በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስፐርገርስ ሲንድሮም የሚያስከትለውን ተፈታታኝ ሁኔታ መቋቋም

አስፐርገርስ ሲንድሮም የሚያስከትለውን ተፈታታኝ ሁኔታ መቋቋም

አስፐርገርስ ሲንድሮም የሚያስከትለውን ተፈታታኝ ሁኔታ መቋቋም

ብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ጓደኞች እንዲኖሩህ ትፈልጋለህ፤ ከሰዎች ጋር መጨዋወት ግን ያስቸግርሃል። ሆኖም በምትወደው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለበርካታ ሰዓታት ማውራት ትችላለህ። በየቀኑ ተመሳሳይ የሆኑ ነገሮችን ማድረግ ትፈልጋለህ፤ በመሆኑም ለውጥ ሲያጋጥምህ ትረበሻለህ። ብዙ ጊዜ ስጋትና ተስፋ መቁረጥ የሚሰማህ ሲሆን አንዳንድ ጊዜም በጭንቀት ትዋጣለህ።

ሰዎች በትክክል አይረዱህም። ባሕርይህ ከሰው እንደማይገጥም፣ አስቸጋሪ ሰው እንደሆንክ ወይም ሥርዓት እንደሌለህ ይናገራሉ። በተለይ የሰዎችን ፊት ማንበብ ወይም አካላዊ መግለጫቸውን መረዳት ስለማትችል ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን ማስተዋል አስቸጋሪ ይሆንብሃል። አስፐርገርስ ሲንድሮም ያለባቸው ብዙ ሰዎች ይህን የመሰለ ሁኔታ በየቀኑ ያጋጥማቸዋል።

አስፐርገርስ ሲንድሮም ያለባቸው ሰዎች ከሌሎች የተለየ አካላዊ ሁኔታ የላቸውም፤ እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ በጣም ጎበዞች ናቸው። ይሁን እንጂ ከነርቭ እድገት ጋር የተያያዘ ችግር ስላለባቸው ከሰዎች ጋር መግባባትም ሆነ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ከባድ ይሆንባቸዋል። ይህ ችግር የተለያዩ ገጽታዎች ስላሉት በአንድ ግለሰብ ላይ የሚታየው ምልክት ከሌላው ሊለይ ይችላል። ይሁን እንጂ አስፐርገርስ ሲንድሮም የሚያስከትለውን ተፈታታኝ ሁኔታ ተቋቁሞ መኖር ይቻላል። እስቲ የክሌርን ታሪክ እንመልከት።

በመጨረሻ የችግሯ ምንነት ታወቀ!

ክሌር ልጅ ሳለች በጣም ዝምተኛና ቁጥብ ነበረች። የሰዎችን ዓይን ማየት የሚከብዳት ከመሆኑም ሌላ ብዙ ሰው ባለበት ቦታ መገኘትም ያስፈራታል። መናገር የቻለችው ገና በሕፃንነቷ ቢሆንም ብዙ አታወራም፤ ከዚህም በላይ የምትናገረው በአንድ ዓይነት የድምፅ ቃና ብቻ ነበር። በየቀኑ የምታደርጋቸው ነገሮች አንድ ዓይነት ሲሆኑ ከተለመደው ወጣ ያለ ነገር ሲያጋጥማት በጣም ትረበሻለች።

የትምህርት ቤት መምህሮቿ ይህን የምታደርገው ሆነ ብላ እንደሆነ ስለሚሰማቸው አይታገሷትም፤ ልጆችም ቢሆኑ ያሾፉባት ነበር። የክሌር እናት፣ ለልጇ ባሕርይ መበላሸት ተጠያቂዋ እሷ እንደሆነች ከሚናገሩ ሰዎች የሚሰነዘርባት አግባብነት የሌለው ወቀሳ በጣም ያስጨንቃት ነበር። በመጨረሻም ክሌርን ከትምህርት ቤት አስወጥታት ትምህርቷን እስክትጨርስ ድረስ ቤት ውስጥ ታስተምራት ጀመር።

ክሌር ትምህርቷን ከጨረሰች በኋላ ብዙ ሥራ አግኝታ ነበር፤ ይሁንና በሥራ ላይ የሚያጋጥሟት ሁኔታዎች ቶሎ ቶሎ ስለሚለዋወጡባትና ከእሷ የሚጠበቁባትን ነገሮች መፈጸም ስላቃታት በሥራ ገበታዋ ላይ መቆየት አልቻለችም። መጨረሻ ላይ በተቀጠረችበት የአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋም ውስጥ አለቃ ሆና የምትሠራው ነርስ፣ ክሌር ከባድ ችግር እንዳለባት ተገነዘበች። ከጊዜ በኋላ ማለትም ክሌር የ16 ዓመት ወጣት ሳለች አስፐርገርስ ሲንድሮም እንዳለባት በምርመራ ታወቀ።

የክሌር እናት የልጇ ባሕርይ ከሌሎች በጣም የተለየ የሆነው ለምን እንደሆነ የተገነዘበችው በዚህ ጊዜ ነበር። ክሌር፣ አንድ ጓደኛዋ ስለዚህ የጤና ችግር የሚገልጽ የጽሑፍ መረጃ ሰጥቷት ካነበበች በኋላ “እውነት እንዲህ አደርጋለሁ? እንዲህ ዓይነት ሰው ነኝ ማለት ነው?” ስትል በመገረም ጠይቃ ነበር። የአካባቢው ማኅበራዊ አገልግሎት መሥሪያ ቤት ክሌር አንድን ሥራ በመለማመድ የሚሰጥ ሕክምና እንድትከታተል መከራት። የተለየ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ልጆች በመርዳት ጥሩ ተሞክሮ ያካበተ ክሪስ የተባለ የይሖዋ ምሥክር፣ የእምነት አጋሩ የሆነችው ክሌር የይሖዋ ምሥክሮችን የመሰብሰቢያ አዳራሽ በማደሱና በመጠገኑ ሥራ በፈቃደኝነት እንድትካፈል የሚያስችላትን ዝግጅት አደረገ።

“የገሐዱን ዓለም ኑሮ” መለማመድ

መጀመሪያ ላይ ክሌር አብረዋት ከሚሠሩት ፈቃደኛ ሠራተኞች ጋር አትነጋገርም ነበር። ሐሳቧን በንግግር ከመግለጽ ይልቅ በጽሑፍ ማስፈር ስለሚቀላት ችግር በሚያጋጥማት ጊዜ ለክሪስ ማስታወሻ ትጽፍለት ነበር። ቀስ በቀስ ክሪስ ክሌር ቁጭ ብላ ስለ ሁኔታው አንዳንድ ነገሮችን እንድታስረዳው ያበረታታት ጀመር። ክሪስ ‘በገሐዱ ዓለም እንዴት መኖር’ እንደምትችል በትዕግሥት አስተማራት። ‘በገሐዱ ዓለም’ ከሌሎች ርቆ መኖርና የፈለጉትን ብቻ ማድረግ እንደማይቻል አስረዳት። ክሌር ባገኘችው እርዳታ አማካኝነት አንድን ሥራ ለማከናወን ከሌሎች ጋር መተባበር እንዳለባት ተማረች።

ክሌር ያሳለፈችው ደስ የማይል ተሞክሮ በራስ የመተማመን መንፈስ ስላሳጣት ምንም ዓይነት ሥራ ሲሰጣት መጀመሪያ የምትመልሰው መልስ “አልችለውም” የሚል ነበር። ክሪስ ይህን ችግር የተወጣው እንዴት ነው? አንድ ቀላል ሥራ ይሰጣትና “የሚሠራው በዚህ መንገድ ነው። ልትሠሪው ትችያለሽ” ይላታል። ሥራውን በትክክል ከሠራችው በኋላ በጣም ደስ ይላታል። ክሪስ ሞቅ ባለ ስሜት ያመሰግናትና ሌላ ሥራ ይሰጣታል። በቃል የሚነገራትን መመሪያ አንድ በአንድ ማስታወስ ስለሚቸግራት ዝርዝር መመሪያዎችን በጽሑፍ ያሰፍርላታል። በዚህም ምክንያት ክሌር ቀስ በቀስ በራስ የመተማመን መንፈስ አደረባት።

ክሌር ሰው በሚበዛበት ቦታ ላይ መገኘት ስለማትወድ ለክርስቲያናዊ አምልኮ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ ሰዎችን ማነጋገር በጣም ያስቸግራት ነበር። ቀደም ሲል በመንግሥት አዳራሹ የፊት ወንበር ላይ ብቻዋን የመቀመጥ ልማድ ነበራት። ከጊዜ በኋላ ግን ስብሰባው እንዳለቀ ወዲያውኑ ወደኋላ ወንበር በመሄድ ከአንድ ሰው ጋር ለመጨዋወት ጥረት ማድረግ ጀመረች።

ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ክሌር ብዙ ሰዎችን ማነጋገር እንደምትችል ተገነዘበች። “ግን ቀላል አልነበረም” ብላለች። ያለችበት ሁኔታ ከሰዎች ጋር ለመጨዋወት የምታደርገውን ጥረት በጣም አስቸጋሪ አድርጎባታል፤ ሆኖም ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ሐሳባቸውን በጥሩ ሁኔታ ለመግለጽ የሚያስችላቸውን ሥልጠና በሚያገኙበት በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት አዘውትራ ክፍል ታቀርባለች።

የበለጠ ፈታኝ የሆነውን ሁኔታ መወጣት

ክሌር ይበልጥ በራሷ እየተማመነች በመጣች መጠን ክሪስ ረዳት አቅኚ ሆና ለማገልገል እንድትሞክር ሐሳብ አቀረበላት። ረዳት አቅኚ የሚባሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነታቸውን ለሌሎች በማካፈል በየወሩ 50 ወይም ከዚያ በላይ ሰዓት የሚያሳልፉ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ክሌር ክሪስን “ይህንንስ አልችለውም” አለችው።

ይሁን እንጂ ክሪስ በዚያ ወር 50 ሰዓት መሙላት ባትችልም በመሞከሯ ብቻ እንኳ ደስ ሊላት እንደሚችል በመግለጽ አበረታታት። ክሌርም ረዳት አቅኚነትን ለአንድ ወር የሞከረችው ሲሆን ባገኘችው ተሞክሮ በጣም ተደሰተች። ከዚያ በኋላም በተደጋጋሚ ረዳት አቅኚ መሆኗ የበለጠ ደስታ አስገኝቶላታል። በተለይ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ለማወቅ የሚፈልጉ ብዙ ሰዎችን ማግኘቷ በራስ የመተማመን ስሜቷን አጠናክሮላታል።

በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የዘወትር አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ስለመሆን የሚሰጠው ማበረታቻ፣ ክሌር በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ እንዳትካፈል የሚያግዳት ነገር መኖር አለመኖሩን ለማወቅ ራሷን እንድትመረምር አነሳሳት። ከዚያም የዘወትር አቅኚ ለመሆን ወሰነች። ታዲያ ምን ተሰማት? ክሌር ራሷ እንደተናገረችው “ከዚህ የተሻለ ሥራ ሊኖር አይችልም!” ከጉባኤዋ አባላት ጋር ይበልጥ መቀራረብ የቻለች ከመሆኑም በላይ ብዙ ጓደኞችም አፍርታለች። ልጆች ከእሷ ጋር መጫወት የሚያስደስታቸው ሲሆን አብረዋት በሚያገለግሉበት ጊዜም በደስታ ትረዳቸዋለች።

ድጋፍ መስጠት

አስፐርገርስ ሲንድሮም ያለበት ሁሉ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ መሆን ይችላል ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ይሁንና ከክሌር ተሞክሮ መመልከት እንደሚቻለው ይህ ችግር ያለባቸው ሁሉ ከሚያስቡት የበለጠ ብዙ ነገር ማከናወን ይችላሉ። ክሌር በፕሮግራም የምትመራ መሆኗ በየቀኑ ተመሳሳይ ነገር የማከናወን ፍላጎቷን ያሟላላት ሲሆን ትጉህና እምነት የሚጣልባት መሆኗ ደግሞ በመረጠችው የሥራ መስክ ውጤታማ እንድትሆን አስችሏታል።

ክሌር ስለ ዓለም ያላት አመለካከትና የኑሮን ውጣ ውረድ ለመቋቋም የምታደርጋቸው ነገሮች ከሌሎች የሚለዩት ለምን እንደሆነ ሰዎች መረዳት እንዲችሉ አስፐርገርስ ሲንድሮም እንዳለባት ማወቃቸው አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማታል። “ሐሳብህን በሚገባ መግለጽ ስላልቻልክ ብቻ ሰዎች በትክክል ማሰብ እንደማትችል ሆኖ ይሰማቸዋል” በማለት ተናግራለች። የልብን የሚያካፍሉት ሰው ማግኘት በጣም ጠቃሚ ነው።

ክሪስና ክሌር እንዲህ ያለ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ትንንሽ ግቦችን ማውጣታቸውና በአንድ ጊዜ አንድ ነገር ብቻ ማድረጋቸው ጥሩ እንደሆነ ሐሳብ ይሰጣሉ። ስለ ችግሩ ከሚያውቅ ሰው እርዳታ ማግኘትም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ይህም በራስ የመተማመን ስሜታቸውን ከፍ የሚያደርግላቸው ከመሆኑም ሌላ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እንዲወጡ ያስችላቸዋል።

ከክሌር ታሪክ መገንዘብ እንደሚቻለው ታጋሽ በመሆንና ማበረታቻ በመስጠት አስፐርገርስ ሲንድሮም ያለባቸውን ሰዎች ብዙ መርዳት ይቻላል። ክሌር “ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ አሁን የማደርጋቸውን እነዚህን ሁሉ ነገሮች እሠራለሁ ብዬ አስቤም አልሜም አላውቅም ነበር” በማለት ይህ ሐቅ መሆኑን አረጋግጣለች።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ክሌር ሰዎች አስፐርገርስ ሲንድሮም እንዳለባት ማወቃቸው አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማታል

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አስፐርገርስ ሲንድሮም

ይህ የጤንነት ችግር ስያሜውን ያገኘው በ1944 ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ችግሩ ምንነት ከገለጹት ከዶክተር ሃንስ አስፐርገር ነው። ይሁን እንጂ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሄደ ሕመምተኞችን ስሜት ለመረዳትና ለእነሱ ድጋፍ ለመስጠት ሲባል ብዙ ምርምር የተደረገው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው። የሕክምና ተመራማሪዎች አስፐርገርስ ሲንድሮም ቀለል ያለ የኦቲዝም ዓይነት ይሁን ወይም ራሱን የቻለ የጤና ችግር እርግጠኞች አይደሉም። እስከ አሁን ድረስ የአስፐርገርስ ሲንድሮም መንስኤ ምን እንደሆነ የሚያውቅ ሰው የለም። ይሁን እንጂ በቂ ፍቅርና እንክብካቤ በማጣት ወይም ጥሩ አስተዳደግ ባለማግኘት የሚመጣ አይደለም።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አስፐርገርስ ሲንድሮም ያለባቸውን ሰዎች መርዳት

አስፐርገርስ ሲንድሮም ላለባቸው ሰዎች አሳቢነት ለማሳየትና እነሱን ቀርበህ ለማወቅ ጥረት አድርግ። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ከሌሎች ጋር መጨዋወት አስቸጋሪ ቢሆንባቸውም ጓደኛ እንደሚፈልጉም ሆነ እንደሚያስፈልጋቸው አትዘንጋ። ባሕርያቸው ከሰው የማይገጥመው ወይም አስቸጋሪ የሆኑት ወደው አይደለም።

ታጋሽ ሆነህ ችግራቸውን ለመረዳት ሞክር። በተጨማሪም ነገሮችን በትክክልና በማያሻማ ሁኔታ ማብራራት እንደሚያስፈልግህ ተገንዘብ። ምክንያቱም የምትናገረውን ነገር ቃል በቃል ሊረዱት ይችላሉ። በለመዱት ሥራ ላይ ለውጥ የሚኖር ከሆነ ስለ ሁኔታው በዝርዝር ግለጽላቸው። ምናልባትም አዲሱን አሠራር በተግባር በማሳየት በሚገባ እንዲረዱት ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል።

ያዩት ወይም የሰሙት መጥፎ ነገር ከአእምሯቸው አልወጣ ብሎ በጣም ካስጨነቃቸው የሚያምር ሥዕል በመመልከት ወይም ዘና የሚያደርግ ሙዚቃ በማዳመጥ ሁኔታውን ለመርሳት እንዲሞክሩ አበረታታቸው።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክሪስ፣ ክሌር አንድን ሥራ ለማከናወን ከሌሎች ጋር መተባበር የምትችለው እንዴት እንደሆነ ያስረዳታል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክሌር፣ ቅድሚያውን ወስዳ ሌሎችን ጓደኛ ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ተምራለች