በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደኋላ የሚፈስ ወንዝ

ወደኋላ የሚፈስ ወንዝ

ወደኋላ የሚፈስ ወንዝ

በካሞቦዲያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ወንዝ ወደኋላ ሲፈስ አይተህ ታውቃለህ? ለመንፈቅ ያህል በውኃ ውስጥ ስለሚቆይ ጫካስ ሰምተህ ታውቃለህ? ከቦታ ቦታ በሚንቀሳቀሱ ተንሳፋፊ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች እንዳሉስ ታውቅ ነበር? “ይህማ እንዴት ሊሆን ይችላል” ብለህ ታስብ ይሆናል። ከባድ ዝናብ በሚዘንብባቸው ወቅቶች ካምቦዲያን ከጎበኘህ በኋላ ግን ሐሳብህን ልትለውጥ ትችላለህ።

ከግንቦት አጋማሽ እስከ ጥቅምት ባሉት ወራት ጠዋት ላይ ብራ የሆነው ሰማይ ይጠቁርና ከቀትር በኋላ ኃይለኛ ዝናብ ይጥላል። በዚህ ወቅት ደረቅና አቧራማ የነበረው መሬት በጎርፍ የሚጥለቀለቅ ሲሆን ወንዞችም ሞልተው ይፈሳሉ።

ወንዙ ወደኋላ የሚፈሰው ለምንድን ነው?

በሚቀጥለው ገጽ ላይ ያለውን ካርታ ተመልከት። ታላቁ የሜኮንግ ወንዝ ከቶንሌ ሳፕ ወንዝ ጋር የሚገናኝበትን ቦታ ልብ በል። እዚህ ቦታ ላይ የሁለቱ ወንዞች ውኃ ይቀላቀልና ብዙም ሳይሄድ የሜኮንግና የባሳክ ወንዝ ሆኖ ይከፈላል። ከዚያም የተከፈሉት ሁለት ወንዞች በስተ ደቡብ አቅጣጫ በመፍሰስ ወደ ቬትናም ከገቡ በኋላ በጣም ሰፊ የሆነውን የሜኮንግ ደለላማ ሥፍራ ይፈጥራሉ።

የዝናቡ ወቅት እንደጀመረ ደለሉ ከሚከማችበት አካባቢ ዝቅተኛ የሆነው ቦታ በጎርፍ ይጥለቀለቃል። ጎርፉ በበጋው ወቅት የሚደርቁትን ገባር ወንዞች ይሞላቸዋል። ከባድ ዝናብ የሚጥልበት ወቅት እየቀጠለ ሲሄድ የቶንሌ ሳፕ ወንዝ ይሞላና እንደተለመደው ወደ ደቡብ አቅጣጫ በመፍሰስ ፈንታ ወደ ሰሜን መፍሰስ ይጀምራል። በዚህ መንገድ ወንዙ ወደ ቶንሌ ሳፕ ሐይቅ እስኪገባ ድረስ ወደኋላ መፍሰሱን ይቀጥላል።

ይህ ሐይቅ የሚገኘው የካምቦዲያ ዋና ከተማ ከሆነችው ከፐኖም ፔን ወደ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ብዙም ጥልቀት የሌለው ቦታ ላይ ነው። ዝናብ በማይኖርባቸው ወራት የሐይቁ ስፋት 3,000 ካሬ ኪሎ ሜትር ገደማ የሚያህል ቦታ ይሸፍናል። በዝናቡ ወቅት ግን የሐይቁ ውኃ በአራት ወይም በአምስት እጥፍ ይጨምራል። ይህ ደግሞ የቶንሌ ሳፕ ሐይቅን በደቡብ ምሥራቅ እስያ ካሉት ጨው አልባ ሐይቆች ሁሉ ትልቁ እንዲሆን ያደርገዋል።

የሩዝ ማሳዎች፣ መንገዶች፣ ዛፎችና መንደሮች የነበሩባቸው ቦታዎች በዚህ ወቅት በሐይቁ ይዋጣሉ። በበጋው ወቅት አንድ ሜትር ጥልቀት ባለው ውኃ ላይ ጀልባቸውን ይቀዝፉ የነበሩት ዓሣ አጥማጆች በዝናቡ ወራት ግን እስከ 10 ሜትር የሚደርስ ቁመት ባላቸው ዛፎች አናት ላይ ይንሳፈፋሉ! በሌላ ቦታ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ያለው የጎርፍ መጥለቅለቅ በአብዛኛው የተፈጥሮ አደጋ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር። ለካምቦዲያ ሕዝቦች ግን ይህ ሁኔታ ብዙውን ጊዜ እንደ በረከት ይቆጠራል። ለምን?

የጎርፍ መጥለቅለቁ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

ወደኋላ የሚፈሰው የቶንሌ ሳፕ ወንዝ ለም የሆነ ደለል ወደ ሐይቁ ያመጣል። በተጨማሪም ብዛት ያላቸው ዓሦች ከሜኮንግ ወንዝ እየዋኙ ወደ ሐይቁ በመምጣት በአልሚ ማዕድናት በበለጸገው በዚህ አካባቢ እንቁላላቸውን ይጥላሉ። ይህም የቶንሌ ሳፕ ሐይቅን በዓለም ላይ ጨው አልባ በሆኑ ውኃዎች ውስጥ የሚኖሩ ዓሦች በብዛት ከሚገኙባቸው ቦታዎች አንዱ እንዲሆን አድርጎታል። የዝናቡ ወቅት ካለፈ በኋላ የሐይቁ ውኃ በፍጥነት ስለሚጎድል አንዳንድ ጊዜ ዓሣ አጥማጆች በዛፎች ቅርንጫፎች ላይ ተይዘው የቀሩ ዓሦችን መልቀም ይችላሉ!

በየዓመቱ የሚከሰተው ይህ የጎርፍ መጥለቅለቅ በሥነ ምሕዳሩ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያስከትላል። በጎርፍ በሚጥለቀለቀው አካባቢ የሚበቅሉት ዛፎችና ሌሎች ተክሎች በጎርፍ በማይጥለቀለቁ ቦታዎች ከሚገኙ ተክሎች የተለየ የእድገት ኡደት አላቸው። ሞቃታማ በሆኑ አካባቢዎች የሚበቅሉ ዛፎች በአብዛኛው በደረቁ ወቅት ቅጠሎቻቸውን በማርገፍ ቀስ ብለው ያድጋሉ። በዝናባማው ወቅት ደግሞ እንደ አዲስ ማቆጥቆጥ ይጀምራሉ። በአንጻሩ ግን በቶንሌ ሳፕ አካባቢ የሚበቅሉ ዛፎች በጎርፉ እስከሚዋጡ ድረስ ቅጠሎቻቸውን አያረግፉም። በተጨማሪም እድገታቸው በዝናቡ ወራት በመፋጠን ፈንታ አዝጋሚ ይሆናል። ውኃው ሲጎድልና ሞቃታማው ወቅት ሲጀምር የዛፎቹ ቅርንጫፎች እምቡጥ የሚይዙ ሲሆን ቅጠሎቻቸውም በፍጥነት ያድጋሉ። የሐይቁ ውኃ ቀንሶ ወደነበረበት መጠን ሲመለስ፣ በመጪዎቹ ሞቃታማ ወራት ለዛፎችና ለሌሎች ዕፅዋት ማዳበሪያ በሚሆኑት የበሰበሱ ቅጠሎች የተሸፈነው መሬት ይታያል።

ከመሬት ከፍ ብለው የተሠሩ ቤቶችና ተንሳፋፊ መኖሪያዎች

ሰዎቹስ የሚኖሩት እንዴት ነው? በሐይቁ ዳርቻ ላይ የሚገኙ አንዳንድ ሰዎች ከመሬት ከፍ ብለው በተሠሩ ትንንሽ ቤቶች ውስጥ ይኖራሉ። ዝናብ በማይኖርባቸው ወራት በመሬቱና በእነዚህ ቤቶች ወለል መካከል ያለው ርዝመት እስከ 6 ሜትር ይደርሳል። ውኃው በጣም በሚጨምርበት ጊዜ ግን የዓሣ ማጥመጃ ጀልባዎችና አንዳንድ ጊዜ ልጆችን ለማጓጓዝ የሚጠቀሙባቸው ትላልቅ ሳፋዎች ቤቱ ደጃፍ ድረስ መጥተው ይቆማሉ።

ሌሎቹ ደግሞ በጀልባ ላይ እንደሚሠሩ ቤቶች በሚንሳፈፉ ርብራቦች ላይ በሠሯቸው ቤቶች ውስጥ ይኖራሉ። የቤተሰቡ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ሌላ ተንሳፋፊ ርብራብ ከቤቱ ጋር በማያያዝ ቤቱ እንዲሰፋ ይደረጋል። በሐይቁ ላይ 170 የሚያህሉ ተንሳፋፊ መንደሮች እንዳሉ ይገመታል።

ቀን ቀን ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች የዓሣ ማጥመጃ ወጥመዶቻቸውንና መረቦቻቸውን ይዘው ዓሣ ሲያጠምዱ ይውላሉ። የውኃው ከፍታ በጨመረ ወይም በቀነሰ ቁጥር፣ የተወሰኑ ቤቶች ወይም በርካታ መንደሮች እየተንሳፈፉ ቀድሞ ከነበሩበት አካባቢ ተነስተው ብዙ ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ሌላ ቦታ ላይ ሊሰፍሩ ይችላሉ። ይህን የሚያደርጉት ወደ አዲሱ የባሕር ዳርቻ ወይም ይበልጥ ዓሣ ወደሚገኝበት አካባቢ ለመጠጋት ሲሉ ነው።

ረጃጅም ታንኳዎች የማኅበረሰቡን ዕለታዊ ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ ሸቀጦችን የሚያቀርቡ መደብሮች ወይም ተንሳፋፊ ገበያዎች በመሆን ያገለግላሉ፤ አልፎ ተርፎም የሕዝብ መጓጓዣ “አውቶቡሶች” ይሆናሉ። ተማሪዎችም ተንሳፋፊ በሆኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ትምህርታቸውን ይከታተላሉ። ወደኋላ በሚፈሰው ወንዝ ላይ ከዕፅዋት አንስቶ እስከ ሰዎች ድረስ ሁሉም፣ ውኃው የሚፈስበትን አቅጣጫ መሠረት አድርጎ ሕይወቱን ይመራል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

በበጋ ወቅት

በዝናብ ወቅት

ካምቦዲያ

ቶንሌ ሳፕ ሐይቅ

ቶንሌ ሳፕ ወንዝ

ሜኮንግ ወንዝ

ፐኖም ፔን

ባሳክ ወንዝ

የሜኮንግ ደለላማ ሥፍራ

ቬትናም

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ትንሽ ልጅ በቶንሌ ሳፕ ወንዝ ላይ ሲቀዝፍ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አንድ መንደር በበጋው ወቅትና በዝናቡ ወቅት የሚኖረውን ልዩነት የሚያሳዩ ፎቶዎች

[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

ካርታ፦ Based on NASA/Visible Earth imagery; የመንደሩ ፎቶዎች፦ FAO/Gordon Sharpless