በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአውሮፓን ጎሽ ከጥፋት መታደግ ተቻለ

የአውሮፓን ጎሽ ከጥፋት መታደግ ተቻለ

የአውሮፓን ጎሽ ከጥፋት መታደግ ተቻለ

ፖላንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

አዳኞቹ ሲፈልጉት የቆዩትን ዱካ በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል። ዱካውን ተከትለው ሲሄዱ በመጨረሻ የሚፈልጉትን ነገር ተመለከቱ። ጠቆር ያለ ቡናማ ፀጉር ያለው ሲሆን ጢሙ ጥቁር ነው ማለት ይቻላል። ጭንቅላቱ ላይ ከፍ ብለው የሚገኙት ሹል ቀንዶቹ ወደ ላይ ተቆልምመዋል። ሥጋውና ቆዳው በጣም ተፈላጊ በመሆኑ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ያስገኛል።

አዳኞቹ የተኮሱት የመጀመሪያው ጥይት አውሬውን አቆሰለው። አውሬው ሸሽቶ ጫካ ውስጥ ሊደበቅ ሞከረ፤ ሆኖም አልተሳካለትም። ለሁለተኛ ጊዜ የተተኮሰው ጥይት ዒላማውን ስላገኘ 500 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ግዙፍ ፍጡር መሬት ላይ ተዘረረ። በዚህ ወቅት አዳኞቹ አንድ ታሪክ የሠሩ መሆናቸውን አልተገነዘቡም። ጊዜው ሚያዝያ 1919 ነበር። አዳኞቹ በፖላንድ ቆላማ አካባቢዎች የሚገኘውን ባይሰን ተብሎ የሚጠራ በዱር የሚኖር የመጨረሻ የአውሮፓ ጎሽ መግደላቸው ነበር። ደግነቱ በወቅቱ በዱር እንስሳት መጠበቂያዎችና በግለሰቦች እጅ የሚገኙ የአውሮፓ ጎሾች ነበሩ።

ይሰን ወይም አንዳንድ ጊዜ ቪዘንት ተብሎ የሚጠራው የአውሮፓ ጎሽ ጥንት በአብዛኛው የአውሮፓ አህጉር በብዛት ይገኝ ነበር። እድገቱን የጨረሰ ወንድ ጎሽ እስከ 900 ኪሎ ግራም ሊመዝን የሚችል ሲሆን ከትከሻው አካባቢ ቢለካ ቁመቱ ከሁለት ሜትር በላይ ሊሆን ይችላል። ይህ ግዙፍ አጥቢ እንስሳ “የጫካው ንጉሥ” ተብሎ ተጠርቷል።

ይህ እንስሳ ተለይቶ ከሚታወቅባቸው ባሕርያት አንዱ ከፊት ያለው የሰውነቱ ክፍል ከኋለኛው ክፍል ጋር ተመጣጣኝ አለመሆኑ ነው። ትከሻው ሰፊና ከፍ ያለ ሲሆን ትልቅ ሻኛ አለው። የኋለኛው የሰውነቱ ክፍል ግን ከፊተኛው ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው። ሰውነቱ ከኋላ በኩል በአጫጭር ፀጉሮች የተሸፈነ ሲሆን ከፊት አካባቢ ረዥምና ጨብራራ ፀጉር እንዲሁም ጢም አለው።

ሊጠፋ ተቃርቦ ነበር

በዛሬው ጊዜ በሕይወት የሚገኙት የአውሮፓ ጎሾች ቁጥር ከጥቂት ሺዎች እንደማያልፍ ይገመታል። የእርሻ መሬት መስፋፋትና የደን መጨፍጨፍ የተፈጥሮ መኖሪያቸውን የነጠቃቸው ሲሆን አዳኞችም ያለምሕረት ጨፍጭፈዋቸዋል። በስምንተኛው መቶ ዘመን በጎውል (የዘመናችን ፈረንሳይና ቤልጅየም) ይኖሩ የነበሩት የአውሮፓ ጎሾች ሞተው አለቁ።

በ16ኛው መቶ ዘመን የፖላንድ ነገሥታት ለእነዚህ የጎሽ ዝርያዎች ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችል እርምጃ ወሰዱ። እርምጃ ለመውሰድ የመጀመሪያ ከነበሩት ነገሥታት መካከል ዳግማዊ ሲገስመንድ ኦገስተስ ይገኙበታል። እኚህ ንጉሥ የአውሮፓውን ጎሽ መግደል በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል እንደሆነ የሚገልጽ ድንጋጌ አወጡ። እንዲህ ያደረጉት ለምን ነበር? የቢያዎቪዛ ብሔራዊ ፓርክ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ዝቢግኒየቭ ክራሽንስኪ እንዳሉት “ዓላማቸው ገዥዎቹና ባለሟሎቻቸው የሚታደን አውሬ እንዳያጡ ነበር።” ይህን እንስሳ ማደን ከባድ ቅጣት የሚያስከትል ቢሆንም ሕጉ እንስሳቱን ከመጥፋት ሊታደግ አልቻለም። በመሆኑም በ18ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ፣ በምሥራቃዊ ፖላንድ በቢያዎቪዛ ጫካና በኮውኬዢያ ከሚገኙት የአውሮፓ ጎሾች በስተቀር በሌሎች አካባቢዎች የነበሩት በሙሉ ጠፉ።

ይሁንና በ19ኛው መቶ ዘመን ጥሩ ለውጥ መታየት ጀመረ። የቢያዎቪዛ ጫካ ወደ ሩሲያ ግዛት ከተቀላቀለ በኋላ ቀዳማዊ አሌክሳንደር የአውሮፓ ጎሾች ጥበቃ እንዲደረግላቸው የሚያዝዝ ሕግ አወጡ። ወዲያው ጥሩ ውጤት ታየ። የእንስሳቱ ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ በ1857 በመንግሥት ጥበቃ ሥር የሚገኙት የአውሮፓ ጎሾች ቁጥር 1,900 ደረሰ። ከጊዜ በኋላም በበረዶ ወራት ለአውሮፓ ጎሾች ምግብ የሚያቀርቡ ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ ተደረገ። ኩሬዎች በጥንቃቄ ከመዘጋጀታቸውም በላይ ለመኖ የሚያገለግሉ ተክሎችን ለማልማት መሬቱ ተመነጠረ።

የሚያሳዝነው ግን ለጎሾች የሚደረገው እንዲህ ያለው እንክብካቤ የዘለቀው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነበር። በ60 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ቁጥራቸው በግማሽ ቀነሰ። በፖላንድ ዱር ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ጎሾች ከሁሉ የከፋ ችግር የደረሰባቸው አንደኛው የዓለም ጦርነት በፈነዳበት ወቅት ነበር። የጀርመን መንግሥት “ጎሾቹን ለመጪው ትውልድ ብርቅዬ የተፈጥሮ ቅርስ አድርጎ ለማቆየት” የሚያስችል አዋጅ ቢያወጣም የጎሾቹ መንጎች በሽሽት ላይ በሚገኙት የጀርመን ወታደሮች፣ በሩሲያ ተከላካይ ተዋጊዎችና ምንጊዜም ተኝተውላቸው በማያውቁት አዳኞች ተጨፈጨፉ። በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው በ1919 በፖላንድ ጫካ ይኖር የነበረው የመጨረሻው የአውሮፓ ጎሽ ተገደለ።

ቁጥሩ እንደገና ጨመረ

እነዚህን የጎሽ ዝርያዎች ከጥፋት ለማዳን በ1923 የአውሮፓ ጎሾች ጥበቃ ዓለም አቀፍ ማኅበር ተቋቋመ። የዚህ ማኅበር ተቀዳሚ ዓላማ በሰዎች ጥበቃ ሥር የሚገኙትን ባይሰን የሚባሉ ያልተዳቀሉ ጎሾች መቁጠር ነበር። * የቆጠራው ውጤት እንዳሳየው በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የተለያዩ የአራዊት መጠበቂያ ተቋማት ውስጥ እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች 54 የሚያክሉ ያልተዳቀሉ የቆላ ባይሰኖች ተገኙ። ይሁን እንጂ እነዚህ በሙሉ ለርቢ ተስማሚ አልነበሩም። አንዳንዶቹ ያረጁ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ በበሽታ የተጠቁ ነበሩ። በመጨረሻ ዝርያዎቹን ለማባዛት የሚያስችሉ 12 ጎሾች ተመረጡ። በአሁኑ ጊዜ በቆላማ አካባቢዎች የሚገኙት የአውሮፓ ጎሾች በሙሉ ከእነዚህ ውስጥ የአምስቱ ዝርያዎች ናቸው።

በ1929 የመፀው ወራት ሁለት የቆላ የአውሮፓ ጎሾች ወደ ዱር ተለቀው በቢያዎቪዛ ጫካ ውስጥ በተዘጋጀላቸው ልዩ አካባቢ እንዲኖሩ ተደረገ። ከአሥር ዓመት በኋላ ቁጥራቸው አድጎ 16 ደረሰ።

ከመጥፋት ድኗል?

በ21ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በመላው ዓለም የሚገኙት ባይሰን የሚባሉ የአውሮፓ ጎሾች 2,900 ነበሩ። ከእነዚህ መካከል 700 የሚያክሉት በፖላንድ የሚገኙ ነበሩ። በቀጣዮቹ ዓመታት የአውሮፓ ጎሽ መንጎች በቤላሩስ፣ በኪርጊስታን፣ በሊቱዌንያ፣ በሩስያና በዩክሬን ተባዝተዋል።

ይህ ማለት ግን በአውሮፓ ጎሾች ላይ ተጋርጦ የነበረው አደጋ ጨርሶ ተወግዷል ማለት አይደለም። ተባዮች፣ በሽታ፣ የምግብና የውኃ እጥረት እንዲሁም አዳኞች አሁንም ሕልውናቸውን በመፈታተን ላይ ናቸው። በተጨማሪም ሁለቱ ጾታዎች የሚያበረክቱት ጂን የተሟላ አለመሆኑ የሚያስከትለው በዘር የሚተላለፍ ጉድለት ከባድ ችግር ሆኖባቸዋል። በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ የአውሮፓው ጎሽ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ የመጥፋት አደጋ ከተደቀነባቸው የአራዊትና የዕፅዋት ዝርያዎች ዝርዝር ውስጥ ሊወጣ አልቻለም።

የሰው ልጅ ይህን የእንስሳ ዝርያ ከመጥፋት ለማዳን ያደረገው ብርቱ ጥረት እንስሳው እስከ ዘመናችን እንዲቆይ አስችሎታል። ይሁን እንጂ ከላይ የተጠቀሱት ዶክተር ክራሽንስኪ “በአውሮፓ ጎሽ ላይ የደረሰው ነገር፣ አንድ ዝርያ እንዴት በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥፋት አፋፍ ላይ ሊደርስ እንደሚችልና ከጥፋት ለመታደግ ግን ምን ያህል ከፍተኛ ጥረት እንደሚጠይቅ ያሳያል” ብለዋል። ስለዚህ እንስሳም ሆነ ስለሌሎች በርካታ እንስሳት የወደፊት ዕጣ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ለጊዜው ግን “የጫካው ንጉሥ” ከመጥፋት ድኗል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 ባይሰን የሚባለው የአውሮፓ ጎሽ ሁለት ዝርያዎች አሉት። እነሱም የቆላው የአውሮፓ ጎሽ ዝርያና የኮውኬዢያ ወይም ተራራማ ቦታዎች ላይ የሚኖረው የአውሮፓ ጎሽ ዝርያ ናቸው። የመጨረሻው የኮውኬዢያ ጎሽ የሞተው በ1927 ነበር። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል የዚህ ጎሽ ዝርያ ከቆላ ጎሽ ጋር እንዲዳቀል በማድረግ የተዳቀለ ዝርያ ማግኘት ተችሎ ነበር። ዛሬም ጥቂት ቁጥር ያላቸው የተዳቀሉ የኮውኬዢያ ጎሾች አሉ።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በቢያዎቪዛ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኝ የአውሮፓ ጎሽ

[ምንጭ]

ሁሉም ፎቶዎች፦ Białowieski Park Narodowy