በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማስታወቂያዎች ያላቸው የማታለል ኃይል

ማስታወቂያዎች ያላቸው የማታለል ኃይል

ማስታወቂያዎች ያላቸው የማታለል ኃይል

ፖላንድ የሚገኘው የንቁ! ጸሐፊ እንዳዘጋጀው

ቶሜክ በቴሌቪዥኑ ላይ ዓይኑን ተክሎ በትኩረት ይመለከታል። ቶሜክ “ልጃችሁ ይህን ሲለብስ ጠንካራ፣ ስፖርተኛና በጓደኞቹ ዘንድ የሚደነቅ ይሆናል። ልትገዙለት ይገባል!” የሚል የአድማጮችን ቀልብ የሚስብ የንግድ ማስታወቂያ በትኩረት ካዳመጠ በኋላ የማስታወቂያውን ሙዚቃ እየደገመ ወደ አባቱ ሮጠ። ከዚያም “አባዬ፣ ትገዛልኛለህ አይደል?” በማለት ጠየቀ።

ልጆች በማስታወቂያ ላይ የሚያዩት ነገር እንዲገዛላቸው የሚፈልጉት ለምንድን ነው? ሬቭያ በተሰኘው የፖላንድ መጽሔት ላይ የተጠቀሱ አንድ የትምህርት ባለሙያ “ሌሎች ያላቸው ነገር እነሱም እንዲኖራቸው ስለሚፈልጉ ነው። ከጓደኞቻቸው አንሰው መታየት አይፈልጉም” ሲሉ ተናግረዋል። ልጆች ሲለማመጡ፣ ሲያለቅሱና ሲያኮርፉ ብዙውን ጊዜ ወላጆች ይሸነፉና የሚፈልጉትን ዕቃ ይገዙላቸዋል።

የልጆችን ቀልብ ለመሳብ ተብሎ የሚዘጋጀው ማስታወቂያ ይህን ያህል አታላይ እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው? የማስታወቂያው ይዘት የሚያተኩረው “በዋጋው፣ በጥራቱ፣ ወይም በምርቱ ጠቃሚነት ላይ አይደለም” በማለት የሥነ ልቦና ምሑር የሆኑት ዮላንታ ቮንስ ይገልጻሉ። ማስታወቂያው የሚዘጋጀው “[ሰዎች] ዕቃውን በጣም እንዲወዱት ለማድረግ” ነው። ቮንስ እንደገለጹት “ትንንሽ ልጆች በማስታወቂያ ላይ የሚነገረውን ነገር አያገናዝቡም። . . . በማስታወቂያው ላይ የቀረበላቸውን መረጃ ከገሐዱ ዓለም እውነታ ጋር አያወዳድሩም።” ይህን ለማድረግ ቢሞክሩ እንኳ ዕቃውን በትክክል ለመገምገም የሚያስችል በቂ ግንዛቤ የላቸውም።

ታዲያ ልጃችሁ በማስታወቂያዎች እንዳይታለል ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? በመጀመሪያ፣ “ከልጃችሁ ጋር ጊዜ በማሳለፍ የአንድ ሰው ዋጋማነት የሚለካው በሚያደርገው ጫማ [ወይም በሚለብሰው ልብስ] ላይ እንዳልሆነ ደጋግማችሁ ልታስረዱት ይገባል” በማለት ሬቭያ ይናገራል። ልጃችሁ አዳዲስ መጫወቻዎች ባይኖሩትም የልጅነት ሕይወቱ አስደሳች ሊሆን እንደሚችል አስረዱት። በሁለተኛ ደረጃ፣ ወላጆች ማስታወቂያዎች በልጆቻቸው ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ማወቅ አለባቸው። ለዚህ ቁልፍ የሆነው ነገር “ለልጃችን የሚበጀው ምን እንደሆነ ማስታወቂያ እንዲነግረን አለመፍቀድ” ነው በማለት ቮንስ ይመክራሉ።

በመጨረሻም፣ ሁሉም ወላጆች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሰፈረው ምክር ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “በዓለም ያለው ነገር ሁሉ ይኸውም የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮትና ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመነጭ አይደለም።”—1 ዮሐንስ 2:15, 16 NW

ብዙ የንግድ ማስታወቂያዎች የሰዎችን “የዓይን አምሮት” የሚቀሰቅሱ እንዲሁም ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች “ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ” እንዲያድርባቸው የሚያደርጉ ናቸው ቢባል አትስማማም? ይሁንና ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል” በማለት አክሎ የተናገረው ሐሳብ ትኩረት የሚስብ ነው።—1 ዮሐንስ 2:17

አዘውትረው ከልጆቻቸው ጋር የሚያንጽ ጭውውት የሚያደርጉ ወላጆች፣ የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶችና ጠቃሚ የሆኑ ሥነ ምግባራዊ እሴቶችን በልጆቻቸው ልብ ውስጥ መቅረጽ ይችላሉ። (ዘዳግም 6:5-7) ይህ ከሆነ ደግሞ ልጆች፣ ወላጆቻቸውን ነዝንዘው የፈለጉትን ዕቃ እንዲያስገዙ ለማድረግ ሲባል ዓለም በሚያዘጋጃቸው አታላይ ማስታወቂያዎች በቀላሉ አይታለሉም።