በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ በመላው ዓለም የደረሱት የተፈጥሮ አደጋዎች ቁጥር በአራት እጥፍ አድጓል። በየዓመቱ ከ250 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች የአደጋዎቹ ሰለባ ይሆናሉ።—ኤል ዩኒቨርሳል፣ ሜክሲኮ

“በፓስፊክ ውቅያኖስ አካባቢ የሚነፍሱት ትሬድ ዊንድስ የተባሉት ኃይለኛ ነፋሳት ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ መጠን ያለው ቆሻሻ በውቅያኖሱ ላይ ሰብስበዋል።” ውቅያኖሱ ላይ የተንሳፈፈው ይህ ቆሻሻ የአውስትራሊያን የቆዳ ስፋት ያክላል።—ላ ዳፓሽ ደ ታሂቲ፣ ታሂቲ

ለመጓጓዣ መኪና የሚውል 50 ሊትር ባዮፊዩል ለማውጣት 200 ኪሎ ግራም በቆሎ የሚያስፈልግ ሲሆን ይህ ደግሞ “አንድን ሰው ለአንድ ድፍን ዓመት ለመመገብ ይበቃል!”—ጋዜታ ቪቦርቻ፣ ፖላንድ

በቻይና የሚታተሙ መጽሐፍ ቅዱሶች

“ቻይና በዓለም ላይ መጽሐፍ ቅዱስን በብዛት ከሚያትሙት አገሮች አንዷ ሆናለች” በማለት የሃይማኖታዊ ጉዳዮች አስተዳደር ዋና ኃላፊ የሆኑት ዬ ሻውወን ተናግረዋል። የጂያንግሱ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው በናንጂንግ የሚገኘው የቻይና ማተሚያ ኩባንያ በአገሪቱ የታተመው ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ 50 ሚሊዮን እንዲደርስ በማድረግ ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል። ፒፕልስ ዴይሊ ኦንላይን እንደገለጸው ከሆነ “ከቅርብ ዓመታት ወዲህ [የኩባንያው] ማተሚያ በየዓመቱ 3 ሚሊዮን የሚያህሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን ሲያትም ቆይቷል።” በቻይና ክርስቲያኖች እንደሆኑ የሚናገሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ተዘግቧል።

ሃይማኖታዊ ምስሎች እየተሰረቁ ነው

“ባለፉት አምስት ዓመታት በሩሲያ ውስጥ ከ1,000 የሚበልጡ አብያተ ክርስቲያናት ተዘርፈዋል” በማለት ሩስኪ ኒውስዊክ ዘግቧል። ወደ 40,000 የሚጠጉ ሃይማኖታዊ ምስሎች መሰረቃቸው ለሩሲያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርት ተደርጓል። በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት በሁሉም የቤተ ክርስቲያኗ ምስሎች ላይ በአልትራቫዮሌት ጨረር ብቻ ሊታይ የሚችል ልዩ ምልክት ለማድረግ ታስቧል። ይህ ምልክት መርማሪዎች ተሰርቀው የተገኙት ምስሎች ሕጋዊ ንብረትነታቸው የማን መሆኑን ለይተው እንዲያውቁ ይረዳቸዋል። ሩስኪ ኒውስዊክ እንደዘገበው የሞስኮ መንበረ ፓትርያርክ ‘“ምድራዊ” ምልክቱ የምስሉን ተአምራዊ ኃይል እንደማይለውጠው’ በመግለጽ እርምጃውን በደስታ ተቀብለውታል።

ጦርነቶች የአፍሪካን ሀብት አሟጠጡት

ዚ ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪቢዩን እንደተናገረው “ከ1990 እስከ 2005 ባሉት ዓመታት ውስጥ 23 የአፍሪካ አገሮች ጦርነት ያካሄዱ ሲሆን በዚህ ምክንያት የወጣው ወጪ በአጠቃላይ ወደ 300 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይጠጋል።” የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት የሆኑት ኤለን ጆንሰን-ሰርሊፍ “አፍሪካ እያወጣች ያለችው ወጪ፣ ኤች አይ ቪ እና ኤድስ በአፍሪካ ያስከተሉትን ቀውስ ለመፍታት ወይም ትምህርትንና ውኃን ለማዳረስ እንዲሁም ሳንባ ነቀርሳንና የወባ በሽታን ለመከላከልም ሆነ ለማከም ይበቃ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል። “በሺህ የሚቆጠሩ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶችና መንገዶች መገንባት ይችሉ ነበር።” ጋዜጣው እንዳስገነዘበው ጦርነት ባይኖር ኖሮ አፍሪካ “ከዓለም የመጨረሻዋ ድሀ አህጉር መሆኗ ቀርቶ ባለጸጋ ትሆን ነበር።”

ጥቂት ማሸለብ ሊጠቅምህ ይችላል

ከ23,000 በሚበልጡ ግሪካውያን ወንዶችና ሴቶች ላይ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው በሳምንት ውስጥ ቢያንስ ሦስቱን ቀን ለጥቂት ደቂቃዎች ማሸለብ በልብ ሕመም የመሞትን አጋጣሚ 37 በመቶ ሊቀንሰው ይችላል። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሃርቫርድ የሕዝብ ጤና ትምህርት ቤት ተመራማሪና ኤፒዴሚዮሎጂስት የሆኑት ዲሚትሪዮስ ትሪኮፑሎስ “ድንገተኛም ሆነ ሥር የሰደደ ውጥረት የልብ በሽታ ሊያስከትል እንደሚችል የሚያሳይ ብዙ ማስረጃ አለ” በማለት ተናግረዋል። እኚህ ሰው “ቀትር ላይ ጥቂት ማሸለብ ውጥረትን እንደሚያስታግሥና ከልብ በሽታ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ሞትን እንደሚቀንስ” ገልጸዋል።