ስለ አምላክ ምንነት ምን ማለት ይቻላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ስለ አምላክ ምንነት ምን ማለት ይቻላል?
መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል” ይላል። ይህ ጥቅስ ስለ አምላክ ምንነት አንድ መሠረታዊ እውነት ይኸውም አምላክ መንፈስ መሆኑን ይገልጻል። (ዮሐንስ 4:19-24) ያም ሆኖ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አምላክ ራሱን የቻለ አንድ አካል እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። ስሙም ይሖዋ ነው።—ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም
አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ስለ አምላክ ምንነት የሚሰጡት መግለጫዎች ግራ እንደሚያጋቧቸው ይናገራሉ። አምላክ በዓይን የማይታይ መንፈስ እንጂ የሚዳሰስና የሚጨበጥ አካል ካልሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታዎች ላይ ዓይን፣ ጆሮ፣ አፍንጫ፣ ልብ፣ ክንድ፣ እጅ፣ ጣት እንዲሁም እግር እንዳለው አድርጎ የሚናገረው ለምንድን ነው? * አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ ሰው በአምላክ አምሳል እንደተፈጠረ ስለሚናገር አምላክ ልክ እንደ ሰው ዓይነት አካል እንዳለው አድርገው ያስቡ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረውን ጠለቅ ብሎ መመርመር ግራ የሚያጋቡ የሚመስሉትን እንዲህ ያሉ ሐሳቦች በግልጽ ለመረዳት ያስችላል።—ዘፍጥረት 1:26
ሰው ያሉት ዓይነት ገጽታዎች እንዳሉት ተደርጎ የተገለጸው ለምንድን ነው?
ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ፣ ሰዎች የእሱን ምንነት በቀላሉ እንዲገነዘቡ ለመርዳት ሲል የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ስለ እሱ በሚገልጹበት ጊዜ የሰውን ገጽታዎች ተጠቅመው እንዲጽፉ በቅዱስ መንፈሱ መርቷቸዋል። እንዲህ ያለው አገላለጽ የሰው ቋንቋ እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ለመግለጽ አቅሙ ውስን መሆኑን የሚያሳይ ነው። ዓላማው የአምላክን ምንነት ሰዎች ሊረዱት በሚችሉት መንገድ ጥሩ አድርጎ መግለጽ ነው። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን እንደ “ዐለት፣” እንደ “ፀሓይ” ወይም እንደ “ጋሻ” አድርጎ ሲገልጸው ቃል በቃል እንደማንረዳው ሁሉ እነዚህንም አገላለጾች ቃል በቃል መውሰድ የለብንም።—ዘዳግም 32:4፤ መዝሙር 84:11
በተመሳሳይም ይሖዋ በተሟላ ሁኔታ የሚያንጸባርቃቸውን ባሕርያት ሰውም በተወሰነ ደረጃ እንደሚያንጸባርቅ ለመግለጽ መጽሐፍ ቅዱስ ሰው በአምላክ አምሳል እንደተፈጠረ ይናገራል። እንዲህ ሲባል ሰዎች መናፍስት ናቸው ወይም አምላክ የሰው ዓይነት አካል አለው ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
አምላክ ጾታው ምንድን ነው?
አምላክ ሰብዓዊ ገጽታ እንዳለው ተደርጎ የሚሰጠው መግለጫ ቃል በቃል የሚወሰድ እንዳልሆነ ሁሉ አምላክን በተባዕታይ
ጾታ የሚገልጹ ዘገባዎችም ቃል በቃል መወሰድ የለባቸውም። የጾታ ልዩነት ሥጋዊ አካል ባላቸው ፍጥረታት ዘንድ ብቻ ያለ ነገር ነው፤ ከዚህም ሌላ አንድን አካል በጾታ ለይቶ መጥቀስ የቋንቋ የአገላለጽ ስልት ሲሆን ይህ ደግሞ የሰው ቋንቋ ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነውን የይሖዋን ምንነት በተሟላ ሁኔታ ለመግለጽ ያለበትን የአቅም ውስንነት ያሳያል።መጽሐፍ ቅዱስ “አባት” የሚለውን ስያሜ የሚጠቀም መሆኑ ፈጣሪያችን አፍቃሪ፣ ጠባቂና ተንከባካቢ ከሆነ ሰብዓዊ አባት ጋር ሊመሳሰል እንደሚችል ለመረዳት ያስችለናል። (ማቴዎስ 6:9) እንዲህ ሲባል ግን አምላክን አልፎ ተርፎም በሰማይ ያሉ ሌሎች መንፈሳዊ ፍጥረታትን ተባዕታይ ወይም አንስታይ ጾታ እንዳላቸው አድርገን መመልከት አለብን ማለት አይደለም። ጾታ የመንፈሳዊ አካላትን ምንነት ለመለየት የሚያስችል ገጽታ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ከክርስቶስ ጋር ሰማያዊ መንግሥቱን አብረው እንዲወርሱ የተጠሩ ሰዎች መንፈሳዊ የአምላክ ልጆች ሆነው ክብራቸውን ሲጎናጸፉ ሰብዓዊ ጾታችንን እንደያዝን እንቀጥላለን ብለው እንደማይጠብቁ መጠቆሙ ትኩረት የሚስብ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ እነዚህ ሰዎች የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች ሆነው ክብራቸውን በሚጎናጸፉበት ጊዜ በመካከላቸው ‘ወንድም ሆነ ሴት’ የሚባል ነገር እንደማይኖር አስገንዝቧቸዋል። በተጨማሪም በምሳሌያዊ መንገድ የበጉ ማለትም የኢየሱስ ክርስቶስ “ሙሽራ” እንደሚሆኑ ተገልጿል። ይህ ሁሉ የሚያሳየው አምላክን፣ አንድያ ልጁ የሆነውን ኢየሱስንም ሆነ ሌሎች መንፈሳዊ ፍጥረታትን ሰብዓዊ ገጽታዎች በማላበስ የተሰጡት መግለጫዎች ቃል በቃል የሚወሰዱ እንዳልሆኑ ነው።—ገላትያ 3:26, 28፤ ራእይ 21:9፤ 1 ዮሐንስ 3:1, 2
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የወንድን ድርሻ በትክክል በመረዳት አምላክን ለማመልከት ተባዕታይ ጾታን ተጠቅመዋል። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ድርሻውን በሚገባ የሚወጣ ወንድ ይሖዋ ለምድራዊ ልጆቹ የሚያሳየውን ፍቅራዊና አባታዊ ስሜት በትክክል እንደሚያንጸባርቅ ተገንዝበው ነበር።—ሚልክያስ 3:17፤ ማቴዎስ 5:45፤ ሉቃስ 11:11-13
የአምላክ ዋነኛ ባሕርይ
የሁሉ የበላይ የሆነው ሉዓላዊው ገዥ መንፈስ ቢሆንም ሊቀረብ የማይችል፣ ሚስጥራዊ ወይም የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ የማይፈልግ አምላክ አይደለም። አምላክ መንፈስ መሆኑ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የማንነቱ መገለጫ ስለሆኑትና በፍጥረት ሥራዎቹ ላይ በግልጽ ስለተንጸባረቁት ባሕርያቱ ማለትም ስለ ፍቅሩ፣ ኃይሉ፣ ጥበቡና ፍትሑ ለመማርና እነዚህን ባሕርያቱን ለማድነቅ እንዳይችሉ እንቅፋት አይሆንባቸውም።—ሮሜ 1:19-21
የሆነ ሆኖ የአምላክ ምንነት ዋነኛ በሆነው ባሕርይው ማለትም በፍቅሩ ተጠቃሎ ሊገለጽ ይችላል። ፍቅሩ እጅግ የላቀ ከመሆኑ የተነሳ ፍቅርን ሙሉ በሙሉ እንደተላበሰ ተገልጿል። (1 ዮሐንስ 4:8) ይህ ባሕርይው እንደ ምሕረት፣ ይቅር ባይነትና ትዕግሥት የመሳሰሉትን ሌሎቹን የማንነቱን ገጽታዎች አጠቃሎ ይዟል። (ዘፀአት 34:6፤ መዝሙር 103:8-14፤ ኢሳይያስ 55:7፤ ሮሜ 5:8) ይሖዋ በእርግጥም እኛን የሰው ልጆችን ወደ እሱ እንድንቀርብ የሚጋብዝ የፍቅር አምላክ ነው።—ዮሐንስ 4:23
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.4 ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት፦ ዘፍጥረት 8:21፤ ዘፀአት 3:20፤ 15:8፤ 31:18፤ ኢዮብ 40:9፤ መዝሙር 10:17፤ 18:9፤ 34:15፤ ምሳሌ 27:11፤ ዘካርያስ 14:4፤ ሉቃስ 11:20፤ ዮሐንስ 12:38፤ ሮሜ 10:21፤ ዕብራውያን 4:13
ይህን አስተውለኸዋል?
▪ የአምላክ ስም ማን ነው?—ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም
▪ የአምላክ ባሕርያት በምን ነገሮች ላይ ተንጸባርቀዋል?—ሮሜ 1:19-21
▪ የአምላክ ዋነኛ ባሕርይ ምንድን ነው?—1 ዮሐንስ 4:8