በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የብሪታንያ ቦዮች አሁንም ድንቅ ናቸው

የብሪታንያ ቦዮች አሁንም ድንቅ ናቸው

የብሪታንያ ቦዮች አሁንም ድንቅ ናቸው

ብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በ19ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በእንግሊዝ፣ በስኮትላንድና በዌልስ 6,000 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው የጀልባ መሄጃ ቦዮች ነበሩ። እነዚያ ቦዮች የተገነቡት ለምን ነበር? በ21ኛው መቶ ዘመን እየተጠቀሙባቸው ያሉትስ እነማን ናቸው?

በ18ኛው መቶ ዘመን በብሪታንያ ተካሂዶ በነበረው የኢንዱስትሪ አብዮት ወቅት ጥሬ ዕቃዎችንና የፋብሪካ ምርቶችን ለማጓጓዝ የሚያስችል ርካሽና ፈጣን መጓጓዣ አስፈልጎ ነበር። ከዚያ በፊት ጭነት የሚጓጓዘው በፈረሶች ወይም በፈረሶች በሚጎተቱ ሠረገላዎች ነበር፤ ይሁን እንጂ በክረምት ወራት መንገዶች በጎርፍ ስለሚሸረሸሩና በጣም ስለሚጨቀዩ ጭነቶችን ማጓጓዝ ከአቅም በላይ ይሆን ነበር። የጀልባ መሄጃ ቦዮች ከተሠሩ በኋላ ግን በአንድ ፈረስ ብቻ እስከ 300 ኩንታል የሚደርስ ጭነት የያዘ ጀልባ በመጎተት ጭነቱን በቀላሉና በፍጥነት ማጓጓዝ ተቻለ።

በ1761 የብሪጅዎተር መስፍን፣ በማዕድን ማውጫው የሚመረተውን የድንጋይ ከሰል 16 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ወደ ማንቸስተር ለማጓጓዝ የጀልባ መሄጃ ቦይ አስገነባ። ይህም ለመስፍኑ ትርፍ ያስገኘለት ከመሆኑም በላይ በማንቸስተር የድንጋይ ከሰል ዋጋ በግማሽ እንዲቀንስ አድርጓል። በ1790 ግራንድ ክሮስ ካናል የሚባል ረቀቅ ያለ የጀልባ መሄጃ ቦይ የተሠራ ሲሆን ይህ ቦይ የኋላ ኋላ አራት ትላልቅ ወንዞችን አልፎ ተርፎም የእንግሊዝን ዋና ዋና የኢንዱስትሪ መናኸሪያዎች ከወደቦች ጋር ለማገናኘት አስችሏል። የብሪታንያ የጀልባ መሄጃ ቦይ ዘመን የጀመረው በዚህ መንገድ ነበር።

ግንባታና አገልግሎት

በራሱ ጥረት የተማረውንና ሥራውን ያላንዳች የሒሳብ ስሌት ወይም ንድፍ የሚያከናውነውን ጀምስ ብሪንድሊን ጨምሮ የተዋጣላቸው መሐንዲሶች፣ ውኃ የተለያዩ መልክአ ምድሮችን አቆራርጦ እንዲያልፍ ማድረግ የሚቻልበትን ዘዴ ቀየሱ። በኋላም ናቪጌተርስ ተብለው የሚጠሩት የቀን ሠራተኞች የውኃ መውረጃ ቦዮችን፣ መተላለፊያ ዋሻዎችን፣ ውኃ መዝጊያዎችንና (locks) ድልድዮችን ሠሩ። እነዚህ የግንባታ ሥራዎች አሁንም ድረስ ድንቅ የፈጠራ ውጤቶች ተደርገው ይታያሉ።

ከዚህም በላይ እንደ ከሰል ድንጋይ፣ ኖራ፣ በሃ ድንጋይ፣ የሸክላ ሰሃን ለመሥራት የሚያገለግል አፈር፣ የብረት ማዕድን፣ ጡብና ዱቄት ያሉ ነገሮችን ለማጓጓዝ የሚያስችሉ 20 ሜትር ርዝመትና 2 ሜትር ስፋት ያላቸው “ጠባብ ጀልባዎች” በእንጨት ተሠርተው ነበር። እነዚህ ጀልባዎች በቦዩ ዳርና ዳር በሚሄዱ ፈረሶች ይጎተቱ የነበረ ሲሆን “በራሪ ጀልባዎች” ተብለው ይጠሩ ነበር። ጀልባዎቹ አስቸኳይ ወይም ቶሎ የሚበላሹ ዕቃዎችን ያለ እረፍት በማጓጓዝ ፈጣን አገልግሎት ይሰጣሉ፤ ሠራተኞቻቸውም ሌሊቱን ሙሉ ይሠሩ ነበር።

በአንዳንድ ቦዮች ላይ ፈረሶች በየተወሰነ ሰዓት እየተቀያየሩ በሰዓት በአማካይ 15 ኪሎ ሜትር በመጋለብ 120 መንገደኞችን ያጓጉዙ ነበር። እንደ በራሪዎቹ ጀልባዎች ሁሉ እነዚህም ሌሎች ጀልባዎችን ቀድመው የማለፍ መብት የነበራቸው ሲሆን በብሪጅዎተር ቦይ ላይ ከፊታቸው የሚያጋጥማቸውን የማንኛውንም ጀልባ መጎተቻ ገመድ ለመቆራረጥ የሚያስችል ትልቅ ስለት ከፊት ለፊታቸው ተገጥሞላቸዋል! የእነዚህ ቦዮች መገንባት ተራው ሕዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ በአነስተኛ ዋጋ ምቾት ባለው መንገድ ረጅም ርቀት እንዲጓዝ አስችሎታል።

ጠባብ በሆነ ጀልባ ላይ እየኖሩ መሥራት

በጀልባ ላይ የሚሠሩት ሰዎች ሕይወት በጣም ከባድ ነበር። የሰዎቹ ሥራ አስቸጋሪ ከመሆኑም ባሻገር ብዙውን ጊዜ አደገኛ ነበር። ሁልጊዜ በጉዞ ላይ በመሆናቸው የመማር አጋጣሚያቸው በጣም ጠባብ ሲሆን እያደር በዙሪያቸው ካለው ሕዝብ እየተገለሉ ይሄዳሉ።

በጀልባዎች ላይ የሚኖሩት ሰዎች ጀልባዎቻቸውን ለማሳመር በውጪ በኩል አልፎ ተርፎም ከበስተኋላ በሚገኘው ጠባብ ክፍል ውስጥ የተለያዩ መልክዓ ምድራዊ ገጽታዎችን፣ አበባዎችንና የጂኦሜትሪ ንድፎችን በደማቅ ቀለማት ይስሉ ነበር። ይህ ልማዳቸው የራሳቸው የሆነ የሥነ ጥበብ ክህሎት እንዲያዳብሩ አድርጓቸዋል። ከኋላ በኩል የሚገኘው መኖሪያ ክፍል 3 ሜትር በ2 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን የጀልባው ነጂ፣ ሚስቱና ልጆቹ ይኖሩበታል። በጀልባ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ተጣጥፈው ለሌላ አገልግሎት የሚውሉ አልጋዎችን እንዲሁም በውስጣቸው ዕቃ ማስቀመጥ የሚችሉ ወንበሮችን በመሥራት ክፍላቸው ይበልጥ እንዳይጣበብ ለማድረግ ይጥሩ ነበር። መደርደሪያዎቹ ላይ የተሰቀሉት ዳንቴሎች፣ የሚያማምሩት የሸክላ ዕቃዎችና በምድጃው ዙሪያ የተቀመጡት የሚያብረቀርቁ የናስ ጌጣጌጦች ለክፍሉ ድምቀት ይጨምሩለታል። ይህ ሁሉ ነዋሪው ምቾት እንዲሰማው የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ደስ የሚል ስሜት ይፈጥርለታል። ታታሪ የሆነችው የጀልባው ነጂ ሚስት ተደራራቢ ሥራ ቢኖርባትም እንዲሁም ብዙውን ጊዜ በጭነት ምክንያት አካባቢው ቶሎ ቶሎ ቢቆሽሽም ቤተሰቧንም ሆነ ጀልባቸውን በንጽሕና ለመያዝ ብርቱ ጥረት ታደርጋለች። ሌላው ቀርቶ በመቅዘፊያው እጀታ ላይ ለጌጥ ተብሎ የተጠመጠመውን ገመድ እንኳ ሁልጊዜ ፈትጋ ስለምታጥበው በጣም ነጭ ነው።

ቦዮቹ የሚሰጡት አገልግሎት መዳከምና ዛሬ ያሉበት ሁኔታ

በ1825 የጀልባ መሄጃ ቦዮቹ ቀሪ ክፍል ተሠርቶ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ጆርጅ ስቴፈን የተባለ ሰው የስቶክተንንና የዳርሊንግተንን የባቡር መሥመር ከፈተ፤ ይህም በእንፋሎት ለሚንቀሳቀሱ የሕዝብ ማጓጓዣ ባቡሮች የተሠራ የመጀመሪያው የባቡር መሥመር ነው። በቀጣዮቹ 20 ዓመታት ውስጥ ባቡር፣ የጀልባዎቹን ገበያ በመቀማቱ ቦዮቹ ከአገልግሎት ውጪ እየሆኑ ከመምጣታቸውም በላይ ጥገና የሚያደርግላቸው ሰው አጡ። አልፎ ተርፎም የባቡር አገልግሎት ኩባንያዎች ገበያውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ሲሉ አንዳንዶቹን ቦዮች ገዟቸው። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አዳዲስና የተሻሉ መንገዶች ሲሠሩ ቦዮቹ የሚሰጡት አገልግሎት ይበልጥ እየተዳከመ መጣ። ጀልባዎቹ ስለሚሰጡት አገልግሎት ብሩህ ተስፋ የነበራቸው ሰዎችም እንኳ ቦዮቹ ከዚያ በኋላ ይቆያሉ የሚል እምነት አልነበራቸውም።

ይሁን እንጂ ባለፉት 50 ዓመታት አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች ብርቱ ጥረት በማድረጋቸው ቦዮቹ ከአገልግሎት ውጪ ከመሆን ድነዋል። በአሁኑ ጊዜ ጭነት የሚያጓጉዙ ጥቂት ጀልባዎች ቢኖሩም አብዛኞቹ ተቀይረው ቋሚ መኖሪያ ቤቶች ወይም የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያዎች ሆነዋል። ዛሬ ብሪታንያ ውስጥ እጅግ ውብ የሆኑ ተፈጥሯዊ አካባቢዎችን አቆራርጠው በሚያልፉና 3,000 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባላቸው ቦዮች ላይ በመጓዝ አገር መጎብኘት ይቻላል። ጠባብ የሆኑትን ጀልባዎች የሚወዱ ሰዎች፣ የድሮ ዘመን ልማዶችን እንደገና ማዘውተር የጀመሩ ሲሆን በቦዮቹ ላይ የሚከበሩት ዓመታዊ በዓላትም እነዚህ ልማዶች በብዙዎች ዘንድ እንዲታወቁ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በቀለማት ያሸበረቁት የመዝናኛ ጀልባዎች ተወዳጅነት እያገኙ በመምጣታቸው በዛሬው ጊዜ፣ የጦፈ ንግድ ይካሄድበት ከነበረው ዘመን የበለጠ ብዛት ያላቸው ጀልባዎች ሊኖሩ ችለዋል፤ በአሁኑ ወቅት የጀልባ መሄጃ ቦዮቹ ከ200 ዓመታት በፊት ይገነቡ በነበሩበት ፍጥነት በመታደስ ላይ ናቸው።

ያም ሆኖ ግን በዛሬው ጊዜ በቦዮቹ አካባቢ ከሚዝናኑት ሰዎች መካከል በጀልባ የሚጠቀሙት ጥቂቶቹ ናቸው። ለምን? ምክንያቱም የጀልባ መሄጃ ቦዮቹ በታደሱበት ወቅት በየቦታው መናፈሻዎች በመሠራታቸው ነው። የእነዚህ መናፈሻዎች መሠራት እግረኞች፣ ብስክሌተኞችና ዓሣ አጥማጆች ቀደም ሲል እምብዛም ወደማይታወቁ የገጠር ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች በመሄድ መዝናናት የሚችሉበት አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል። የቦዮቹ የውኃ መጠን እንዳይቀንስ ለማድረግ ሲባል ሰው ሠራሽ ሐይቆች ተሠርተዋል፤ የሐይቆቹ መሠራት ለዱር እንስሳት ምቹ መኖሪያ የፈጠረላቸው ሲሆን የቦዮቹ መኖር ብዙ ዓይነት ዕፅዋት፣ ወፎችና እንስሳት እንዲኖሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

የብሪታንያ የጀልባ መሄጃ ቦዮች መገንባት አስደናቂ የሆነ አዲስ የለውጥ ዘመን አስከትሏል፤ ይሁንና በአሁኑ ጊዜ ቦዮቹ ከታቀደላቸው ዓላማ የተለየ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው። እነዚህ ቦዮች በእነሱ እርዳታ የተፈጠረው ዘመናዊ ዓለም ከሚያስከትለው ውጥረት እፎይታ ለማግኘት ያስችላሉ።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በመተላለፊያ ዋሻዎች ውስጥ መጓዝ

ብዙዎቹ መተላለፊያ ዋሻዎች፣ ጀልባ የሚጎትቱ ፈረሶች የሚሄዱባቸው መንገዶች የሏቸውም። በመሆኑም የሞተር ጀልባ ከመሠራቱ በፊት ጀልባዎችን በመተላለፊያ ዋሻዎች ውስጥ ማሳለፍ የሚቻለው ሌጊንግ በሚባል አደገኛ ዘዴ አማካኝነት ነበር። በጀልባው ላይ ከፊት በኩል በግራና በቀኝ ሁለት ጣውላዎች ይገጠማሉ። ከዚያም ሁለት የጀልባ ሠራተኞች በጣውላዎቹ ላይ በጀርባቸው ተንጋለው ጣውላውን በእጃቸው ግጥም አድርገው ይይዙና በእግራቸው ግድግዳውን በመግፋት ጀልባው ወደፊት እንዲሄድ ያደርጋሉ። በጨለማ ወቅት ብዙውን ጊዜ የሚያበሩት አንድ ሻማ ብቻ ስለሚሆን ሰውየው ግድግዳውን ስቶ ውኃው ውስጥ ሊወድቅ ይችላል፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በጀልባውና በዋሻው መካከል ወድቆ ተጣብቆ ሊሞት ይችላል። የብሪታንያ የጀልባ መሄጃ ቦዮች በአንድ ወቅት 68 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው መተላለፊያ ዋሻዎች ነበሯቸው፤ በዚህም ምክንያት ረጅም ርቀት ባላቸው ዋሻዎች ውስጥ ለማለፍ ጥሩ ሥልጠና ያገኙ ሰዎች ይቀጠሩ ነበር። በቅርቡ ዮርክሻየር ውስጥ ስታንዴጅ በሚባል ከተማ እንደገና የተከፈተው በርዝመቱ ተወዳዳሪ የሌለው መተላለፊያ ዋሻ አምስት ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው።

[ምንጭ]

Courtesy of British Waterways

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የቦይ መዝጊያዎችና የተራቀቀ ጀልባ ማንሻ

ውኃ ዳገት መውጣት እንደማይችል የታወቀ ነው፤ በመሆኑም አንድ የጀልባ መሄጃ ቦይ አቀበት ላይ ሲደርስ ምን ይደረጋል? መንገዱን የሚያረዝምበት ቢሆንም እንኳ እየተጠማዘዘ ዳገቱን እንዲያልፍ ይደረጋል፤ ወይም ጋራውን በመቦርቦር መተላለፊያ ዋሻ ይሠራል። ሦስተኛው አማራጭ ደግሞ በውኃ መዝጊያ በሮች አማካኝነት የውኃውን ከፍታ መጨመር ነው። እነዚህ መዝጊያዎች እንደ ደረጃ ከፍና ዝቅ ብለው የሚገኙ ሁለት ቦዮችን ለማገናኘት ያስችላሉ። አንድ ጀልባ በሁለቱ መዝጊያ በሮች መካከል ሲደርስ የኋለኛውም መዝጊያ ይዘጋል፤ ከዚያም ጀልባውን ወደላይኛው ቦይ ለማውጣት ከተፈለገ ጀልባው ያለበት ክፍል ውኃ ይሞላል። ጀልባው ወደታችኛው ቦይ እንዲወርድ ከተፈለገ ደግሞ በመዝጊያዎቹ መካከል ያለው ውኃ ይለቀቅና ጀልባው ከታችኛው ቦይ ጋር እንዲገናኝ ይደረጋል።

የቀድሞዎቹ የውኃ መዝጊያ በሮች ተበላሽተው መታደስ ባይችሉስ? ስኮትላንድ ውስጥ በግላስጎውና በኤዲንበርግ መካከል ለረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት አቁመው የነበሩ ሁለት ቦዮችን ለማገናኘት አንድ ትልቅ ፕሮጀክት በተጀመረበት ወቅት እንዲህ ዓይነት ችግር አጋጥሞ ነበር። ፎልከርክ በምትባል ከተማ ዩኒየን የሚባለውን ቦይ በዓለም ላይ በጣም ረጅም ዘመን ካስቆጠረው ከፎርዝና ክላይድ ቦይ ጋር የሚያገናኝ 11 በሮች ያሉት ውኃ መዝጊያ ነበር፤ ይህን መዝጊያ እንደገና ለመሥራት የተደረገው ጥረት ሊሳካ አልቻለም። በዚህ ጊዜ ዓይነተኛ መፍትሔ ሆኖ የተገኘው በረቀቀ መንገድ የሚሠራ 35 ሜትር ዲያሜትር ያለው ፎልከርክ ዊል የሚባል ጀልባ ማንሻ ማሽን መሥራት ነበር። ይህ ጀልባ ማንሻ በአንድ ጊዜ ስምንት ጀልባዎችን ማንሳት የሚችል ሲሆን ይህን ለማድረግ የሚፈጅበት ጊዜ 15 ደቂቃ ብቻ ነው።

የለንደኑ ዘ ታይምስ መጽሔት “በምሕንድስናው መስክ የተፈጸመ አስደናቂ ጀብድ” ሲል የዘገበለት ይህ ማሽን ከ20 በላይ ጀልባዎችን ለማቆም የሚያስችል ቦታ ባለው ትልቅ ክብ ኩሬ ውስጥ ይገኛል።

[ምንጭ]

ከላይ በስተቀኝ:- Courtesy of British Waterways

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በቦዮቹ ላይ መቅዘፍ የምንወድበት ምክንያት

እኔና እንደኔው አረጋዊ የሆነችው ባለቤቴ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእነዚህ ቦዮች ላይ በጀልባ በመንሸራሸር ጸጥ ያለና የተረጋጋ የእረፍት ጊዜ አሳልፈናል። ጸጥ ያለና የተረጋጋ ያልነው ከምን አንጻር ነው? አንደኛ ነገር፣ በከተማ ውስጥ ካለው የመኪና ግርግርና ሩጫ የበዛበት ሕይወት ስለራቅን ነው። በጀልባ ስትሄድ ብትፈጥን እንኳ በሰዓት ከ5 ኪሎ ሜትር በላይ አትጓዝም። ለምን? ጀልባው በፍጥነት ሲሄድ የሚፈጠረው ኃይለኛ የውኃ ግፊት ቦዩን እንዳያበላሸው ነው። በዚህም ምክንያት ውሾቻቸውን ለማንሸራሸር በእግራቸው የሚሄዱ ሰዎች እንኳ ብዙውን ጊዜ ከኋላችን ተነስተው ቀድመውን ያልፋሉ!

በዝግታ መሄድ ያለው ሌላው ጥቅም ደግሞ የአካባቢውን የተፈጥሮ ውበት ለማየት አልፎ ተርፎም አላፊ አግዳሚውን ሰላም ለማለት የሚያስችል መሆኑ ነው። ደግሞም የአካባቢው የተፈጥሮ ውበት በጣም የሚያስደስት ነው። አብዛኛውን ጊዜ ጀልባ የምንከራየው በደቡብ ዌልስ ከሞንማውዝሻየርና ከብሬኮን ቦይ ነው። ይህ ቦይ 50 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ከዌልስ ድንበር አንስቶ 886 ሜትር ከፍታ እስካላቸው የብሬኮን ተራሮች ይደርሳል። ውኃ መዝጊያዎች ባሉበት ቦታ ደርሰን ጀልባችን ወደላይኛው ቦይ ለመውጣት ወይም ወደታችኛው ቦይ ለመውረድ ከፍ ዝቅ ባለ ቁጥር ለትንሽ ጊዜም ቢሆን ልዩ ስሜት ይሰማናል።—በገጽ 15 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

ጀልባዎቹ የተሟላ አገልግሎት የሚሰጡ ከመሆናቸውም በላይ ከፍተኛ ምቾት አላቸው። እንዲያውም አንዳንዶቹ የራሳቸው የሆነ ገላ መታጠቢያና መጸዳጃ ቤት ያላቸው ሁለት መኝታ ክፍሎች አሏቸው። በተጨማሪም ጀልባዎቹ ኃይለኛ ብርድ በሚኖርባቸው ምሽቶች ክፍሎቹን ለማሞቅ የሚያስችሉ ማሞቂያ መሣሪያዎች ተገጥመውላቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ ምግባችንን የምናበስለው እኛው ራሳችን ስንሆን ማብሰል ካልፈለግን ደግሞ ጀልባችንን አቁመን በቦዩ ዳርቻ ከሚገኙ ምግብ ቤቶች ውስጥ ወደ አንዱ በመሄድ ጣፋጭ ምግብ መብላት እንችላለን።

በተለይም የቦዩ ውኃ እንደ መስታወት አንጸባርቆ የዛፎችንና የኮረብታዎችን መልክ በሚያሳይበት በማለዳው ሰዓት ላይ አካባቢው ሰላማዊና የተረጋጋ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ሁሉም ነገር ጸጥ እረጭ ከማለቱ የተነሳ የወፎች ዝማሬ በግልጽ ይሰማል። ሳቢሳዎች ከፊት ከፊታችን በቀስታና በእርጋታ እየተንቀሳቀሱ ድምፃቸውን አጥፍተው የቦዩን ዳርና ዳር በንቃት ይከታተላሉ።—ተጽፎ የተላከልን

[ምንጮች]

Courtesy of British Waterways

ከላይ በስተቀኝ:- By kind permission of Chris & Stelle on Belle (www.railwaybraking.com/belle)

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Courtesy of British Waterways