በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን በደስታ ማምለክ የምችለው እንዴት ነው?

አምላክን በደስታ ማምለክ የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ

አምላክን በደስታ ማምለክ የምችለው እንዴት ነው?

የ16 ዓመቱ ጆሽዋ አልጋው ላይ ጋደም ብሏል። እናቱ መኝታ ቤቱ በር ላይ ቆማ ኮስተር በማለት “ጆሽዋ፣ ተነሳ እንጂ! ስብሰባ እንዳለን ታውቅ የለም!” አለችው። ጆሽዋ ያደገው በይሖዋ ምሥክር ቤተሰብ ውስጥ ሲሆን ቤተሰቡ ከሚያከናውናቸው ቋሚ የአምልኮ እንቅስቃሴዎች መካከል ክርስቲያናዊ ስብሰባ ይገኝበታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጆሽ ወደ ስብሰባ የመሄድ ፍላጎቱ ቀንሷል።

ጆሽ እየተነጫነጨ “እማዬ! እኔ ባልሄድስ፤ የግድ መሄድ ይኖርብኛል?” አላት።

እናቱ “እንግዲህ መነጫነጩን ተውና ተነስተህ ለባብስ፤ ዛሬም አርፍጄ መድረስ አልፈልግም!” ብላው መሄድ ጀመረች።

ጆሽ እናቱ ከአጠገቡ ብዙም ሳትርቅ “እማ፣ ይህ ያንቺ ሃይማኖት ሊሆን ይችላል፤ ይህ ሲባል ግን የኔም ሃይማኖት ነው ማለት አይደለም” በማለት ተናገረ። ይህን ሲል እናቱ ኮቴዋ ስላልተሰማ ቆማ የተናገረውን እንደሰማች ገብቶታል። እሷም ምንም መልስ ሳትሰጠው ሄደች።

ጆሽዋ በተናገረው ነገር ትንሽ የጸጸት ስሜት ተሰማው። በእርግጥ እናቱን ማሳዘን አይፈልግም። ይሁን እንጂ ይቅርታ ለመጠየቅም አላሰበም። ማድረግ የሚችለው ነገር ቢኖር መነሳት ነው።

ጆሽ በረጅሙ ተንፍሶ ከአልጋው ላይ ተነሳና ልብሱን መለባበስ ጀመረ። ከዚያም ለራሱ እንዲህ አለ:- “ይዋል ይደር እንጂ የራሴን ውሳኔ ማድረጌ አይቀርም። እኔ በጉባኤያችን እንዳሉት ሌሎች ልጆች አይደለሁም። ክርስቲያን የመሆን ፍላጎት ያለኝ አይመስለኝም!”

አንተስ እንደ ጆሽ ዓይነት ስሜት ተሰምቶህ ያውቃል? አንዳንድ ጊዜ፣ ሌሎች በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ደስ ብሏቸው ሲካፈሉ አንተ ግን ግዴታ ስለሆነብህ ብቻ እንደምታደርጋቸው ይሰማሃል? ለምሳሌ ያህል:-

▪ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት አስተማሪህ የሰጠህን የቤት ሥራ እንደመሥራት ይሆንብሃል?

▪ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ያስፈራሃል?

▪ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ብዙውን ጊዜ አሰልቺ ይሆንብሃል?

እንደነዚህ ላሉት ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ “አዎ” የሚል ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ጥቂት ማስተካከያዎችን ብቻ በማድረግ ለአምላክ በምታቀርበው አገልግሎት እንዴት መደሰት እንደምትችል መማር ትችላለህ። እስቲ ይህን ማድረግ የምትችልበትን መንገድ እንመልከት።

አንደኛው ተፈታታኝ ሁኔታ:- መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት

ቀላል የማይሆነው ለምንድን ነው? ምናልባት ጥሩ የጥናት ልማድ ያለህ ሰው እንዳልሆንክ ይሰማህ ይሆናል። አእምሮህን መሰብሰብ ሊያስቸግርህ ማለትም ረጅም ሰዓት ቁጭ ብለህ በአንድ ነገር ላይ ማተኮር ከባድ ሊሆንብህ ይችላል! ከዚህም በላይ ከትምህርትህ ጋር በተያያዘ ማጥናት የሚኖርብህ ብዙ ነገር ይኖር ይሆናል።

ማጥናት የሚኖርብህ ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ከመሆኑም ሌላ “እውነትን ለማስተማር፥ የተሳሳቱትን ለመገሠጽ፥ ስሕተትን ለማረምና ለትክክለኛ ኑሮ የሚበጀውን መመሪያ ለመስጠት ይጠቅማል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:16፣ የታረመው የ1980 ትርጉም) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህና ባነበብከው ነገር ላይ ማሰላሰልህ አዲስ እውቀት ሊያስገኝልህ ይችላል። ምንጊዜም ቢሆን ጥሩ ነገር ለማግኘት መልፋት እንደሚያስፈልግ መገንዘብ ይኖርብሃል። አንድን ጨዋታ ጥሩ አድርገህ ለመጫወት ከፈለግህ ሕጎቹን መማርና መለማመድ አለብህ። ሰውነትህ ጤናማና ጠንካራ እንዲሆን ከፈለግህ ስፖርት መሥራት ይኖርብሃል። ስለ ፈጣሪህ ለማወቅ ከፈለግህ ደግሞ የአምላክን ቃል ማጥናት ያስፈልግሃል።

አንዳንድ እኩዮችህ ምን ይላሉ? “በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ያደረግሁት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስገባ ነበር። በምማርበት ትምህርት ቤት ያሉት ልጆች የማይፈጽሙት መጥፎ ድርጊት አልነበረም፤ ስለዚህ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ አንዳንድ ውሳኔዎችን ማድረግ ነበረብኝ:- ‘ልጆቹ የሚያደርጉትን ነገር የማድረግ ፍላጎት አለኝ? ወላጆቼ የሚያስተምሩኝ ነገር በእርግጥ እውነት ነው?’ መልሱን ራሴ መርምሬ ማግኘት ነበረብኝ።”—ትሼድዛ

“የተማርኩት ነገር እውነት መሆኑን የተጠራጠርኩበት ጊዜ አልነበረም፤ ይሁን እንጂ እውነት መሆኑን ራሴ ማረጋገጥ ፈለግሁ። አምላክን ማምለክ ያለብኝ አምኜበት እንጂ ወላጆቼ ስለሚጠብቁብኝ መሆን የለበትም።”—ኔሊሳ

ማድረግ የምትችለው ነገር። ለአንተ የሚስማማህን የጥናት ፕሮግራም አውጣ። ምርምር ልታደርግባቸው የምትፈልጋቸውን ርዕሰ ጉዳዮች አንተው ራስህ ምረጥ። ከየት መጀመር ትችላለህ? ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? * እንደተሰኘው ያለ መጽሐፍ ተጠቅመህ መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት በማጥናት የምታምንባቸውን ነገሮች በጥንቃቄ ለምን አትመረምርም?

የድርጊት መርሃ ግብር። ለመንደርደሪያ ያህል ከዚህ በታች ከቀረቡት ውስጥ ይበልጥ ልትመረምራቸው የምትፈልጋቸውን ሁለት ወይም ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሶች ምረጥ። ካልሆነ ደግሞ ከምትፈልጋቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዳንዶቹን መጻፍ ትችላለህ።

□ በእርግጥ አምላክ አለ?

□ መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት ሰዎች በአምላክ መንፈስ እንደተመሩ እንዴት እርግጠኛ መሆን እችላለሁ?

□ ነገሮች ወደ ሕልውና የመጡት በዝግመተ ለውጥ ሳይሆን በመፈጠር ነው ብዬ እንዳምን የሚያደርገኝ ምንድን ነው?

□ የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? እውን የሆነ መስተዳድር እንደሆነ ማረጋገጥ የምችለውስ እንዴት ነው?

□ ከሞት በኋላ የሚኖረውን ሁኔታ በሚመለከት የማምንበትን ነገር ለሌሎች ማስረዳት የምችለው እንዴት ነው?

□ ትንሣኤ ይኖራል ብዬ እንዳምን የሚያደርገኝ ምንድን ነው?

□ እውነተኛው ሃይማኖት የቱ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን የምችለው እንዴት ነው?

□ ․․․․․

ሁለተኛው ተፈታታኝ ሁኔታ:- በአገልግሎት መካፈል

ቀላል የማይሆነው ለምንድን ነው? ለሌሎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መናገር ወይም ደግሞ በአገልግሎት ላይ ሳለህ የትምህርት ቤት ጓደኛህን ማግኘት ሊያስፈራ ይችላል።

በአገልግሎት መካፈል የሚኖርብህ ለምንድን ነው? ኢየሱስ ተከታዮቹን “ሕዝቦችን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው” በማለት አዟቸዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ለመስበክ የሚያነሳሱን ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በአንዳንድ ቦታዎች በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ አብዛኞቹ ወጣቶች በአምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ ያምናሉ። ሆኖም እነዚህ ወጣቶች ስለ ወደፊቱ ጊዜ እውነተኛ ተስፋ የላቸውም። አንተ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ አማካኝነት አብዛኞቹ እኩዮችህ የሚፈልጉትንና የሚያስፈልጋቸውን መረጃ አግኝተሃል!

አንዳንድ እኩዮችህ ምን ይላሉ? “እኔና ጓደኛዬ ውጤታማ መግቢያዎችን የተዘጋጀን ከመሆኑም በላይ ሰዎች ለሚያነሷቸው የተቃውሞ ሐሳቦች እንዴት መልስ መስጠት እንደምንችልና ተመላልሶ መጠየቆችን እንዴት እንደምናደርግ ተለማመድን። በአገልግሎት ለመካፈል የበለጠ ጥረት ባደረግሁ መጠን አገልግሎቴ ይበልጥ አስደሳች እየሆነልኝ መጣ።”—ኔሊሳ

“አንዲት እህት በጣም ረድታኛለች! በዕድሜ ስድስት ዓመት የምትበልጠኝ ሲሆን አገልግሎት ይዛኝ ትወጣ እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ ቁርስ አብሬያት እንድበላ ትጋብዘኝ ነበር። አስተሳሰቤን እንዳስተካክል የረዱኝን አበረታች ጥቅሶች አሳይታኛለች። በአሁኑ ጊዜ ሰዎችን የመርዳት ፍላጎት ሊኖረኝ የቻለው በእሷ ግሩም ምሳሌነት የተነሳ ነው። ውለታዋን መመለስ የምችል አይመስለኝም!”—ሻንቲ

ማድረግ የምትችለው ነገር። ወላጆችህን አስፈቅደህ፣ ከጉባኤህ ውስጥ አብረኸው ልታገለግል የምትችል በዕድሜ ከአንተ የሚበልጥ ሰው ፈልግ። (የሐዋርያት ሥራ 16:1-3) መጽሐፍ ቅዱስ “ብረት ብረትን እንደሚስል፣ ሰውም ሌላውን ሰው እንደዚሁ ይስለዋል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 27:17) ተሞክሮ ካካበቱ በዕድሜ የሚበልጡህ ሰዎች ጋር መቀራረብ ብዙ ጥቅሞች አሉት። የ19 ዓመቷ አሌክሲስ “እንደ እውነቱ ከሆነ በዕድሜ ከሚበልጡህ ሰዎች ጋር መሆን ሁሉን ነገር ቀላል ያደርግልሃል” በማለት ተናግራለች።

የድርጊት መርሃ ግብር። ከዚህ በታች ከወላጆችህ ሌላ በአገልግሎት ሊረዳህ የሚችል በጉባኤህ ውስጥ ያለ ሰው ስም ጻፍ።

․․․․․

ሦስተኛው ተፈታታኝ ሁኔታ:- በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት

ቀላል የማይሆነው ለምንድን ነው? ቀኑን ሙሉ ክፍል ውስጥ ቁጭ ብለህ ስትማር ውለህ እንደገና ለአንድ ወይም ለሁለት ሰዓት ተቀምጠህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ንግግሮችን ማዳመጥ በጣም ሊከብድህ ይችላል።

መሰብሰብ የሚኖርብህ ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖችን እንዲህ በማለት ይመክራል:- “እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ።”—ዕብራውያን 10:24, 25

አንዳንድ እኩዮችህ ምን ይላሉ? “ለጉባኤ ስብሰባዎች መዘጋጀት ልናደርገው የሚገባ ነገር ነው። አንዳንድ ጊዜ ራስህን ማሳመን ያስፈልግሃል። ከተዘጋጀህ ጉባኤ ላይ ውይይት እየተደረገበት ያለው ነገር እንግዳ ስለማይሆንብህ አልፎ ተርፎም ልትሳተፍ ስለምትችል ስብሰባው አስደሳች ይሆንልሃል።”—ኤልዳ

“በአንድ ወቅት፣ በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ስሰጥ ስብሰባዎቹ ይበልጥ አስደሳች እንደሚሆኑልኝ ማስተዋል ጀመርኩ።”—ጀሲካ

ማድረግ የምትችለው ነገር። በቅድሚያ ጊዜ መድበህ ተዘጋጅ። ከቻልክ ደግሞ በስብሰባዎቹ ላይ ሐሳብ ስጥ። እንዲህ ማድረግህ አንተም ቦታ እንዳለህ እንዲሰማህ ያደርጋል።

ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- ይበልጥ የሚያስደስትህ አንድን የጨዋታ ዓይነት በቴሌቪዥን መመልከት ነው ወይስ ሜዳ ውስጥ ገብቶ መጫወት? በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ተመልካች ከመሆን ይልቅ ተሳታፊ መሆን ይበልጥ አስደሳች ነው። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ረገድም እንዲህ ያለ አመለካከት እንዲኖርህ ለምን አታደርግም?

የድርጊት መርሃ ግብር። ከታች በተሰጠው ክፍት ቦታ ላይ በየሳምንቱ 30 ደቂቃ መድበህ ለጉባኤ ስብሰባዎች መዘጋጀት የምትችለው መቼ እንደሆነ ጻፍ።

․․․․․

ብዙ ወጣቶች “እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ” የሚሉትን የመዝሙር 34:8 ቃላት እውነተኝነት በራሳቸው ተሞክሮ እያዩት ነው። ሰዎች በጣም ስለሚጣፍጥ ምግብ ሲናገሩ መስማት ምን ያህል እርካታ ያስገኛል? እርካታ የሚያስገኘው ምግቡን ራሳችን መቅመሳችን አይደለም? አምላክን በማምለክ ረገድም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ አንተው ራስህ ቀምሰህ እይ። መጽሐፍ ቅዱስ ቃሉን የሚሰማ ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ የሚያደርግ ሰው “በሥራው የተባረከ [“ደስተኛ፣” NW] ይሆናል” በማለት ይናገራል።—ያዕቆብ 1:25

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.19 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ በአሥራዎቹ ዕድሜ ለሚገኝ ወጣት በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል አሰልቺ መስሎ ሊታየው የሚችለው ለምንድን ነው?

▪ በዚህ ርዕሰ ትምህርት ውስጥ ከተጠቀሱት ሦስት የአምልኮ ገጽታዎች መካከል አንተ ማሻሻያ ማድረግ የምትፈልገው በየትኛው ላይ ነው? እንዴትስ?

[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰውነትህ ጤናማና ጠንካራ እንዲሆን ከፈለግህ ስፖርት መሥራት አለብህ። በመንፈሳዊም ጤናማና ጠንካራ መሆን ከፈለግህ የአምላክን ቃል ማጥናት ያስፈልግሃል