ችግሩ ምን ይሆን?
ችግሩ ምን ይሆን?
ትዳር ሙሉ በሙሉ ከችግር ነጻ ይሆናል ብሎ መጠበቅ ከእውነታው የራቀ ነው። ደግሞም በጣም ይጣጣማሉ የሚባሉ የትዳር ጓደኛሞችም እንኳ በሁሉም ነገር ይስማማሉ ማለት ዘበት ነው። በመሆኑም አንድ ዓይነት ችግር ማጋጠሙ አይቀሬ ነው። ዝገት፣ ቀለም የተቀባን ብረት ውስጥ ውስጡን ሊበላው እንደሚችል ሁሉ ትዳርን የሚሸረሽሩ በርካታ ነገሮች አሉ። ትዳርን ለማሻሻል ምን ማድረግ እንደሚቻል ከመመልከታችን በፊት በትዳር ውስጥ ከሚያጋጥሙ ችግሮች መካከል አንዳንዶቹን እስቲ እንመርምር።
ውጥረት የበዛበት ዘመን
መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን ያሉ ብዙ ሰዎች ‘ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎችና በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ እንደሚሆኑ’ አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:2-4) እንዲህ ዓይነቶቹ ባሕርያት ፍጽምና በጎደላቸው ሰዎች መካከል በቀላሉ የሚከሰቱትን እንደ አለመግባባት፣ አንድን ሰው በተሳሳተ መንገድ መረዳትና አሳቢነት የጎደለው ሐሳብ መሰንዘር ያሉ ነገሮች ከልክ በላይ እንዲጋነኑ ሊያደርጉ ይችላሉ።
አንድ ተመራማሪ እንደሚከተለው ብለዋል:- “ዘመናችን ትዳር መያዝ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ግራ የሚያጋባ ነገር የሆነበት ወቅት ነው። በአንድ በኩል . . . ትዳራችንን ማጠናከር የምንችለው እንዴት እንደሆነ የሚገልጹ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው መረጃዎች ማግኘት እንችላለን። . . . በሌላ በኩል ደግሞ ትዳራችን እንዲሰምር የምናደርገውን ጥረት መና የሚያስቀሩ በርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖዎች አሉብን።”
ከእውነታው የራቀ ተስፋ
አንዲት የትዳር አማካሪ “ሰዎች በትዳራቸው ደስተኞች እንዳይሆኑ ከሚያደርጓቸው ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ከእውነታው የራቀ ተስፋ ያላቸው መሆኑ ነው” ብለዋል። ብዙ ባለትዳሮች ትዳርን እንደጠበቁት ሆኖ ሳያገኙት ሲቀሩና የትዳር ጓደኛቸውም ቢሆን እንዳለሙት ዓይነት ሰው አለመሆኑን ሲገነዘቡ ግራ ይጋባሉ። በትዳር ጓደኛቸው ላይ ቀደም ሲል ያላዩትን እንከን ሲመለከቱ ወይም ከዚያ በፊት አቅልለው ያዩት ጉድለት ከገመቱት በላይ ከባድ መሆኑን ሲያስተውሉ እጅግ ያዝናሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ ትዳር “ሥቃይና ሐዘን” ሊያስከትል እንደሚችል በግልጽ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 7:28 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ለምን? አንዱ ምክንያት ፍጹማን ባልሆኑ ሁለት ሰዎች መካከል የሚመሠረት ዝምድና ውሎ አድሮ ያለባቸው ጉድለት ጎልቶ እንዲታይ ስለሚያደርግ ነው።
በተጨማሪም በርካታ ሰዎች ትዳራቸውን የሰመረ ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ ባይታዩም ደስተኛ ትዳር እንዲኖራቸው ይጠብቃሉ። ትዳር ወዲያውኑ ደስተኞች እንደሚያደርጋቸው አድርገው ስለሚያስቡ ደስታ ያለበት ትዳር ለመመሥረት እጅግ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ማከናወን ማለትም ኃላፊነት
መቀበልና ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው ይዘነጋሉ። ከዚህም የተነሳ እውነታውን ሲገነዘቡ በተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚዋጡ ከመሆኑም ሌላ ግራ ይጋባሉ። አብዛኛውን ጊዜ፣ ከትዳር እጅግ ብዙ ነገሮችን ይጠብቁ ከነበረ ከእውነታው ጋር ሲፋጠጡ የሚገጥማቸው ሐዘንም የዚያኑ ያህል የከፋ ይሆናል።ጥሩ የሆነ የሐሳብ ግንኙነት አለመኖር
ጠንካራ ትዳር ለመመሥረት እንዲቻል፣ ባለትዳሮች ከሐሳብ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ሊያስወግዷቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? አንዳንድ ባልና ሚስት ከልብ የማይደማመጡ ከመሆናቸውም ሌላ ስሜታቸውን በግልጽ አይነጋገሩም። በመሆኑም በፍቅር የተሞላው ሞቅ ያለ ጭውውታቸው ዕለታዊ እንቅስቃሴን ብቻ በሚመለከት አጭርና ድርቅ ያለ አነጋገር ይተካል። ያደርጉት የነበረው ዓላማ ያለው ግልጽ ጭውውት እየጠፋ ሄዶ በረባ ባልረባው ወደ መነታረክ ያመራሉ። የትዳር ጓደኛቸው ለሚሰነዝረው ቃል ያልሆነ ትርጉም መስጠት የሚጀምሩ ሲሆን ይህም አለመግባባት ይፈጥራል፤ ከዚያም መሰዳደብና መኮራረፍ ይከተላል።
ብዙ ባለትዳሮች የትዳር ጓደኛቸውን መልካም ባሕርይ የማያስተውሉ ወይም ቢያስተውሉ እንኳ አድናቆታቸውን የማይገልጹ መሆናቸው ያሳዝናል። በተጨማሪም ብዙ ያገቡ ሴቶች በአሁኑ ጊዜ ባለው የሥራ ሁኔታ ምክንያት ከቤት ውጭ የሚሠሩ ሲሆን ቤት ውስጥ ያለውን አብዛኛውን ሥራም የሚያከናውኑት እነሱው ናቸው፤ ይህ ደግሞ ያበሳጫቸዋል። ከዚህም በላይ፣ ብዙ ሚስቶች ስሜታዊ ፍላጎታቸው ችላ እንደተባለ ይሰማቸዋል።
ታዲያ ትዳራችሁ የሰመረ እንዲሆን ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ቀጥሎ የቀረቡትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተወሰዱ ጠቃሚ ምክሮች ልብ በሏቸው።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አንዳንድ ባልና ሚስቶች ከልብ የማይደማመጡ ከመሆናቸውም ሌላ ስሜታቸውን በግልጽ አይነጋገሩም
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በርካታ ሰዎች ትዳራቸውን የሰመረ ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ ባይታዩም ደስተኛ ትዳር እንዲኖራቸው ይጠብቃሉ