በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ትዳሮች

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ትዳሮች

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ትዳሮች

“ከእንግዲህ በቃኝ!” ሰዎች ትዳራቸውን አስመልክተው እንዲህ ሲሉ ሰምተህ ታውቃለህ? ያገባህ ከሆንህ፣ አንተስ እንዲህ የተሰማህ ወቅት አለ?

በሺህ የሚቆጠሩ ባለትዳሮች ወደ ትዳር ዓለም የሚገቡት በጣም ስለተዋደዱ አሊያም በጊዜያዊ ፍቅር ተገፋፍተው ሲሆን ከተጋቡ በኋላም ሕይወታቸው በደስታ የተሞላ እንደሚሆን ተስፋ ያደርጋሉ። “ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ወደ እኔ የሚመጡት ተስፋቸው ተሟጦ ነው” በማለት አንዲት የጋብቻ አማካሪ ይናገራሉ። አክለውም “እነዚህ ሰዎች በትዳር ጓደኛቸው እንዲሁም በራሱ በትዳር፣ በፍቅር አንዳንድ ጊዜም በሕይወት ጭምር እጅግ ግራ ይጋባሉ” ብለዋል። ከእነዚህ ባለትዳሮች ውስጥ አብዛኞቹ ከጋብቻ የምሥክር ወረቀትና ከሚኖሩበት ቤት በቀር አንድ የሚያደርጋቸው ምንም ነገር የላቸውም።

አንዳንድ ትዳሮች እንዲፈርሱ ምክንያት የሆነው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የኑሮ ውጥረትና ጭንቀት ነው። በጣም የሚዋደዱ ባልና ሚስትም እንኳ ሥራቸው ፋታ የሚያሳጣ መሆኑ ብሎም ምሽት ላይና ሌሊት እንዲሁም ረዘም ላሉ ሰዓታት መሥራታቸው ጫና ስለሚፈጥርባቸው ግንኙነታቸው ውጥረት የሰፈነበት ሊሆን ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ የገንዘብ ችግር፣ ልጆችን ከማሳደግ ጋር የተያያዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች፣ ቤት መቀየር፣ ሥራ መለወጥና የጤንነት ችግሮች በትዳር ጓደኛሞች መካከል ያለውን የፍቅርና የአክብሮት ስሜት ሊሸረሽሩት ይችላሉ። በአጭር አነጋገር፣ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙት ለውጦች ባልና ሚስት እንዲራራቁ ሊያደርጉ የሚችሉ ውጥረቶችን ያስከትሉ ይሆናል።

ብዙ እናቶች ከቤት ውጪ የሚሠሩ ሲሆን በቤታቸው ውስጥም ያንኑ ያህል ጊዜ የሚወስድ ተደራቢ ሥራ አለባቸው። ይህ ደግሞ ሁሉን ነገር ትተው ሙሉ ትኩረታቸውን በሥራቸውና ልጆቻቸውን በመንከባከቡ ላይ እንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል። ባለትዳሮች ያለባቸው ውጥረትና ድካም ከትዳር ጓደኞቻቸው ጋር የሚያሳልፉትን ጊዜ ያጣብብባቸዋል። በመሆኑም ብዙዎቹ ሕይወታቸው ከቁጥጥራቸው ውጭ እንደሆነ ስለሚሰማቸው የተስፋ መቁረጥና የባይተዋርነት ስሜት ያድርባቸዋል። ብዙ ትዳሮች እንዲህ ባለ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የወደቁት ለምንድን ነው? ትዳራችሁ ደስተኛና የሰመረ እንዲሆን ምን ማድረግ ትችላላችሁ?