በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በመርፌ ቀዳዳ ማለፍ’

‘በመርፌ ቀዳዳ ማለፍ’

‘በመርፌ ቀዳዳ ማለፍ’

አውስትራሊያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ብሪታንያ አሳሾች በ1798 ባስ ስትሬት የተባለውን የባሕር ወሽመጥ ባገኙ ጊዜ የባሕር ኃይል ባለሥልጣናት በጣም ተደስተው ነበር። ታዝሜንያ የተባለችውን ደሴት ከአውስትራሊያ ዋና መሬት የሚለየው ይህ የውቅያኖስ መተላለፊያ ከእንግሊዝ ወደ ሲድኒ የሚደረገውን ጉዞ በ1,100 ኪሎ ሜትር ያህል አሳጥሮታል።

ይሁንና ባስ ስትሬት በዓለም ላይ ለባሕር ጉዞ በጣም አደገኛ ከሆኑት ቦታዎች አንዱ ነበር። ከምዕራብ በኩል የሚመጣው አውሎ ነፋስ፣ በአካባቢው ያለው ኃይለኛ የውኃ ፍሰትና በአማካይ ከ50-70 ሜትር የማይበልጠው የባሕሩ ጥልቀት አንድ ላይ ተዳምረው ኃይለኛ ሞገድ እንዲፈጠር ስለሚያደርጉ በዚህ ቦታ በመርከብ መጓዝ አስቸጋሪ ነው። በተጨማሪም በባሕር ወሽመጡ መሃል ላይ በምትገኘው በኪንግ አይላንድ ያሉት ያገጠጡ አለቶች ከምዕራብ አቅጣጫ ወደዚህ ቦታ ለሚመጡ መርከቦች አደገኛ ናቸው።

በአሁኑ ጊዜ በባስ ስትሬት መጓዝ ያን ያህል አስቸጋሪ አይደለም። በተወጠሩ ሸራዎች አማካኝነት የሚጓዙ መርከቦችና ኋላቀር የሆኑ የባሕር ላይ ጉዞ መሣሪያዎች በነበሩበት ዘመን ግን ሁኔታው እንዲህ ቀላል አልነበረም። ከምዕራብ አቅጣጫ ወደዚህ የባሕር ወሽመጥ የሚደረገው ጉዞ በጣም የሚያስጨንቅና የሚያስፈራ ከመሆኑ የተነሳ ‘በመርፌ ቀዳዳ እንደ ማለፍ’ ተደርጎ መቆጠሩ ተገቢ ነው።

አቢይ ክበቡን ተከትሎ መጓዝ

በ19ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ መርከቦች ከእንግሊዝ ተነስተው 19,000 ኪሎ ሜትር ያህል በመጓዝ ምሥራቅ አውስትራሊያ ለመድረስ አምስት ወር የሚወስድባቸው ሲሆን ጉዞው አስደሳች አልነበረም። ብዙውን ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች በመርከቡ ታችኛው ክፍል በጣም አስከፊ በሆነ ሁኔታ አንድ ላይ ታጭቀው ይጓዙ ነበር፤ ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ ስደተኞችና የተፈረደባቸው ወንጀለኞች ነበሩ። ብዙ ሰዎች በመርከቡ ንቅናቄ ሳቢያ የሚታመሙ ከመሆኑም ሌላ ለተመጣጠነ ምግብ እጥረትና ለተለያዩ በሽታዎች ይጋለጡ ነበር፤ በተጨማሪም እንደ አይጥ የመሳሰሉ በሽታ አስተላላፊ ትናንሽ እንስሳትን ማየት የተለመደ ነበር። ከዚህም በላይ በርካታ ሰዎች በጉዞው ወቅት ይሞቱ ነበር። * ያም ሆኖ የተሻለ ኑሮ አገኛለሁ የሚለው ተስፋ ብዙዎቹ መንገደኞች ጥንካሬና ብርታት እንዲያገኙ ረድቷቸዋል።

በ1852 ካፒቴን ጄምስ ፎርብዝ አቋራጭ መንገድ ባገኘ ጊዜ ጉዞው እየቀለለ መጣ። ፎርብዝ አጭር ተደርጎ ይታሰብ የነበረውንና በደቡባዊ የሕንድ ውቅያኖስ በኩል ወደ አውስትራሊያ የሚወስደውን 39ኛውን የኬክሮስ የሐሳብ መስመር ትቶ አቢይ ክበቡን ማለትም ይበልጥ ቀጥተኛ የሆነውን መንገድ ተከትሎ ተጓዘ፤ ይህ መንገድ ከእንግሊዝ ተነስቶ በስተደቡብ ወደ አንታርክቲካ አቅጣጫ ይወርድና ወደ ደቡብ ምሥራቅ አውስትራሊያ ያቀናል። * ማርኮ ፖሎ የተባለችው የፎርብዝ መርከብ ትልልቅ የበረዶ አለቶችና ኃይለኛ የባሕር ሞገዶች ቢያጋጥሟትም 701 ስደተኞችን አሳፍራ በ68 ቀናት ውስጥ በቪክቶሪያ ግዛት ወደሚገኘው የሜልቦርን ወደብ ደረሰች፤ ይህም ለጉዞ ይወስድ የነበረውን ጊዜ በግማሽ ያህል ቀንሶታል። ብዙ ሰዎች ወርቅ ፍለጋ ወደ ቪክቶሪያ ይሄዱ ስለነበር ካፒቴን ፎርብዝ ይህን አዲስ መንገድ ያገኘው ጥሩ ጊዜ ላይ ነው። ይበልጥ አጭር የሆነ መንገድ እንደተገኘ የሚገልጸው ዜና ወርቅ የማውጣት ፍላጎት ያደረባቸው ብዙ ሰዎች ወደ አውስትራሊያ ለመሄድ እንዲነሳሱ አደረጋቸው።

መርከቦች ከእንግሊዝ ከተነሱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያርፉባትን ኬፕ ኦትዌይ ወደብ የሚያገኙት 16,000 ኪሎ ሜትር ከተጓዙ በኋላ ነው። ባሕረተኞች የኬክሮስን መስመር ለማስላት አንግሎችን የሚለካ መሣሪያና የመረጃ ሰንጠረዦችን፣ ኬንትሮስን ለማስላት ደግሞ በግሪኒች ሰዓት አቆጣጠር የተስተካከለ የመርከብ ሰዓት ይጠቀሙ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የፀሐይዋን አቅጣጫ በመመልከት ያሉበትን አካባቢ ሰዓት ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ። በአካባቢው ሰዓትና በግሪኒች ሰዓት መካከል ያለው እያንዳንዱ የአንድ ሰዓት ልዩነት 15 ዲግሪ የኬንትሮስ አንግልን ይወክላል። አንድ የተዋጣለት መርከበኛ የኬክሮስንና የኬንትሮስን መስመሮች በሚገባ ማስላቱ ያለበትን ቦታ በትክክል ማወቅ እንዲችል ይረዳዋል።

ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ስህተት ሊፈጠር ይችላል። ፀሐይ ለብዙ ቀናት በደመና ትሸፈን ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ የቀድሞዎቹ የመርከብ ሰዓቶች ሁልጊዜ ትክክለኛ መረጃ ላይሰጡ ይችላሉ። በየቀኑ አንድ ሴኮንድ ወደፊት ቢሄድ ወይም ወደኋላ ቢቀር መርከቧ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ መንገዷን ስታ 50 ኪሎ ሜትር ያህል ልትርቅ ትችላለች። በዝናብ፣ በጭጋግ ወይም በጨለማ ምክንያት መንገዳቸውን ስተው የሚሄዱ መርከቦች ወደ ባስ ስትሬት የባሕር ወሽመጥ ከሚወስደው አቅጣጫ ሊርቁና በኪንግ አይላንድ ወይም በቪክቶሪያ የባሕር ዳርቻዎች ካሉ አለቶች ጋር ሊላተሙ ይችላሉ። በርካታ ተጓዦች፣ በአንድ ወቅት ኬፕ ኦትዌይን ከሩቅ ሲመለከት “አምላክ የተመሰገነ ይሁን! መንገዳችንን አልሳትንም” ብሎ የተናገረው ካፒቴን ተሰምቶት የነበረውን ስሜት ተጋርተው ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም። በ19ኛው መቶ ዘመን የነበሩ አብዛኞቹ ባሕረተኞች አደጋ ሳይደርስባቸው ‘በመርፌ ቀዳዳ ማለፍ’ መቻላቸው ለነበራቸው ድንቅ ችሎታ ግሩም ምሥክር ነው። አንዳንዶቹ ግን ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

የመርከብ መካነ መቃብር

ሰኔ 1, 1878 ጎህ ከመቅደዱ በፊት ሎኽ አርድ የተባለችው ፈጣን መርከብ ጥቅጥቅ ባለ ጉም ውስጥ ወደ ቪክቶሪያ የባሕር ዳርቻ አቅጣጫ እየተጓዘች ነበር። ጉሙ ቀደም ሲል ከነበረው ቀን አንስቶ ሳይገፈፍ መቆየቱ ካፒቴኑ የፀሐይዋን አቅጣጫ በመመልከት ያለበትን ቦታ ማወቅ እንዳይችል እንቅፋት ፈጥሮበት ነበር። በዚህም ምክንያት ከጠበቀው በላይ ወደ አውስትራሊያ የባሕር ዳርቻ ተጠግቶ ነበር። በድንገት ጉሙ ሲገፈፍ 90 ሜትር ከፍታ ካላቸው ትልልቅ ቋጥኞች ጋር ለመላተም የቀራቸው 2 ኪሎ ሜትር ያህል ብቻ ነበር። ሠራተኞቹ የመርከቧን አቅጣጫ ለመቀየር ያለ የሌለ ኃይላቸውን ቢጠቀሙም ነፋሱና ማዕበሉ ድካማቸውን መና አስቀረው። አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መርከቧ ከቋጥኙ ጋር የተላተመች ሲሆን ከ15 ደቂቃ በኋላ ሰጠመች።

መርከቧ ውስጥ ከነበሩት 54 ሰዎች መካከል የተረፉት ሁለት ብቻ ሲሆኑ እነሱም በመርከበኝነት ሥልጠና ላይ የነበረው ቶም ፒርስ እና ኢቫ ካርማይክል የተባለች መንገደኛ ነበሩ፤ ሁለቱም ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ነበር። ቶም በዚያ የክረምት ወቅት በጣም ቀዝቃዛ በሆነው ውኃ ላይ ተገልብጣ የነበረችን አንዲት ሕይወት አድን ጀልባ ሙጭጭ አድርጎ ይዞ በርከት ላሉ ሰዓታት ቆየ። በመጨረሻ ማዕበሉ በቋጥኞቹ መሃል ወዳለ ጠባብ ሸለቆ እየገፋ ወሰደው። ከዚያም የመርከቧ ስብርባሪ የተበታተነበት አንድ አነስተኛ የባሕር ዳርቻ ተመለከተና እየዋኘ ወደዚያ ወጣ። ኢቫ መዋኘት ስለማትችል አንድ የመርከብ ስብርባሪ ላይ ተንጠልጥላ ለአራት ሰዓታት ያህል ከቆየች በኋላ ማዕበሉ እሷንም በቋጥኞቹ መሃል ወዳለው ሸለቆ እየገፋ ወሰዳት። ቶምን በባሕሩ ዳርቻ ስታየው የእርዳታ ጥሪ አሰማች። ቶም ዘሎ ውኃ ውስጥ በመግባት ለአንድ ሰዓት ያህል ሲታገል ከቆየ በኋላ በተወሰነ መጠን ራሷን የሳተችውን ኢቫን እየጎተተ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ይዟት ወጣ። ኢቫ እንዲህ በማለት ሁኔታውን ገልጻለች፦ “ከባሕሩ ዳርቻ ከሃምሳ ሜትር በላይ ርቆ ወደሚገኝ አንድ አስፈሪ ዋሻ የወሰደኝ ሲሆን ብራንዲ የያዘ ሣጥን አገኘና አንዱን ጠርሙስ ሰብሮ አስጎነጨኝ፤ ይህ ደግሞ በደንብ እንድነቃ አደረገኝ። ረጃጅም ሣርና ቁጥቋጦ ሰብስቦ በማምጣት እዚያ ላይ አስተኛኝ። ወዲያውኑ በድጋሚ ራሴን የሳትኩ ሲሆን በዚህ ሁኔታ ለብዙ ሰዓታት የቆየሁ ይመስለኛል።” በዚህ መካከል ቶም ተራራው ላይ ወጥቶ የጥሪ ድምፅ አሰማ። ሎኽ አርድ በሰጠመች 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ቶምና ኢቫ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የአንድ ገበሬ ቤት ተወሰዱ። ኢቫ ወላጆቿን እንዲሁም ሦስት ወንድሞቿንና ሁለት እህቶቿን በአደጋው ሳቢያ አጥታለች።

በዛሬው ጊዜ፣ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አነስተኛም ሆኑ ትልልቅ መርከቦች በባስ ስትሬት የባሕር ወሽመጥ አለምንም ችግር ይጓዛሉ። በዚህ ቦታ በሚጓዙበት ጊዜ አደጋ የደረሰባቸውን ከመቶ በላይ የሚሆኑ መርከቦች አልፈው ይሄዳሉ። በቪክቶሪያ፣ በፖርት ካምብል ብሔራዊ ፓርክ የሚገኘውን የሎኽ አርድ ሸለቆ የመሰሉ የመርከብ አደጋ የደረሰባቸው አንዳንድ ቦታዎች በቱሪስቶች ይጎበኛሉ። እነዚህ ቦታዎች፣ የተሻለ ሕይወት ለማግኘት ሲሉ ዓለምን በግማሽ ያህል ከዞሩ በኋላ የጉዟቸው የመጨረሻ ክፍል የሆነውን “የመርፌ ቀዳዳ” ያለፉትን በ19ኛው መቶ ዘመን የነበሩ ደፋር ሰዎች እንድናስታውስ ያደርጉናል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 በ1852 ከእንግሊዝ ወደ አውስትራሊያ በተደረገ ጉዞ አንድ ዓመት ወይም ከዚያ ያነሰ ዕድሜ ካላቸው አምስት ሕፃናት መካከል አንዱ በሞት ተቀጭቷል።

^ አን.8 በአንድ ሉል ላይ ያሉ ሁለት ቦታዎች በተወጠረ ክር ሲገናኙ ክሩ የሚያርፈው አቢይ ክበብ በሚባለው በጣም አጭር በሆነው መስመር ላይ ነው።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ቶምና ኢቫ ምን ሆኑ?

ሎኽ አርድ የተባለችው መርከብ ካጋጠማት አደጋ የተረፉት ቶም ፒርስና ኢቫ ካርማይክል በድፍን አውስትራሊያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ታዋቂ ሆነዋል። ኬፕ ኦትዌይ—ኮስት ኦቭ ሴክሬትስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “ጋዜጦች ስለ አደጋው በስፋት የዘገቡ ሲሆን ፒርስን ጀግና፣ ኢቫ ካርማይክልን ደግሞ ቆንጆ ብለው በመጥራት አወድሰዋቸዋል፤ በተጨማሪም ጋዜጦቹ ሁለቱ መጋባት አለባቸው ብለው የወሰኑ ይመስል ነበር።” ቶም እንድታገባው ጥያቄ ያቀረበላት ቢሆንም ኢቫ ጥያቄውን ሳትቀበል ቀርታለች፤ ከሦስት ወር በኋላም ወደ አየርላንድ የተመለሰች ከመሆኑም ሌላ አግብታ ልጆች ወልዳለች። በ1934 በ73 ዓመቷ ሕይወቷ አልፏል። ቶም ወደ መርከበኝነት ሥራው የተመለሰ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ለሁለተኛ ጊዜ የመርከብ አደጋ አጋጥሞታል። ይሁንና በዚህ ጊዜም ቢሆን ተርፏል። ለብዙ ዓመታት በእንፋሎት የሚሠሩ መርከቦች ካፒቴን ሆኖ ሲሠራ ከቆየ በኋላ በ1909 በ50 ዓመቱ ሕይወቱ አልፏል።

[ምንጭ]

ሁለቱም ፎቶዎች፦ Flagstaff Hill Maritime Village, Warrnambool

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ፎርብዝ “ማርኮ ፖሎ” (ከላይ) የተባለችውን መርከብ በመጠቀም በጣም አጭር የሆነውን መስመር ይኸውም አቢይ ክበቡን ተከትሎ ከእንግሊዝ ወደ አውስትራሊያ ተጉዟል

[ሥዕላዊ መግለጫ]

የቀድሞው መንገድ

39ኛው የኬክሮስ መስመር

አቢይ ክበቡን ተከትሎ የሚጓዘው መንገድ

የአንታርክቲካ ክበብ

[ካርታ]

አትላንቲክ ውቅያኖስ

የሕንድ ውቅያኖስ

አንታርክቲካ

[ምንጭ]

የካቲት 19, 1853 ከታተመው ዚ ኢለስትሬትድ ለንደን ኒውስ ከተባለው ጋዜጣ የተወሰደ

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት )

ከምዕራብ አቅጣጫ ወደ ባስ ስትሬት የባሕር ወሽመጥ የሚደረገው ጉዞ ‘በመርፌ ቀዳዳ ማለፍ’ ተብሎ ተገልጿል

[ካርታ]

አውስትራሊያ

ቪክቶሪያ

ሜልቦርን

ፖርት ካምብል ብሔራዊ ፓርክ

ኬፕ ኦትዌይ

ባስ ስትሬት

ኪንግ አይላንድ

ታዝሜንያ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ሎኽ አርድ” የተባለችው መርከብ ከቋጥኝ ጋር ከተጋጨች ከ15 ደቂቃ በኋላ ሰጠመች

[ምንጭ]

La Trobe Picture Collection, State Library of Victoria

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

(1) “ሎኽ አርድ” ከቋጥኙ ጋር የተላተመችበት ቦታና (2) የቶም ፒርስ ዋሻ ያለበት ቦታ የሚገኝበት ፖርት ካምብል ብሔራዊ ፓርክ

[ምንጭ]

Photography Scancolor Australia