ጎማ አልባ ባቡር
ጎማ አልባ ባቡር
ሆንግ ኮንግ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
መንገደኞች በሻንጋይ፣ ቻይና ወደሚገኘው ባቡር ጣቢያ ደርሰው ባቡሩን ገና ሲያዩት የሚጓዙት እንደ ውኃ በሚፈስ ልዩ በሆነ አዲስ ባቡር እንደሆነ ይሰማቸዋል። ባቡሩ እጅግ ዘመናዊ ከሆነው ጣቢያው ተነስቶ ምንም ድምፅ ሳያሰማ በሰዓት 430 ኪሎ ሜትር መክነፍ ሲጀምር መንገደኞቹ እውነትም ልዩ በሆነ ባቡር እንደተሳፈሩ ያረጋግጣሉ፤ ይህ ፍጥነቱ በምድር ላይ የመጨረሻው ፈጣን የንግድ ባቡር እንዲሆን አድርጎታል። ባቡሩ ፑዶንግ ወደሚባለው 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ለመድረስ የሚፈጅበት ስምንት ደቂቃ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ይህን ባቡር ልዩ የሚያደርገው ሌላም ነገር አለ፤ ጎማ የለውም!
ከሻንጋይ ወደ ፑዶንግ የሚወሰደው የባቡር መሥመር በማግኔት ኃይል የሚሠራ በዓለም ብቸኛው አንሳፋፊ ሐዲድ ነው። ባቡሩ የሚሄደው በብረት ጎማ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ በማግኔት የስበት ኃይል ተደግፎ ነው። በተጨማሪም ባቡሩ የሚነዳው በሰው ሳይሆን ትክክለኛ መሥመሩን ጠብቆ እንዲጓዝና ወደ ዋናው መቆጣጠሪያ ጣቢያ መረጃ እንዲልክ በሚያስችለው የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ አማካኝነት ነው። በዋናው መቆጣጠሪያ ጣቢያ ያሉ ሰዎች በኮምፒዩተር እየታገዙ የባቡሩን እንቅስቃሴዎች በትክክል ይቆጣጠራሉ።
አንሳፋፊው የባቡር መሥመር ከመደበኛው ሐዲድ የሚለየው በምንድን ነው?
ይህ ልዩ ባቡርም ሆነ የማንሳፈፍ ኃይል ያለው የባቡር መሥመር በተገነቡበት ወቅት አንዳንድ ተፈታታኝ ችግሮች አጋጥመው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በሚበረው ባቡርና ባቡሩ በሚንሳፈፍበት መሥመር መካከል ያለው ክፍተት ሁለት ሴንቲ ሜትር እንኳ አይሞላም። በመሆኑም የሻንጋይ መሬት አፈሩ ልል በመሆኑ መሐንዲሶቹ በመሬት መክዳት ምክንያት የሚፈጠረውን ክፍተት በየጊዜው ለማስተካከል የሚረዱ ልዩ መገጣጠሚያዎችን በባቡሩ መሥመር ላይ መግጠም አስፈልጓቸዋል።
በተጨማሪም መሐንዲሶቹ የአርማታ ምሰሶዎቹ በአየር ጠባዩ መለዋወጥ ምክንያት ሲለጠጡና ሲኮማተሩ ሊፈጠር የሚችለውን መጠነኛ ለውጥ ግምት ውስጥ ማስገባት ጠይቆባቸዋል።ያም ሆኖ የተንሳፋፊ ባቡር ቴክኖሎጂ ብዙ ጥቅሞች አሉት። ለምሳሌ ያህል፣ ምንም ዓይነት የሞተር ወይም የጎማ ድምፅ አያሰማም፤ እንዲሁም ከባቡሩ የሚወጣ ጎጂ ጪስ የለም። መንገዱም ሆነ ባቡሩ እምብዛም ጥገና አያስፈልጋቸውም። ከዚህም ሌላ ባቡሩ ለመንገደኞች መጓጓዣ አገልግሎት እንዲሰጥ የተሠራ እንደመሆኑ መጠን የኃይል ቆጣቢነቱ ከመኪና በሦስት እጥፍ፣ ከአውሮፕላን ደግሞ በአምስት እጥፍ ይበልጣል። እንዲያውም ይህ ባቡር ለመንሳፈፍ የሚጠቀመው የኃይል ፍጆታ ለአየር ማቀዝቀዣ መሣሪያው ከሚያስፈልገው እንኳ ያነሰ ነው! በተጨማሪም ባቡሩ ጎማ ካላቸው ባቡሮች በተሻለ ሁኔታ ቀጥ ያሉ ዳገቶችን መውጣትና ጠመዝማዛ ኩርባዎችን በቀላሉ ማለፍ ይችላል፤ ይህ ደግሞ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡን ለማስተካከል የሚደረገውን ጥረት ይቀንሳል።
ይህ ባቡር እነዚህ ሁሉ ጥቅሞች ያሉት ከመሆኑ አንፃር ብዙ አንሳፋፊ የባቡር መሥመሮች አለመሠራታቸው የሚያስገርም ሊመስል ይችላል። ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት ባቡሩን ለመሥራት የሚያስፈልገው ወጪ በጣም ከፍተኛ መሆኑ ነው። እንዲያውም ሻንጋይንና ቤጂንግን የሚያገናኝ አንሳፋፊ የባቡር መሥመር ለመሥራት የሚያስፈልገው ወጪ ከመደበኛው ፈጣን ባቡር ወጪ በእጥፍ ስለሚበልጥ የቻይና ባለ ሥልጣናት እንዲህ ያለውን ባቡር ለመገንባት የቀረበውን ሐሳብ ለጊዜው ሳይቀበሉት ቀርተዋል። እንዲሁም ተንሳፋፊው ባቡር የተለየ መሥመር ስለሚያስፈልገው ከበፊቶቹ የቻይና ባቡሮች ጋር ተቀናጅቶ መሥራት አይችልም።
የሻንጋይ ተንሳፋፊ ባቡር አገልግሎት የጀርመንን ቴክኖሎጂ የተጠቀመ ሲሆን በዚህ መስክ የሚደረገው ምርምር በጀርመን፣ በጃፓንና በሌሎችም ቦታዎች ቀጥሏል። በታኅሣሥ 2003 በጃፓን የሚገኘው የተንሳፋፊ ባቡር ድርጅት በሰዓት 581 ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚችል ፈጣን ባቡር ሠርቷል፤ ይህ ፍጥነት በዓለም ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል። ይሁንና ከተንሳፋፊ ባቡሮች መካከል እስካሁን ለሕዝብ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የሻንጋዩ ባቡር ብቻ ነው።
ተንሳፋፊ ባቡሩ ከፑዶንግ ወደ ሻንጋይ የመልስ ጉዞ ሲጀምር መንገደኞቹ ባቡሩ የሚበርበትን ከፍተኛ ፍጥነት ለማወቅ ካላቸው ጉጉት የተነሳ በእያንዳንዱ ፉርጎ ላይ የተገጠመውን የፍጥነት መለኪያ ፍጥጥ ብለው ይመለከታሉ። በዚህም ምክንያት በርካታ መንገደኞች በመጀመሪያ ጉዟቸው ወቅት መልክዓ ምድሩን የማየት አጋጣሚ ስለሚያመልጣቸው ለሁለተኛ ጊዜ ይጓዛሉ። ወደ ውጭ ሲመለከቱ አካባቢው በፍጥነት እልፍ እልፍ ሲልባቸው ባቡሩ “ክንፍ አልባው አውሮፕላን” የተባለበት ምክንያት ይገባቸዋል።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕላዊ መግለጫ]
የማግኔት ማንሳፈፊያው የሚሠራው እንዴት ነው?
በእያንዳንዱ ፉርጎ የታችኛው ክፍል ላይ ከጫፍ እስከ ጫፍ የተገጠሙት በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ኤሌክትሮማግኔቶች (1) በባቡሩ መሥመር (2) ላይ ካሉት ማግኔቶች ጋር እርስ በርስ በመሳሳብ ወደ 1.3 ሴንቲ ሜትር የሚጠጋ ክፍተት እስኪኖር ድረስ ባቡሩን ያንሳፍፉታል። ሌሎች ማግኔቶች (3) ባቡሩ ወደ ጎን ሳያፈነግጥ መሥመሩን ጠብቆ እንዲሄድ ያደርጉታል። በመንገዱ ላይ የተዘረጉት ጥቅልል ሽቦዎች (4) ባቡሩ ወደፊት እንዲከንፍ የሚያደርግ የማግኔት ኃይል ይፈጥሩለታል።
የባቡሩ መሥመር የተሠራው በክፍል በክፍል ነው። ዋናው የመቆጣጠሪያ ጣቢያ ኤሌክትሪክ ለመቆጠብ ሲል ለአንድ ክፍል (5) ኃይል የሚለቀው ባቡሩ እዚያ ክፍል ላይ ሲደርስ ብቻ ነው። ባቡሩ መፍጠን ወይም ዳገት መውጣት በሚያስፈልገው ቦታ ላይ ከፍተኛ ኃይል ይሰጠዋል። ባቡሩ ፍጥነት መቀነስ ወይም ወደኋላ መመለስ በሚያስፈልገው ጊዜ ሐዲዱ ላይ በተዘረጋው ጥቅልል ሽቦ ውስጥ ያለው የማግኔት ኃይል ወደተቃራኒው አቅጣጫ እንዲለወጥ ይደረጋል።
አደጋ የለውም?
ምንም እንኳ ተንሳፋፊ ባቡሩ የሚጓዘው በጣም ከፍተኛ በሆነ ፍጥነት ቢሆንም በእያንዳንዱ ፉርጎ ጫፍና ጫፍ ያሉት አቃፊዎች (6) ሐዲዱን አቅፈው ስለሚይዙት መሥመር ስቶ የመውጣት አጋጣሚው እጅግ አናሳ ነው። ለመንገደኞቹ የአደጋ መከላከያ ቀበቶዎች የማያስፈልጉ ሲሆን ባቡሩ በመደበኛ ፍጥነቱ በሚጓዝበትም ጊዜም እንኳ እንደልባቸው ወዲያ ወዲህ መንቀሳቀስ ይችላሉ። ድንገት ኃይል ቢቋረጥ በባቡሩ ላይ በተገጠሙ ባትሪዎች የሚሠሩ ልዩ ፍሬኖች ባቡሩ በሰዓት 10 ኪሎ ሜትር ድረስ ዝግ እንዲል የሚያደርግ ተቃራኒ የማግኔት ኃይል ይፈጥራሉ። ከዚያም ባቡሩ ቀስ በቀስ እየተንሸራተተ ይቆማል።
የባቡሩ ኃይለኛ ማግኔቶች የጤና ችግር ያስከትሉ ይሆን? ለምሳሌ የተስተካከለ የልብ ምት እንዲኖራቸው ለማድረግ ሲባል ኤሌክትሮኒክ መሣሪያ በተገጠመላቸው መንገደኞች ላይ ምንም ችግር አያመጣም? የተገኙት የምርመራ ውጤቶች ሁኔታው አሳሳቢ እንዳልሆነ ያሳያሉ። እንዲያውም ይህ ባቡር በውጪ በኩል ያለው የማግኔት ኃይል አንዳንድ መደበኛ ባቡሮች ካላቸው የማግኔት ኃይል ጋር ሲወዳደር አነስተኛ ነው።
[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በሰዓት ከ430 ኪሎ ሜትር በላይ ይበራል!
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ገጽ 24 እና 25፦ ሁሉም ፎቶዎችና ሥዕላዊ መግለጫዎቹ፦ © Fritz Stoiber Productions/Courtesy Transrapid International GmbH & Co. KG