በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የታይላንድ ምግብ

የታይላንድ ምግብ

የታይላንድ ምግብ

ማሌዥያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በታይላንድ፣ ባንኮክ በሰው በተጨናነቁ ጎዳናዎች ላይ በእግርህ ስትዘዋወር ከጎዳናው ጥግ የሚማርክ የምግብ ሽታ ውልብ ይልብህ ይሆናል። መንገድ ላይ ምግብ የሚያበስሉ ሰዎች የታይላንድን ባሕላዊ ምግብ እያዘጋጁ ነው። የሚያስጎመጀውን ምግብ መዓዛ ካሸተትክና የተለያዩ ቀለማት ያሉትን ማራኪ ምግብ ካየህ በኋላ ያለህ ምርጫ አንድና አንድ ነው፤ ይህን ጣፋጭ ምግብ ለመቅመስ ትገደዳለህ።

የታይላንድን ምግብ ማራኪ የሚያደርገው በጥንቃቄ የተመረጡ ለማጣፈጫነት የሚያገለግሉ ዕፅዋት፣ ሥራ ሥሮች፣ ቅጠላ ቅጠሎችና የእህል ዘሮች በአንድ ላይ የተቀላቀሉበት መሆኑ ነው። እነዚህ በአንድ ላይ ሲዋሐዱ ጣፋጭ፣ ኮምጣጣ፣ ጨዋማ፣ መራራና የሚያቃጥል ጣዕም እንዲሁም ቢያንስ ቢያንስ ምግቡን ቀምሰህ እንድትሄድ የሚያስገድድህ መዓዛ ይፈጥራሉ። ታይላንድ እንዲህ ዓይነት ልዩ የምግብ አሠራር ዘዴ ሊኖራት የቻለው እንዴት ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ ከታይላንድ ታሪክ ጋር ይያያዛል።

የተለያዩ አገሮች የምግብ ጣዕም ቅይጥ

ታይላንድ ለብዙ የእስያ አገሮች መተላለፊያ ቦታ ሆና ታገለግላለች። ለበርካታ መቶ ዘመናት ቻይናውያን፣ ላኦስያውያን፣ ካምቦዲያውያን፣ ኢንዶኔዥያውያን፣ አውሮፓውያንና ሌሎችም ታይላንድን አቋርጠው ይጓዙ የነበረ ሲሆን ብዙዎቹም መኖሪያቸውን እዚያው አድርገዋል። እነዚህ ሰዎች የትውልድ አገራቸውን የምግብ አሠራር ሙያ ይዘው በመምጣታቸው የእነዚያ ሁሉ የተለያዩ ምግቦች ጣዕምና መዓዛ ታይላንድ ውስጥ ሊቀር ችሏል።

ከብዙ ዘመናት በፊት አንድ ወቅት ላይ ሕንዳውያን ተጓዦች፣ ምግብ ሲዘጋጅ ኬሪ የተባለ የተቀመመ ማባያ እንዴት እንደሚሠራ ለታይላንዳውያን አሳዩአቸው። በ16ኛው መቶ ዘመን ደግሞ የፖርቱጋል ተወላጆች እንደ ሚጥሚጣ ያለ የሚያቃጥል ቃሪያና ምናልባትም ቲማቲምን ወደ ታይላንድ አመጡ። በዛሬው ጊዜ የታይላንድ የምግብ አዘገጃጀት ብዙ ነገሮችን የሚያካትት ቢሆንም አብዛኞቹ የታይላንድ ምግቦች ቢጫ፣ አረንጓዴና ቀይ ቀለም ያላቸው የተለያዩ ዓይነት ቃሪያዎችን እንዲሁም እንደ ቃሪያዎቹ ዓይነት ቀለም ያላቸው የተቀመሙ ፈሳሽ ማባያዎችን (ኬሪ) ያካትታሉ። የታይላንድ ምግብ፣ በኬሪ የተሠሩ ማባያዎችና የተለያዩ ቃሪያዎች የተቀላቀሉበት መሆኑ የምሥራቃውያን ምግብ መለያ የሆነውን ኃይለኛ ጣዕም ይሰጠዋል።

ብዙ ምግቦች፣ ብዙ ዓይነት ጣዕሞች

የታይላንድ ባሕላዊ ገበታ ልዩ ልዩ ምግቦችን የሚያካትት ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሾርባ፣ ሰላጣ፣ ጥብሳ ጥብስ፣ በኬሪ የተቀመመ ማባያ እንዲሁም ማጥቀሻ ወጦች ይገኙበታል። ትኩስ ነጭ ሩዝ ምንጊዜም ከገበታ አይጠፋም። ከዚያም ከምግብ በኋላ ከስኳርና ከእንቁላል የሚሠሩ ጣፋጮች ይቀርባሉ። በተጨማሪም ኮኮናትና የኮኮናት ወተት የታይላንድን ጣፋጮች ለማዘጋጀት ይውላሉ።

በየትኛውም ቦታ ቢሆን ጥሩ ምግብ ለማዘጋጀት ወሳኙ ነገር ትኩስ ምርቶችን ማግኘት መቻል ሲሆን በታይላንድ ደግሞ እነዚህን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። በትልልቅና በትንንሽ ከተሞች በሚገኙ ገበያዎች፣ ከተቆረጡ ብዙም ያልቆዩ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች እንዲሁም እንደ ጠጅ ሣር፣ ድንብላል፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ዝንጅብል፣ ኮረሪማ፣ እርድና ከሙን ያሉ ቅመሞች እንዲሁም ዓሣ ይሸጣሉ። በእነዚህ ገበያዎች ውስጥ የታይላንድ ምግብ ዋና ክፍል የሆኑትን የሚያቃጥሉ ቃሪያዎችና ኮምጣጤዎች በብዛት ታገኛለህ።

ታይላንድን የምትጎበኝም ሆንክ የታይላንድን ምግብ በአካባቢህ መቅመስ የምትፈልግ፣ የታይላንድ መለያ ምግብ የሆነውን ቶም ያም ጉንግ ተብሎ የሚጠራውን የሚያቃጥልና ኮምጣጣ ጣዕም ያለው የሽሪምፕ ሾርባ ቅመስ። ሌሎች ጥሩ አማራጮች ደግሞ ቅመማ ቅመሞች የገቡበት ከፓፓያ የሚሠራ ሰላጣ እንዲሁም ከዶሮ ወይም ከዳክዬ አሮስቶ፣ በቀጫጭኑ ከተከተፈ የአሳማ ሥጋ ወይም በተቀመመ ፈሳሽ ውስጥ ተዘፍዝፎ ከተጠበሰ ዓሣ ጋር የሚቀርብ የውኃ መልክ ያለው ፓስታ ናቸው። “የሚጋልቡ ፈረሶች” የሚል ትርጉም ያለው ማ ሆ ተብሎ የሚጠራው የምግብ ዓይነት የአሳማ ሥጋ፣ እንደ ሸርጣን ያለ ዓሣና ኦቾሎኒ አንድ ላይ ተቀላቅለው የተቆረጠ አናናስ ላይ ከተደረጉ በኋላ ቀይ ቃሪያና የድንብላል ቅጠል ለመልክ ጣል ጣል ይደረግበታል። ከማዕድ ከመነሳትህ በፊት ከኮኮናት ወተትና ከማንጎ ጋር የሚበላውን ከሩዝ የተሠራ ጣፋጭ ቅመሰው።

የታይላንድን ምግብ ለመብላት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምንድን ነው? በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ባሕላዊው የአመጋገብ ሥርዓት፣ ለየት ባለ መንገድ የተዘጋጀውን የተለወሰ ሩዝ በጣቶችህ ካድቦለቦልክ በኋላ ወጥ ውስጥ አጥቅሰህ መጉረስ ነው። ከፓስታ የሚዘጋጁ ምግቦችን ስትበላ የሩቅ ምሥራቅ ሰዎች እንደ ሹካ የሚገለገሉበትን ቾፕስቲክ ተብሎ የሚጠራ መመገቢያ መጠቀም ትመርጥ ይሆናል። ነገር ግን በቾፕስቲክ መብላት የሚያስቸግርህ ከሆነ ሹካና ማንኪያ መጠቀም ትችላለህ።

የታይላንድን ምግብ የመብላት ፍላጎትህ ተቀሰቀሰ? እስያ ውስጥ የምትገኘው የዚህች ውብ አገር የሚጣፍጡ ምግቦች፣ ስለ ምሥራቃውያን እጅ የሚያስቆረጥሙ ምግቦች ይበልጥ የማወቅ ፍላጎት ሊቀሰቅስብህ ይችላል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

1 ቶም ያም ጉንግ ሾርባ

2 ከተፈጨ አሳማና ሽሪምፕ ጋር የተዘጋጀ የውኃ መልክ ያለው ፓስታ

3 ቅመማ ቅመሞች የገቡበት ከፓፓያ የተሠራ ሰላጣ

4 ማ ሆ

5 ከኮኮናት ወተትና ከማንጎ ጋር የሚበላው ከሩዝ የተሠራ ጣፋጭ