በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ያለ ቀዶ ሕክምና የሰውነትን ውስጣዊ አካል መመልከት

ያለ ቀዶ ሕክምና የሰውነትን ውስጣዊ አካል መመልከት

ያለ ቀዶ ሕክምና የሰውነትን ውስጣዊ አካል መመልከት

በኮምፒውተር፣ በሂሳብና በሳይንስ መስኮች ከፍተኛ እድገት በመታየቱ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ሳያስፈልግ አንዳንድ በሽታዎችን መመርመር ተችሏል። ከመቶ ዓመታት በላይ ካስቆጠረው ከኤክስሬይ በተጨማሪ ኮምፒውትድ ቶሞግራፊ (ሲቲ ስካንስ)፣ ፖዘትሮን-ኢሚሽን ቶሞግራፊ (ፒኢቲ ስካንስ)፣ ማግኔቲክ ሬዞናንስ ኢሜጂንግ (ኤምአርአይ) እና አልትራሳውንድ ኢሜጂንግ ወይም ሶኖግራፊ የተባሉ ቴክኖሎጂዎች ይገኛሉ። * እነዚህ የሕክምና ዘዴዎች የሚከናወኑት እንዴት ነው? በጤና ላይ ምን ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ? ያላቸውስ ጥቅም ምንድን ነው?

ኤክስሬይ ሬዲዮግራፊ

ምርመራው የሚከናወነው እንዴት ነው? የኤክስሬይ የሞገድ ርዝመት በዓይናችን ልናየው የምንችለው ብርሃን ካለው የሞገድ ርዝመት ያነሰ ሲሆን ወደ ሰውነታችን ሕብረ ሕዋሳት በቀላሉ ዘልቆ መግባት ይችላል። አንድ የአካል ክፍል ኤክስሬይ በሚነሳበት ጊዜ እንደ አጥንት ያሉ ጠንከር ያሉ ሕብረ ሕዋሳት ጨረሩን ወደ ውስጥ ስለሚያስገቡት ሬዲዮግራፍ በሚባለው ምስል ላይ ደመቅ ብለው ይታያሉ። ለስለስ ያሉት ሕብረ ሕዋሳት ደግሞ ደብዘዝ ብለው ይታያሉ። ኤክስሬይ በአብዛኛው ከጥርስ፣ ከአጥንት፣ ከጡትና ከደረት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመመርመር ይረዳል። ሐኪሞች አንድ ሕብረ ሕዋስ ጎኑ ካለው ተመሳሳይ የሆነ ሕብረ ሕዋስ ጎላ ብሎ እንዲታይ ማድረግ ሲፈልጉ ሕብረ ሕዋሱ ለየት ብሎ እንዲታይ የሚያደርግ ማቅለሚያ በደም ሥር አማካኝነት ይሰጣሉ። በአሁኑ ጊዜ የኤክስሬይ ምስሎችን በኮምፒውተር መመልከት ይቻላል።

በጤና ላይ ሊያስከትል የሚችለው ችግር፦ ኤክስሬይ በሴሎችና በሕብረ ሕዋሳት ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችልበት በጣም አነስተኛ አጋጣሚ ያለ ቢሆንም ካለው ጠቀሜታ ጋር ሲነጻጸር ከቁጥር የሚገባ አይደለም። * ነፍሰ ጡር እንደሆኑ የሚያስቡ ሴቶች ኤክስሬይ ከመነሳታቸው በፊት ለሐኪማቸው ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። እንደ አዮዲን ያሉ ማቅለሚያዎች አለርጂ ሊሆኑ ይችላሉ። ለአዮዲን ወይም አዮዲን ላለባቸው ከባሕር የሚገኙ ምግቦች አለርጂክ ከሆንክ ለሐኪምህ ወይም ለኤክስሬይ ባለሞያ ማሳወቅ ይኖርብሃል።

ያሉት ጥቅሞች፦ ኤክስሬይ በፍጥነትና በቀላሉ የሚከናወን ምርመራ ሲሆን በአብዛኛው ሕመም የማያስከትል ከመሆኑም ሌላ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ብዙ ወጪ አይጠይቅም። በመሆኑም በጡት ውስጥ እብጠት መኖር አለመኖሩን ለማወቅ፣ ድንገተኛ አደጋ ሲደርስ ምርመራ ለማድረግና እነዚህን ለመሳሰሉ ሌሎች ምርመራዎች በጣም ጠቃሚ ነው። ኤክስሬይ ከተነሳ በኋላ በሰውነት ውስጥ የሚቀር ጨረር የለም፤ ብዙውን ጊዜም ይህ ምርመራ የሚያስከትለው ጉዳት አይኖርም። *

ኮምፒውትድ ቶሞግራፊ

ምርመራው የሚከናወነው እንዴት ነው? ሲቲ ስካን ይበልጥ ኃይለኛ የሆኑና የተወሳሰቡ ጨረሮችን እንዲሁም መረጃ የሚሰጡ ለየት ያሉ መሣሪያዎችን የያዘ ነው። ታካሚው እየተንሸራተተ በሚሄድ ዝርግ ነገር ላይ ተኝቶ ቱቦ በሚመስል መሣሪያ ውስጥ ያልፋል። በርካታ ጨረሮችና መመርመሪያ መሣሪያዎች በሽተኛውን 360 ዲግሪ እየዞሩ የተለያዩ ምስሎች ያነሳሉ። ይህ የምርመራ ሂደት አንድን ዳቦ በቀጭኑ እየቆረጡ እያንዳንዱን ቁራጭ ፎቶ ከማንሳት ጋር ይመሳሰላል። ከዚያም ሐኪሞች በኮምፒውተር በመታገዝ እነዚህን “ቁርጥራጭ” ምስሎች አንድ ላይ አሰባስበው የሰውነትን የውስጥ ክፍል በሚገባ መመልከት ይችላሉ። በቅርብ ጊዜ የተሠሩት ሲቲ ስካኖች በርከት ያሉ የተለያዩ ምስሎችን ከማውጣት ይልቅ እየተጥመዘመዘ የሚሄድ አንድ ወጥ ምስል ስለሚያነሱ ምርመራውን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማከናወን ያስችላሉ። ሲቲ ስካን ጥቃቅን የሆኑ ነገሮችንም የሚያሳዩ ምስሎችን ስለሚያወጣ ብዙውን ጊዜ ደረትን፣ የሆድ ዕቃን፣ አጥንትን እንዲሁም የተለያዩ የካንሰር በሽታዎችንና ሌሎች የጤና ችግሮችን ለመመርመር ይረዳል።

በጤና ላይ ሊያስከትል የሚችለው ችግር፦ ብዙውን ጊዜ ሲቲ ስካን ከኤክስሬይ የበለጠ መጠን ያለው ጨረር ይጠቀማል። ይህም አንድ ሰው በካንሰር የመያዝ አጋጣሚውን በጥቂቱ ከፍ ሊያደርገው ይችላል፤ በመሆኑም ጥቅሙንና ጉዳቱን በሚገባ አመዛዝኖ መወሰን ያስፈልጋል። አንዳንድ ሕሙማን እንደ አዮዲን ያሉ ማቅለሚያዎች አለርጂ ሊሆኑባቸው ይችላሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ኩላሊታቸውም ሊጎዳ ይችላል። የሚያጠቡ እናቶች እንዲህ ያለ ማቅለሚያ በደም ሥራቸው ከተሰጣቸው ማጥባት የሚችሉት ከ24 ሰዓት በኋላ ነው።

ያሉት ጥቅሞች፦ የሲቲ ስካን ምርመራ ምንም ዓይነት ሕመም የማያስከትል ከመሆኑም ሌላ ሰውነትን መክፈት ወይም ማንኛውንም ዓይነት መሣሪያ ሰውነት ውስጥ ማስገባት አይጠይቅም፤ በተጨማሪም ሲቲ ስካን እያንዳንዷን ነገር በዝርዝር የሚገልጽ መረጃ የሚሰጥ ሲሆን ይህ መረጃ በኮምፒውተር አማካኝነት በተለያየ አቅጣጫ ሊታይ ወደሚችል ምስል ሊለወጥ ይችላል። ይህ ምርመራ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ፈጣንና ቀላል ነው፤ እንዲሁም በውስጥ አካል ላይ የደረሰን ጉዳት ስለሚያሳይ ሕይወትን ሊታደግ ይችላል። ሲቲ ስካን በሰውነት ውስጥ በተገጠሙ ሰው ሠራሽ ነገሮች ላይ የሚያስከትለው ጉዳት የለም።

ፖዘትሮን-ኢሚሽን ቶሞግራፊ

ምርመራው የሚከናወነው እንዴት ነው? የፒኢቲ ስካን ምርመራ በሚደረግበት ጊዜ የሬዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገር በአብዛኛው እንደ ግሉኮስ ካለ ተፈጥሯዊ ውሁድ ጋር በመርፌ አማካኝነት ይሰጣል። በሕብረ ሕዋሳቱ ውስጥ ካለው ሬዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገር የሚመነጩት ፖዘቲቭ የሆኑ ቅንጣቶች አንድ ምስል እንዲገኝ ያደርጋሉ። የፒኢቲ ስካን ምርመራ የሚካሄደው ካንሰር ያለባቸው ሴሎች ከጤነኞቹ ሴሎች የበለጠ ግሉኮስ ስለሚጠቀሙ ሬዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገሩን በብዛት ይወስዳሉ የሚለውን ሐሳብ መሠረት በማድረግ ነው። በመሆኑም ችግር ያለባቸው ሕብረ ሕዋሳት ከፍተኛ መጠን ያለው ጨረር ስለሚያመነጩ በምስሉ ላይ የተለየ ቀለም ያላቸው ወይም ይበልጥ ደመቅ ያሉ ሆነው ይታያሉ።

ሲቲ ስካንና ኤምአርአይ ስካን የተለያዩ የአካል ክፍሎችንና የሕብረ ሕዋሳትን ቅርጽ እንዲሁም መዋቅር የሚያሳዩ ሲሆን ፒኢቲ ስካን ግን እነዚህ የአካል ክፍሎችና ሕብረ ሕዋሳት በምን ሁኔታ እየሠሩ እንዳሉ ስለሚያሳይ እየተከሰቱ ያሉትን ለውጦች ገና በእንጭጩ ለማወቅ ይረዳል። የፒኢቲ ስካንና የሲቲ ስካን ምርመራዎችን በአንድነት ማከናወን የሚቻል ሲሆን በምርመራው የሚገኙትን ምስሎች አንድ ላይ በማቀናጀት ይበልጥ ዝርዝር የሆነ መረጃ ማግኘት ይቻላል። ይሁን እንጂ ታካሚዎቹ የፒኢቲ ስካን ምርመራ ከማድረጋቸው ከተወሰነ ሰዓት በፊት ምግብ ከበሉ ወይም እንደ ስኳር በሽታ ባሉ ምክንያቶች ደማቸው ውስጥ ያለው የስኳር መጠን መሆን ካለበት መጠን ውጪ ከሆነ መሣሪያው የተሳሳተ መረጃ ሊሰጥ ይችላል። በተጨማሪም ለታካሚው የተሰጠው ሬዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገር የሚሠራው ለአጭር ጊዜ በመሆኑ ምርመራው ቶሎ መከናወን ይኖርበታል።

በጤና ላይ ሊያስከትል የሚችለው ችግር፦ ለምርመራው የሚሰጠው ሬዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገር መጠኑ አነስተኛ በመሆኑና ንጥረ ነገሩ የሚሠራው ለአጭር ጊዜ ስለሆነ ታካሚው ለጨረር እምብዛም አይጋለጥም። ያም ሆኖ በማደግ ላይ ባለ ጽንስ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ስለሆነም ነፍሰ ጡር እንደሆኑ የሚያስቡ ሴቶች ለሐኪማቸውና ለፒኢቲ ስካን ባለሞያው ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። ለአቅመ ሔዋን የደረሱ ሴቶች እርጉዝ መሆን አለመሆናቸውን ለማወቅ የደም ወይም የሽንት ምርመራ እንዲያደርጉ ሊጠየቁ ይችላሉ። የፒኢቲ ስካንና የሲቲ ስካን ምርመራ በአንድነት የሚከናወን ከሆነ ደግሞ ሲቲ ስካን ሊያስከትላቸው የሚችላቸው ችግሮችም ግምት ውስጥ መግባት አለባቸው።

ያሉት ጥቅሞች፦ ፒኢቲ ስካን የተለያዩ የአካል ክፍሎችና ሕብረ ሕዋሳት ምን ዓይነት ቅርጽ እንዳላቸው ብቻ ሳይሆን ምን ያህል በጥሩ ሁኔታ እየሠሩ እንዳሉ ጭምር ማሳየት ይችላል፤ ይህ ደግሞ በሕብረ ሕዋሳቱ መዋቅር ላይ የሚከሰቱ ለውጦች በሲቲ ስካን ወይም በኤምአርአይ መታየት የሚችሉበት ደረጃ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ችግሮችን ለይቶ ለማወቅ ይረዳል።

ማግኔቲክ ሬዞናንስ ኢሜጂንግ

ምርመራው የሚከናወነው እንዴት ነው? ኤምአርአይ ኃይለኛ መግነጢሳዊ መስክ (ማግኔቲክ ፊልድ) እና የሬዲዮ ሞገዶች በመጠቀም (ኤክስሬይ አይጠቀምም) እንዲሁም በኮምፒውተር በመታገዝ ሁሉንም የሰውነት የውስጥ ክፍሎች ማለት ይቻላል፣ አንድ በአንድ “እየቆራረጠ” በማንሳት እያንዳንዱን ነገር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ምስል ያወጣል። በዚህ መንገድ የሚገኘው መረጃ ሐኪሞች በሰውነት ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ጥቃቅን ነገር መመልከትና በሌሎች ዘዴዎች ሊከናወን በማይችል መንገድ በሽታን ለይተው ማወቅ እንዲችሉ ይረዳቸዋል። ለምሳሌ ኤምአርአይ በአጥንት የተሸፈኑ ነገሮችን ለማየት ከሚያስችሉ ጥቂት መሣሪያዎች አንዱ ሲሆን ይህም አንጎልንና ሌሎች ለስላሳ የሆኑ ሕብረ ሕዋሳትን ለመመርመር የሚረዳ ጥሩ መሣሪያ እንዲሆን አድርጎታል።

ይህ ምርመራ በሚካሄድበት ወቅት ታካሚዎቹ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ የለባቸውም። በተጨማሪም በምርመራው ወቅት ታካሚው እየተንሸራተተ በሚሄድ ዝርግ ነገር ላይ ተኝቶ ጠባብና ዝግ ወደሆነ ቱቦ መሰል መሣሪያ ውስጥ ስለሚገባ በጣም ሊጨነቅና ሊረበሽ ይችላል። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ለሚጨነቁ ወይም ከመጠን በላይ ወፍራም ለሆኑ ሰዎች ክፍት የሆነ ኤምአርአይ ስካን ተሠርቷል። እንደ እስክሪብቶ፣ ሰዓት፣ ጌጣጌጥ፣ የጸጉር ማስያዣና ዚፕ ያሉ ብረት ነክ ነገሮችን እንዲሁም ክሬዲት ካርዶችንና በማግኔት ሊሳቡ የሚችሉ ሌሎች ነገሮችን ወደ ምርመራ ክፍሉ ማስገባት አይፈቀድም።

በጤና ላይ ሊያስከትል የሚችለው ችግር፦ በምርመራው ወቅት ማቅለሚያ የሚሰጥ ከሆነ አለርጂ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል፤ ይሁን እንጂ በኤክስሬይና በሲቲ ስካን ምርመራ ወቅት በአብዛኛው የሚሰጡት አዮዲን ያላቸው ማቅለሚያዎች ሊያስከትሉ ከሚችሉት ጉዳት ጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ ነው። ከዚህ ውጭ ግን ኤምአርአይ በታካሚው ላይ የሚያስከትለው ይህ ነው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ጉዳት የለም። ሆኖም ምርመራውን ለማካሄድ ጥቅም ላይ የሚውለው ኃይለኛ መግነጢሳዊ መስክ በሚያሳድረው ተጽዕኖ ሳቢያ እንደ ሰው ሠራሽ መገጣጠሚያ ያሉ ነገሮች በቀዶ ሕክምና የተገጠሙላቸው ወይም በደረሰባቸው አደጋ ምክንያት በሰውነታቸው ውስጥ የቀሩ የብረት ስብርባሪዎች ያሉባቸው ታካሚዎች የኤምአርአይ ምርመራ ማድረግ አይችሉ ይሆናል። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች በሰውነትህ ውስጥ ካሉ ይህ ምርመራ በሚታዘዝልህ ጊዜ ለሐኪምህና ለኤምአርአይ ባለሞያው ማሳወቅ ይኖርብሃል።

ያሉት ጥቅሞች፦ ኤምአርአይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ጨረር የማይጠቀም ከመሆኑም ሌላ በተለያዩ ሕብረ ሕዋሳት በተለይ ደግሞ በአጥንት በተሸፈኑ ሕብረ ሕዋሳት ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል ጥሩ መሣሪያ ነው።

አልትራሳውንድ ኢሜጂንግ

ምርመራው የሚከናወነው እንዴት ነው? አልትራሳውንድ ስካኒንግ ወይም ሶኖግራፊ ተብሎም የሚጠራው ይህ ቴክኖሎጂ በዋነኝነት ከሰው የመስማት ችሎታ በላይ የሆኑ የድምፅ ሞገዶችን ይጠቀማል። ሞገዱ የተለያየ ይዘት ያላቸው ሕብረ ሕዋሳት የሚገናኙበት ቦታ ላይ ሲደርስ ያስተጋባል። ከዚያም ኮምፒውተሩ የተፈጠረውን ድምፅ አገናዝቦ የዚያን የአካል ክፍል ጥልቀት፣ መጠን፣ ቅርጽ፣ ውፍረትና ሌሎች ገጽታዎች የሚያሳይ ምስል ይሰጣል። ዝግ ብለው የሚርገበገቡ ሞገዶች የውስጥ የአካል ክፍሎችን ለማየት ያስችላሉ፤ በከፍተኛ ፍጥነት የሚርገበገቡ ሞገዶች ደግሞ እንደ ዓይንና ቆዳ ያሉ ውጫዊ የአካል ክፍሎችን ለመመርመር ስለሚረዱ የቆዳ ካንሰርን ለይቶ ለማወቅ ያስችላሉ።

አብዛኛውን ጊዜ ምርመራውን የሚያካሂደው ባለሞያ ትራንስዱሰር የሚባል በእጅ የሚያዝ መሣሪያ ይጠቀማል። ታካሚው ምንም ዓይነት ቀለም የሌለው ቅባት መሰል ነገር ቆዳው ላይ ከተቀባ በኋላ ባለሞያው ትራንስዱሰሩን ምርመራ በሚደረግበት የአካል ክፍል ላይ ወዲያና ወዲህ ያንቀሳቅሰዋል፤ በዚህ ጊዜ ምስሉ ወዲያውኑ ኮምፒውተሩ ላይ ይታያል። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የውስጥ የአካል ክፍሎችን ለመመርመር አንድ አነስተኛ ትራንስዱሰር ረጅምና ቀጭን በሆነ መሣሪያ ላይ ተገጥሞ ክፍት በሆነ የሰውነት ክፍል በኩል ወደ ውስጥ እንዲገባ ሊደረግ ይችላል።

ዶፕለር አልትራሳውንድ የተባለው ቴክኖሎጂ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በቀላሉ መለየት የሚችል ሲሆን የደም ዝውውርን ለመመርመር ይረዳል። ይህ ደግሞ የአካል ክፍሎችንና ከተለመደው በላይ በርካታ የደም ሥሮች የሚኖሯቸውን እብጠቶች በመመርመር ረገድ ጥሩ እገዛ ሊያደርግ ይችላል።

አልትራሳውንድ ሐኪሞች የተለያዩ ዓይነት ችግሮችን ለይተው ማወቅ እንዲችሉ ይረዳቸዋል፤ እንዲሁም የደምን ዝውውር ከሚቆጣጠር በልብ ውስጥ ከሚገኝ ሕብረ ሕዋስ ጋር ለተያያዙ ችግሮች፣ በጡት ውስጥ ለሚፈጠሩ እብጠቶችና እነዚህን ለመሳሰሉ የጤና እክሎች መንስኤ የሆኑ ነገሮችን ለመረዳት ወይም አንድ ጽንስ የሚገኝበትን ሁኔታ ለመመርመር ያስችላቸዋል። በሌላ በኩል ግን የአልትራሳውንድ ሞገዶች በጋዝ ውስጥ አልፈው መሄድ ስለማይችሉ መሣሪያው አንዳንድ የሆድ ዕቃ ክፍሎችን ጥርት አድርጎ ላያሳይ ይችላል። በተጨማሪም እንደ ኤክስሬይ ያሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ያህል ጥርት ያለ ምስል ላያሳይ ይችላል።

በጤና ላይ ሊያስከትል የሚችለው ችግር፦ በጥቅሉ ሲታይ የአልትራሳውንድ ምርመራ በአግባቡ እስከተከናወነ ድረስ ችግር አያስከትልም፤ ሆኖም ከመሣሪያው የሚወጣው ኃይል የጽንስንም ሆነ የማንኛውንም ታካሚ ሕብረ ሕዋሳት ሊጎዳ ይችላል። በመሆኑም በእርግዝና ወቅት የሚደረግ የአልትራሳውንድ ምርመራ ምንም ዓይነት ጉዳት አያስከትልም ተብሎ መታሰብ የለበትም።

ያሉት ጥቅሞች፦ ይህ ቴክኖሎጂ በስፋት የሚሠራበት ሲሆን በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ብዙ ወጪ አይጠይቅም። በተጨማሪም ምስሉ ወዲያውኑ ሊታይ ይችላል።

ወደፊት ጥቅም ላይ የሚውሉ ቴክኖሎጂዎች

በአሁኑ ጊዜ እየተደረጉ ያሉት ምርምሮች እየተሠራባቸው ያሉ ቴክኖሎጂዎችን በማሻሻል ላይ ያተኮሩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ተመራማሪዎች ቀደም ሲል ከተሠሩት መሣሪያዎች ጋር ሲነጻጸሩ በጣም አነስተኛ መግነጢሳዊ መስክ የሚጠቀሙ ኤምአርአይ ስካነሮችን እየሠሩ ሲሆን ይህም ምርመራው የሚጠይቀውን ወጪ በእጅጉ ለመቀነስ ያስችላል። ሞለኪውለር ኢሜጂንግ (ኤምአይ) የተባለ አዲስ ቴክኖሎጂ በመፈልሰፍ ላይ ነው። ኤምአይ በሰውነት ውስጥ በሞለኪውል ደረጃ የሚከሰቱ ለውጦችን ለመለየት እንዲረዳ ታስቦ እየተሠራ ያለ ቴክኖሎጂ በመሆኑ በሽታን ገና በእንጭጩ ለማወቅና ለማከም ያስችላል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል።

የሰውነትን የውስጥ አካል ክፍሎች ለማየት የሚረዳው ቴክኖሎጂ በሽታን ለመመርመር ተብለው ይደረጉ የነበሩ የሚያሠቃዩ፣ ለጉዳት የሚያጋልጡ አልፎ ተርፎም አላስፈላጊ የሆኑ በርካታ ቀዶ ሕክምናዎችን ለማስቀረት አስችሏል። በዚህ ቴክኖሎጂ አማካኝነት በሽታን ቶሎ ማወቅና ማከም በሚቻልበት ጊዜ በጣም የተሻለ ውጤት ይገኛል። ይሁንና መሣሪያዎቹ በጣም ውድ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ናቸው።

እርግጥ ነው፣ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ እንደሚባለው በሽታን ለይቶ ለማወቅና ለማዳን ጥረት ከማድረግ ይልቅ አስቀድሞ መከላከል ይመረጣል። ስለዚህ ጥሩ የአመጋገብ ሥርዓት በመከተል፣ አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ፣ በቂ እረፍት በመውሰድና አዎንታዊ አመለካከት በመያዝ ጤናማ ሆናችሁ ለመኖር ጥረት አድርጉ። ምሳሌ 17:22 “ደስ ያላት ልብ መልካም መድኃኒት ናት” ይላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 ቶሞግራፊ የሰውነትን የውስጥ አካል ክፍሎች በተለያየ አቅጣጫ ለማየት የሚያስችል ምስል ለማንሳት የሚረዳ ዘዴ ነው። ይህ ቃል “ክፍል” ወይም “ድርብርብ” የሚል ትርጉም ካለው ቶሞ ከሚለው ቃልና “መጻፍ” የሚል ትርጉም ካለው ግራፊን ከተባለው ቃል የተገኘ ነው።

^ አን.5 የጨረርን መጠን ለማነጻጸር  “ለጨረር ምን ያህል የተጋለጥን ነን?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

^ አን.6 የዚህ ርዕስ ዓላማ የሰውነት የውስጥ ክፍሎችን ለማየት የሚያስችሉ ዘዴዎችን እንዲሁም እነዚህ ዘዴዎች ያላቸውን ጉዳትና ጥቅም በአጭሩ መግለጽ ነው። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በዚህ ጉዳይ ላይ ጠለቅ ያለ ትንተና የሚሰጡ ጽሑፎችን መመልከት ወይም የኤክስሬይ ባለሞያዎችን ማማከር ትችላለህ።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

 ለጨረር ምን ያህል የተጋለጥን ነን?

በየዕለቱ ከከባቢ አየር ውጪ ለሚመጡ ጨረሮችም ሆነ እንደ ሬዶን ጋዝ ካሉ ሬዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገሮች ለሚመነጩ ጨረሮች በተወሰነ መጠን የተጋለጥን ነን። ከዚህ ቀጥሎ የቀረበው ንጽጽር አንዳንድ የምርመራ ዓይነቶች ሊያስከትሉ የሚችሉትን ጉዳት እንድታመዛዝን ሊረዳህ ይችላል። ንጽጽሩ የቀረበው ሚሊሰቨርት (ኤምኤስቪ) በተባለ የጨረር መለኪያ ሲሆን ቁጥሮቹም በአማካይ የተቀመጡ ናቸው።

በመንገደኞች አውሮፕላን ለአምስት ሰዓት የሚደረግ በረራ፦ 0.03 ኤምኤስቪ

በአሥር ቀን ውስጥ ተፈጥሯዊ ከሆኑ ነገሮች የሚመነጭ ጨረር፦ 0.1 ኤምኤስቪ

አንድ የጥርስ ኤክስሬይ፦ 0.04-0.15 ኤምኤስቪ

አንድ የደረት ኤክስሬይ፦ 0.1 ኤምኤስቪ

አንድ የጡት ኤክስሬይ፦ 0.7 ኤምኤስቪ

አንድ የደረት ሲቲ ስካን፦ 8.0 ኤምኤስቪ

ምርመራ ማድረግ የሚያስፈልግህ ከሆነ ሕክምናው ለጨረር ምን ያህል ሊያጋልጥህ እንደሚችል ወይም ሌላ የሚያሳስብህን ነገር በተመለከተ ግልጽ የሆነ መረጃ ለማግኘት ሐኪምህን ወይም የኤክስሬይ ባለሞያውን ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤክስሬይ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሲቲ

[ምንጭ]

© Philips

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፒኢቲ

[ምንጭ]

Courtesy Alzheimer’s Disease Education and Referral Center, a service of the National Institute on Aging

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤምአርአይ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አልትራሳውንድ