በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስኬት አልጨበጥ ሲል

ስኬት አልጨበጥ ሲል

ስኬት አልጨበጥ ሲል

የተዋጣላት ዘፋኝና በጣም ሀብታም የሆነችው ገና በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ነበር። በዚህ ዕድሜያቸው በጣም ዝነኛና ሀብታም የሚሆኑ ሰዎች ከስንት አንድ ናቸው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ሕይወቷ መመሰቃቀል ጀመረ። ትዳሯ ሁለት ጊዜ ከፈረሰባት በኋላ የመጠጥና የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኞች በሚረዱባቸው ተቋማት ውስጥ መግባት ግድ ሆነባት። መላ ሕይወቷ እንዳልነበረ መሆን ጀመረ።

የሚያሳዝነው፣ እንዲህ ያለው ሁኔታ የሚደርሰው በዚህች ወጣት ላይ ብቻ አይደለም፤ ዝነኛ ስለነበሩ ሰዎች የሚገልጹ አሳዛኝ ታሪኮችን መስማት በጣም የተለመደ ነው። ሌላው ቀርቶ በንግዱ ዓለም ውስጥ እንኳ ስኬታማ መስለው የሚታዩ ሰዎች ብዙ ጊዜ ሕይወታቸው የተመሰቃቀለ ነው። አንድ ጋዜጣ በኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ በጣም ስኬታማ ናቸው የሚባሉ ሰዎችን በሚመለከት እንደሚከተለው ብሎ ነበር፦ “ከፍተኛ ትርፍ ለማግኘት የሚደረገው ሩጫ ሙያውን እያበላሸ፣ ቤተሰቦችን እያፈራረሰና ለአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች የሥራ መስክ እየፈጠረላቸው ነው። . . . ለኮከብ ሠራተኞች የሚሰጠው ከፍተኛ መጠን ያለው ጉርሻ አንዳንድ የዎል ስትሪት የባንክ ሠራተኞች የማይበገሩ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ያደረጋቸው ሲሆን ሌሎቹን ደግሞ ከሥራው ጫና የተነሳ የስሜት ቀውስ ውስጥ እንዲገቡ እንዲያውም አንዳንዶቹን ዳግመኛ እንዳያንሰራሩ እያደረጋቸው ነው።”

እንዲህ ዓይነቶቹ ችግሮች የሚመጡት ደስታንና ስኬትን በተሳሳተ መንገድ ለማግኘት በሚደረጉ ጥረቶች ሳቢያ ነው? ሁላችንም ለመኖር የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ እንደሚያስፈልገን የተረጋገጠ ነው። ይሁን እንጂ በሕይወታችን ውስጥ ስኬታማ መሆናችን ሀብት በማካበት ላይ የተመካ ነው? ጥናቶች የሚያሳዩት ተቃራኒውን ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በቻይና የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው በቅርቡ የሕዝቡ አማካይ ገቢ 250 በመቶ ቢያድግም ከኑሯቸው የሚያገኙት እርካታ ቀንሷል።

እንግዲያው እውነተኛ ስኬት የሚለካው በሰብዓዊ ሥራና የአንድ ሰው ቤት፣ መኪና፣ ወይም ሰዓት በተገዛበት ዋጋ ሳይሆን ከዚህ የበለጠ ትርጉም ባለው ሌላ ነገር ነው። ስኬት መለካት ያለበት አንድ ሰው የሚመራበትን መሠረታዊ መመሪያና የሕይወቱን ዓላማ ጨምሮ በግለሰቡ ማንነት መሆን አይኖርበትም? ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ቀልጣፋና ኃይለኛ ቢሆንም ሥነ ምግባሩ የተበላሸ አልፎ ተርፎም ፍቅርም ሆነ እውነተኛ ጓደኛ የሌለው ሊሆን ይችላል። ሌላው ሰው ደግሞ ዝናና ሀብት ይኖረው ይሆናል፤ ሆኖም ስለ ሕይወቱ ቆም ብሎ ሲያስብ ‘ይኼ ሁሉ ሩጫ ለዚሁ ነው? የሕይወቴ ትርጉም ምንድን ነው?’ የሚሉት ጥያቄዎች ይፈጠሩበት ይሆናል።

ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው እውነተኛ ስኬት ያገኙ ሰዎች አስተማማኝ በሆኑ መመሪያዎች የሚመሩ ከመሆኑም በላይ ሕይወታቸው የሚያተኩረው ይበልጥ ትርጉም ባላቸው ነገሮች ላይ ነው። በዚህም ምክንያት እነዚህ ሰዎች ውስጣዊ ሰላም ይኖራቸዋል፤ እንዲሁም ለራሳቸው ጥሩ ግምት የሚያዳብሩ ከመሆኑም ሌላ የሌሎችን አክብሮት ያተርፋሉ። በተጨማሪም በግል ስለሚያገኙት ጥቅም ስለማይጨነቁ እርካታ የተሞላበት ዓላማ ያለው ሕይወት ይመራሉ። አንዳንዶች ‘ታዲያ እነዚህ ሰዎች የሚመሩባቸው መመሪያዎች የትኞቹ ናቸው? የሕይወታቸውስ ዓላማ ምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ የምናገኘው ከራሳችን ነው? ወይስ ሌላ ምንጭ አለ? የሚቀጥሉት ርዕሶች እነዚህን ጉዳዮች የሚዳስሱ ይሆናሉ።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሰዎች ለስኬት ያላቸው የተዛባ አመለካከት

የሕክምና ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ በውድድሮች ላይ አሸናፊ ለመሆን ሲሉ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ጉልበት ሰጪ መድኃኒቶችን የሚወስዱ ወጣት ስፖርተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። ኤጁኬሽን አፕዴት የተሰኘው ድረ ገጽ እንደሚከተለው በማለት ዘግቧል፦ “በቅርቡ በተደረገ አንድ ጥናት ላይ ለኮሌጅ ተማሪዎች ‘ስቴሮይድ የሚባለውን ብርታት ሰጪ መድኃኒት በመውሰድ እንደምታሸንፍ ወይም በቡድኑ ውስጥ እንደምትታቀፍ፣ ሆኖም በአምስት ዓመት ውስጥ እንደምትታመም ብታውቅ መድኃኒቱን ትወስደው ነበር?’ የሚል ጥያቄ ሲቀርብላቸው ሁሉም ለማለት ይቻላል አዎን የሚል መልስ ሰጥተዋል። ‘መድኃኒቱን በመውሰድህ ምክንያት በአምስት ዓመት ውስጥ ልትሞት እንደምትችል ብታውቅስ?’ የሚል ጥያቄ ሲቀርብላቸውም 65 በመቶ የሚሆኑት አዎን ብለው መልሰዋል።”