በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትዳር የሰመረ እንዲሆን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

ትዳር የሰመረ እንዲሆን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

ትዳር የሰመረ እንዲሆን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

ትዳር አንዳንዴ አስደሳች ሌላ ጊዜ ደግሞ አሳዛኝ ገጠመኞች ከሞሉበት ረዥም ጉዞ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አንዳንድ ጊዜ በጉዞው ላይ ሳይታሰብ የሚያጋጥሙት የማይዘለቁ የሚመስሉ “አቀበቶችና ቁልቁለቶች” ያልተጠበቁ እንቅፋቶችን ሊፈጥሩ ይችላሉ። ያም ሆኖ ብዙ ሰዎች፣ ችግሮች ቢያጋጥሟቸውም ጉዞውን የተሳካና አስደሳች ያደርጉታል። እርግጥ ነው፣ የትዳር ስኬታማነት የሚለካው ባልና ሚስቱ በመንገዳቸው ላይ በሚያጋጥሟቸው ውጣ ውረዶች ብዛት ሳይሆን እነዚህን ችግሮች በሚፈቱበት መንገድ ነው።

ታዲያ የትዳርን ጉዞ ይበልጥ ስኬታማና አስደሳች ሊያደርግ የሚችል ነገር ያለ ይመስልሃል? ብዙ ባልና ሚስቶች ‘የትዳር ጉዟቸውን የሚመሩበት ካርታ’ እንደሚያስፈልጋቸው ይሰማቸዋል። የጋብቻ መሥራች የሆነው ይሖዋ አምላክ ከሁሉ ይበልጥ አስተማማኝ የሆነ የትዳር “ካርታ” ሰጥቶናል። ይሁን እንጂ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የተጻፈው ቃሉ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ ቤታችን ውስጥ መኖሩ ብቻ ያሉብንን ችግሮች ወዲያውኑ ያስወግድልናል ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ባልና ሚስት ትዳራቸው የሰመረ እንዲሆን ከፈለጉ ሊከተሏቸው የሚገቡ ጠቃሚ መመሪያዎችን ይዟል።—መዝሙር 119:105፤ ኤፌሶን 5:21-33፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16

ትዳራችሁን የሰመረና አስደሳች እንዲሆን ለማድረግ ሊረዷችሁ ከሚችሉት እንደ መንገድ ምልክት ሆነው ከሚያገለግሉት ከእነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችና ቁልፍ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።

ትዳርን ቅዱስ አድርጋችሁ ተመልከቱት። “እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።” (ማቴዎስ 19:6) የጋብቻን ዝግጅት የመሠረተው ፈጣሪ ሲሆን ይህም የሆነው የመጀመሪያውን ሰው አዳምን ከሚስቱ ከሔዋን ጋር ባስተዋወቀበት ጊዜ ነበር። (ዘፍጥረት 2:21-24) ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የመጀመሪያው ጋብቻ ሲፈጸም የተመለከተው ክርስቶስ ኢየሱስ የአዳምና የሔዋን ጥምረት ዘላቂ ለሆነ ዝምድና ጅማሬ እንዲሆን ታስቦ የተደረገ መሆኑን አረጋግጧል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸው አላነበባችሁምን? እንዲህም አለ፤ ‘ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ የተባለው በዚህ ምክንያት አይደለምን? ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።”—ማቴዎስ 19:4-6

ኢየሱስ “እግዚአብሔር ያጣመረውን” ሲል የጋብቻ ዝግጅትን ያቋቋመው አምላክ መሆኑንና ከዚህም የተነሳ ትዳር ቅዱስ ተደርጎ መታየት እንደሚገባው አበክሮ መናገሩ ነበር። *

እርግጥ ነው፣ ባሎችም ሆኑ ሚስቶች ቀዝቃዛ በሆነና ፍቅር በሌለው ዝምድና ‘ተጣምረው’ መኖር አይፈልጉም። ከዚህ ይልቅ ለሁለቱም ደስታና እርካታ የሚያስገኝ ጥሩ ትዳር እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ፈጣሪ የሰጣቸውን ጠቃሚ ምክሮች በሥራ ላይ ካዋሉ በደስታ ‘ሊጣመሩ’ ይችላሉ።

ሁላችንም ፍጹማን ባለመሆናችን አለመግባባቶችና ልዩነቶች መኖራቸው የማይቀር ነገር ነው። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ትዳርን ስኬታማ የሚያደርገው የትዳር ጓደኛሞቹ ምን ያህል ይጣጣማሉ የሚለው ሳይሆን ልዩነቶቻቸውን የሚያስታርቁት እንዴት ነው የሚለው ነጥብ ነው። ፍቅር ‘ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስር’ በመሆኑ በትዳር ውስጥ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ችሎታዎች አንዱ አለመግባባትን ፍቅራዊ በሆነ መንገድ መፍታት ነው።—ቈላስይስ 3:14

በአክብሮት ተናገሩ። “ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል።” (ምሳሌ 12:18) አብዛኞቹ ጭውውቶች የሚደመደሙት እንደ አጀማመራቸው መሆኑን ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። ስለሆነም አንድ ጭውውት የተጀመረው አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ ከሆነ በዚያው መንገድ ሊደመደም ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ የምትወዱት ሰው አሳቢነት በጎደለው መንገድ ሲያናግራችሁ ምን ያህል እንደምትጎዱ ታውቁታላችሁ። ስለዚህ እናንተም የሌላውን ክብር በማይነካ እንዲሁም አክብሮትና ፍቅር በተንጸባረቀበት መንገድ መናገር እንድትችሉ ጸሎት የታከለበት ጥረት አድርጉ። (ኤፌሶን 4:31) በትዳር ውስጥ 44 ዓመታት ያሳለፈች ሀሩኮ * የተባለች አንዲት ጃፓናዊት እንዲህ ብላለች:- “አንዳችን የሌላውን ድክመት የምናይ ቢሆንም በአክብሮት ለመነጋገርና የትዳር ጓደኛችንን መልካም ባሕርይ ለማድነቅ እንጥራለን። ይህም ትዳራችን የሰመረ እንዲሆን ረድቶናል።”

ደግና ርኅሩኅ ለመሆን ጣሩ። “እርስ በርሳችሁ ቸሮችና [“ደጎችና፣” NW] ርኅሩኆች ሁኑ።” (ኤፌሶን 4:32) ከባድ አለመግባባቶች በሚፈጠሩበት ወቅት፣ አንዱ የትዳር ጓደኛ በንዴት ሲናገር ሌላውም አጸፋውን ለመመለስ ይገፋፋ ይሆናል። በጀርመን የምትኖረውና ለ34 ዓመታት ደስታ የሰፈነበት የትዳር ሕይወት ያሳለፈችው አኔት እንደሚከተለው ስትል ሳትሸሽግ ተናግራለች:- “ውጥረት በሚሰፍንበት ወቅት ራስን ማረጋጋት ቀላል ባለመሆኑ የትዳር ጓደኛችሁን የሚያበሳጭ ነገር መናገር ይቀናችሁ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ችግሩን ከማባባስ በቀር ምንም የሚፈይደው ነገር የለም።” ደግና ርኅሩኅ በመሆን ትዳራችሁ ሰላም የሰፈነበት እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት ትችላላችሁ።

ትሕትና አሳዩ። “ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቍጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ።” (ፊልጵስዩስ 2:3) ብዙ ግጭቶች የሚነሱት የትዳር ጓደኛሞች የተፈጠረውን ችግር በትሕትና ለመፍታት ከመጣር ይልቅ አንዳቸው ሌላውን ተጠያቂ ለማድረግ ስለሚሞክሩ ነው። ራስን ዝቅ የማድረግ መንፈስ ወይም ትሕትና፣ በክርክሩ ለመርታትና ትክክለኛ መሆናችሁን ለማሳወቅ የሚገፋፋችሁን ውስጣዊ ስሜት ለመቆጣጠር ሊረዳችሁ ይችላል።

ቶሎ አትቀየሙ። “በመንፈስህ ለቍጣ አትቸኵል።” (መክብብ 7:9) የትዳር ጓደኛችሁን አመለካከት የመቃወም ወይም እናንተ በተናገራችሁት ወይም ባደረጋችሁት ነገር ላይ ጥያቄ ሲያነሱ ወዲያውኑ ራሳችሁን ለመከላከል የመሞከርን ዝንባሌ አስወግዱ። ከዚህ ይልቅ የትዳር ጓደኛችሁ የሚናገረውን በጥሞና አዳምጡ፤ እንዲሁም ስሜቱን መረዳታችሁን ግለጹለት። መልስ ከመስጠታችሁ በፊት በጥንቃቄ አስቡ። ብዙ ባልና ሚስት፣ የትዳር ጓደኛቸውን በፍቅር መርታት በክርክር ከመርታት ይልቅ ታላቅ ድል መሆኑን የሚገነዘቡት ዘግይተው ነው።

መቼ ዝም ማለት እንዳለባችሁ እወቁ። “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ፣ ለቊጣም የዘገየ ይሁን።” (ያዕቆብ 1:19) ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት በትዳር ውስጥ ደስታ ለማግኘት ከሚረዱት ነገሮች አንዱ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ “ለዝምታ ጊዜ አለው” በማለት የሚናገረው ለምንድን ነው? (መክብብ 3:7) ዝምታ የትዳር ጓደኛችሁ በእርግጥ ምን እንደሚሰማውና እንደዚያ የተሰማው ለምን እንደሆነ ለማወቅ የሚረዳችሁ የሐሳብ ግንኙነት አስፈላጊ ክፍል ነው፤ ‘የዝምታ ጊዜ’ የትዳር ጓደኛችሁን በንቃትና በቁም ነገር የምታዳምጡበት ወቅት ሊሆን ይችላል።

ስታዳምጡ ራሳችሁን በትዳር ጓደኛችሁ ቦታ ለማስቀመጥ ጣሩ። “ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያዝኑም ጋር እዘኑ።” (ሮሜ 12:15) ራስን በሌላው ቦታ ማስቀመጥ የትዳር ጓደኛን ውስጣዊ ስሜት ለመረዳት ስለሚያስችል ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት እንዲኖር ለማድረግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ከዚህም በላይ አንዳቸው የሌላውን አስተያየትና ስሜት በአክብሮት ለመመልከት ሊረዳቸው ይችላል። ለ32 ዓመታት በትዳር ዓለም የቆየችውና በብራዚል የምትኖረው ኔላ እንዲህ ብላለች:- “ስለ ችግሮቻችን ስንነጋገር የማኑዌልን ሐሳብና ስሜት መረዳት እንድችል ምንጊዜም በጥሞና አዳምጠዋለሁ።” የትዳር ጓደኛችሁ በሚናገርበት ወቅት ስሜቱን ለመረዳት መጣር እንዲሁም ‘በዝምታ’ ማዳመጥ ይኖርባችኋል።

አድናቆታችሁን የመግለጽ ልማድ ይኑራችሁ። ‘የምታመሰግኑ ሁኑ።’ (ቈላስይስ 3:15) ጠንካራ ትዳር ያላቸው ባሎችና ሚስቶች ለትዳር ጓደኛቸው ያላቸውን አድናቆት አዘውትረው ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ አንዳንድ የትዳር ጓደኛሞች ይህንን አስፈላጊ የሐሳብ ግንኙነት ዘርፍ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ውስጥ ችላ ከማለታቸውም ሌላ ‘የትዳር ጓደኛዬ እንደማደንቀው ያውቃል’ ብለው ያስባሉ። “አብዛኞቹ ባልና ሚስቶች ቢያስቡበት ኖሮ እርስ በርሳቸው የአድናቆት ስሜታቸውን ሊገላለጹ ይችሉ ነበር” በማለት ዶክተር ኤለን ዋችቴል ይናገራሉ።

በተለይም ባሎች፣ ሚስቶቻቸውን እንደሚወዷቸው ሊያረጋግጡላቸውና አድናቆታቸውን ሊገልጹላቸው ይገባል። እናንተ ባሎች በቁም ነገር አስባችሁበት ስለ ሚስቶቻችሁ መልካም ተግባሮችና ባሕርያት አድናቆታችሁን በመግለጽ፣ የትዳራችሁን ጤንነት ለመጠበቅ እንዲሁም የሚስቶቻችሁንም ሆነ የራሳችሁን ደስታ ለመጨመር ብዙ ነገር ማድረግ ትችላላችሁ።

በቃልም ሆነ በድርጊት ፍቅርን መግለጽ አስፈላጊ ነው። እናንተ ባሎች ሚስቶቻችሁን በመሳም፣ በመደባበስና ብሩሕ ፈገግታ በማሳየት ፍቅራችሁን ስትገልጹ “እወድሻለሁ” ከማለት የበለጠ መልእክት ታስተላልፋላችሁ። ይህም ሚስቶቻችሁ ለእናንተ ልዩ እንደሆኑና እንደምትፈልጓቸው ያረጋግጥላቸዋል። ለሚስቶቻችሁ ስልክ ደውሉላቸው አሊያም “ናፍቀሽኛል” ወይም “እንዴት ዋልሽ?” የሚል መልእክት ላኩላቸው። ለትዳር ስትጠናኑ ከነበራችሁበት ጊዜ በኋላ የፍቅር መግለጫዎችን መናገር ትታችሁ ከነበረ እንዲህ ማድረግ መጀመራችሁ ጠቃሚ ነው። የትዳር ጓደኛችሁን ልብ የሚማርከው ነገር ምን መሆኑን ለማወቅ ጥረት ማድረጋችሁን ቀጥሉ።

በጥንቷ እስራኤል ትኖር የነበረችው የንጉሥ ልሙኤል እናት የተናገረቻቸው የሚከተሉት ቃላት በእርግጥም አግባብነት ያላቸው ናቸው:- “ባሏም እንዲሁ፤ ሲያመሰግናትም እንዲህ ይላል፤ ‘ብዙ ሴቶች መልካም አድርገዋል፤ አንቺ ግን ሁሉንም ትበልጫለሽ።’” (ምሳሌ 31:1, 28, 29) ለሚስትህ አድናቆትህን ከገለጽክላት ምን ያህል ጊዜ ሆኖሃል? ወይም ሚስት ከሆንሽ፣ ለባልሽ አድናቆትሽን ከገለጽሽለት ምን ያህል ጊዜ ሆኖሻል?

ይቅር ለማለት ፈጣኖች ሁኑ። “በቊጣችሁ ላይ ፀሓይ አይግባ።” (ኤፌሶን 4:26) በትዳር ውስጥ እናንተም ሆናችሁ የትዳር ጓደኛችሁ ስህተት መፈጸማችሁ አይቀርም። በመሆኑም ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆን አስፈላጊ ነው። ከተጋቡ 43 ዓመት የሆናቸውና በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩት ክላይቭ እና ሞኒካ ይህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በጣም ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። ክላይቭ እንዲህ ይላል:- “በኤፌሶን 4:26 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት በተግባር ለማዋል እንጥራለን፤ እንዲሁም ይቅር መባባላችን አምላክን እንደሚያስደስተው ስለምናውቅ እርስ በርሳችን ቶሎ ይቅር ለመባባል እንሞክራለን። ከዚያ በኋላ ስለ ሁኔታው ጥሩ ስሜት ይሰማናል፤ ሕሊናችን ንጹሕ ሆኖ ወደ መኝታችን ስለምንሄድ ጥሩ እንቅልፍ ይወስደናል።”

አንድ ጥበብ የሞላበት ጥንታዊ ምሳሌ ‘በደልን ንቆ መተው መከበሪያ ነው’ በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 19:11) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው አኔት “ይቅር መባባል ከሌለ ትዳር ጥሩ ሊሆን አይችልም” በማለት በዚህ ሐሳብ እንደምትስማማ ገልጻለች። ምክንያቱንም ስታስረዳ እንዲህ ብላለች:- “ይቅር የማትባባሉ ከሆነ ጥላቻና አለመተማመን ሊፈጠር ይችላል፤ ይህ ደግሞ ለትዳር መርዝ ነው። ይቅር የምትባባሉ ከሆነ የትዳራችሁ ሠንሠለት ይጠናከራል፤ እርስ በርስም ይበልጥ ትቀራረባላችሁ።”

የትዳር ጓደኛችሁን ካስቀየማችሁ በቀላሉ ትረሳዋለች ወይም ይረሳዋል ብላችሁ አታስቡ። ሰላም ለማውረድ ብዙውን ጊዜ የትዳር ጓደኞች ሊያደርጉት የሚገባውን በጣም አስፈላጊ ነገር ማድረግ ይጠይቅባችኋል:- ይኸውም ጥፋታችሁን አምኖ መቀበል ነው። እንዲሁም ትሕትና በተላበሰ መንገድ “አጥፍቻለሁ፣ የኔ ፍቅር ይቅርታ አድርጊልኝ/ግልኝ” ብላችሁ ከመናገር ወደኋላ አትበሉ። በትሕትና ይቅርታ መጠየቅ አክብሮት የሚያተርፍላችሁ ከመሆኑም ሌላ ትዳራችሁ መተማመን የሰፈነበት እንዲሆን ብሎም የአእምሮ ሰላም እንዲኖራችሁ ይረዳችኋል።

ለትዳር ጓደኛችሁም ሆነ ለትዳራችሁ ታማኞች ሁኑ። “[ባልና ሚስት] ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።” (ማቴዎስ 19:6) ምንም ይምጣ ምን ሳትለያዩ ለመኖር፣ በአምላክና በሰው ፊት ቃል ገብታችኋል። * ይሁን እንጂ የገባችሁትን ቃል የምትጠብቁት ሕጉ ስለሚያስገድዳችሁ ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በቅንነትና ከልብ በመነጨ ፍቅር ተነሳስታችሁ የምታደርጉት ይሁን፤ ይህም አንዳችሁ ለሌላውም ሆነ ለአምላክ አክብሮት እንዳላችሁ የሚያንጸባርቅ ነው። ስለዚህ ሌሎችን በማሽኮርመም ቅዱስ የሆነ ትዳራችሁን እንዳትሸረሽሩት ተጠንቀቁ። የፍቅር ስሜት ልታሳዩ የሚገባው ለትዳር ጓደኛችሁ ብቻ ነው።—ማቴዎስ 5:28

ራስን የመሠዋት መንፈስ ቃል ኪዳንን ያጠናክራል። “ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ።” (ፊልጵስዩስ 2:4) የትዳር ጓደኛችሁን ፍላጎቶችና ምርጫዎች ማስቀደማችሁ ትዳርን ለማጠናከር ከሚረዷችሁ መንገዶች አንዱ ነው። በትዳር ውስጥ 20 ዓመታትን ያሳለፈው ፕሪምጂ የሙሉ ቀን ሥራ የምትሠራውን ባለቤቱን በቤት ውስጥ ሥራ ያግዛታል። ፕሪምጂ “ሪታ የሚያስደስቷትን ነገሮች የምታከናውንበት ጊዜ እንድታገኝ እንዲሁም እንዳይደክማት ስል ምግብ ማብሰልንና ቤት ማጽዳትን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎችን አግዛታለሁ” ብሏል።

ጥረት ማድረግ ይክሳል

ትዳር አስደሳች እንዲሆን ማድረግ ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑ አንዳንዶች ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርገው ለመተው እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ችግሮች መኖራቸው ቃል ኪዳናችሁን እንድትተዉ አያድርጋችሁ፤ በትዳር ዓለም አብራችሁ ያደረጋችሁት ጉዞ በአጭር እንዲቀጭ ማለትም ትዳራችሁ አስደሳች እንዲሆን ያደረጋችሁት ጥረት ሁሉ መና እንዲቀር አትፍቀዱ።

ለ33 ዓመታት ደስታ የሰፈነበት የትዳር ሕይወት ሲመራ የቆየው ሲድ “ልባዊ ጥረት ካደረጋችሁና ትዳራችሁ እንዲሰምር የምትፈልጉ መሆናችሁን ካሳያችሁ ይሖዋ ይባርካችኋል” ብሏል። አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያት በታማኝነት እርስ በርስ መደጋገፋችሁና ደስታችሁን መጋራታችሁ አርኪ በሆነው የትዳር ጎዳና ላይ በደስታ እንድትጓዙ ያስችላችኋል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.6 አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን ፈትቶ ሌላ ማግባት የሚችለው የትዳር ጓደኛው ካመነዘረ ማለትም ከጋብቻ ውጭ የፆታ ግንኙነት ከመፈጸመ ብቻ እንደሆነ ኢየሱስ ተናግሯል።—ማቴዎስ 19:9

^ አን.9 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.22 መጽሐፍ ቅዱስ ምንዝር የፈጸመውን የትዳር ጓደኛ ለመፍታት ወይም ላለመፍታት የመወሰን መብት ያለው ያልበደለው የትዳር ጓደኛ እንደሆነ ይገልጻል። (ማቴዎስ 19:9) በዚህ ረገድ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በነሐሴ 8, 1995 ንቁ! (እንግሊዝኛ) መጽሔት ላይ የወጣውን “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት:- ምንዝር—ይቅር ማለት አለብኝ ወይስ የለብኝም?” የሚለውን ርዕስ ተመልከቱ።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

መጽሐፍ ቅዱስ በትዳር ሕይወት ውስጥ እንደ መንገድ ካርታ ሆኖ ያገለግላል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ስለ አንድ ችግር መወያየት ሲያስፈልጋችሁ

ሁለታችሁም ድካም የማይጫጫናችሁን ጊዜ ምረጡ

ከመነቃቀፍ ተቆጠቡ፤ አንዳችሁ ለሌላው አዎንታዊ አመለካከት ይኑራችሁ።

ንግግር ከማቋረጥ ተቆጠቡ፤ ተራ በተራ ተነጋገሩ።

የትዳር ጓደኛችሁን ስሜት ተረዱ።

በትዳር ጓደኛችሁ ሐሳብ በማትስማሙበት ጊዜም እንኳ ስሜቱን መረዳታችሁን ግለጹለት።

ምክንያታዊና የሌላውን ሐሳብ የምትቀበሉ ሁኑ።

ስህተት ስትሠሩ በትሕትና ይቅርታ ጠይቁ።

ፍቅራችሁንና አድናቆታችሁን ግለጹ።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ትዳርን የሰመረ ለማድረግ

ትዳርን የሚያጠናክሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች አጥብቃችሁ ያዙ።

ለትዳራችሁና ለትዳር ጓደኛችሁ ጊዜ መድቡ።

ደግነትንና ፍቅርን አዳብሩ።

እምነት የሚጣልባችሁና ቃል ኪዳናችሁን የምታከብሩ ሁኑ።

ደግና ሰው አክባሪ ሁኑ።

በቤት ውስጥ ያለውን ሥራ ተጋገዙ።

በመካከላችሁ አስደሳች ጭውውት እንዲኖር ጥረት አድርጉ።

አንድ ላይ በመጫወትና በመዝናናት ጊዜ አሳልፉ።

ትዳራችሁን ለማጠናከር ተግታችሁ ሥሩ።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በግል የምታሰላስሉበት

በትዳሬ ውስጥ ይበልጥ ልሠራበት የሚያስፈልገኝ ነጥብ የትኛው ነው?

ይህን ለማድረግ ምን እርምጃዎችን እወስዳለሁ?