በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

‘በ2002 አንድም ቢሊየነር ያልነበራት ቻይና [በ2006] 15 ያገኘች ሲሆን [በ2007] ደግሞ በቢሊዮን የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ያላቸው ሰዎች ቁጥር 106 ደርሷል።’—ቻይና ደይሊ፣ ቻይና

“በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን የማይንከባከቡ ሕንዳውያን አዲስ በተረቀቀ ሕግ መሠረት እሥራት ሊፈረድባቸው ይችላል፤ ይህ ሕግ ፈጣን የሆነው ሥልጣኔ . . . ለዘመናት የቆየውን የቤተሰብ ትስስር እየሸረሸረው መምጣቱ የፈጠረውን ስጋት የሚያንፀባርቅ ነው።”—ሮይተርስ፣ ሕንድ

“በዛሬው ጊዜ እንግሊዝ ውስጥ ሃይማኖታቸውን በቁም ነገር የሚከተሉ ሙስሊሞች ቁጥር ከአጥባቂ አንግሊካኖች ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ ሳይሆን አይቀርም።”—ዚ ኢኮኖሚስት፣ ብሪታንያ

ውድ የሆኑ ማዕድናትን “የሚያወጡት” የሳይቤሪያ ዛፎች

በሳይቤሪያ ደኖች ውስጥ “ከበሰበሱ የዛፍ ጉቶዎች ወርቅ ማግኘት ይቻላል” በማለት ቨክሩግ ስቬተ የተሰኘው የሩሲያ መጽሔት ዘግቧል። ከኡላን ኡዴ፣ ከኢርኩትስክ እና ከኖቨሰቢርስክ የተውጣጡ የሳይንስ ሊቃውንት፣ የተለያዩ ማዕድናት በብዛት በሚገኙባቸው የሳይቤሪያ አካባቢዎች የሚበቅሉና ዓመቱን ሙሉ ለምለም እንደሆኑ የሚቆዩ ዛፎች ከአፈሩ ውስጥ የሟሙ ማዕድናትን ስበው እንደሚያወጡ ደርሰውበታል። ዛፎቹ አርጅተው ሲበሰብሱ በውስጣቸው ያከማቹት ማዕድን በመሬቱ ላይ ይቀራል። የሳይቤሪያ የሳይንስ ሊቃውንት አሥር ኩንታል ከሚመዝን የእነዚህ ዛፎች ብስባሽ ውስጥ አምስት ግራም ፕላቲነም፣ ወደ 200 ሚሊ ግራም የሚጠጋ ወርቅና ሦስት ኪሎ ግራም ብር አግኝተዋል።

በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የሚሰጥ የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና እርዳታ

በአውስትራሊያ በሚገኝ አንድ የመቃብር ሥፍራ ለሚሠሩ የመቃብር ጉድጓድ ቆፋሪዎች፣ የልብ ምት እንዲቀጥል የሚያደርግ መሣሪያ ተሰጣቸው። ይህ መሣሪያ የተሰጣቸው ለምንድን ነው? በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የልብ ሕመም የሚያጋጥማቸውን በሐዘን የተደቆሱ ሰዎች ለመርዳት ሲባል መሆኑን የሲድኒው ሰን-ሄራልድ ሪፖርት አድርጓል። ይህን ዝግጅት በበላይነት የሚከታተለው የሴንት ጆን አምቡላንስ አገልግሎት ቃል አቀባይ የሆኑት ሲሴናንዳ ሳንቶስ “የቀብር ሥነ ሥርዓት የልብ በሽታ ላለባቸው ሰዎች አደገኛ ነው” በማለት ተናግረዋል። “[በቀብር ሥነ ሥርዓቶች ላይ] በርካታ ሰዎች የሚገኙ ከመሆኑም በላይ ሁሉም በሐዘን ተደቁሰዋል፤ የሐዘንተኞቹ አለባበስም ቢሆን በአብዛኛው ሞቃት ለሆነ ቀን የሚስማማ አይደለም።” ይህ መሣሪያ፣ የሕክምና እርዳታውን ለሚያደርገው ሰው መመሪያ የሚሰጥ የተቀዳ ንግግር አለው። መሣሪያው የሐዘንተኛው ሰው ልብ መምታቱን እንዳቆመ የሚጠቁም ምልክት ሲያገኝ በኤሌክትሪክ ንዝረት አማካኝነት ልቡ እንደገና መምታት እንዲጀምር ያደርጋል።

ፍቺ የአካባቢ ጠንቅ ሆኗል

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመላው ዓለም በከፍተኛ ፍጥነት እያሻቀበ የመጣው የፍቺ ቁጥር፣ ውስን አቅርቦት ያላቸው ነገሮች ፍጆታ እንዲጨምር በማድረጉ በአካባቢ ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው። ፍቺ፣ ጥቂት አባላት ያሏቸው ብዙ ቤተሰቦች እንዲፈጠሩ ምክንያት ስለሚሆን የነፍስ ወከፍ ፍጆታ እንዲጨምር ያደርጋል በማለት ፕሮሲዲንግስ ኦቭ ዘ ናሽናል አካዳሚ ኦቭ ሳይንስስ በተሰኘ ጽሑፍ ላይ የወጣ አንድ ጥናታዊ ዘገባ ተናግሯል። “[በዩናይትድ ስቴትስ] በፍቺ ምክንያት የተለያዩ ቤተሰቦች ፍጆታ፣ በትዳር አብረው ከሚኖሩ ቤተሰቦች ጋር እኩል ቢሆን ኖሮ በ2005 ብቻ ከ2.4 ትሪሊዮን ሊትር በላይ ውኃ፣ በሰዓት ከ73 ቢሊዮን ኪሎ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይልና ከ38 ሚሊዮን በላይ ክፍሎች መቆጠብ ይቻል ነበር።” በ2000 በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በዚህ መንገድ “ሀብት ያባከኑ” 6.1 ሚሊዮን ቤተሰቦች ነበሩ።

የስፒል አናት የሚያህል መጽሐፍ ቅዱስ

የእስራኤል ሳይንቲስቶች በዕብራይስጥ ቋንቋ የተዘጋጀውን ሙሉውን “ብሉይ ኪዳን” “ከስፒል አናት ያነሰ” መጠን ባለው የኮምፒውተር ሲሊከን ቺፕ ላይ መጫን እንደቻሉ ሳይንስ ዴይሊ የተሰኘው የኢንተርኔት ዜና ምንጭ ዘግቧል። ይህ ታላቅ ሥራ የተከናወነው ጽሑፉን በወርቅ በተለበጠችው በዚህች የስፒል ጫፍ የምታክል ሲሊከን ቺፕ ላይ ለመገልበጥ ጋሊየም አዮንስ የሚባሉ ረቂቅ ቅንጣቶችን ጨረር በመጠቀም ነው። “[ይህ] የመጽሐፍ ቅዱስ ፕሮጀክት፣ የምንፈልገውን ነገር በጣም አነስተኛ በሆኑ ነገሮች ላይ መሥራት እንደምንችል ያሳያል” በማለት የቴክኒዮን-እስራኤል የቴክኖሎጂ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ኡሪ ሲቫን ተናግረዋል። በተጨማሪም ይህ ፕሮጀክት “በጣም አነስተኛ በሆኑ ነገሮች ላይ ብዙ መረጃዎችን መያዝ” የሚቻልበትን መንገድ ያመላከተ ነው።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

AP Photo/Ariel Schalit