በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከኮዋቲ ጋር እናስተዋውቅህ

ከኮዋቲ ጋር እናስተዋውቅህ

ከኮዋቲ ጋር እናስተዋውቅህ

ብራዚል የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በጫካ ውስጥ እየተንሸራሸርክ ነው እንበል። ኮዋቲ የተባሉት እንስሳት ድንገት ወዳንተ ግር ብለው ሲመጡ አየህ። ጥቃት ያደርሱብኝ ይሆን ብለህ እንደ መፍራት ብለህ ይሆናል። ግን አይዞህ! እነዚህ ትንንሽ እንስሳት እንደሚናከሱ ቢታወቅም አሁን ትኩረታቸው ያረፈው ባንጠለጠልከው ቦርሳ ላይ ነው። እነሱ ምንጊዜም የሚፈልጉት የሚበሉት ነገር ብቻ ነው። እንዲያውም ትሎችን፣ እንሽላሊቶችን፣ ሸረሪቶችን፣ አይጦችን፣ ፍራፍሬዎችን፣ ሌላው ቀርቶ የወፎችን እንቁላል ጨምሮ ያገኙትን ማንኛውንም ነገር ስልቅጥ አድርገው ይበላሉ።

ኮዋቲ፣ ሸለምጥማጥ መሰል እንስሳ ሲሆን ረዘም ያለ ሰውነትና ጅራት እንዲሁም ሾጠጥ ያለ ለስላሳ አፍንጫ አለው። የሰውነቱ ርዝማኔ 66 ሴንቲ ሜትር የሚደርሰውና የጅራቱ ርዝማኔም ያንኑ ያህል የሆነው ይህ የአሜሪካ የሐሩር ክልል አጥቢ እንስሳ በአብዛኛው የሚኖረው ከደቡባዊ ምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ እስከ ሰሜናዊ አርጀንቲና ባለው አካባቢ ነው።

እንስቶቹ ኮዋቲዎች እስከ 20 በሚደርስ ቁጥር በመንጋ ሆነው የሚጓዙ ሲሆን ተባዕቶቹ ግን ብቻቸውን መሆን ይወዳሉ። በየዓመቱ የመራቢያቸው ወቅት ሲደርስ አንዱ ተባዕት ይሄድና ከእንስቶቹ መንጋ ጋር ይቀላቀላል። ይህ ከሆነ በኋላ ከሰባት እስከ ስምንት ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ፣ ያረገዙት እንስቶች ከመንጋው ተለይተው በመሄድ በዛፎች ላይ ጎጆ ይሠራሉ። እያንዳንዷ እንስት ሦስት ወይም አራት ልጆች ትወልዳለች። አዲሶቹ እናቶች ከወለዱ በኋላ ስድስት ሳምንታት ቆይተው ከነልጆቻቸው በመምጣት ከመንጋው ጋር ይቀላቀላሉ። ጨቅላዎቹ ኮዋቲዎች ሲታዩ የሚንከባለሉ ትንንሽ የፀጉር ኳሶች ይመስላሉ።

ኮዋቲዎች በጫካ ውስጥ በሚዘዋወሩበት ጊዜ አሁንም አሁንም አየሩን ያነፈንፋሉ እንዲሁም መሬቱን በጥፍሮቻቸው ይጭራሉ። በበቆሎ ሰብሎችና በዶሮ ቤቶች ላይ ከባድ ጥፋት የሚያደርሱ በመሆናቸው ገበሬዎች እነሱን ሲያዩ ደስ አይላቸውም። እነዚህ እንስሳት ከአዳኞች እንዴት ማምለጥ እንደሚችሉ ያውቁበታል። እነዚህ ትንንሽ ጮሌ ፍጥረታት በዛፎች ውስጥ ይሸሸጋሉ። ሌላም ዓይነት የማምለጫ ዘዴ አላቸው። የተኩስ ድምፅ ወይም የእጅ ጭብጨባ ሲሰሙ መሬት ላይ በመውደቅ የሞቱ ያስመስላሉ! አዳኙ ሊይዛቸው ወደ ወደቁበት ቦታ ሲቀርብ ፈትለክ ብለው ይሮጣሉ!

በሚቀጥለው ጊዜ ብራዚልን ስትጎበኝ ምናልባት የኮዋቲ መንጋ ያጋጥምህ ይሆናል። ከሆነ አትፍራ። አብዛኛውን ጊዜ ሰውን አይጎዱም። ይሁን እንጂ ትንሽ የምግብ ፍርፋሪ ብትጥልላቸው ይበልጥ ደስ ይላቸዋል!