ሮቦቶች ዛሬ ምን ደረጃ ላይ ደርሰዋል?
ሮቦቶች ዛሬ ምን ደረጃ ላይ ደርሰዋል?
ጃፓን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ሮቦት። ይህን ቃል ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? አንዳንድ ሰዎች፣ ሮቦቶችን ጥሩ ረዳቶች እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ሌሎች ግን ወደፊት የሰው ልጆችን ሊተኩ የሚችሉ ላቅ ያለ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ማሽኖች እንደሆኑ ስለሚያስቡ ይፈሯቸዋል። በርካታ ሰዎች ደግሞ ሮቦቶች በገሃዱ ዓለም ያሉ ነገሮች ሳይሆኑ ሳይንሳዊ ልቦለዶች እንደሆኑ ይሰማቸዋል።
ሮቦቶች በዛሬው ጊዜ ያሉበት ሁኔታ ምን ይመስላል? ዓለም አቀፉ የሮቦት ሳይንስ ፌዴሬሽን በ2006 ባወጣው አንድ ጥናታዊ መረጃ መሠረት በዓለም ዙሪያ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሮቦቶች በኢንዱስትሪው መስክ አገልግሎት እንደሚሰጡ ይገመታል፤ ከእነዚህ መካከል ግማሽ ያህሉ የሚገኙት በእስያ ነው። ሮቦቶች ይህን ያህል ተፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?
ሮቦቶች ምን እያከናወኑ ነው?
ሁልጊዜ በሥራ ገበታው ላይ የሚገኝ፣ ፈጽሞ የማያጉረመርም እንዲሁም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ሳምንቱን ሙሉ በቀን 24 ሰዓት ሥራውን ማከናወን የሚችል አንድ ሠራተኛ ለማሰብ ሞክር። በኢንዱስትሪው መስክ አገልግሎት የሚሰጡት ሮቦቶች እንደዚህ ዓይነት ሠራተኛ ናቸው። እነዚህ ሮቦቶች ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ተሽከርካሪዎችን፣ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መሣሪያዎችንና ለቤት ውስጥ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎችን ያለማቋረጥ ያመርታሉ። ሮቦቶች ከስማቸው ጋር የሚስማማ ሥራ ያከናውናሉ፤ ሮቦት የሚለው ቃል ሮቦታ ከሚለው የቼክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም “የግዳጅ ሠራተኛ” ወይም “ባሪያ” ማለት ነው። በ2005 በመኪና አምራች ድርጅቶች ውስጥ ከነበሩት 11 ሠራተኞች አንዱ ሮቦት እንደነበረ ይገመታል!
ይሁን እንጂ ሮቦቶች የሚሰጡት አገልግሎት በፋብሪካ ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም። አንዳንድ ሮቦቶች ድምፅ መለየት የሚችል የኮምፒውተር ፕሮግራም፣ ሽቦ አልባ የመገናኛ መሥመር እንዲሁም ከሳተላይት በሚመጡ መልዕክቶች አማካኝነት አንድ ነገር ያለበትን ቦታ ለማወቅ የሚያስችል መሣሪያ አላቸው። ከዚህም በተጨማሪ ሙቀትን፣ ግፊትን፣ የድምፅ ሞገዶችን፣ ኬሚካሎችን፣ ጨረሮችንና የመሳሰሉትን ነገሮች ለመለየት የሚያስችል መሣሪያ የተገጠመላቸው ሮቦቶች አሉ። ሮቦቶች ከምንጊዜውም ይበልጥ ጉልበት እንዲኖራቸውና የተለያዩ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ ተደርገው ስለሚሠሩ ከጥቂት ዓመታት በፊት የማይቻሉ ይመስሉ የነበሩ ተግባሮችን እያከናወኑ ነው። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።
▪ አገልግሎት የሚሰጡ ሮቦቶች። በታላቋ ብሪታንያ በአንድ ሆስፒታል መድኃኒት ቤት ውስጥ የሚሠራ ሮቦት አለ፤ እጆች የተገጠሙለት ይህ ሮቦት በጥቂት ሴኮንዶች ውስጥ መድኃኒቶችን ከተቀመጡበት ፈልጎ በማምጣት ለሰዎች ይሰጣል። የዩናይትድ ስቴትስ የፖስታ አገልግሎት ድርጅት የታሸጉ ዕቃዎችን በመልክ በመልኩ የሚለዩ፣ የሚያነሱና አስተካክለው የሚደረድሩ በርካታ ሮቦቶች አሉት። የእባብ ዓይነት ቅርጽ ያለው እጅ የተገጠመላቸው ሮቦቶች ደግሞ እንደ አውሮፕላን ክንፍ ባሉ ጠባብ ቦታዎች ውስጥ ፍተሻ ለማካሄድ ወይም የጥገና ሥራ ለመሥራት ያገለግላሉ።
▪ ጓደኛ የሚሆኑ ሮቦቶች። በጃፓን በሚገኝ የአረጋውያን መጦሪያ ተቋም ውስጥ የሚኖሩ በዕድሜ የገፉ ሕሙማን አቆስጣ በተባለው የባሕር እንስሳ መልክ የተሠራ ለስላሳ ጸጉር ያለው ደስ የሚል ሮቦት ተራ በተራ እየተቀባበሉ ያቅፋሉ። ሮቦቱ ሲደባብሱት፣ ብርሃን ሲያርፍበት፣ ድምፅ ሲሰማ እንዲሁም ሙቀት ሲሰማው በተለያየ መንገድ ምላሽ ይሰጣል፤ ሌላው ቀርቶ ሮቦቱ የሚታቀፍበት መንገድ እንኳ በሚሰጠው ምላሽ ላይ ለውጥ ያመጣል። ሮቦቱ ሕይወት እንዳለው አቆስጣ ለስለስ ያለ ድምፅ በማሰማት፣ ዓይኖቹን በማርገብገብ እንዲሁም ክንፎቹን በማንቀሳቀስ ምላሽ ይሰጣል። አንዳንዶች፣ በአቆስጣ መልክ የተሠራው ይህ ሮቦት የሰው ልጆች ጓደኛ ለማግኘት ያላቸውን መሠረታዊ ፍላጎት እንደሚያሟላ እንዲሁም ሕክምና ለመስጠት እንደሚረዳ ያምናሉ።
▪ በሕክምናው መስክ እገዛ የሚያደርጉ ሮቦቶች። ሦስት እጆች ያሉት አንድ ሮቦት ታማሚው አጠገብ ይቆማል። ከሮቦቱ ትንሽ ራቅ ብሎ ደግሞ አንድ የቀዶ ጥገና ሐኪም በአንድ መሣሪያ አማካኝነት የታካሚውን ልብ ይመለከታል። ከዚያም ሐኪሙ የሮቦቱን እጆች በመቆጣጠር የልብ ቀዶ ጥገና ያከናውናል። በሮቦቱ እጆች አማካኝነት የሚከናወነው ይህ ዓይነቱ ቀዶ ጥገና የታመመውን ክፍል ለይቶ ለማከም ስለሚያስችል በቀዶ ሕክምናው ወቅት የሚነካካው የተፈለገው የሰውነት ክፍል ብቻ ይሆናል፤ ይህም የታካሚው ሰውነት ብዙ እንዳይጎዳ፣ ብዙ ደም እንዳይፈስ እንዲሁም ታካሚው ቶሎ እንዲያገግም ይረዳል።
▪ የቤት ውስጥ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ሮቦቶች። አንድ ቁልፍ በመጫን ብቻ ጠፍጣፋና ክብ ቅርጽ ያለው ሮቦት የቤትህን ወለል እንዲያጸዳ ማድረግ ትችላለህ። ሮቦቱ በቤት ውስጥ እየተሽከረከረ ዕቃ ያልተቀመጠባቸውን ቦታዎች የሚያጸዳ ሲሆን ከጊዜ በኋላ የክፍሉን አቀማመጥ “ያጠናዋል።” ይህ ሮቦት ደረጃዎችን መለየት የሚችል ሲሆን ደረጃ ሲያጋጥመው አቅጣጫውን ይቀይራል። ሮቦቱ ቤቱን አጽድቶ ሲጨርስ ሞተሩን ያጠፋና የኤሌክትሪክ ኃይል ወደሚያገኝበት ቦታ ይመለሳል። በአሁኑ ጊዜ ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ የዚህ ዓይነት ሮቦቶች አገልግሎት ይሰጣሉ።
▪ በሕዋ ላይ ምርምር ለማድረግ የሚረዱ ሮቦቶች። ስፒሪት የሚል ስያሜ የተሰጠው ስድስት ጎማዎች ያሉት ተንቀሳቃሽ ሮቦት በማርስ ላይ እየተዘዋወረ ለሳይንቲስቶች መረጃ ይልካል። ምርምር ለማድረግ የሚረዱ መሣሪያዎች በእጆቹ ላይ የተገጠሙለት ይህ ሮቦት በማርስ ላይ እየተዘዋወረ የአፈሩንና የአለቶቹን ዓይነት ይመረምራል። ስፒሪት፣ በተገጠመለት ካሜራ በመጠቀም የማርስን ገጽታ፣ እሳተ ገሞራ የፈነዳባቸውን ቦታዎች፣ ደመናዎችን፣ አቧራማ አውሎ ንፋሶችን እንዲሁም ፀሐይ ስትጠልቅ የሚያሳዩ ምስሎችን ጨምሮ ከ88,500 በላይ ፎቶግራፎችን አንስቷል። ስፒሪት በአሁኑ ጊዜ በማርስ ላይ በመዘዋወር ምርምር ከሚያደርጉት ሮቦቶች አንዱ ነው።
▪ የሕይወት አድን ሥራ የሚያከናውኑ ሮቦቶች። የዓለም የንግድ ማዕከል ሕንፃዎች በወደሙበት ወቅት ከሚጨሰውና ከፍተኛ ሙቀት ካለው ብረታ ብረትና የሲሚንቶ ፍርስራሽ በታች በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ለመፈለግ 17 ሮቦቶች ተሠማርተው ነበር፤ እነዚህ ሮቦቶች መጠናቸው የቅርጫት ኳስ ያክላል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ከታች ባለው ሥዕል ላይ እንደሚታየው ያሉ የተሻሻሉ ሮቦቶች ተሠርተዋል።
▪ ውቅያኖስ ውስጥ ምርምር ለማድረግ የሚረዱ ሮቦቶች። የሳይንስ ሊቃውንት እስካሁን ምርምር ሊያደርጉ ባልቻሉባቸው ቦታዎች ማለትም ጥልቅ በሆነው የውቅያኖሶች ክፍል ላይ ጥናት ለማካሄድ ራሳቸውን ችለው በውቅያኖስ ውስጥ መንቀሳቀስ የሚችሉ ሮቦቶችን ሠርተዋል። በውስጣቸው ሰው ሳይዙ የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ተሽከርካሪዎች የራሳቸውን ኃይል ያመነጫሉ። ሮቦቶች በውቅያኖስ ውስጥ ከሚያከናውኗቸው ሌሎች ሥራዎች መካከል የሰመጡ ነገሮችን ፈልጎ ማውጣት፣ የስልክ መሥመሮችን መፈተሽ፣ ዓሣ ነባሪዎችን መከታተል እንዲሁም ውቅያኖሶችን ከፈንጂ ማጽዳት ይገኙበታል።
እንደ ሰው የሆኑ ሮቦቶች አሉ?
የሰው ልጅ፣ እንደ ሰው የሆኑ ሮቦቶችን ለመሥራት ለበርካታ ዘመናት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ሆኖም ይህን ማድረግ በጣም ከባድ ሆኖበታል። ቢዝነስ ዊክ የተባለው መጽሔት እንዲህ ብሏል:- “ፈጣንና ግዙፍ የሆኑ ኮምፒውተሮችንና ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎችን መሥራት ወይም የከተሞችን ንድፍ ማውጣት እንኳ እንደ ሰው ማየት፣ ማሽተት፣ መስማትና መዳሰስ የሚችሉ እንዲሁም ከሰው ልጆች ጋር የሚቀራረብ የአእምሮ ችሎታ ያላቸውና ሰዎች በሰውነታቸው ክፍሎች ተጠቅመው የሚያከናውኗቸውን ተግባራት ማከናወን የሚችሉ ሮቦቶችን ከመሥራት ጋር ሲወዳደር ያን ያህል ከባድ አይደለም።”
ለምሳሌ ያህል፣ እንደ ሰው የሚራመድ ሮቦት መሥራትን እንመልከት፤ እንዲህ ዓይነት ሮቦት መሥራት ቀላል ይመስል ይሆናል። የጃፓን ተመራማሪዎች ለ11 ዓመታት የዘለቀ እንዲሁም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የፈጀ ሰፊ ምርምርና የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ መራመድ የሚችል ሮቦት መስከረም 1997 መሥራት ችለዋል። ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ደረጃ መውጣት፣ መሮጥ፣ መደነስ፣ ዕቃዎችን በትሪ ላይ አድርገው መያዝ፣ ጋሪ መግፋትና ሌላው ቀርቶ ሲወድቁ ማንም ሳይረዳቸው መነሳት የሚችሉ ሮቦቶች ተሠርተዋል!
ሮቦቶች ወደፊት ምን ዓይነት አገልግሎት ይሰጡ ይሆን?
ሮቦቶች ወደፊት ምን ዓይነት አገልግሎት ይሰጡ ይሆን? የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የበረራና የሕዋ አስተዳደር (NASA) በሕዋ ላይ አደገኛ የሆኑ ሥራዎችን ማከናወን የሚችል እንደ ሰው ያለ ሮቦት እየሠራ ነው። በኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የቻለው ታዋቂው ቢል ጌትስ “ሮቦቶች፣ ለአረጋውያን የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በማድረግ አልፎ ተርፎም ለእነሱ ጓደኛ በመሆን ረገድ ጠቃሚ ሚና” ሊጫወቱ እንደሚችሉ ገልጿል።
በተመሳሳይም የጃፓን መንግሥት ያወጣው አንድ ሪፖርት፣ በ2025 ሮቦቶች ከሰው ልጆች ጋር አብረው በመኖር ሰዎችን እንደሚንከባከቡ፣ ልጆችን በማሳደግ ረገድ እገዛ እንደሚያደርጉ እንዲሁም የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ ገልጿል። ተመራማሪዎች በ2050 ከሰዎች ጋር ተጋጥሞ ሊያሸንፍ የሚችል ሮቦቶችን ብቻ ያቀፈ የእግር ኳስ ቡድን እንደሚኖር ያስባሉ። ከዚህም በላይ በጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ከሰዎች አእምሮ በላይ የሆነ ችሎታ ያላቸው ማሽኖች እንደሚሠሩ ተስፋ ያደርጋሉ።
ተመራማሪዎች እነዚህ ነገሮች እንደሚፈጸሙ በእርግጠኝነት ቢናገሩም ይህ ሊሆን እንደሚችል የሚሰማው ሁሉም ሰው አይደለም። የማሰብ ችሎታ ያላቸው ሮቦቶችን ለመሥራት በሚደረገው ጥረት የሚካፈሉት ጆርዳን ፓላክ የተባሉ ተመራማሪ ያጋጠሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በተመለከተ እንዲህ ብለዋል:- “ሕይወት ያላቸው ነገሮች አፈጣጠራቸው ምን ያህል ውስብስብ እንደሆነ ፈጽሞ አልገባንም ነበር።”
ሮቦቶች ምን ያህል መሻሻል እንደሚያደርጉ ወደፊት የምናየው ነገር ይሆናል። ይሁን እንጂ ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን:- የማፍቀር፣ ጥበብን የማንጸባረቅና ፍትሕን የማስፈን ችሎታ ሊኖራቸው የሚችለው የሰው ልጆች ብቻ ናቸው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ከሌሎች ሕያዋን ፍጥረታት በተለየ፣ በአምላክ መልክ የተፈጠረው የሰው ልጅ ብቻ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:27) የሰው ልጆች በተቀረጸላቸው ፕሮግራም የሚመሩ ስሜት የሌላቸው ማሽኖች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ የራሳቸውን ምርጫ የማድረግ ነፃነትና አምላክን የማምለክ ችሎታ እንዲሁም ሕሊና ያላቸው ፍጥረታት ናቸው። ይህን እውነት ማወቅህ ፈጣሪያችን ወደሆነው ወደ ይሖዋ አምላክ ለመቅረብ እንዲያነሳሳህ እንመኛለን!—ያዕቆብ 4:8
[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
Courtesy Aaron Edsinger
Courtesy OC Robotics
[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
Courtesy AIST
© 2008 Intuitive Surgical, Inc.
Courtesy iRobot Corp.
[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
ከላይ:- NASA/JPL-Solar System Visualization Team; በስተግራ:- NASA/JPL/Cornell University
© The RoboCup Federation
Greg McFall/NOAA/Gray’s Reef National Marine Sanctuary
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© 2007 American Honda Motor Co., Inc.