በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስተማማኝ መመሪያ ከየት ማግኘት እንችላለን?

አስተማማኝ መመሪያ ከየት ማግኘት እንችላለን?

አስተማማኝ መመሪያ ከየት ማግኘት እንችላለን?

በዓለም አመለካከት ስኬት የሚባለውን ሳይሆን፣ በግለሰብ ደረጃ ስኬታማ መሆን የምንችልበትን ትክክለኛ መንገድ ማን ሊጠቁመን ይችላል? ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው፣ እውነተኛ ስኬት አስተማማኝ በሆኑ የሥነ ምግባር መመሪያዎች በመመራትና ቀና የሆነ የሕይወት ዓላማ በመያዝ ላይ የተመካ ነው፤ እነዚህ ደግሞ ከዝና፣ ከሀብት ወይም ከሥልጣን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም።

ታዲያ አስተማማኝ የሆኑ መመሪያዎችን እንዲሁም የሕይወትን ዓላማ በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎችን መልስ ከየት ማግኘት እንችላለን? በራሳችን መመለስ እንችላለን? ፍጽምና የሚጎድለን ሰዎች ስለሆንን በተሳሳተ ጎዳና ላይ እንድንሄድ ሊያደርጉን ለሚችሉ መጥፎ ምኞቶች የተጋለጥን መሆናችንን አምነን መቀበል አለብን። (ዘፍጥረት 8:21) በመሆኑም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ “የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት” በማለት የሚገልጻቸውን ከንቱ ነገሮች ማሳደዳቸውን ቀጥለዋል። (1 ዮሐንስ 2:16) እውነተኛ ስኬት የሚገኘው በዚህ መንገድ አይደለም፤ እንዲያውም እንዲህ ያለው አካሄድ ለተስፋ መቁረጥና ለብስጭት ይዳርጋል። በመሆኑም ብዙዎች በሕይወት ውስጥ ለሚያጋጥሙ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ከፈጣሪያችን መልስ ለማግኘት መሞከራቸው የተገባ ነው። *

ከፈጣሪያችን መመሪያ ለማግኘት መፈለጋችን ተገቢ ነው?

ከፈጣሪያችን መመሪያ ለማግኘት መፈለጋችን ምክንያታዊ ነው የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እሱ ለምን እንደፈጠረን ማለትም የሕይወታችን ዓላማ ምን እንደሆነ ያውቃል። በተጨማሪም አካላችንን፣ አእምሯችንን እና ስሜታችንን እንዴት አድርጎ እንደሠራ ያውቃል። በመሆኑም አምላክ ሰዎች ሊመሩበት የሚገባውን ከሁሉ የተሻለ መመሪያ ያውቃል። ከዚህም በላይ አምላክ ሁለንተናው ፍቅር በመሆኑ እውነተኛ ደስታና ስኬት እንድናገኝ ይፈልጋል። (1 ዮሐንስ 4:8) ታዲያ የእርሱን ፍቅራዊ አመራር ከየት ማግኘት እንችላለን? አምላክ 40 የሚያህሉ ሰብዓዊ ጸሐፊዎችን ተጠቅሞ ባስጻፈልን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። * (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ይሁንና በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ባለው መመሪያ መተማመን የምንችለው እንዴት ነው?

ከሁሉ የላቀ የአምላክ ወኪል የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ጥበብ የምትጸድቀው በሥራዋ’ ይኸውም በውጤቷ እንደሆነ ተናግሯል። (ማቴዎስ 11:19፤ ዮሐንስ 7:29) አምላካዊ ጥበብ ስኬትና ዘላቂ ደስታ ወደሚያስገኝ “መልካም መንገድ ሁሉ” የሚመራ ሲሆን የአምላክን መመሪያ ችላ የሚል ሰብዓዊ ጥበብ ግን ወደ ውድቀትና ሐዘን ይመራል።—ምሳሌ 2:8, 9፤ ኤርምያስ 8:9

ለምሳሌ ያህል፣ በ1960ዎቹ ዓመታት ወደ ዓለም መድረክ ብቅ ያለውን የሂፒዎች ዘመን ተመልከት። ብዙ ሂፒዎች የቀድሞውን ትውልድ የሥነ ምግባር መመሪያና ሥልጣን ገሸሽ በማድረግ ሰዎች አደንዛዥ ዕፅ እንዲወስዱና ለዛሬ ብቻ እንዲኖሩ ማበረታታት እንዲሁም የወሲብ ነፃነት ሊኖር ይገባል የሚል ፍልስፍና ማስፋፋት ጀመሩ። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው አኗኗር እውነተኛ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ነው? ሰዎች እውነተኛ የሕይወት ዓላማ እንዲኖራቸው እንዲሁም እውነተኛ ውስጣዊ ሰላምና ዘላቂ ደስታ በሚያስገኝ ሥነ ምግባራዊ መሥፈርት እንዲመሩ ሊያደርጋቸው ይችላል? ታሪክ እንደሚያሳየው እንዲህ ዓይነቱ አኗኗር የሰዎችን ሕይወት ከማሻሻል ይልቅ ሰብዓዊው ኅብረተሰብ በሥነ ምግባር እያሽቆለቆለ እንዲሄድ አስተዋጽኦ አድርጓል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

ከሰብዓዊ ፍልስፍናዎች በተቃራኒ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ጊዜ የሚሽረው አይደለም። (ኢሳይያስ 40:8) የሚቀጥለው ርዕስ በሁሉም አገሮች የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ደረጃቸው ምንም ይሁን ምን እውነተኛ ደስታና ስኬት እንዲያገኙ ያስቻሏቸውን ስድስት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ መመሪያዎች ያብራራል፤ ይህን ርዕስ ማንበብህ መለኮታዊው ጥበብ ጊዜ የማይሽረው የሆነበትን ምክንያት እንድትረዳ ያስችልሃል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 “በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት መጣል ትችላለህ?” በሚል ጭብጥ የተዘጋጀውን የኅዳር 2007 ንቁ! መጽሔት ልዩ እትም ተመልከት። በዚህ እትም ውስጥ የቀረቡት ርዕሶች መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መሆኑን የሚያስረዱ አርኪኦሎጂያዊ፣ ታሪካዊ፣ ሳይንሳዊና ሌሎች ማስረጃዎችን ይዘዋል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

 ስኬት ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ከንቱ የሚያደርጉ አስተሳሰቦች

ብዙ ሰዎች አምላክ እንደሌለና ሕይወት የተገኘው የማሰብ ችሎታ በማይጠይቀው ዝግመተ ለውጥ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ አመለካከት እውነት ቢሆን ኖሮ ሕይወት በኬሚካላዊና ባዮሎጂያዊ ሂደቶች ወቅት ድንገት የተገኘ ነገር ስለሚሆን የመኖራችንን ዓላማ ለመረዳት ብሎም በሁሉም ቦታ የሚሠሩ መመሪያዎችን ለማግኘት የምናደርገው ጥረት ከንቱ ይሆን ነበር።

ሌሎች ደግሞ አምላክ ከፈጠረን በኋላ ትቶናል ብለው ያምናሉ። እውነቱ ይህ ከሆነ በመንፈሳዊ የሙት ልጆች ነን ማለት ነው። ትርጉም ያለው ሕይወት የመምራት ፍላጎት ቢኖረንም እንኳ እውነተኛ ዓላማም ሆነ መሠረታዊ መመሪያ ሊኖረን አይችልም ማለት ነው። እስቲ አስበው፣ አምላክ ለእያንዳንዱ እንስሳ በተፈጥሮ ማድረግ የሚያስፈልገውን ነገር እንዲያደርግ የሚያስችል የደመ ነፍስ ጥበብ ሰጥቶታል። በመሆኑም በዙሪያችን ያሉት የፍጥረት ሥራዎች የአምላክን ጥልቅ ጥበብ ያንጸባርቃሉ። ታዲያ እንዲህ ያለ ጥበብ ያለው ፈጣሪ እኛን ከፈጠረ በኋላ በጨለማ እንድንደናበር ያለ ምንም መመሪያ ይተወናል? በጭራሽ!—ሮሜ 1:19, 20

አምላክ የለም ባዮች የሚከተሉት ፍልስፍና ሰዎች የሕይወትን ዓላማና በማንኛውም ሥፍራ የሚሠሩ መመሪያዎችን ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት ስለሚያዳክምባቸው ለስኬት የተዛባ አመለካከት እንዲኖራቸው አድርጓል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ አስተማማኝ መሆኑ ባስገኛቸው ጥሩ ውጤቶች ተረጋግጧል