በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለአምልኮ ይረዳሉ ስለሚባሉ ነገሮች አምላክ ምን አመለካከት አለው?

ለአምልኮ ይረዳሉ ስለሚባሉ ነገሮች አምላክ ምን አመለካከት አለው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ለአምልኮ ይረዳሉ ስለሚባሉ ነገሮች አምላክ ምን አመለካከት አለው?

በቡዲዝም፣ በሂንዱይዝም፣ በእስልምና፣ በአይሁድ እምነት፣ በሮማ ካቶሊክ ሃይማኖትና በምሥራቃዊው ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ውስጥ ለጸሎት ይረዳሉ በሚባሉ ነገሮች መጠቀም የተለመደ ነው። በመሆኑም በሁሉም አገሮች ያሉ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ማለት ይቻላል፣ እንዲህ ዓይነቶቹ ቁሳቁሶች ወደ አምላክ ለመቅረብ እንዲሁም የእሱን ሞገስና በረከት ለማግኘት እንደሚረዷቸው ያምናሉ። ይህን ጉዳይ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል?

ለጸሎት ይረዳሉ በሚባሉ ነገሮች መጠቀም ብዙ ሺህ ዓመታት ያስቆጠረ ልማድ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የጥንቷ ነነዌ በነበረችበት ሥፍራ ላይ አርኪኦሎጂስቶች “ክንፍ ያላቸው ሁለት ሴቶች በአንድ ቅዱስ ዛፍ ፊት ጎንበስ ብለው ሲጸልዩ” የሚያሳይ ምስል ከመሬት ውስጥ ቆፍረው አውጥተዋል፤ “እነዚህ ሴቶች . . . በግራ እጃቸው የአበባ ጉንጉን ወይም መቁጠሪያ ይዘዋል።”—ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ

የመቁጠሪያዎች አገልግሎት ምንድን ነው? ይኸው ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “ማንኛውም ጸሎት ብዙ ጊዜ መደጋገም በሚኖርበት ጊዜ አንድ ሰው ጸሎቱን በጣት ከመቁጠር ይልቅ በቀላሉ ለመቁጠር የሚረዳ ነገር መጠቀም ይመርጣል።”

አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ጸሎትን ይበልጥ ቀላል በሆነ መንገድ ለመደጋገም በእንዝርት ላይ የሚሽከረከር የቱቦ ዓይነት ቅርጽ ያለው ዕቃ ይጠቀማሉ። ዕቃው በእጅ፣ በንፋስ፣ በውኃ፣ ወይም በኤሌክትሪክ አማካኝነት አንድ ጊዜ በዞረ ቁጥር ጸሎት አቅራቢው አንድ ጸሎት እንዳቀረበ አድርጎ ይቆጥረዋል። ግለሰቡ እነዚህን ዕቃዎች በሚጠቀምበት ጊዜ በአብዛኛው ማንትራ ተብለው የሚጠሩ ሚስጥራዊ ጥቅሶችን ይደግማል። አምላክ እንዲህ ስላሉት ነገሮች ምን አመለካከት እንዳለው እንመልከት።

“አትድገሙ”

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎችም እንኳን ሳይቀሩ የአምላክ ነቢይ አድርገው የሚመለከቱት ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ፈጣሪ ስለሚደገሙ ጸሎቶች ያለውን አመለካከት ሲገልጽ “አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ” ብሏል። *ማቴዎስ 6:7 የ1954 ትርጉም

በመሆኑም አምላክ አንድን ጸሎት ‘እየደገምን’ እንድንጸልይ የማይፈልግ ከሆነ ተደጋጋሚ ጸሎቶች ለማቅረብ ይረዳሉ የሚባሉ ቁሳቁሶች በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ሊኖራቸው ይችላል? ታማኝ የእውነተኛው አምላክ አገልጋይ የሆነ ሰው አምላክን ለማምለክ መቁጠሪያዎችን ወይም ሌሎች ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ ቁሳቁሶችን እንደተጠቀመ የሚጠቁም አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የለም። የጸሎትን ምንነትና ዓላማ ስንረዳ ይህ የሆነበት ምክንያት ይበልጥ ግልጽ ይሆንልናል።

አምላክን የሚያስደስት ጸሎት

ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ላይ አምላክን “አባታችን” በማለት ለይቶ ጠቅሶታል። አዎ፣ ፈጣሪያችን የተወሰኑ ቃላትን እየደጋገሙ በመጸለይ፣ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችን በመፈጸም ወይም ሚስጥራዊ ጥቅሶችን በመደጋገም ሊለማመኑት የሚገባ፣ የማይቀረብ ሚስጥራዊ ኃይል አይደለም። ከዚህ ይልቅ እሱ አፍቃሪ አባት ሲሆን እኛም ይህን ተገንዝበን እንድንወደው ይፈልጋል። ኢየሱስ ‘አብን እንደሚወደው’ ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:31) በጥንቷ እስራኤል የነበረ አንድ ነቢይ “እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አባታችን ነህ” ብሏል።—ኢሳይያስ 64:8

ይሖዋን በሰማይ እንዳለ አባታችን አድርገን በመቁጠር ወደ እሱ ልንቀርብ የምንችለው እንዴት ነው? (ያዕቆብ 4:8) ማንኛውንም ዝምድና ስንመሠርት እንደምደርገው ሁሉ ወደ አምላክ ለመቅረብም የእኛን ሐሳብና ስሜት ለእሱ መግለጽ እንዲሁም እሱ የሚለንን መስማት ይኖርብናል። አምላክ “የሚያናግረን” ሥራውን፣ ባሕርይውንና ዓላማውን ለእኛ በገለጠበት በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ ይኸውም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) እኛ ደግሞ በምላሹ በጸሎት አማካኝነት አምላክን እናናግረዋለን። እንዲህ ዓይነቱ ጸሎት ደግሞ ከልብ፣ የውስጥ ስሜትን አውጥቶ መናገርን የሚጠይቅ እንጂ የተወሰነ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓትን የተከተለና በዘልማድ የሚቀርብ መሆን የለበትም።

እስቲ አስበው፦ ሞቅ ያለ ፍቅር በሰፈነበት ቤተሰብ ውስጥ ጤናማ የሆኑና ጥሩ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር የሚነጋገሩት እንዴት ነው? እንደዚህ ባለው ቤተሰብ ውስጥ ልጆቹ ከወላጆቻቸው ጋር የሚነጋገሩት አንድ ዓይነት ቃላትን ወይም ሐረጎችን እየደገሙ፣ ምናልባትም ደግሞ ምን ያህል እንደደገሙ ለመቁጠር በሚረዱ መሣሪያዎች እየተጠቀሙ ነው? እንዲህ እንደማያደርጉ የተረጋገጠ ነው! ከዚህ ይልቅ ትርጉም ባለው መንገድና በአክብሮት የልባቸውን አውጥተው ይናገራሉ።

ለአምላክ የሚቀርብ ጸሎትም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል መሆን ይኖርበታል። በእርግጥም የሚያሳስበንን ማንኛውንም ነገር ለአምላክ መንገር እንችላለን። ፊልጵስዩስ 4:6, 7 እንዲህ ይላል፦ “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ። . . . የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን . . . ይጠብቃል።” አብዛኛውን ጊዜ የሆነ ነገር ሲያስጨንቀን ስለዚያ ጉዳይ በተደጋጋሚ እንጸልያለን። ይህ ግን ቃላትን አንድ በአንድ እየደገሙ ከመጸለይ ጋር አንድ አይደለም።—ማቴዎስ 7:7-11

መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር መጽሐፍ ላይ የሚገኙትን እንዲሁም ኢየሱስ ራሱ ያቀረባቸውን ጸሎቶች ጨምሮ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ አምላክን የሚያስደስቱ ብዙ ጸሎቶች ይዟል። * (መዝሙር 17 እና 86 በመዝሙሮቹ አናት ላይ ያሉ መግለጫዎች፤ ሉቃስ 10:21, 22፤ 22:40-44) ኢየሱስ ካቀረባቸው ጸሎቶች አንዱ በዮሐንስ ምዕራፍ 17 ላይ ይገኛል። ጥቂት ደቂቃዎች ወስደህ ይህን ጸሎት አንብበው። በምታነብበት ጊዜም ኢየሱስ የልቡን ስሜት አውጥቶ እንዴት ለአምላክ እንደጸለየ ልብ በል። በተጨማሪም ኢየሱስ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ለተከታዮቹ ያለውን ጥልቅ ፍቅር በሚያሳይ ሁኔታ እንዴት እንደጸለየ ተመልከት። ‘ቅዱስ አባት ሆይ፣ ከክፉው [ከሰይጣን] ጠብቃቸው’ በማለት ጸልዮአል።—ዮሐንስ 17:11, 15

ኢየሱስ ያቀረበውን ጸሎት ስትመረምር ምንም ዓይነት ስሜት ያልተንጸባረቀበት እንዲሁ በዘልማድ የቀረበ ጸሎት ነው የሚያሰኝ አንድ ፍንጭ እንኳ ታገኛለህ? በጭራሽ አታገኝም! ኢየሱስ ለእኛ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል! አዎ፣ ወደ እውነተኛው አምላክ መቅረብ የሚፈልጉ ሁሉ እሱን እንደ አንድ እውን አካል አድርገው በመመልከት በትክክል ማወቅ ይኖርባቸዋል። ከዚያም በዚህ እውቀት ላይ ተመርኩዘው ለአምላክ የሚያሳዩት ፍቅር እሱን ከማያስደስቱ ልማዶችና ተግባሮች እንዲርቁ ሊገፋፋቸው ይገባል። እንደዚህ ላሉት ሰዎች ይሖዋ “እኔ አባት እሆናችኋለሁ፤ እናንተም ወንዶችና ሴቶች ልጆቼ ትሆናላችሁ” ይላቸዋል።—2 ቆሮንቶስ 6:17, 18

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 ኢየሱስ አቡነ ዘበሰማያት ወይም የጌታ ጸሎት ተብሎ የሚጠራውን የናሙና ጸሎቱን ሲያስተምር “ይህን ጸሎት መጸለይ አለባችሁ” አላለም። ከዚህ ይልቅ “እናንተስ እንዲህ ጸልዩ” ብሏል። (ማቴዎስ 6:9-13 የ1954 ትርጉም) ኢየሱስ ሊያስተምር የፈለገው ቁም ነገር ምን ነበር? ያስተማረው የናሙና ጸሎት እንደሚያሳየው ከቁሳዊ ፍላጎቶቻችን ይበልጥ ቅድሚያ መስጠት ያለብን ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ነው።

^ አን.15 ምንም እንኳን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት መዝሙራት በተለያዩ ወቅቶች ይዘመሩ የነበረ ቢሆንም እንደ ማንትራ የሚደገሙ አልነበሩም፤ እንዲሁም መቁጠሪያዎችን ወይም ጸሎትን ለመድገም የሚረዱ ሌሎች ዕቃዎችን መጠቀም በሚጠይቁ ልማዳዊ የሆኑ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ የሚዘመሩ አልነበሩም።

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ ኢየሱስ የተወሰኑ ቃላትን እየደጋገሙ መጸለይ ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ የሰጠው ምክር በመቁጠሪያዎችና ጸሎትን ለመድገም በሚረዱ ሌሎች ዕቃዎች መጠቀምን በተመለከተም ይሠራል?—ማቴዎስ 6:7 የ1954 ትርጉም

▪ ጸሎታችን ለአምላክ ያለንን አመለካከት በተመለከተ ምን የሚያንጸባርቅ መሆን ይኖርበታል?—ኢሳይያስ 64:8

▪ ሃይማኖታዊ ውሸቶችን ካስወገድን አምላክ እንዴት ይመለከተናል?—2 ቆሮንቶስ 6:17, 18