በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕፃኗ ጎሪላ ለቅሶ

የሕፃኗ ጎሪላ ለቅሶ

የሕፃኗ ጎሪላ ለቅሶ

ካሜሩን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ፒትቹ የተባለችው ጎሪላ የተወለደችው በመካከለኛው አፍሪካ በሚገኝ አንድ ደን ውስጥ ነው። አንድ ዓመት ገደማ ሲሆናት አዳኞች እናቷን ጨምሮ መላውን መንጋ ለምግብነት ሲሉ ገደሏቸው። ይሁንና ፒትቹ ትንሽ ስለነበረች እሷን ከመግደል ይልቅ የቤት እንስሳ እንድትሆን ሸጧት። ፒትቹ ታምማ የነበረ ሲሆን ሳታቋርጥ ትጮኽ ነበር።

ፒትቹ፣ ወላጆቻቸው ከተገደሉባቸው በሺህ የሚቆጠሩ አጥቢ እንስሳት መካከል አንዷ ናት። እንዲህ ያለ አሳዛኝ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደረጉ በርካታ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ የዱር እንስሳትን በሕገ ወጥ መንገድ እያደኑ ለምግብነት መሸጥ ነው። የሠለጠኑ አዳኞች፣ የእነዚህን እንስሳት ሥጋ በውድ ዋጋ ለሚገዟቸው ምግብ ቤቶችና ግለሰቦች ለመሸጥ ሲሉ እንስሳቱን ለማደን ቀንና ሌሊት ጫካውን ያስሳሉ። አትራፊ ነጋዴዎች እነዚህን እንስሳትና ሥጋቸውን ለአገር ውስጥ እንዲሁም ለውጪ ገበያ በማቅረብ በርካታ ገንዘብ የሚያስገኘውን ይህን ሕገ ወጥ ሥራ ያካሂዳሉ።

የዱር እንስሳትን ስጋት ላይ የጣለው ሌላው ነገር ደግሞ የደን መመንጠር ነው። ደኖች ሲመነጠሩ እንስሳት መኖሪያቸውንና መሸሸጊያቸውን እንዲሁም ምግብ የሚያገኙበትንና ጎጇቸውን የሚቀልሱበትን ቦታ ያጣሉ። ከዚህም በላይ የደን መመንጠር ለአደን ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። እንዴት? ደን መመንጠር አዳኞች ወደ ጫካው ዘልቀው በመግባት መኖሪያቸውን በማጣታቸው ምክንያት ግራ የተጋቡትን እንስሳት በቀላሉ ለማደን ያስችላቸዋል። የሕዝብ መብዛት፣ የፕሮቲን ምግቦች ፍላጎት መጨመር፣ የከተሞች መስፋፋትና ይበልጥ ውጤታማ የሆኑ የአደን መሣሪያዎች ጥቅም ላይ መዋል እንዲሁም ጦርነትና የጦር መሣሪያዎች በብዙ ሰዎች እጅ መግባት የዱር እንስሳትን ለአደጋ ካጋለጧቸው ነገሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በዚህም የተነሳ አጥቢ እንስሳትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ዝርያዎች ለመጥፋት ተቃርበዋል። ይህም ደኖችን እንስሳት አልባ እንዳያደርጋቸው ያሰጋል። ሆኖም ችግሩ በዚህ ብቻ አያበቃም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ለምሳሌ ያህል፣ እንስሳት የደን ሥነ ምሕዳር የተስተካከለና ብዙ ዓይነት ዝርያዎችን ያቀፈ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። በመሆኑም እንስሳት ጠፉ ማለት የዕፅዋት ሕይወት አደጋ ላይ ወደቀ ማለት ነው።

ያም ሆኖ ሰዎች እንስሳትን ከማደን ወደኋላ አላሉም። በተወሰኑ የምዕራብ አፍሪካ አገሮች፣ በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ የአንዳንድ አጥቢ እንስሳት ቁጥር ቀደም ሲል ከነበረው ዘጠና በመቶ ቀንሷል። በካሜሩን የሚገኙ የዱር እንስሳ ጥበቃ ባለሙያዎች “ሕገ ወጥ አደኑ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ በደኑ ውስጥ ያሉት ጎሪላዎች በሙሉ በቅርቡ ይጠፋሉ” ብለዋል። *

ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን እንስሳት መታደግ

በዱር እንስሳት ላይ እየደረሰ ያለውን አሳዛኝ ሁኔታ ለማስቀረት የሊሚ የዱር እንስሳት እንክብካቤ ማዕከልን የመሳሰሉ የዱር እንስሳ ጥበቃ ተቋሞች ተቋቁመዋል። በምዕራብ አፍሪካ በሚገኘው የካሜሩን ተራራ ግርጌ ያለው ይህ ማዕከል የመጥፋት አደጋ የተደቀነባቸውን ዝርያዎች ለመንከባከብ ጥረት ያደርጋል። በሊሚ ማዕከል ጎብኚዎች ጎሪላዎችን፣ ቺምፓንዚዎችን፣ ማንድሪል የተባሉ ጦጣዎችንና ሌሎች 13 የአጥቢ እንስሳት ዝርያዎችን እንዲሁም የተለያዩ እንስሳትን መመልከት ይችላሉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ማዕከሉ፣ ወላጆቻቸው ለሞቱባቸውና ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ 200 የሚሆኑ እንስሳት መጠለያ፣ ምግብና ሕክምና በመስጠት እንክብካቤ እያደረገ ነው። በተጨማሪም ይህ ማዕከል ካሜሩንንና የጎረቤት አገሮችን ጨምሮ ከመላው ዓለም ለመጡ ከ28,300 በላይ ለሚሆኑ ጎብኚዎች ተፈጥሮን መንከባከብ ያለውን አስፈላጊነት አስመልክቶ ትምህርት ሰጥቷል።

ይህ ሁኔታ ወደ ፒትቹ ታሪክ ይመልሰናል። ይህች ሕፃን ጎሪላ ስታለቅስ የሰሙ ሰዎች ሁኔታው በጣም ስላሳዘናቸው ፒትቹን ከአዳኞቹ በመግዛት ለሊሚ ማዕከል ሰጧት። ይህች ጎሪላ ወደ ማዕከሉ ስትደርስ ሙሉ ምርመራ ተደረገላት። ፒትቹ ከደረሰባት የስሜት መረበሽ በተጨማሪ በሳል፣ በውኃ ጥም፣ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ በተቅማጥ እንዲሁም በቆዳ በሽታ ትሠቃይ ነበር። ይህች ትንሽ ጎሪላ ፒትቹ የሚል ስም የተሰጣት በነበረባት የቆዳ ችግር ምክንያት ሲሆን ትርጓሜውም “ነጠብጣባማ” ማለት ነው። የሚያስደስተው ፒትቹ በተደረገላት ሕክምና ምክንያት ጤንነቷ በፍጥነት በመሻሻሉ ቀዶ ሕክምና አላስፈለጋትም። ይህ ማዕከል አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለእንስሳቱ ቀዶ ሕክምና ያደርጋል።

ማንኛውም እንስሳ ወደ ማዕከሉ ሲመጣ እንደሚደረገው ሁሉ ፒትቹም ለ90 ቀናት ለብቻዋ እንክብካቤ ተደረገላት። ከዚያም የእሷ ዝርያ የሆኑ 11 ጎሪላዎች ወዳሉበትና ተፈጥሯዊ ገጽታ እንዲላበስ ተደርጎ ወደተሠራው አካባቢ ተወሰደች። የማዕከሉ ሠራተኞች ትላልቆቹ ጎሪላዎች ፒትቹን ወዳጃዊ በሆነ መንገድ ሲቀበሏት በማየታቸው ተደስተዋል። ጎሪላዎቹ እንዲህ ማድረጋቸው የተለመደ ስለነበር ፒትቹ ከቡድኑ ጋር ለመቀላቀል አልተቸገረችም።

በማዕከሉ ውስጥ ባሉት እንስሳትና በሚንከባከቧቸው ሰዎች መካከል ያለው ወዳጃዊ ቅርርብ በመካከላቸው ጥሩ ግንኙነት እንዲፈጠር አድርጓል። በመሆኑም አንድ ጎብኚ በማዕከሉ ውስጥ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ሲመለከት አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ምድርንና እንስሳትን እንዲገዙ የሰጣቸው መመሪያ በሰው ልጆች ላይ የሞራል ግዴታ እንዳስከተለባቸው ማስተዋል ይችላል።—ዘፍጥረት 1:28

ወላጆቻቸው የሞቱባቸው እንስሳት የወደፊት ዕጣ ምን ይሆን?

የማዕከሉ ዋነኛ ግብ እንስሳቱን ወደመጡበት ደን መመለስ ነው። ይህን ማድረግ ግን ቀላል አይደለም። በሰዎች እንክብካቤ ሥር የቆዩ እንስሳት ወደ ደኑ ሲመለሱ ራሳቸውን ችለው ለመኖር ይቸገራሉ። በተጨማሪም ሰዎች ለምግብነት ሊያድኗቸው ይችላሉ። በርካታ የአፍሪካ አገሮች በድንበሮቻቸው አካባቢ የእንስሳት ጥበቃ ተቋሞችን ለማቋቋምና ያሉትን ማዕከላት ይበልጥ ለማጠናከር ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ይህም ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን እንስሳት ወደ ደን ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያፋጥነውና አጥቢ እንስሳትን ጨምሮ በአካባቢው የሚኖሩትን የዱር እንስሳት ሕይወት እንደሚያሻሽለው ተስፋ ተጥሎበታል።

ያም ሆኖ ስግብግብነት፣ ድህነት፣ የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት መጨመርና የደኖች መመንጠር በአጥቢም ሆኑ በሌሎች እንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል። የሊሚ የዱር እንስሳት እንክብካቤ ማዕከል ፕሮጀክት ኃላፊ የሆኑት ፊሊክስ ላንክስተር እንደገለጹት ለዱር እንስሳት በአፋጣኝ ጥበቃ ካልተደረገላቸው “ቁጥራቸው ሊያንሰራራ በማይችል ሁኔታ እየተመናመነ ሊሄድ እንደሚችል” ገልጸዋል። አክለውም “በዚህም ሳቢያ . . . ለመንከባከብ የምንደክምላቸው እንስሳት ጭራሹኑ ሊጠፉ ይችላሉ” ብለዋል።

ይህ እንዴት የሚያሳዝን ነው! ከዚህ የከፋው ግን ሰዎች በተመጣጠነ ምግብ እጥረትና በበሽታ ሲሠቃዩ እንዲሁም ሕፃናት በምግብ እጦት ሆዳቸው ተቆዝሮና ዓይናቸው በእንባ ተሞልቶ ሲሞቱ ማየቱ ነው። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በፒትቹ ላይ የደረሰው ችግር የዓለም ሁኔታ በተለይም ደግሞ በምድር ላይ የሚታየው የኑሮ ልዩነትና ኢፍትሐዊነት እጅግ አስከፊ መሆኑን ያጎላል።

ፈጣሪ የምድር ሁኔታ እንደሚያሳስበው ማወቃችን ያስደስታል። ጭካኔን፣ ሥቃይንና ሞትን በቅርቡ ያጠፋል። በተጨማሪም ሁሉም ፍጥረታት ለዘላለም በሰላም የሚኖሩበትን ጊዜ ያመጣል።—ኢሳይያስ 11:6-9

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 የዱር እንስሳትን መያዝና ሥጋቸውን መመገብ አንትራክስንና ኢቦላን የመሳሰሉ አደገኛ በሽታዎች እንዲሁም ኤች አይ ቪን የሚመስሉ ቫይረሶች ወደ ሰው እንዲተላለፉ ሊያደርግ እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፒትቹ ሕክምና ከማግኘቷ በፊትና በኋላ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቀይ ጆሮ ያላት ግኖን የተባለች የጦጣ ዝርያ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ድሪል የተባለች የጦጣ ዝርያ ልጇን ስትንከባከብ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሊሚ የዱር እንስሳት እንክብካቤ ማዕከል መግቢያ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆቿን ያጣችው ቦሎ የተባለችው ጎሪላ እንክብካቤ ሲደረግላት

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

በገጽ 22 እና 23 ላይ የሚገኙት ፎቶዎች በሙሉ የተወሰዱት:- Limbe Wildlife Centre, Cameroon

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ሁለቱም ፎቶዎች የተወሰዱት:- Limbe Wildlife Centre, Cameroon