ረጅም ዕድሜ የመኖር ሚስጥር በኦኪናዋ ተገኝቶ ይሆን?
ረጅም ዕድሜ የመኖር ሚስጥር በኦኪናዋ ተገኝቶ ይሆን?
ጃፓን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
▪ በጃፓን ባሉት የኦኪናዋ ደሴቶች ውስጥ በ2006 ከነበረው 1.3 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል 740 የሚያህሉት ዕድሜያቸው 100 ዓመትና ከዚያ በላይ እንደሚሆናቸው ተገምቷል፤ ከእነዚህም ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። በኦኪናዋ ዕድሜያቸው 100 ዓመትና ከዚያ በላይ በሆናቸው ሰዎች ላይ የተደረገውን ጥናት የመሩት ዶክተር ማኮቶ ሱዙኪ እንደገለጹት ከ100,000 ሕዝብ መካከል 50 የሚያህሉት ዕድሜያቸው 100 እና ከዚያ በላይ ነው። በአብዛኞቹ የበለጸጉ አገሮች ውስጥ በዚህ ዕድሜ ላይ የሚገኙ አረጋውያን ብዛት ከ100,000 ሕዝብ መካከል ከ10 እስከ 20 እንደሚሆን ይገመታል።
“ዕድሜያቸው 100 ዓመትና ከዚያም በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ ከሚደረጉት ጥናቶች መካከል ባስቆጠረው ጊዜ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት” እንደሆነ የሚነገርለት አንድ ጥናት እንዳመለከተው “ከሚጠበቀው በላይ በርካታ የሆኑ በዚህ ዕድሜ ላይ የሚገኙ አረጋውያን እጅግ ጤነኞች [ነበሩ።]” ይህ የሆነበትን ምክንያት ለመረዳት ሱዙኪና ቡድናቸው በዚህ ዕድሜ ላይ በሚገኙ ከ900 በሚበልጡ አረጋውያን እንዲሁም በ70ዎቹ ወይም ከዚያ በላይ ዕድሜ ባላቸው የኦኪናዋ ሰዎች የአኗኗር ዘይቤና የጂን አወቃቀር ላይ ምርምር አካሄዱ። ጥናት የተካሄደባቸው አረጋውያን በአመዛኙ ቀጠን ያሉና ጤነኞች እንደሆኑ፣ የደም ሥራቸው ከኮሌስትሮል የጸዳ እንደሆነ፣ የሚገርመው ደግሞ በካንሰርና በልብ በሽታ የመጠቃት አጋጣሚያቸው ዝቅተኛ እንደሆነ ተመራማሪዎቹ ደርሰውበታል። እንዲሁም በኦኪናዋ የሚኖሩት በ90ዎቹ መገባደጃ ላይ የሚገኙ አረጋውያን ለአእምሮ በሽታ የመጋለጣቸው አጋጣሚ በሌሎች የበለጸጉ አገሮች ከሚገኙት የዕድሜ እኩዮቻቸው ጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ ነው። ሚስጥሩ ምን ይሆን?
በዋነኝነት የሚጠቀሰው የጂናቸው ባሕርይ ነው። ይሁን እንጂ ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። ከእነዚህም ውስጥ ከትንባሆ መራቅ፣ በአልኮል መጠጥ አወሳሰድ ረገድ ልከኛ መሆንና ጥሩ አመጋገብ ይገኙበታል። ኦኪናዋውያን አነስተኛ የካሎሪ መጠን ያለው ምግብ የሚመገቡ ከመሆኑም በላይ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ በአሰር የበለፀጉ ምግቦችና አነስተኛ የኮሌስትሮል መጠን ያላቸው የቅባት ምግቦች ያዘወትራሉ። ከዚህም በላይ ሕዝቡ እስኪጠግብ ደረስ የመብላት ልማድ የለውም። በጥናቱ ውስጥ የተካፈሉት ዶክተር ብራድሌይ ዊልኮክስ “ትንሽ የመጥገብ ስሜት ሲሰማህ መብላትህን ማቆም አለብህ” በማለት ይናገራሉ። “ሆድህ እንደሞላ ለአእምሮህ መልእክት የሚልከው ከ20 ደቂቃ በኋላ ነው።”
ኦኪናዋውያን የሚቀመጡበት ጊዜ የላቸውም ለማለት ይቻላል፤ አትክልት ይንከባከባሉ፣ በየቀኑ በእግር ይሄዳሉ፣ ባሕላዊ ጭፈራ ይጨፍራሉ ወይም በሌሎች እንቅስቃሴዎች ይካፈላሉ። ዕድሜያቸው 100 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው አረጋውያን ባሕርያቸው ሲጠና ብሩሕ አመለካከት ያላቸውና ከሁኔታዎች ጋር በቀላሉ የሚላመዱ እንደሆኑ ተደርሶበታል። ውጥረትን በጥሩ ሁኔታ የሚቋቋሙ እንደሆኑና በተለይም ሴቶቹ “ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስር” እንዳላቸው ታይቷል።
ረዥም ዕድሜ ለመኖር የሚረዳ “ተአምራዊ መድኃኒት የለም” በማለት ዊልኮክስ ይናገራሉ። ረዥም ዕድሜ መኖር በዘር ውርስ፣ በጥሩ አመጋገብ፣ በአካላዊ እንቅስቃሴ፣ በጥሩ ልማዶች፣ “እንዲሁም ውጥረትን በተሳካ መንገድ በመቋቋም ችሎታ” ላይ የተመካ እንደሆነ ጥናቱ አመልክቷል።