በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

“በዚህ ዓመት [በ2007] የቀለጠው [የአርክቲክ] በረዶ መጠን ፍጹም አስደንግጦናል፤ ምክንያቱም በዚህ ዓመት የቀለጠው የበረዶ መጠን ቀደም ሲል ከተመዘገቡት ሪኮርዶች ሁሉ መብለጥ ብቻ ሳይሆን ፈጽሞ ሊነጻጸር የማይችል ሆኗል።”—ማርክ ሴሬይ፣ ናሽናል ስኖው ኤንድ አይስ ዴታ ሴንተር፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ዘ ኒው ኤኮኖሚክስ ፋውንዴሽን የተሰኘው ተቋም እንደገለጸው ከሆነ “በዓለም ላይ ያለ ሰው ሁሉ በተፈጥሮ ሀብቶች የዩናይትድ ስቴትስን ሕዝብ ያህል የሚጠቀም ቢሆን ኖሮ በዚህ ደረጃ ለመኖር እንደ ምድር ያሉ 5.3 ፕላኔቶች ያስፈልጋሉ። . . . በተሰጠው ግምት መሠረት በፈረንሳይና በብሪታንያ ሕዝብ ደረጃ ለመኖር 3.1፣ በስፔን ሕዝብ ደረጃ ለመኖር 3.0፣ በጀርመን ሕዝብ ደረጃ ለመኖር 2.5 እና በጃፓን ሕዝብ ደረጃ ለመኖር 2.4 ፕላኔቶች ያስፈልጋሉ።”—ሮይተርስ ኒውስ ሰርቪስ፣ ብሪታንያ

“ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል”?

በዩናይትድ ስቴትስ ኖርዝ ካሮላይና፣ ዱራም ውስጥ የሚገኘው የዱክ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ማዕከል “ለአብዛኞቹ ሕሙማን፣ ከደም ባንክ የተወሰደ ደም መስጠት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል” የሚል ዘገባ አውጥቷል። ጥናቶች እንዳመለከቱት ደም የተሰጣቸው ሕሙማን ደም ካልወሰዱት ታካሚዎች ይልቅ “ለልብ በሽታ፣ በጭንቅላት ውስጥ ለሚከሰት የደም መፍሰስ ችግር አልፎ ተርፎም ለሞት የመዳረግ አጋጣሚያቸው ከፍተኛ ነው።” ለምን? “በቀይ የደም ሕዋሳት ውስጥ ያለው ናይትሪክ ኦክሳይድ፣ ደሙ ገና ከሰውነት እንደወጣ ወደ ሌላ ዓይነት ውህድ መለወጥ ይጀምራል።” ቀይ የደም ሕዋሳት ኦክስጂን ተሸክመው ወደ ሰውነት ክፍሎች ለማድረስ ሲሄዱ የደም ሥሮች ክፍት ሆነው በቀላሉ እንዲያሳልፏቸው ወሳኝ ድርሻ ያለው ናይትሪክ ኦክሳይድ ነው። “በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕሙማን እየተሰጣቸው ያለው ደም ኦክስጅን ለማድረስ በቂ አቅም የሌለው ነው” በማለት ሪፖርቱ ይናገራል።

የቴሌቪዥን ሱሰኝነት በቡታን

በሂማልያ የምትገኘው በንጉሥ የምትተዳደር ቡታን የተባለች ትንሽ አገር በዘመኑ መገናኛ ብዙኃን ላለመማረክ ለአሥርተ ዓመታት ስትከላከል ቆይታለች። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ነዋሪዎቿ በ1998 የተካሄደውን የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ለማየት ባለመቻላቸው ቅሬታቸውን ካሰሙ ወዲህ መንግሥት በ1999 ቴሌቪዥን ወደ አገሪቱ እንዲገባ ፈቀደ። አሁን ሕዝቡ 40 ጣቢያዎችን እያቀያየረ ማየት የሚችል ሲሆን ገና ከአሁኑ የሆሊዉድ ፊልሞችና በሕንድ ቴሌቪዥን የሚቀርቡ ተከታታይ ፊልሞች ሱስ እንደያዘው ከቡታን የተገኘ ዘገባ ይናገራል። ቤተሰቦች ቀደም ሲል ያደርጉት እንደነበረው አንድ ላይ ተቀምጠው በመዝፈንና በማውራት ፈንታ አሁን የሚሰበሰቡት ቴሌቪዥን ለማየት ነው። አንዲት ሴት ጸሎትን ጨምሮ ለሌላው ነገር የምታውለውን ጊዜ ሁሉ እንደሚሻማባት በምሬት ተናግራለች። “ለመጸለይ ከፍተኛ ጥረት ባደርግም አእምሮዬ ግን ሁልጊዜም የሚያስበው ስለ ቴሌቪዥን ነው” ማለቷን ዘ ፔኒንሱላ የተሰኘው የኳታሩ ዕለታዊ ጋዜጣ ዘግቧል። “ብዙዎቹ የሚፈሩት፣ እንደ አብዛኛው የውጪ ዓለም ሁሉ እነሱም የማያስፈልጓቸውን ነገሮች የመግዛት አባዜ እንዳይጠናወታቸው ነው። ‘ቴሌቪዥንና ማስታወቂያዎች ሕዝቡ አሁን ባለው ኢኮኖሚያዊ አቅም ሊያሟላው የማይችለውን ነገር የመግዛት ፍላጎት ይቀሰቅሳሉ።’”

ትኩረቱ የተከፋፈለ ሠራተኛ

“የቢሮ ሕይወት አንዳንድ ጊዜ ለማያባሩ የስልክ ጥሪዎች፣ የማስጠንቀቂያ ደወሎችና ሥራን ለሚያስተጓጉሉ ሌሎች ጉዳዮች ምላሽ መስጠት ብቻ ሊመስል ይችላል” በማለት ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ይገልጻል። ተመራማሪዎች ያደረጉት ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ ጥናቱ የተካሄደባቸው የመረጃ አገልግሎት የሚሰጡ ሠራተኞች ሥራቸውን የሚያስተጓጉል ጉዳይ ሳያጋጥማቸው ሥራቸውን መሥራት የሚችሉት በአማካይ ለሦስት ደቂቃ ብቻ ነው። ሥራን የሚያስተጓጉሉ ጉዳዮች ከእያንዳንዱ የሥራ ቀን ላይ ሁለት ሰዓት ሊያባክኑ ስለሚችሉ አንዳንድ ሥራ የሚበዛባቸው የቢሮ ሠራተኞች አስቸኳይ የሆነውን ጉዳይ አስቸኳይ ካልሆነው ለመለየት እንዲረዳቸው ኮምፒውተር ይጠቀማሉ። ሁሉም ሠራተኞች እንዲጠቀሙበት ከቀረበው ሐሳብ መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:- “ለሰዎች ሐቁን ንገራቸው፤ . . . ምንም ጊዜ ከሌለህ ይህንኑ በግልጽ ንገራቸው።” በተጨማሪም “ሥራህን እስክትጨርስ ድረስ ኢሜይልህን፣ ስልክህንና ፈጣን የኮምፒውተር መልእክት መቀበያዎችን ለመዝጋት” የሚያስችል ቆራጥነት ይኑርህ።