በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፖርቶ ሪኮ—በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች ደሴት

ፖርቶ ሪኮ—በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች ደሴት

ፖርቶ ሪኮ—በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች ደሴት

ኅዳር 19, 1493 ክሪስቶፈር ኮሎምበስ በስፔን መርከቦች ታጅቦ ወደ አንዲት ለምለም የካሪቢያን ደሴት ደረሰ። እዚያ እያለም ደሴቲቷን ሳን ህዋን ባውቲስታ (ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቁ) ብሎ ሰየማት። ቀለብ ለማሟላት በደሴቲቱ ላይ ጥቂት ቆይታ ካደረገ በኋላ ከዚያ ተነስቶ የጀመረውን ሁለተኛ የአሰሳ ጉዞ ቀጠለ።

በዘንባባ ዛፎች ያጌጡት ወርቃማ የባሕር ዳርቻዎችና ማራኪ የሆኑት የሐሩር ክልል ዕፅዋት ለዚህ አሳሽ ምኑም አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ ኮሎምበስ ቆርጦ የተነሳው ትልልቅ ደሴቶችን ለማግኘትና ሀብት ለመሰብሰብ ነበር።

በዚህ ጉዞ ላይ ከኮሎምበስ ጋር አብሮ እንደነበረ የሚታመነው ፖንሴ ዴ ሌዮን የተባለ ስፔናዊ፣ ያገሬው ሰዎች ቦሪኩየን ብለው ወደሚጠሯት ወደዚህች ደሴት ተመልሶ ለመምጣት ወሰነ። ያገሬው ተወላጆች የወርቅ ጌጣጌጦች እንዳላቸው ሲሰማ በደሴቲቱ ላይ ያሉ ኮረብቶች ወርቅ ሊገኝባቸው እንደሚችል አስቦ ነበር። ከአሥራ አምስት ዓመታት በኋላ ወርቅ ለመፈለግ ወደ ደሴቲቱ ተመለሰ። በ1521 ስፔናውያኑ በዋነኝነት በደሴቲቱ ሰሜናዊ የባሕር ዳርቻ ላይ ሰፈሩ። ፖንሴ ዴ ሌዮን ብዙ የወርቅ ሀብት አገኝበታለሁ በሚል ተስፋ አዲሱን ከተማ ፖርቶ ሪኮ ማለትም “ሀብታም ወደብ” ብሎ ሰየመው። *

የፖንሴ ዴ ሌዮን ምኞት መና ሆኖ ቀረ። በፖርቶ ሪኮ የተገኘው በጣም ጥቂት መጠን ያለው ወርቅ ወዲያውኑ ከማለቁም በላይ የፖለቲካ ችግሮችም እየጨመሩ መጡ። በመጨረሻም ፖንሴ ዴ ሌዮን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ወደሚገኘው በዛሬው ጊዜ ፍሎሪዳ ተብሎ ወደሚጠራው ግዛት ሄደ።

ምንም እንኳ ደሴቲቱ የነበራት የማዕድን ሀብት ጥቂት ቢሆንም ስፔናውያን፣ የፖርቶ ሪኮ ዋና ወደብ ጠቃሚ ሀብት ሊሆን እንደሚችል ወዲያውኑ ተገነዘቡ። በ16ኛው መቶ ዘመን ወርቅ ጭነው ከአሜሪካ አገሮች ወደ ስፔን የሚሄዱት መርከቦችን ከአደጋ ለመጠበቅ ሲባል የደሴቲቱን ዋና ከተማ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት ወደብ አደረጉት። ብዙም ሳይቆይ ሳን ህዋን “በአሜሪካ ያለ የስፔን ዋነኛ ግዛት” በመባል ይታወቅ ጀመር።

ከፍታቸው 13 ሜትርና ውፍረታቸው እስከ 6 ሜትር የሚደርስ ጠንካራ ቅጥሮችና በጣም ግዙፍ የሆኑት ሁለት የግንብ ምሽጎች የሳን ህዋን ሕዝቦች ከተማቸውን ለመጠበቅ ላደረጉት ለየት ያለ ጥረት ምሥክር ናቸው። ሳን ህዋን ዛሬም በካሪቢያን ካሉት ተወዳጅ የቱሪስት መስህቦች መካከል አንዱ ነው። ጎብኚዎች የከተማውን ቅጥሮች እየተዘዋወሩ ሲመለከቱ እንዲሁም ጥንታዊ ሕንፃዎችን ሲጎበኙ በቅኝ ግዛት ዘመን ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር በዓይነ ሕሊናቸው መሳል አይከብዳቸውም።

አሮጌውን ሳን ህዋን መጎብኘት

አሮጌው ሳን ህዋን ተብሎ የሚጠራው በቅጥር የተከበበ ከተማ በዙሪያው ካለው ሕዝብ የሚተራመስበት ዘመናዊ ከተማ አንፃር ሲታይ ግርግር የሚበዛበት አይደለም። አሮጌው ሳን ህዋን ከርቀት ሲታይ በውቅያኖስ ላይ የሚንሳፈፍ መርከብ ይመስላል። ዙሪያውን በባሕር ተከቦ የሚገኘውና የመርከብን ፊት ለፊት የሚመስለው የሳን ህዋን ክፍል ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ የገባ ነው። በዚህ ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ ስፔኖች የወደቡን መግቢያ ለመጠበቅ የገነቡት ኤል ሞሮ የሚባል የግንብ ምሽግ ይገኛል። ከኤል ሞሮ በስተጀርባ ደግሞ የመርከብ አፍንጫ የሚመስለውን ሾጠጥ ብሎ የወጣውን ልሳነ ምድር የሚከብ በሁለቱም ጠረፎች ዙሪያ የተገነባ ግዙፍ ግንብ ይገኛል። በምሥራቅ በኩል 1.6 ኪሎ ሜትር ያህል ራቅ ብሎ ሳን ክሪስቶባል ተብሎ የሚጠራ ግዙፍ ምሽግ የሚገኝ ሲሆን ይህም የመርከብን ኋለኛ ክፍል የሚመስለውን የከተማውን ክፍል ከማንኛውም ዓይነት ጥቃት ለመከላከል ያገለግል ነበር። ዩኔስኮ በ1983 በዓለም ቅርስነት የመዘገበው አሮጌው ሳን ህዋን በእነዚህ ሁለት የግንብ ምሽጎች መካከል ይገኛል።

አሮጌው ከተማ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እድሳት ሲደረግለት ቆይቷል። የከተማው ነዋሪዎች ቤቶቻቸውን የሚያምሩ ደማቅ ቀለማት የሚቀቡ ሲሆን ከብረት የተሠሩ ሰገነቶቻቸውን ደግሞ በአበቦች ያስጌጣሉ፤ ግቢዎቻቸውም በሐሩር ክልል ተክሎች የተሞሉ ናቸው። በሳን ህዋን ጠባብ ጎዳናዎች ላይ የተነጠፉት ሰማያዊ ግራጫ ቀለም ያላቸው ትንንሽ ድንጋዮች የተገኙት ከስፔን የብረት ማዕድን ማውጫዎች ነው። ከማዕድን ማውጫዎቹ ከሚገኘው የብረት ዝቃጭ ትንንሽ ድንጋዮች የሚሠሩ ሲሆን እነዚህ ድንጋዮች ወደ ፖርቶ ሪኮ የሚጓዙ መርከቦችን ሚዛን ለመጠበቅ ያገለግሉ ነበር።

በሳን ክሪስቶባል ግንብ ላይ የሚገኙት ጥንታዊ የስፔን መድፎች አሁንም ድረስ ወደ ወደቡ እንዳነጣጠሩ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ በወደቡ ላይ የሚያዘወትሩት ወርቅ ጭነው የሚመጡ የስፔን መርከቦች ሳይሆኑ አገር ጎብኚዎችን የጫኑ ግዙፍ የሽርሽር መርከቦች ናቸው። ዘና የሚያደርገው የአካባቢው ሁኔታና የደሴቲቱ ነዋሪዎች ተግባቢነት ከተማው ተወዳጅ የቱሪስት መስህብ እንዲሆን አድርጎታል። በአሮጌው ከተማ ውስጥ አሁንም ድረስ ቅድሚያ የሚሰጠው ለእግረኞች ስለሆነ ጎብኚዎች በመንገድ ላይ ቆመው ፎቶ ሲያነሱ ባለመኪናዎች በትዕግሥት ይጠብቋቸዋል።

ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገቡ አራት የተፈጥሮ ሀብቶች

ምንም እንኳ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የደሴቲቱ ሕዝብ የሚኖረው በሳን ህዋን ቢሆንም ፖርቶ ሪኮ ሌሎች ብዙ መስህቦች አሏት። ደሴቲቷ በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ ትንሽ ብትሆንም የተለያየ የአየር ንብረትና መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ያላት መሆኑ ለብዙ ዓይነት ዕፅዋትና እንስሳት መኖሪያነት ተስማሚ እንድትሆን አድርጓታል። የፖርቶ ሪኮ ባለሥልጣናት ጥበቃ ለማድረግ ከሚጣጣሩላቸው የተፈጥሮ ሀብቶች መካከል አራቱ የሚከተሉት ናቸው።

ኤል ዩንኬ ብሔራዊ ደን በካሪቢያን ከቀሩት ጥበቃ የሚደረግላቸውና ዝናብ የሚበዛባቸው የሐሩር ክልል ደኖች መካከል አንዱ ነው። በደኑ ውስጥ የሚገኙት ኮረብቶች በፏፏቴዎች ያጌጡ ናቸው። ኦሬንጅ ብሮሚሊያድ የሚባለው ተክል የሚያወጣው አበባ ሁልጊዜ ደመና በማያጣው ጫካ ውስጥ ለሚገኙት ዛፎች ድምቀት የሚጨምርላቸው ሲሆን ግዙፍ የሆኑት የፈርን ዝርያዎች ደግሞ ሊያና ከሚባሉት ወፋፍራም ሐረጎችና ከዘንባባዎች ጋር ቦታ ይሻማሉ። ምንም እንኳ የፖርቶ ሪኮው በቀቀን ከምድር ገጽ ለመጥፋት የተቃረበ ቢሆንም በዚህ ደን ውስጥ ያለ ምንም ሥጋት ይኖራል። ኮኪ የሚባለው በዛፍ ላይ የሚኖረው የፖርቶ ሪኮው ትንሽ እንቁራሪትም በማያቋርጥ ዝማሬው ጫካውን ያደምቀዋል።

የኤል ዩንኬ ተረተሮች ከርቀት ሲታዩ ብርማ ቀለም ያለው መጎናጸፊያ የደረቡ ይመስላሉ። እንዲህ ዓይነት ቀለም ሊኖራቸው የቻለው ሁጎ የሚባለው ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ከአያሌ ዓመታት በፊት ጥፋት ካደረሰ በኋላ ያግሩሞ ተብሎ የሚጠራው ዛፍ በብዛት በመብቀሉ ምክንያት ነው። ይህ ዛፍ መብቀሉ አንድ የሚጠቁመው ነገር አለ። አንድ የፓርክ ባዮሎጂስት “ደኑ ከተፈጥሮ አደጋ በኋላ ብዙም ልፋት ሳይጠይቅ እንደገና ማንሰራራት ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል። “[ለደን] ቀንደኛው ጠላት ሰው ነው።” ፓርኩ በውስጡ 225 ዓይነት ዛፎችን፣ 100 የፈርን ዝርያዎችንና 50 የኦርኪድ ዝርያዎችን ይዟል። ይህ ፓርክ በውስጡ በርካታ የዕፅዋት ዝርያዎች ስላሉት የተባበሩት መንግሥታት ጥበቃ ከሚያደርግላቸው ክልሎች መካከል አንዱ ሆኗል።

ጉዋኒካ የሥነ ሕይወት ጥበቃ ክልል። በዓለም ላይ ካሉት ዝናብ የማይበዛባቸው የሐሩር ክልል ደኖች ውስጥ እስካሁን ሳይጠፋ የቀረው 1 በመቶ ያህሉ ብቻ ሳይሆን አይቀርም። ከዚህ ውስጥ ከኤል ዩንኬ በመኪና ጥቂት ሰዓታት በሚያስኬድ ቦታ ላይ ያለው ደን ይገኝበታል። አንዳንድ የዕፅዋት ተመራማሪዎች ጉዋኒካን “በዓለም ላይ ባሉ ከፊል ሞቃታማ ክልሎች ውስጥ ለሚገኘው ዝናብ የማይበዛው ደን ዓይነተኛ ምሳሌ ሳይሆን አይቀርም” በማለት ይገልጹታል። ይህ ደን ለአብዛኞቹ የፖርቶ ሪኮ ብርቅዬ አእዋፍና 750 ለሚሆኑ የዕፅዋት ዝርያዎች መኖሪያ ነው፤ ከእነዚህ የዕፅዋት ዝርያዎች መካከል 7 በመቶ የሚሆኑት ከምድር ገጽ ለመጥፋት የተቃረቡ ናቸው። በዓይነታቸው ልዩ የሆኑት አበቦች ሃሚንግበርድ ተብለው የሚጠሩትን ወፎችንም ሆነ በርካታ ቢራቢሮዎችን ይስባሉ። በዚህ ደን ዳር ዳር አረንጓዴ ዔሊዎችና ሌዘርባክ የሚባሉ የዔሊ ዝርያዎች እንቁላላቸውን የሚጥሉበት የተፈጥሮ ውበቱን የጠበቀ የባሕር ዳርቻ ይገኛል።

ማንግሩቭ እና ኮራል ሪፍ። ጉዋኒካ የሥነ ሕይወት ጥበቃ ክልል ከሚያካትታቸው የተፈጥሮ ሀብቶች መካከል በባሕሩ ዳርቻ ላይ ያለው የማንግሩቭ ደን ይገኝበታል። አንድ የፓርኩ ጠባቂ “በጥበቃ ክልሉ ውስጥ ከኢንዱስትሪ የሚለቀቅ ፍሳሽም ሆነ ከእርሻዎች ላይ ታጥቦ የሚሄድ ኬሚካል ስለሌለ የማንግሩቭ ደኑን ደኅንነት ለመጠበቅ ተችሏል” በማለት ተናግሯል። “የማንግሩቭ ደን ደግሞ በኮራል ሪፍ ውስጥ ለሚገኙት ብዙ የዓሣ ዝርያዎች ምቹ የመራቢያ ሥፍራ ሆኗል።” የተፈጥሮ ውበቱን ጠብቆ ከሚገኘው የማንግሩቭ ደን ጋር በተያያዘ የሚጠቀሰው ሌላው የቱሪስት መስህብ ደግሞ ብርሃን ፈንጣቂ የባሕር ወሽመጥ ነው፤ በዓለም ላይ ካሉት ብርሃን ፈንጣቂ የባሕር ወሽመጦች መካከል አብዛኞቹ የሚገኙት በፖርቶ ሪኮ ነው።—ከታች ያለውን ሣጥን ተመልከት።

ከባሕሩ ዳርቻ ትንሽ ራቅ ብለው በሚገኙት ኮራል ሪፎች ውስጥ ብዙ ዓሣ የማጥመድ ሥራ እንዳይካሄድ የተከለከለ ሲሆን በርካታ ትንንሽ ደሴቶችና በውኃ ውስጥ የሚገኙ ሪፎች ለብሔራዊ ፓርክነት ተከልለዋል። በባሕር ውስጥ የሚገኙት እነዚህ የአትክልት ሥፍራዎች ጠልቀው ለሚዋኙ ሰዎች የባሕር ዔሊዎችን፣ ማናቴ የሚባሉ ቅጠል በል አጥቢ እንስሳትንና የተለያየ ዓይነት መልክ ያላቸው የዓሣ ዝርያዎችን በቀጥታ ለማየት የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ይፈጥሩላቸዋል።

ፖርቶ ሪኮ ምንም እንኳ የኮሎምበስን ቀልብ መሳብ ባትችልም እንዲሁም ሀብት ፍለጋ ወደ እሷ የመጡትን ስፔናውያን ወራሪዎች ለሐዘን ብትዳርግም በዛሬው ጊዜ ላሉ ጎብኚዎች የደስታ ምንጭ ትሆናቸዋለች። ለእነዚህ ጎብኚዎች ፖርቶ ሪኮ በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች ደሴት ናት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በካርታ አዘጋጆች መካከል የሐሳብ አለመግባባት በመፈጠሩ የደሴቲቱ ስም ከከተማው ስም ጋር ተምታታ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሳን ህዋን ከተባለው ዋና ከተማ ይልቅ መላዋ ደሴት ፖርቶ ሪኮ በመባል ትጠራ ጀመር።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ልዩ የሆነ የምርምር ጣቢያ

ሊጎበኝ የሚገባው አንዱ ቦታ ከሳን ህዋን በስተ ምዕራብ 80 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ የሚገኘው አረሲቦ የምርምር ጣቢያ ነው። በዚህ የምርምር ጣቢያ የዓለም ትልቁ የሬዲዮ ቴሌስኮፕ የሚገኝ ሲሆን ይህ ቴሌስኮፕ ዳያሜትሩ 305 ሜትር የሆነ ዲሽ አለው። ቴሌስኮፑ ትልቅ መሆኑ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች በሌሎች ቴሌስኮፖች ሊታዩ የማይችሉ ነገሮችን እንዲያዩ ያስችላቸዋል።

[ምንጭ]

Courtesy Arecibo Observatory/ David Parker/Science Photo Library

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“በከዋክብት ውስጥ መታጠብ”

ከፖርቶ ሪኮ የባሕር ዳርቻ ትንሽ ራቅ ብላ በምትገኘው በቫይኩዌስ ደሴት ላይ ባዮሉሚኒሰንት ቤይ የተባለ ብርሃን የሚፈነጥቅ አነስተኛ የባሕር ወሽመጥ አለ። ይህ የባሕር ወሽመጥ ይህን ስም ያገኘው በውኃ ውስጥ የሚኖሩ በፎስፈረስ የበለጸጉ ብርሃን ፈንጣቂ ሕዋሳት ከየትኛውም ሥፍራ በተለየ መልኩ በከፍተኛ መጠን ስለሚገኙበት ነው። ዳይኖፍላጄሌትስ ተብለው የሚጠሩት ጥቃቅን ፍጥረታት ባዕድ ነገር ሲገባባቸው ወደ አረንጓዴ የሚያደላ ሰማያዊ ብርሃን ይፈነጥቃሉ። ይህ ባሕሪያቸው በጣም እንግዳ የሆነ የተፈጥሮ ክስተት ይፈጥራል።

ምሽት ላይ ወደ እነዚህ አካባቢዎች የመጡ ጎብኚዎች ይህን ክስተት ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋሉት አንድ ዓሣ ጀልባቸውን ፈርቶ በሸሸበት ወቅት ነበር። ዓሣው ያለፈባቸው በጨለማ የተዋጡ ቦታዎች እንደ አረንጓዴ ተወርዋሪ ኮኮቦች ብርሃን ይፈነጥቁ ጀመር። ሰዎች በዚህ ውኃ ውስጥ በሚዋኙበት ጊዜ በጨለማ ውስጥ የሚያደርጉት እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በግልጽ ይታያል። እጃቸውን ከውኃው ሲያወጡ ከእጆቻቸው ላይ የሚፈናጠሩት የውኃ ነጠብጣቦች ብልጭ ድርግም የሚሉ ከዋክብት መስለው ይታያሉ። አንድ ጎብኚ ሁኔታውን አስመልክቶ ሲናገር “በከዋክብት ውስጥ መታጠብ ይመስላል!” ብሏል።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤል ሞሮ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አሮጌው ከተማ ከሳን ክሪስቶባል ላይ ሆኖ ሲታይ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አሮጌው ሳን ህዋን

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤል ዩንኬ ደን ውስጥ የሚገኝ የፈርን ዛፍ

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጉዋኒካ የባሕር ዳርቻ

[ምንጭ]

© Heeb Christian/age fotostock

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፖርቶ ሪኮ በቀቀኖች

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኮራል ሪፍ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Passport Stock/age fotostock

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ሁሉም ፎቶዎች፦ Passport Stock/age fotostock

[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

በቀቀኖች፦ U.S. Geological Survey/Photo by James W. Wiley; ሪፍ፦ © Stuart Westmorland 2005; ዋናተኛ፦ Steve Simonsen