለስ ባቡር እሳፈራለሁ። አብዛኛውን ጊዜ የምደርሰው እኩለ ሌሊት ላይ ሲሆን ሁልጊዜ ጥሩ አቀባበል የሚያደርጉልኝ አረጋዊ ባልና ሚስት ቀሪውን ሌሊት በቤታቸው እንዳሳልፍ ይፈቅዱልኝ ነበር። ከዚያም በቀጥታ ወደ ሥራዬ እሄድና ሰኞ ማታ በክራይኔ መንደር ወደሚገኙት ቤተሰቦቼ እመለሳለሁ። እቤት በማልኖርባቸው በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ኦልጋ ልጆቻችንን ትንከባከብ ነበር።
ከዚያም በ1956 በአካባቢያችን ያሉትን ጉባኤዎች በመንፈሳዊ ማጠናከርን በሚጨምረው በወረዳ የበላይ ተመልካችነት እንዳገለግል ተጋበዝኩ። በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ያገለግሉ የነበሩት ብዙ ወንድሞች ታስረው ስለነበር ይህን ኃላፊነት መቀበል አስፈላጊ መሆኑን ተገነዘብኩ። እኔና ባለቤቴ ይሖዋ ቤተሰባችንን እንደሚደግፍ እርግጠኞች ነበርን።
በኮሚኒስት ሕግ መሠረት ሁሉም ዜጎች ተቀጥረው መሥራት ነበረባቸው። መንግሥት ሥራ የሌላቸውን ሰዎች እንደ ጥገኛ ተሕዋስያን አድርጎ በመቁጠር ያስራቸው ነበር። ስለዚህ ሰብዓዊ ሥራዬን እንደያዝኩ ቀጠልኩ። በየወሩ ሁለት ቅዳሜና እሁዶችን ከቤተሰቤ ጋር በመንፈሳዊና በሌሎችም እንቅስቃሴዎች እየተካፈልኩ የማሳልፍ ሲሆን በሌሎቹ ሁለት ቅዳሜና እሁዶች ደግሞ በአቅራቢያችን ካሉት ስድስት ጉባኤዎች መካከል አንዱን እጎበኝ ነበር።
በእገዳ ውስጥ ጽሑፎችን ማዘጋጀት
የወረዳ የበላይ ተመልካቾች በክልላቸው ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ጉባኤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች እንዲደርሱት ዝግጅት የማድረግ ኃላፊነት ነበረባቸው። መጀመሪያ ላይ መጽሔቶች በእጅ ወይም በታይፕ እየተጻፉ ይባዙ ነበር። በኋላ ግን የመጠበቂያ ግንብ መጽሔትን በፎቶ ፊልም ማግኘት ስለቻልን ይህንን ለየጉባኤዎቹ መላክ ጀመርን። በመሆኑም ከዚያን ጊዜ በኋላ መጽሔቶች በፎቶግራፍ ወረቀት ላይ ይባዙ ነበር። የማተሚያ ወረቀቶቹን በብዛት መግዛት ጥርጣሬ ሊፈጥር ስለሚችል የሚገዙት ወንድሞች ደፋር መሆንና ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር።
ስቴፋን ሁችኮ ለዚህ ሥራ ፍቅር ስለነበረው እጅግ ውጤታማ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት ስቴፋን ከትውልድ ከተማው ራቅ ብሎ ወደሚገኝ ከተማ ሄዶ የፎቶግራፍ ወረቀት ለመግዛት ወደ አንድ ሱቅ ገባ፤ ያም ሆኖ ወረቀቱ በሙሉ ተሸጦ አልቆ ነበር። ይሁን እንጂ ከሱቁ ሊወጣ ሲል ቀደም ሲል ወረቀቱን በትእዛዝ እንደምታስመጣለት ቃል ገብታለት የነበረችውን አንዲት ተግባቢ የሱቅ ሠራተኛ አያት። ስቴፋን ሊያነጋግራት ሲል አንድ ፖሊስ ወደ ሱቁ ሲገባ አየ። በዚያው ቅጽበት ይህች የሱቅ ሠራተኛ ስቴፋንን አየችውና በደስታ ስሜት “ዕድለኛ ነህ። የምትፈልጋቸው የፎቶግራፍ ወረቀቶች ደርሰውናል” አለችው።
ስቴፋንም በፍጥነት “ይቅርታ የኔ እመቤት፣ ከሌላ ሰው ጋር ተመሳስዬብሽ ይሆናል። እኔ የምፈልገው አንዲት ነጠላ ፊልም ብቻ ነው” አላት።
ይሁንና ስቴፋን ወደ መኪናው ከተመለሰ በኋላ እዚያ ድረስ የለፋበትን የፎቶግራፍ ወረቀት ሳይዝ ወደ ቤቱ መመለስ አልሆነለትም። ስለዚህ ሌላ ሰው ለመምሰል ካፖርቱንና ባርኔጣውን ካወለቀ በኋላ እንደገና ወደ ሱቁ በመግባት በቀጥታ ወደ ሠራተኛዋ ሄዶ “ከሳምንት በፊት መጥቼ ነበር። የፎቶግራፍ ወረቀት በትእዛዝ እንደምታስመጪልኝ ቃል ገብተሽልኝ ነበር። ወረቀቶቹን አግኝተሽ ይሆን?” ሲል ጠየቃት።
“አዎን፣ ተገኝቶልሃል” በማለት መለሰችለት። “የሚገርም ነው፣ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት አንተን የሚመስል ሰው መጥቶ ነበር። መንትያህ ይመስላል!” አለችው። ስቴፋንም ወረቀቱን በፍጥነት ተቀብሎ ይሖዋን እያመሰገነ ሄደ።
በ1980ዎቹ ዓመታት በምድር ቤቶችና በሌሎችም ሰወር ያሉ ቦታዎች ውስጥ የማባዣ ማሽኖችንና ትንንሽ ማተሚያ መሣሪያዎችን በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማዘጋጀት ጀመርን። ከጊዜ በኋላ፣ የእያንዳንዱ
መጽሔት እትም እንዲሁም የመጻሕፍትና የቡክሌት ብዛት በአካባቢው ላሉት የይሖዋ ምሥክሮች ከመብቃት አልፎ ተጨማሪ ቅጂዎችን ማተም ተቻለ።ተደጋጋሚ ምርመራ
በ1960ዎቹ ውስጥ ነው፤ አንድ ቀን፣ ተቀጥሬ በምሠራበት ኩባንያ ውስጥ ወደሚገኘው ወታደራዊ ክፍል እንድሄድ ተነገረኝ። የሲቪል ልብስ የለበሱ ሦስት ሰዎች “ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስትሰበሰብ ምን ያህል ጊዜ ሆኖሃል? የምትሰበሰበውስ ከእነማን ጋር ነው?” በማለት ጠየቁኝ። የወንድሞችን ስም ጨምሮ ዝርዝር ጉዳዮችን ለመናገር ፈቃደኛ ባለመሆኔ ሌላ ጊዜ እንደሚጠሩኝ ገልጸው አሰናበቱኝ። ከመንግሥት የደህንነት ሠራተኞች ጋር ስገናኝ ይህ የመጀመሪያዬ ነበር።
ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከሥራ ቦታዬ ላይ ተጠርቼ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰድኩ። ባዶ ወረቀት ከፊቴ ተቀመጠልኝና የማውቃቸውን የይሖዋ ምሥክሮች ስም እንድጽፍ ተጠየቅሁ። ወረቀቱን የሰጠኝ ሰው ከአንድ ሰዓት በኋላ ሲመለስ ወረቀቱ ባዶ ሆኖ አገኘው፤ እኔም የማንንም ስም እንደማልናገር ገለጽኩለት። በቀጣዩ ሳምንትም ተመሳሳይ ጥያቄ ቀረበልኝና በድጋሚ ያንኑ መልስ ሰጠሁ። በዚህ ጊዜ ግን የደበደቡኝ ሲሆን ኮሪደሩን ጨርሼ እስክወጣ ድረስ በእርግጫ ይመቱኝ ነበር።
ከዚያ በኋላ፣ ለአንድ ዓመት ያህል ምንም ሳያደርጉኝ ቆዩ። ከዚያም ፖሊሶቹ አንድ ሰው ሁኔታዬን እንዲያይ ወደ እኔ ላኩ። ሰውየው በናዚ ማጎሪያ ካምፕ አብሮኝ ታስሮ ነበር። እሱም “እናንተን በቁጥጥር ሥር የምናውልበትን ዘዴ መቀየር አለብን። አንድ የይሖዋ ምሥክር እስር ቤት ስናስገባ አምስት ሆነው ይወጣሉ” አለኝ። የመንግሥት ፍላጎት በሥራችን ላይ ቢያንስ ቢያንስ መጠነኛ ቁጥጥር ማድረግ ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ለማድረግ የሚያስችላቸውን አንዳችም መረጃ ላለመስጠት ቁርጥ ውሳኔ አድርጌ ነበር።
የደህንነት ፖሊሶች ለብዙ ዓመታት አልፎ አልፎ ከሚጎበኟቸው ወንድሞች መካከል አንዱ ነበርኩ። አንዳንዴ የወዳጅነት ስሜት ያሳዩናል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከመካከላችን አንዱን ወደ እስር ቤት ይከቱታል። ደግነቱ ታስሬ አላውቅም፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ጉብኝቶች ኮሚኒዝም በቼኮዝሎቫኪያ ውስጥ እስከወደቀበት እስከ 1989 ድረስ ቀጥለው ነበር።
ኮሚኒዝም ከወደቀ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በብራትስላቫ የሚኖር አንድ ከፍተኛ የደህንነት ባለ ሥልጣን ሊጠይቀኝ መጣ። ይቅርታ ከጠየቀኝ በኋላ “እንደ እኔ ፍላጎት ቢሆን ኖሮ አናስቸግርህም ነበር” አለኝ። ከዚያም ሁለት ከረጢት ሙሉ በቆርቆሮ የታሸገ ፍራፍሬ ከመኪናው ውስጥ አወጣና ሰጠኝ።
ይሖዋ የጸና ግንብ ነው
የይሖዋ ምሥክር ሆኜ ባሳለፍኳቸው የመጀመሪያዎቹ 40 ዓመታት አምላክን ያገለገልኩት በእገዳ ሥር ቢሆንም አስደሳችና የሚያረካ ሕይወት ኖሬያለሁ። በእነዚያ ዓመታት ያጋጠሙን ነገሮች ታማኝ የሆኑ የእምነት አጋሮቻችንን ከምንጊዜውም የበለጠ አቀራርበዋቸዋል። በመካከላችን ያለውን ወዳጅነት ከፍ አድርገን እንመለከተው የነበረ ሲሆን አንዳችን ለሌላው ታማኝ ስለመሆናችን አንጠራጠርም ነበር።
መጋቢት 2003 ውዷን ባለቤቴን ኦልጋን በሞት በማጣቴ ከባድ ሐዘን ደረሰብኝ። በትዳር ዘመናችን ሁሉ ታማኝ አጋሬ ነበረች። በእነዚያ ዓመታት ሁሉ በክርስቲያናዊ አገልግሎት አብረን በትጋት ተካፍለናል። አሁን በጉባኤያችን ውስጥ በሽምግልና በማገልገል ላይ የምገኝ ስሆን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የማካፍላቸው ምሥራቹን ለመስማት የሚጓጉ ሰዎችን መፈለጌን ቀጥያለሁ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በቦምብ መጠለያ ምሽግ ውስጥ ሳለሁ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ይሖዋ የሚለው ስም የጸና ግንብ ሆኖልኛል። *—ምሳሌ 18:10
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.33 ወንድም ፓቮል ኮቫር የሕይወት ታሪኩ በመዘጋጀት ላይ እያለ ሐምሌ 14, 2007 በ85 ዓመቱ አርፏል።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1942 በስሎቫኪያ ሠራዊት ውስጥ ሳለሁ
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኋላም፣ በጉዘን ካምፕ ውስጥ ታስሬ ነበር (ከበስተጀርባ ያለው ፎቶ)
[ምንጭ]
© ČTK
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አባቴ ሁልጊዜ እሁድ ጠዋት መጽሐፍ ቅዱስ ያነብልን ነበር
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1946 በሠርጋችን ዕለት
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኦልጋ ከመሞቷ ከጥቂት ጊዜ በፊት የተነሳነው ፎቶግራፍ