በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በኮሪያ ታላላቅ ለውጦች በተካሄዱበት ዘመን መኖር

በኮሪያ ታላላቅ ለውጦች በተካሄዱበት ዘመን መኖር

በኮሪያ ታላላቅ ለውጦች በተካሄዱበት ዘመን መኖር

ቾንግ ኢል ፓክ እንደተናገረው

“ፈሪ! በጦር ግንባር እንዳትሞት ፈርተህ ነው። በሃይማኖትህ አሳብበህ ከወታደራዊ አገልግሎት ለማምለጥ እየሞከርክ ነው።” ይህን ውንጀላ የሰነዘረው ካውንተር ኢንተለጀንስ ኮር (CIC) የተሰኘው የደህንነት ቢሮ አዛዥ ሲሆን እንዲህ ያለውም ከ55 ዓመታት በፊት ሰኔ 1953 ፊቱ ቀርቤ በነበረበት ወቅት ነው።

ህ ሁኔታ የተከሰተው በኮሪያ በተደረገው ጦርነት ወቅት ነበር። አዛዡ ሽጉጡን አውጥቶ ጠረጴዛው ላይ ካስቀመጠው በኋላ “ወደ ጦር ግንባር ሳትሄድ እዚሁ ትሞታለህ” አለኝ። ከዚያም “ሐሳብህን ለመቀየር ትፈልጋለህ?” በማለት ጠየቀኝ።

እኔም “በፍጹም” በማለት መለስኩለት። በዚህ ጊዜ አዛዡ እኔን ለመግደል ዝግጅት እንዲደረግ አንዱን መኮንን አዘዘው።

ይህ ሁኔታ ከመፈጠሩ በፊት ወታደራዊ አገልግሎት እንድሰጥ ተጠርቼ የነበረ ቢሆንም እኔ ግን በዚህ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ አልነበርኩም። መኮንኑ እኔን ለመግደል የሚደረገውን ዝግጅት እስኪያጠናቅቅ እየጠበቅን እያለ ለአዛዡ፣ ሕይወቴን ቀደም ሲል ለአምላክ እንደወሰንኩና ለአምላክ አገልግሎት ካልሆነ በቀር ለሌላ ዓላማ መሥዋዕት ባደርገው ትክክል እንዳልሆነ እንደማምን ነገርኩት። ከዚያ ሁለታችንም ምንም ሳንናገር ጥቂት ደቂቃዎች አለፉ። ብዙም ሳይቆይ መኮንኑ ተመልሶ መጣና እኔን ለመግደል ሁሉም ነገር እንደተዘጋጀ ተናገረ።

በወቅቱ በደቡብ ኮሪያ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙም የሚያውቁት ነገር አልነበረም፤ በመሆኑም የትኛውም መንግሥት በሚያካሂደው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለመካፈል ሕሊናችን እንደማይፈቅድልን ስንገልጽ አይረዱንም ነበር። አዛዡ ምን እንዳደረገ ከመግለጼ በፊት በወታደራዊ እንቅስቃሴ ላለመካፈል ልወስን የቻልኩት እንዴት እንደሆነ ላውጋችሁ።

የልጅነት ሕይወቴ

የተወለድኩት በጥቅምት ወር 1930 ሲሆን ለቤተሰቤ የመጀመሪያ ልጅ ነበርኩ፤ ቤተሰባችን የሚኖረው በወቅቱ የኮሪያ ዋና ከተማ በነበረችው በሴኡል አቅራቢያ በምትገኝ ከተማ ውስጥ ነበር። አያቴ የኮንፊሽየስ ሃይማኖትን አጥብቆ ይከተል የነበረ ሲሆን እኔም እንደ እሱ እንድሆን አሠልጥኖኝ ነበር። አያቴ ትምህርት ቤት ገብቼ እንድማር ስላልፈለገ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ትምህርት ቤት አልገባሁም ነበር፤ እሱ ሲሞት 10 ዓመቴ ነበር። ከዚያም በ1941 ጃፓንና ዩናይትድ ስቴትስ በተቃራኒ ጎራ ተሰልፈው ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ገቡ።

ኮሪያ በጃፓን አገዛዝ ሥር ስለነበረች ሁልጊዜ ጠዋት ላይ ተማሪዎች ለጃፓኑ ንጉሠ ነገሥት ክብር በሚደረግ ሥነ ሥርዓት መካፈል ነበረብን። በዚህ ወቅት አክስቴና ባሏ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው ነበር፤ በሃይማኖታዊ እምነታቸው የተነሳ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለጦርነቱ ድጋፍ ለመስጠት ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ኮሪያ ውስጥ ታስረው ነበር። ጃፓናውያን በይሖዋ ምሥክሮች ላይ በፈጸሙባቸው የጭካኔ ድርጊት የተነሳ የአክስቴን ባል ጨምሮ አንዳንዶች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በኋላም አክስቴ ከእኛ ቤተሰብ ጋር መኖር ጀመረች።

በ1945 ኮሪያ ከጃፓን አገዛዝ ነፃ ወጣች። አክስቴና ከእስር ቤት በሕይወት የተረፉ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠኑኝ ሲሆን በ1947 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የሠለጠኑት ዶንና ኧርሊን ስቲል የሚባሉ ሚስዮናውያን ነሐሴ 1949 ወደ ሴኡል መጡ፤ በኮሪያ የተመደቡት የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናውያን እነዚህ ባልና ሚስት ናቸው። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ደግሞ ሌሎች ሚስዮናውያንም መጡ።

ጥር 1, 1950 እኔና ሦስት ኮሪያውያን የይሖዋ ምሥክሮች አቅኚዎች (የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ሆነን ማገልገል ጀመርን። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በኮሪያ የመጀመሪያዎቹ አቅኚዎች እኛ ነበርን።

በኮሪያው ጦርነት ወቅት የነበረው ሁኔታ

ሰኔ 25, 1950 እሁድ ዕለት በሰሜን ኮሪያና በደቡብ ኮሪያ መካከል ጦርነት ተጀመረ። በወቅቱ በመላው ኮሪያ የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ አንድ ብቻ ሲሆን 61 አባላት ያሉት ይህ ጉባኤ የሚገኘው በሴኡል ነበር። የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ሁሉም ሚስዮናውያን ለራሳቸው ደህንነት ሲባል ኮሪያን ለቀው እንዲወጡ አዘዘ። የአገሩ ተወላጅ የሆኑ አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮችም ሴኡልን ለቀው ወደ ደቡባዊው የአገሪቱ ክፍል ሄዱ።

ይሁን እንጂ የደቡብ ኮሪያ መንግሥት በውትድርና ለማገልገል በሚችሉበት ዕድሜ ላይ የደረሱ እንደ እኔ ያሉ ወጣቶች ከሴኡል እንዳይወጡ አገደ። በድንገት የኮሚኒስት ወታደሮች ወደ ከተማዋ የገቡ ሲሆን የኮሚኒስት ወታደራዊ ኃይል ሴኡልን ይቆጣጠር ጀመር። በዚህ ጊዜ ለሦስት ወራት በአንዲት ትንሽ ክፍል ውስጥ ለመደበቅ ብገደድም ለሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ለመመስከር ችዬ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ከኮሚኒስቶች ተደብቆ ከነበረ አንድ መምህር ጋር ተገናኘሁ። እሱም ከእኔ ጋር በዚያች ጠባብ ክፍል መኖር ስለጀመረ በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስ አስጠናው ነበር። ከጊዜ በኋላ ይህ ሰው ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆኗል።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ ከሰሜን ኮሪያ የመጡ የኮሚኒስት ባለ ሥልጣናት የተደበቅንበት ቦታ ደረሱበት። እኛም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መሆናችንን ከነገርናቸው በኋላ ስለ አምላክ መንግሥት የሚያስተምረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ አብራራንላቸው። የሚገርመው ነገር ባለ ሥልጣናቱ አላሰሩንም፤ እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለማወቅ እንደሚፈልጉ ገለጹልን። አንዳንዶቹ ከዚያ በኋላ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተመልሰው የመጡ ሲሆን ስለ አምላክ መንግሥት ተጨማሪ ነገር መስማት ፈልገው ነበር። ይህ አጋጣሚ ይሖዋ ጥበቃ እንደሚያደርግልን ያለንን እምነት አጠናክሮልናል።

የተባበሩት መንግሥታት ሠራዊት ሴኡልን እንደገና ከተቆጣጠረ በኋላ መጋቢት 1951 ወደ ታይጉ ከተማ ለመሄድ ልዩ ፈቃድ አግኝቼ ነበር። እዚያም ከእምነት ባልንጀሮቼ ጋር በመሆን ለአያሌ ወራት የመስበክ አጋጣሚ አገኘሁ። ከዚያም ጦርነቱ ከማብቃቱ በፊት በኅዳር ወር 1951 ዶን ስቲል ወደ ኮሪያ ተመልሶ መጣ።

እኔም የስብከቱን ሥራ እንደገና በማደራጀት አግዘው ነበር። መጠበቂያ ግንብን እና የይሖዋ ምሥክሮች የስብከት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ጠቃሚ መመሪያዎች የሚሰጠውን ኢንፎርማንት የተባለውን ቡክሌት ወደ ኮሪያኛ ቋንቋ መተርጎም፣ በታይፕ መጻፍና ማባዛት ያስፈልግ ነበር። ከዚያም እነዚህ ጽሑፎች በወቅቱ በተለያዩ ከተሞች ውስጥ ይገኙ ወደነበሩት ጉባኤዎች ይላኩ ነበር። አልፎ አልፎ እኔና ዶን ጉባኤዎችን ለማበረታታት አብረን እንጓዝ ነበር።

ጥር 1953 ኒው ዮርክ በሚገኘው የጊልያድ ትምህርት ቤት ገብቼ ለሚስዮናዊነት አገልግሎት እንድሠለጥን የሚጋብዝ ደብዳቤ ሲደርሰኝ እጅግ ተደስቼ ነበር። ይሁን እንጂ በአውሮፕላን ወደ ኒው ዮርክ ለመጓዝ የሚያስፈልገው ዝግጅት ከተደረገልኝ በኋላ ለወታደራዊ አገልግሎት እንደተጠራሁ የሚገልጽ ደብዳቤ ከኮሪያ መንግሥት ደረሰኝ።

ሕይወቴ አደጋ ላይ የወደቀበት ሁኔታ

ወደ ምልመላ ማዕከሉ ሄድኩና ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ መሆኔን እንዲሁም ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆንኩ ለአዛዡ ገለጽኩለት። በዚህ ጊዜ ኮሚኒስት መሆን አለመሆኔ እንዲጣራ ሲል ካውንተር ኢንተለጀንስ ኮር ወደሚባለው የደህንነት ቢሮ ላከኝ። ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ሕይወቴ አደጋ ላይ የወደቀው በዚህ ጊዜ ነበር። አዛዡ እኔን በመግደል ፈንታ ከተቀመጠበት ተነሳና ለአንድ መኮንን ወፍራም ዱላ ሰጥቶ እንዲደበድበኝ አዘዘው። ድብደባው ኃይለኛ ሥቃይ ቢያስከትልብኝም ለመጽናት በመቻሌ ደስተኛ ነበርኩ።

የደህንነት ቢሮው ወደ ምልመላ ማዕከሉ መልሶ የላከኝ ሲሆን በዚያ የሚገኙት ባለ ሥልጣናት ደግሞ እምነቴን ከምንም ባለመቁጠር ወታደራዊ የመታወቂያ ቁጥር ሰጡኝ፤ ከዚያም ወታደራዊ ሥልጠና ወደሚሰጥባት በኮሪያ አቅራቢያ ወደምትገኘው ቼጁ ደሴት ላኩኝ። በቀጣዩ ቀን እኔን ጨምሮ አዳዲሶቹ ምልምሎች፣ ወታደሮች ለመሆን ቃለ መሐላ እንድንፈጽም ፕሮግራም ተይዞ ነበር። እኔም ቃለ መሐላውን ለመፈጸም ፈቃደኛ አለመሆኔን ገለጽኩ። በዚህም የተነሳ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ቀረብኩና የሦስት ዓመት እስራት ተበየነብኝ።

በሺዎች የሚቆጠሩ ታማኝነታቸውን ጠብቀዋል

ለሚስዮናዊነት ሥልጠና ልሄድ በነበረበት ቀን አንድ አውሮፕላን ሲበር ተመለከትሁ፤ ወደ ጊልያድ የምሄደው በዚህ አውሮፕላን ነበር። በዚህ ወቅት ወደ ጊልያድ መሄድ ባለመቻሌ በማዘን ፈንታ ለይሖዋ ታማኝነቴን በመጠበቄ ጥልቅ እርካታ ተሰማኝ። ደግሞም ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልነበርኩት ኮሪያዊ የይሖዋ ምሥክር እኔ ብቻ አይደለሁም። በቀጣዮቹ ዓመታት ከ13,000 የሚበልጡ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ተመሳሳይ አቋም ወስደዋል። በዚህም ምክንያት እነዚህ ወንድሞች በኮሪያ እስር ቤቶች ውስጥ በድምሩ 26,000 ዓመታት አሳልፈዋል።

ለሁለት ዓመት ከታሰርኩ በኋላ ለእስረኞች ጥሩ ምሳሌ በመሆኔ በ1955 በአመክሮ ተለቀቅሁ። ከእስር ቤት ከወጣሁ በኋላ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈሌን ቀጠልኩ። በጥቅምት ወር 1956 በደቡብ ኮሪያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቢሮ እንዳገለግል ተመደብኩ። ከዚያም በ1958 እንደገና ወደ ጊልያድ ተጠራሁ። ከጊልያድ ከተመረቅኩ በኋላ ኮሪያ ተመደብኩ።

ወደ ኮሪያ ከተመለስኩ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ታማኝ የይሖዋ ምሥክር ከሆነችው ከኢን-ሂዩን ሰንግ ጋር የተዋወቅን ሲሆን በግንቦት ወር 1962 ተጋባን። ኢን-ሂዩን ሰንግ ቤተሰቦቿ የቡድሂዝም ሃይማኖት ተከታዮች ሲሆኑ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ያወቀችው ከአንዲት የክፍል ጓደኛዋ ነበር። ከተጋባን በኋላ በነበሩት ሦስት ዓመታት በየሳምንቱ አንድ ጉባኤ እየጎበኘን በኮሪያ የሚገኙትን ወንድሞችና እህቶች በመንፈሳዊ እናበረታታ ነበር። ከ1965 ወዲህ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ከሴኡል 60 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እያገለገልን ነው።

የተደረጉትን ለውጦች መለስ ብሎ ማሰብ

ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስብ በዚህች አገር ውስጥ የተከናወኑት በርካታ ለውጦች ያስገርሙኛል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዲሁም ከሰሜን ኮሪያ ጋር ከተደረገው ጦርነት በኋላ ደቡብ ኮሪያ እንዳልነበረች ሆና ነበር። ከተሞቿ ፈራርሰው እንዲሁም መንገዶቿ ተበላሽተው ነበር። የኤሌክትሪክ ኃይል የምናገኘው አልፎ አልፎ ሲሆን እስከ ጭራሹ የማይኖርበትም ጊዜ ነበር። የአገሪቷ ኢኮኖሚም ተንኮታኩቶ ነበር። ከጦርነቱ በኋላ ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ግን ደቡብ ኮሪያ አስደናቂ የሆነ እድገት አሳይታለች።

ዛሬ ደቡብ ኮሪያ በዓለም ላይ ካሉት በኢኮኖሚ ያደጉ አገሮች 11ኛውን ደረጃ ይዛለች። በዘመናዊ ከተሞቿ፣ ከፍተኛ ፍጥነት ባላቸው ባቡሮቿ፣ በኤሌክትሮኒክ መሣሪዎቿ እንዲሁም መኪና በማምረት የታወቀች ሆናለች። ደቡብ ኮሪያ በአሁኑ ጊዜ መኪና በብዛት በማምረት በዓለም ላይ አምስተኛውን ደረጃ ይዛለች። ይሁን እንጂ ለእኔ ከሁሉ ይበልጥ ትልቅ ትርጉም ያለው ለውጥ ደቡብ ኮሪያ የዜጎቿን ሰብአዊ መብት በማክበር ረገድ ያደረገችው መሻሻል ነው።

በ1953 በወታደራዊ ፍርድ ቤት በቀረብኩበት ወቅት አንዳንድ ግለሰቦች ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው እንደማይፈቅድላቸው የሚገልጹት ለምን እንደሆነ ለኮሪያ መንግሥት ግልጽ አልነበረም። አንዳንዶቻችን ኮሚኒስቶች ናችሁ ተብለን የተከሰስን ሲሆን ጥቂት የእምነት አጋሮቻችን ደግሞ በደረሰባቸው ድብደባ የተነሳ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው ስላልፈቀደላቸው ወጣት ሳሉ ታስረው የነበሩ ብዙዎች ከጊዜ በኋላ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ጭምር በተመሳሳይ ምክንያት ሲታሰሩ ተመልክተዋል።

ባለፉት በርካታ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች በማንኛውም አገር ወታደራዊ ጉዳይ ለመካፈል ሕሊናቸው እንደማይፈቅድላቸው በመግለጻቸው ምክንያት ከተፈጠሩ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ የመገናኛ ብዙሐን ያቀረቧቸው ዘገባዎች በጥቅሉ ሲታይ አዎንታዊ ነበሩ ማለት ይቻላል። የይሖዋ ምሥክር በመሆኑ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባልሆነ ወንድም ላይ ክስ መሥርቶ የነበረ አንድ የሕግ ባለሞያ፣ ላደረገው ነገር ይቅርታ በመጠየቅ የጻፈው ደብዳቤ በታወቀ መጽሔት ላይ ታትሞ ነበር።

በሌሎች በርካታ አገሮች በሕሊና ምክንያት በወታደራዊ ጉዳይ ያለመካፈል መብት እንደሚከበር ሁሉ በደቡብ ኮሪያም ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መብታችን እንደሚከበርልን ተስፋ አደርጋለሁ። “በሰላምና በጸጥታ እንድንኖር” የደቡብ ኮርያ ባለሥልጣናት፣ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት እንደ እኔ ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸውን ግለሰቦች እምነት ግምት ውስጥ እንዲያስገቡና እንደነዚህ ያሉት ወጣቶች መታሰራቸው እንዲቀር አዘውትሬ እጸልያለሁ።—1 ጢሞ. 2:1, 2

የአምላካችን የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ይሖዋ በእኛ ላይ ገዢ ለመሆን ያለውን መብት የመደገፍ አጋጣሚያችንን ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። (የሐዋርያት ሥራ 5:29) ለይሖዋ ታማኞች በመሆን የእሱን ልብ ለማስደሰት ከልባችን እንፈልጋለን። (ምሳሌ 27:11) ‘በፍጹም ልባቸው በይሖዋ ለመታመንና በራሳቸው ማስተዋል ላለመደገፍ’ ከመረጡት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል በመሆኔ ደስተኛ ነኝ።—ምሳሌ 3:5, 6

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የሚገርመው ነገር ባለ ሥልጣናቱ አላሰሩንም፤ እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለማወቅ እንደሚፈልጉ ገለጹልን”

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በኮሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኞች ባለመሆናቸው የተነሳ በእስር ቤት 26,000 ዓመታት አሳልፈዋል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1953 በወታደራዊ እስር ቤት ሳለሁ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1952 በጦርነቱ ወቅት ከዶን ስቲል ጋር ጉባኤዎችን ስንጎበኝ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1961 ከሠርጋችን በፊት

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተጓዥ የበላይ ተመልካቹ አስተርጓሚ ሆኜ አገለግል ነበር፣ 1956

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ ከኢን-ሂዩን ሰንግ ጋር