የጸሎቴን ይዘት ማሻሻል የምችለው እንዴት ነው?
የወጣቶች ጥያቄ
የጸሎቴን ይዘት ማሻሻል የምችለው እንዴት ነው?
“በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ ወይም ከጓደኞችህና ከቤተሰብ ጋር በተያያዘ ውጥረት ሲበዛብህ በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ቦታ ልትሰጠው የሚገባውን አምላክህን አንዳንድ ጊዜ ትረሳለህ።” —የ15 ዓመቷ ፋቪዮላ፣ ዩናይትድ ስቴትስ
“ሳታቋርጡ ጸልዩ።” (1 ተሰሎንቄ 5:17) “በጸሎት ጽኑ።” (ሮሜ 12:12) “ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ።” (ፊልጵስዩስ 4:6) ክርስቲያን ከሆንክ እነዚህን ጥቅሶች በሚገባ ሳታውቃቸው አትቀርም። በተጨማሪም ጸሎት በጣም አስደናቂ የመገናኛ መሥመር እንደሆነ ተገንዝበህ ይሆናል። እስቲ አስበው በቀን ውስጥ በማንኛውም ሰዓት ወይም ምሽት ላይ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ማነጋገር ትችላለህ! መጽሐፍ ቅዱስ “እርሱ ይሰማናል” በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል። *—1 ዮሐንስ 5:14
ሆኖም በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ እንደተጠቀሰችው ወጣት አንተም መጸለይ አስቸጋሪ እንደሆነብህ ይሰማህ ይሆናል። ታዲያ ምን ማድረግ ትችላለህ? ይህ ርዕስ (1) ችግሩ ምን ላይ እንደሆነ ለይተህ እንድታውቅ፣ (2) ከጸሎት ጋር በተያያዘ ግብ እንድታወጣና (3) ግብህ ላይ ለመድረስ የሚያስችልህን “በር” እንድትከፍት ይረዳሃል።
በመጀመሪያ ችግሩ ምን ላይ እንደሆነ ለይተን እንወቅ። ከጸሎት ጋር በተያያዘ ለአንተ ይበልጥ ፈታኝ የሆነብህ ነገር ምንድን ነው? መልስህን ከዚህ በታች ጻፍ።
․․․․․
ቀጥሎ ልትወስደው የሚገባህ እርምጃ ግብ ማውጣት ነው። ከዚህ በታች ከቀረቡት ግቦች መካከል አንተ ልትደርስበት በምትፈልገው ላይ ምልክት አድርግ፤ ወይም “ሌላ” በሚለው ክፍት ቦታ ላይ ግብህን ጻፍ።
□ ከአሁኑ የበለጠ ብዙ ጊዜ መጸለይ እፈልጋለሁ።
□ የጸሎቴን ይዘት መቀያየር እፈልጋለሁ።
□ ይበልጥ ከልብ በመነጨ ስሜት መጸለይ እፈልጋለሁ።
□ ሌላ ․․․․․
“በሩን” መክፈት
ጸሎት በማንኛውም ጊዜ ልትከፍተው እንደምትችለው በር ነው። ይሁን እንጂ ብዙ ወጣቶች የሚገባቸውን ያህል በሩን አዘውትረው እንደማይጠቀሙበት ወይም እንደልባቸው እንደማይከፍቱት ይናገራሉ። አንተም እንደዚህ የሚሰማህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ! ምክንያቱም ችግሩን ለይተህ ከማወቅህም ሌላ ግብ አውጥተሃል። አሁን የሚያስፈልግህ የበሩን ቁልፍ ማግኘት ብቻ ነው። ከጸሎት ጋር በተያያዘ ሊያጋጥሙህ
የሚችሉ አንዳንድ ችግሮችና እነሱን ለማሸነፍ የሚረዱህ ጠቃሚ ሐሳቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል።▪ ችግሩ፦ መዘንጋት። “አንዳንድ ጊዜ በተለያዩ ሥራዎች ስዋከብ መጸለይ እዘነጋለሁ።”—የ20 ዓመቷ ፕሪቲ፣ ብሪታንያ
ቁልፉ፦ “እንግዲህ ጥበብ እንደ ሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ። ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ።”—ኤፌሶን 5:15, 16
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ በቅድሚያ በየቀኑ መጸለይ የምትችልበትን አመቺ ሰዓት ምረጥ። የያዝከውን ቀጠሮ በማስታወሻ ላይ እንደምትጽፍ ሁሉ የመረጥከውን ሰዓትም በጽሑፍ ማስፈር ትችላለህ። “ለመጸለይ የተወሰነ ሰዓት ካልመደብኩ ጊዜዬ በሙሉ በሌሎች ሥራዎች ስለሚያዝብኝ ቀኑ ሳላስበው ያልፍብኛል” በማለት በጃፓን የምትኖረው የ18 ዓመቷ ዮሺኮ ተናግራለች።
▪ ችግሩ፦ ሐሳብን መሰብሰብ አለመቻል። “ሐሳቤን መሰብሰብ ስለምቸገር በምጸልየው ነገር ላይ ማተኮር ያቅተኛል።”—የ17 ዓመቷ ፓመላ፣ ሜክሲኮ
ቁልፉ፦ “በልብ ውስጥ የሞላውን አንደበት ይናገረዋል።”—ማቴዎስ 12:34
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ሐሳብህ እየተበታተነ የምትቸገር ከሆነ በአንድ ነገር ላይ የማተኮር ችሎታህ እስኪሻሻል ድረስ አጭር ጸሎት ለማቅረብ ሞክር። ሌላው አማራጭ ደግሞ፣ አንተን በጣም ስለሚያሳስቡህ ጉዳዮች መጸለይ ነው። በሩሲያ የምትኖረው የ14 ዓመቷ መሪና “ወደ አሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ስገባ፣ ጸሎት በእርግጥም ከአምላክ ጋር መነጋገር የሚቻልበት መንገድ እንደሆነ በቁም ነገር ማሰብ ጀመርኩ። ይህ ደግሞ ልቤን ለአምላክ በጸሎት እንድከፍት አነሳሳኝ።”
▪ ችግሩ፦ ነጋ ጠባ አንድ ዓይነት ጸሎት መጸለይ። “በምጸልይበት ጊዜ አንድ ዓይነት ቃላት እደጋግማለሁ።”—የ17 ዓመቷ ዱፔ፣ ቤኒን
ቁልፉ፦ “ሥራህን ሁሉ አሰላስላለሁ፤ ድንቅ ሥራህን ሁሉ አውጠነጥናለሁ።”—መዝሙር 77:12
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ጸሎትህ በዘልማድ የሚቀርብና ተደጋጋሚ ከሆነብህ በየዕለቱ ከይሖዋ ያገኘኸውን አንድ በረከት ጻፍ። ከዚያም ለዚህ በረከት ይሖዋን አመስግነው። ለአንድ ሳምንት እንዲህ ካደረግህ ስለ ሰባት አዳዲስ ጉዳዮች ጸልየሃል ማለት ነው። በተመሳሳይ በየዕለቱ ስለምታከናውናቸው ነገሮችም መጸለይ ትችላለህ። “በምጸልይበት ጊዜ በዚያን ቀን ባከናወንኳቸው ነገሮች ላይ ለማተኮር እሞክራለሁ” በማለት በብራዚል የሚኖረው የ21 ዓመቱ ብሩኖ ተናግሯል። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው የ18 ዓመቷ ሳማንታም ተመሳሳይ ነገር እንደምታደርግ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ዛሬ ያጋጠሙኝን ከሌሎቹ ቀኖች የተለዩ ነገሮች ሁሉ ለማስታወስ እሞክርና ስለእነዚያ ነገሮች እጸልያለሁ። ይህ ደግሞ ጸሎቴ ተደጋጋሚ እንዳይሆን ይረዳኛል።” *
▪ ችግሩ፦ መጠራጠር። “በአንድ ወቅት በትምህርት ቤት ስለገጠመኝ ችግር ጸልዬ ነበር፤ ሆኖም ችግሩ አልተወገደልኝም። እንዲያውም ተጨማሪ ችግሮች ደረሱብኝ። ከዚህም የተነሳ ‘ለምን እጸልያለሁ? ይሖዋ እንደሆነ አይሰማኝም!’ ብዬ አሰብኩ።”—የ15 ዓመቷ ሚኖሪ፣ ጃፓን
ቁልፉ፦ “በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ [ይሖዋ አምላክ] መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።”—1 ቆሮንቶስ 10:13
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ ሁን፦ ይሖዋ ‘ጸሎት ሰሚ’ አምላክ ነው። (መዝሙር 65:2) ስለዚህ ስለ አንድ ነገር ከጸለይክ በኋላ ጉዳዩን በተሟላ ሁኔታ ለመረዳት ሞክር። አንተ ባሰብከው መንገድ ለጸሎትህ መልስ ለማግኘት ከመጠበቅ ይልቅ አምላክ ባላሰብከው መንገድ መልስ ሰጥቶህ ሊሆን ስለሚችል ሁኔታውን ለማስተዋል ሞክር። በክርስቲያናዊ አቋምህ መጽናትህ በራሱ፣ ይሖዋ ችግሩን በማስወገድ ሳይሆን ለመጽናት የሚያስችልህን ጥንካሬ በመስጠት ጸሎትህን እንደመለሰልህ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል።—ፊልጵስዩስ 4:13
▪ ችግሩ፦ የሃፍረት ስሜት። “ምሳዬን ለመብላት ስጸልይ የትምህርት ቤት ጓደኞቼ ቢያዩኝ ምን ይሉኛል ብዬ ስለማስብ በእነሱ ፊት መጸለይ ያሳፍረኛል።”—የ17 ዓመቱ ሂካሩ፣ ጃፓን
ቁልፉ፦ ‘መሥራት ለምንፈልገው ለማንኛውም ነገር መክብብ 3:1 የቤክ ትርጉም
ሁሉ የራሱ የሆነ ትክክለኛ ጊዜ አለው።’—እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ አንዳንድ ሰዎች ስትጸልይ ሲመለከቱህ መጸለይህ ጥሩ እንደሆነ ሊሰማቸው ቢችልም እየጸለይክ መሆንህን ሌሎች እንዲያዩልህ ለማድረግ መሞከር አያስፈልግህም። ለምሳሌ ያህል፣ ታማኙ ነህምያ በንጉሥ አርጤክስስ ፊት አጭር ጸሎት ያቀረበው ድምፅ ሳያሰማ እንደነበረና ንጉሡም እንኳ ነህምያ እየጸለየ እንደነበረ እንዳላወቀ ከታሪኩ መረዳት ይቻላል። (ነህምያ 2:1-5) አንተም ወደ ራስህ ትኩረት ሳትስብ በልብህ ለይሖዋ ጸሎት ማቅረብ ትችላለህ።—ፊልጵስዩስ 4:5
▪ ችግሩ፦ ይሖዋን ለማነጋገር አልበቃም የሚል ስሜት። “ይሖዋ ችግሮቼን ያውቃቸዋል። ያሉብኝ ችግሮች እኔን ካሰለቹኝ እሱም ሊሰማቸው እንደማይፈልግ ይሰማኛል! አንዳንድ ጊዜ እሱን ለማነጋገር እንደምበቃ ሆኖ አይሰማኝም።”—የ20 ዓመቷ ኤሊዛቤት፣ አየርላንድ
ቁልፉ፦ “[አምላክ] ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።”—1 ጴጥሮስ 5:7
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ የግል ጥናት በምታደርግበት ወቅት በሚከተሉት ጥቅሶች ላይ ምርምር በማድረግ አሰላስልባቸው፦ ሉቃስ 12:6, 7፤ ዮሐንስ 6:44፤ ዕብራውያን 4:16፤ 6:10፤ 2 ጴጥሮስ 3:9። እነዚህ ጥቅሶች ይሖዋ አንተን መስማት እንደሚፈልግ እንዲሁም የእሱን ተሰሚነት ለማግኘት የተለየ መንፈሳዊ ብቃት ማሟላት እንደማያስፈልግህ እንድትገነዘብ ይረዱሃል። በሕይወት ዘመኑ የተለያዩ ጭንቀቶችና መከራዎች ያጋጠሙት መዝሙራዊው ዳዊት፣ ይሖዋ “ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ [እንደሆነና] መንፈሳቸው የተሰበረውንም [እንደሚያድናቸው]” በእርግጠኝነት ተናግሯል። *—መዝሙር 34:18
ጸሎትህን የሚሰማው ይሖዋ ራሱ መሆኑ ስለ አንተ እንደሚያስብ ያሳያል። በጣሊያን የምትኖረው የ17 ዓመቷ ኒኮል እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ጸሎታችንን እንዲሰሙ መላእክትን አልወከላቸውም። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የምናቀርበውን ጸሎት ይሖዋ ራሱ የሚሰማው ከቁም ነገር ቢቆጥረው መሆን አለበት።”
www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.4 ፈጣሪ እኛን ለመስማት ያለው ችሎታ በድምፅ ሞገድ ላይ የተመካ ባለመሆኑ በልባችን የምንናገረውንም እንኳን ሳይቀር “ይሰማል።”—መዝሙር 19:14
^ አን.23 በገጽ 18 ላይ የሚገኘውን “መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?—ለአምልኮ ይረዳሉ ስለሚባሉ ነገሮች አምላክ ምን አመለካከት አለው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
^ አን.32 አምላክ ጸሎትህን ለመስማት እንደማይፈልግ የሚሰማህ ከባድ ኃጢአት በመፈጸምህ ምክንያት ከሆነ ስለ ሁኔታው ለወላጆችህ ልትነግራቸው ይገባል። በተጨማሪም ‘የጉባኤ ሽማግሌዎችን እንዲረዱህ ጥራቸው።’ (ያዕቆብ 5:14) ሽማግሌዎች ከይሖዋ ጋር የነበረህን ዝምድና እንድታድስ ሊረዱህ ይችላሉ።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
▪ በጸሎትህ ልታካትታቸው የምትችላቸው ይሖዋ ከፍ አድርጎ የሚመለከታቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
▪ ሌሎችን አስመልክተህ ስትጸልይ ስለ ምን ነገሮች ልትጠቅስ ትችላለህ?
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
እኩዮችህ የሰጡት አስተያየት
“ጸሎት፣ አንድ ሰው የቀን ውሎውን ከሚመዘግብበት የግል ማስታወሻ ጋር ይመሳሰላል። በጸሎትህ የገለጽከውን ነገር የምታውቁት አንተና ይሖዋ ብቻ ናችሁ።”—ኦላይንካ፣ ናይጄሪያ
“አንድ የቅርብ ጓደኛ እንዳለህና ለዚህ ጓደኛህ ደግሞ ብዙ ስጦታ እንደሰጠኸው አድርገህ አስብ። አንድ ቀን ይህ ጓደኛህ አንተን ማነጋገሩን ቢያቆም ምን ይሰማሃል? ይሖዋም ወደ እሱ መጸለያችንን ብናቆም የሚሰማው ልክ እንደዚሁ ነው።” —ቺንታ፣ አውስትራሊያ
“ስሜቴን አውጥቼ መግለጽ ስህተት እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። የጸሎት መብት ግን መደሰትም ሆነ ማዘን፣ እንዲሁም ግራ መጋባት ሊያጋጥም የሚችል ነገር እንደሆነና ስሜቴን በጸሎት ለይሖዋ መግለጽ ስህተት እንዳልሆነ እንድገነዘብ ረድቶኛል። አሁን የሚሰማኝን ስሜት ተገቢና ገንቢ በሆነ መልኩ መግለጽ እችላለሁ።” —አምበር፣ ዩናይትድ ስቴትስ
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጸሎት በር እንደተዘጋብህ ሆኖ ከተሰማህ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ቁልፎች ተጠቀም