በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዕለት ተዕለት የመግባቢያ ቋንቋ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ

በዕለት ተዕለት የመግባቢያ ቋንቋ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ

በዕለት ተዕለት የመግባቢያ ቋንቋ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ

መጽሐፍ ቅዱስ ለሰው ልጆች የተሰጠ የአምላክ ቃል ነው ብለህ የምታምን ከሆነ አምላክ ለእኛ ሐሳቡን እየገለጸልን ነው ማለት ነው። . . . ሃይማኖትህ መላ ሕይወትህን የሚቆጣጠረው ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በዕለት ተዕለት የመግባቢያ ቋንቋ መዘጋጀት ይኖርበታል።” ይህ ሐሳብ አለን ደቲ የተባሉት ምሑር ካዘጋጁት ባይብል ትራንስሌሽንስ፦ ኤንድ ሃው ቱ ቹዝ ቢትዊን ዘም ከተባለው መጽሐፍ ላይ የተወሰደ ነው።

ለአምላክ ቃል ፍቅር ያላቸው ሰዎች በዚህ አባባል ሙሉ በሙሉ የሚስማሙ ከመሆኑም ሌላ “ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እንዲሁም ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ነገሮችን ለማቅናትና በጽድቅ ለመምከር ይጠቅማል” በሚለው ሐሳብም ከልብ ያምናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜ ያለፈበት ትርጉም የለሽ የሃይማኖት መጽሐፍ አይደለም። በዕለት ተዕለት ሕይወት ለሚያጋጥሙ ችግሮች ተጨባጭ መፍትሔ የሚሰጥ፣ ‘ሕያው የሆነና ኃይል ያለው’ መጽሐፍ ነው። (ዕብራውያን 4:12) ይሁንና አንባቢዎቹ ይህን ቅዱስ መጽሐፍ መረዳትና በተግባር ማዋል እንዲችሉ በዕለት ተዕለት የመግባቢያ ቋንቋ መዘጋጀት ይኖርበታል። በተለምዶ አዲስ ኪዳን ተብሎ የሚጠራው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልም ቢሆን የተጻፈው እንደ ፕላቶ የመሳሰሉ ፈላስፎች ይጠቀሙበት በነበረው የተራቀቀ ግሪክኛ ሳይሆን ኮይኔ ተብሎ በሚጠራውና የዕለት ተዕለት መግባቢያ በሆነው ተራ ግሪክኛ ነበር። አዎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ተራው ሕዝብ አንብቦ መረዳት በሚችልበት መንገድ ነው።

ለዚህም ሲባል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ዘመናዊ ትርጉሞች በተለያዩ ቋንቋዎች ተዘጋጅተዋል። ይህም በአብዛኛው በጣም ጠቃሚ ውጤት አስገኝቷል። አሁን ብዙ ሰዎች ቅዱሳን መጻሕፍትን በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይሁንና ከእነዚህ አዳዲስ ትርጉሞች መካከል አብዛኞቹ በትክክልና ወጥነት ባለው መንገድ በመተርጎም ረገድ የጎላ ድክመት ይታይባቸዋል፤ ይህም ሊሆን የቻለው ተርጓሚዎቹ የግል አመለካከታቸው ተጽዕኖ ስለሚያደርግባቸው ነው። ለምሳሌ አንዳንዶች ሙታን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ፣ የሰው ነፍስ ምን እንደሆነ እንዲሁም የእውነተኛውን አምላክ ስም በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ግልጽ ትምህርት ወደ መሰወር ያዘነብላሉ።

በመሆኑም ለአምላክ ቃል ፍቅር ያላቸው ሰዎች የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በአማርኛ ቋንቋ መውጣቱ አስደስቷቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ይህ ዘመናዊ ትርጉም መውጣቱን በመስከረም 23, 2001 (ጥቅምት 3, 2008) አሳውቀዋል። ተርጓሚዎቹ ሃይማኖታዊ ቀኖናዎች ተጽዕኖ ያላሳደሩባቸው በመሆናቸው የትርጉም ሥራው በትክክለኛነቱ ተወዳዳሪ የለውም፤ ከዚህም የተነሳ የጥንቶቹን ቋንቋዎች የማያውቁ ሰዎች ተሰውሮባቸው የነበረው ጥልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ግልጽ እንዲሆንላቸው አስችሏል። ሆኖም ‘ይህን ድንቅ የትርጉም ሥራ ያከናወነው ማን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

ለአምላክ ክብር የሰጡ ተርጓሚዎች

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ለአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች አዲስ ቢሆንም እንኳ መጽሐፉ ከ1950 ጀምሮ ጥቅም ላይ ውሏል። በዚያን ጊዜ መጽሐፉ የወጣው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሲሆን አዘጋጁም መጽሐፍ ቅዱስ በማሳተም ረጅም ታሪክ ያለው ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ማለትም ዋች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን ሁለት ክፍሎች “ብሉይ” እና “አዲስ” ኪዳን ብሎ መጥራት የተለመደ ነው፤ ለዚህ አዲስ ትርጉም የተሰጠው ስያሜ ይህን መጽሐፍ ልዩ ከሚያደርጉት በርካታ ገጽታዎች መካከል አንዱ ነው። የመስከረም 15, 1950 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ወጥቶ ነበር፦ “የትርጉም ኮሚቴው አባላት የነበሩት ሰዎች . . . ማንነታቸው እንዳይገለጽ በተለይ ደግሞ በሕይወት እያሉም ሆነ ከሞቱ በኋላ ስማቸው በጽሑፍ እንዳይወጣ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። የትርጉም ሥራው ዓላማ የእውነተኛውን ሕያው አምላክ ስም ከፍ ከፍ ማድረግ ነው።”

መላውን መጽሐፍ ቅዱስ ያካተተው አዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በአንድ ጥራዝ ታትሞ የወጣው በ1961 ነበር። የተርጓሚዎቹ ስም እስከ ዛሬ ድረስ አለመገለጹ የዓላማቸው ምንነት ወይም ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ያደሩ መሆናቸው ጥያቄ ውስጥ መግባት ይኖርበታል ማለት አይደለም። የ1984 እትም በመቅድሙ ላይ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ቅዱሳን መጻሕፍትን መተርጎም ማለት ይሖዋ አምላክ ያስተላለፈውን መልእክትና የተናገረውን ነገር በሌላ ቋንቋ ማስፈር ማለት ነው። . . . ቅዱሳን መጻሕፍትን ላስጻፈው አምላክ ፍርሃትና ፍቅር ያላቸው በዚህ የትርጉም ሥራ የተካፈሉ ሰዎች አምላክ የእሱን ሐሳብና መመሪያ በተቻለ መጠን በትክክል የማስተላለፍ ከባድ ኃላፊነት እንደጣለባቸው ይሰማቸዋል።”

የኮሚቴው አባላት መልካም ዓላማ ይዘው መነሳታቸው ምንም ጥያቄ የለውም፤ ሆኖም ይህን ሥራ ለማከናወን ያላቸውን ብቃት በተመለከተስ ምን ሊባል ይችላል? በትርጉም ሥራው ያልተደሰቱ አንዳንድ ምሑራን የተርጓሚዎቹ ስምና የትምህርት ደረጃ ባለመገለጹ የትርጉም ሥራው ልምድ በሌላቸው ሰዎች የተሠራ ስለሆነ ተቀባይነት ሊያገኝ አይገባውም ብለው ይከራከራሉ። ይሁንና እንዲህ ዓይነት ምክንያታዊነት የጎደለው አቋም ያላቸው ሁሉም ምሑራን አይደሉም። አለን ደቲ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የተረጎሙት ወይም ያሳተሙት ሰዎች እነማን መሆናቸውን ማወቃችን የትርጉም ሥራው ጥሩ ወይም መጥፎ መሆኑን ለመወሰን ይረዳናል? እንደዚያ ብሎ መደምደም አይቻልም። የእያንዳንዱን የትርጉም ሥራ ይዘት በቅርበት መመርመርን የመሰለ ነገር የለም።” *

በሺዎች የሚቆጠሩ አንባቢያንም ይህንኑ አድርገዋል። እስከዛሬ ድረስ የአዲስ ዓለም ትርጉም በሙሉ ወይም በከፊል በ68 ቋንቋዎች ከ151,000,000 በላይ በሚሆኑ ቅጂዎች በዓለም ዙሪያ ታትሟል። ይህን እትም ያነበቡ ብዙ ሰዎች የተገነዘቡት ነገር ምንድን ነው?

የአምላክን ስም የሚያስቀድስ ትርጉም

በማቴዎስ 6:9 ላይ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ ስምህ ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። ይሁንና አብዛኞቹ ትርጉሞች አምላክን የገለጹት “አምላክ” ወይም “ጌታ” በሚሉት የማዕረግ ስሞች ብቻ የሚጠራ ስም የለሽ አካል እንደሆነ አድርገው ነው። ይሁን እንጂ ጥንትም ቢሆን ሁኔታው እንዲህ ነበር ማለት አይደለም። በጥንቶቹ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ አምላክ፣ “ይሖዋ” በሚለው የግል ስሙ 7,000 ጊዜ ያህል በግልጽ ተለይቶ ተጠቅሷል። (ዘፀአት 3:15 NW፤ መዝሙር 83:18 NW) ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ግን አይሁዳውያን አጉል እምነት ካሳደረባቸው ፍርሃት የተነሳ መለኮታዊውን ስም መጥራት አቆሙ። የኢየሱስ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ይህ አጉል እምነት በክርስቲያን ጉባኤ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ አሳደረ። (ከሐዋርያት ሥራ 20:29, 30​ና ከ1 ጢሞቴዎስ 4:1 ጋር አወዳድር።) በግሪክኛ የተጻፉትን ቅዱሳን መጻሕፍት የገለበጡት ሰዎች ይሖዋ የሚለውን የአምላክ የግል ስም ኪሪዮስ እና ቴኦስ (“ጌታ” እና “አምላክ” ማለት ነው) በሚሉት የግሪክኛ ቃላት መተካት ጀመሩ።

ደስ የሚለው ነገር አዲስ ዓለም ትርጉም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት (“አዲስ ኪዳን”) ውስጥ ይሖዋ የሚለውን ስም ወደ ቦታው በመመለስ ድፍረት የሚጠይቅ እርምጃ ወስዷል። ይህ ስም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ 237 ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። ተርጓሚዎቹ ስሙን መልሰው ያስገቡት በስሜት ተነሳስተው ሳይሆን ጥልቅ ምርምር አድርገው ባገኟቸው አሳማኝ ምክንያቶች የተነሳ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ሉቃስ 4:18 በኢሳይያስ 61:1 ላይ የሚገኙትን ቃላት ይጠቅሳል። በዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፍ ላይ በኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ በሚገኘው በዚህ ጥቅስ ላይ ይሖዋ የሚለው ስም ይገኛል። * በመሆኑም በአዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ሉቃስ 4:18 “የይሖዋ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች ምሥራች እንዳውጅ ቀብቶኛል” ተብሎ መተርጎሙ የተገባ ነው።

በተጨማሪም እንዲህ ያለው አተረጓጎም አንባቢዎች ይሖዋ አምላክን፣ አንድያ ልጁ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ለይተው እንዲያውቁት ይረዳቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አብዛኞቹ ትርጉሞች ማቴዎስ 22:44ን “ጌታ ጌታዬን” እንደሚል አድርገው ተርጉመውታል። ሆኖም እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው ማን ነው? የሚናገረውስ ለማን ነው? እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ጥቅስ የተወሰደው ከመዝሙር 110:1 ሲሆን የዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፍ ደግሞ እዚህ ቦታ ላይ የአምላክን ስም ይጠቀማል። ስለዚህ አዲስ ዓለም ትርጉም ይህን ጥቅስ “ይሖዋ ጌታዬን፦ ‘ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ’ አለው” ሲል ተርጉሞታል። ቅዱሳን መጻሕፍት በይሖዋ አምላክና በልጁ መካከል ስላለው ልዩነት የሚገልጹትን ሐሳብ መረዳት ከፍተኛ ትምህርት አይጠይቅም። (ማርቆስ 13:32፤ ዮሐንስ 8:17, 18፤ 14:28) ይህ ጉዳይ ለአንድ ሰው መዳን ወሳኝ የሆነ ነገር ነው። የሐዋርያት ሥራ 2:21 “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ይላል።

ትክክለኛና ግልጽ

አዲስ ዓለም ትርጉም ሌሎች ለየት ያሉ ገጽታዎችም አሉት። ለዚህ የትርጉም ሥራ በዋነኝነት መሠረት ሆኖ እንዲያገለግል የተመረጠው ከፍተኛ ጥራት ባለው መንገድ የተዘጋጀው የዌስትኮት እና ሆርት የግሪክኛ ዋና ቅጂ ነው። የግሪክኛውን በኩረ ጽሑፍ ቀላልና ዘመናዊ በሆነ ቋንቋ፣ በተቻለ መጠን ቃል በቃልና በትክክል ለመተርጎም ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል። እንዲህ መደረጉ የበኩረ ጽሑፉን ለዛና ግልጽ የሆነ የአጻጻፍ ስልት እንዳለ ለማስተላለፍ ከማስቻሉም በተጨማሪ ቀደም ሲል ግልጽ ያልነበሩ ብዙ ነገሮችን ማስተዋል እንዲቻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች “ለበላይ ባለሥልጣናት” ወይም ለሰብዓዊ መንግሥታት እንዲገዙ ምክር የሰጠበትን ሮም 13:1ን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ብዙዎቹ ትርጉሞች እነዚህ መንግሥታት “በእግዚአብሔር የተሾሙ” እንደሆኑ ይገልጻሉ። (የ1954 ትርጉም፤ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) አንዳንድ ነገሥታት አምባገነናዊ አገዛዛቸውን ትክክለኛ እንደሆነ አድርገው ለማቅረብ እንዲህ ያሉ ትርጉሞችን ይጠቀማሉ። ሆኖም አዲስ ዓለም ትርጉም ይህን ጥቅስ “ያሉት ባለሥልጣናት አንጻራዊ ሥልጣናቸውን ያገኙት ከአምላክ ነው” በማለት ቃል በቃልና በትክክል ተርጉሞታል። * በመሆኑም አምላክ ራሱ የዚህን ዓለም ገዥዎች በቀጥታ ባይመርጥም እንዲህ ያሉ ሰዎች አንዳቸው በሌላው ላይ የተወሰነ ሥልጣን እንዲኖራቸው እንደሚፈቅድ መረዳት ተችሏል፤ ይሁንና ምንጊዜም ቢሆን ሥልጣናቸው ከእሱ ያነሰ ነው።

በተጨማሪም አዲስ ዓለም ትርጉም የግሪክኛዎቹ ግሶች በውስጣቸው የያዟቸውን ሰወር ያሉ ስሜቶችና ትርጉሞች ለማስተላለፍ ጥረት አድርጓል። በብዙ ዘመናዊ ቋንቋዎች ግሶች አንድ ድርጊት የተፈጸመበትን ጊዜ ይኸውም ያለፈ፣ የአሁን ወይም የወደፊት ጊዜን ለማመልከት በተለያየ የግስ እርባታ ይሠራባቸዋል። የግሪክኛ ቋንቋ ግሶች የድርጊቱን ዓይነት ይኸውም ጊዜያዊ፣ ያበቃ ወይም ቀጣይ መሆን አለመሆኑን ያመለክታሉ። በማቴዎስ 6:33 ላይ የሚገኙትን የኢየሱስ ቃላት ተመልከት። “መፈለግ” የሚል ትርጉም ያለው የግሪክኛው ግስ የአንድን ድርጊት ቀጣይነት የሚያመለክት ሐሳብ ይዟል። በመሆኑም ጥቅሱ “እንግዲያው ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ መፈለጋችሁን ቀጥሉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል” ተብሎ መተርጎሙ ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት ስሜትና መልእክት በተሟላ ሁኔታ ያስተላልፋል። በተመሳሳይም ማቴዎስ 7:7 “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል” ተብሎ ተተርጉሟል።—በተጨማሪም ሮም 1:32ን፣ 6:2ንና ገላትያ 5:15ን ተመልከት።

አዲስ ዓለም ትርጉም ቁልፍ የሆኑ ቃላትን ወጥና ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ለመተርጎም ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ለምሳሌ ያህል፣ ፕስሂ የሚለው የግሪክኛ ቃል በሁሉም ቦታዎች ላይ “ነፍስ” ተብሎ ተተርጉሟል። ከዚህም የተነሳ አንባቢያን የተለያዩ ሃይማኖቶች ከሚያስተምሩት ትምህርት በተለየ ሁኔታ ነፍስ ሟች መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይችላሉ። ነፍስ ሊጠፋና ሊሞት የሚችል ነገር ነው።—ማቴዎስ 2:20፤ ማርቆስ 3:4፤ ሉቃስ 6:9፤ 17:33

የአምላክ ቃል ለሰዎች ሁሉ እንዲዳረስ ማድረግ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በአማርኛ መውጣቱ የሥራው የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው። በጊዜ ሂደት መላውን መጽሐፍ ቅዱስ ለመተርጎም እቅድ ተይዟል። ይሁንና አንባቢዎች የአማርኛው ትርጉም እንደ እንግሊዝኛው ሁሉ ትክክለኛና ወጥነት ባለው መንገድ የተተረጎመ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን ይችላሉ?

አዎ፣ ይችላሉ። ይህ ሊሆን የቻለው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል የትርጉም ሥራውን በቅርብ ይከታተል ስለነበረ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ሌሎች ቋንቋዎች የመተርጎሙ ሥራ በቡድን መከናወኑ የተሻለ ውጤት እንደሚኖረው ስለታመነበት በዚህ መንገድ እንዲሠራ ተወስኗል። በመሆኑም በዓለም ዙሪያ በበርካታ አገሮች ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ቡድኖች እንዲቋቋሙ ተደርጓል። እነዚህ ቡድኖች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት፣ የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች ለመመለስና በተለያዩ ቋንቋዎች የሚዘጋጁ የአዲስ ዓለም ትርጉም እትሞች ተመሳሳይ እንዲሆኑ ለማድረግ በብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ዋና መሥሪያ ቤት የትርጉም አገልግሎት ተብሎ የሚጠራ ቢሮ ተቋቁሟል። ከዚህም በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎችን ለማገዝ በጣም ጠቃሚ የሆነ የኮምፒውተር ፕሮግራም ተዘጋጅቷል። ያም ሆኖ ግን የትርጉም ሥራው የሚከናወነው በተርጓሚዎቹ ከፍተኛ ጥረት እንደሆነ መዘንጋት የለብንም። ሆኖም ሥራው በኮምፒውተር የሚታገዝ መሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ቡድኖች ከፊታቸው የተቀመጠውን ትልቅ ግብ ለማሳካት ይኸውም አዲስ ዓለም ትርጉምን ልክ እንደ እንግሊዝኛው ትክክለኛና ወጥ በሆነ መንገድ ለመተርጎም እንዲችሉ ሥራቸውን በእጅጉ አቅልሎላቸዋል። የኮምፒውተር ፕሮግራሙ ካሉት ገጽታዎች መካከል አንዱ፣ እያንዳንዱ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃል በእንግሊዝኛው እትም ላይ ምን ተብሎ እንደተተረጎመ ለመመልከት የሚያስችል ሲሆን ይህም ተርጓሚዎችን በቋንቋቸው አቻ ቃላት ለመምረጥ በጣም ይረዳቸዋል።

ይህ ዝግጅት ስኬታማ መሆኑን ከተገኘው ውጤት በቀላሉ ማየት ይቻላል። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉምን እንድትመረምር እናበረታታሃለን። ይህን ትርጉም ከዚህ መጽሔት አዘጋጆች ማግኘት ትችላለህ። ይህ ትርጉም ያካተታቸውን ለየት ያሉ በርካታ ገጽታዎች ጠቃሚ ሆነው ታገኛቸዋለህ፤ ጽሑፉ ግልጽና ቁልጭ ባለ መንገድ የተጻፈ መሆኑ ለማንበብ ይጋብዛል፤ ከዚህም በላይ የታወቁ ጥቅሶችን በፍጥነት ለማውጣት የሚረዱ በገጾቹ አናት ላይ የሚገኙ ጠቋሚ ሐሳቦችን፣ የተለያዩ ቦታዎችን የሚያሳዩ ካርታዎችንና ትኩረት የሚስቡ ተጨማሪ መረጃዎችንም የያዘ ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይህን መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብ መጽሐፉ አምላክ ራሱ የተናገራቸውን ቃላት በዕለት ተዕለት የመግባቢያ ቋንቋ በትክክል እንደሚያስተላልፍ ሙሉ በሙሉ መተማመን ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.9 በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ባለማጣቀሻው ኒው አሜሪካን ስታንዳርድ ባይብል (1971) በሽፋኑ ላይ ያሰፈረው የሚከተለው ሐሳብ ልብ ሊባል የሚገባው ነው፦ “የአምላክ ቃል ሊመዘን የሚገባው መጽሐፉ ራሱ ባሉት መልካም ነገሮች እንደሆነ ስለምናምን የማንንም ምሑር ስም ለማስረጃነት በመጥቀስ ትርጉሙ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ አልሞከርንም።”

^ አን.13 በተለምዶ አዲስ ኪዳን ተብሎ በሚጠራው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ለሚገኙት ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ለተወሰዱት ጥቅሶች እንደ መሠረት ሆኖ ያገለገለው ግሪክኛው የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም መሆኑ አይካድም። በኋላ በተዘጋጁት የሰብዓ ሊቃናት ቅጂዎች ላይ መለኮታዊው ስም ስለማይገኝ ብዙ ምሑራን ስሙ ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥም መውጣት አለበት ብለው ይከራከራሉ። ሆኖም ከመጥፋት በተረፉት ጥንታዊ የሰብዓ ሊቃናት ቅጂዎች ላይ ይሖዋ የሚለው ስም በዕብራይስጥ ፊደላት ተጽፎ ይገኛል። ይህም የይሖዋን ስም በግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ለመመለስ የሚያስችል ጠንካራ ማስረጃ ነው።

^ አን.17 በጂ አበት-ስሚዝ የተዘጋጀውን ኤ ማንዋል ግሪክ ሌክሲከን ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት እንዲሁም በሊደል እና ስኮት የተዘጋጀውን ኤ ግሪክ-ኢንግሊሽ ሌክሲከን ተመልከት። እነዚህና ሌሎች ተአማኒነት ያላቸው ምንጮች እንደሚያመለክቱት የግሪክኛው ቃል “ሥርዓት ማስያዝ፣ በቦታ ቦታው ማስቀመጥ” የሚል ቀጥተኛ ትርጉም አለው።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የጻፉት በዕለት ተዕለት የመግባቢያ ቋንቋ ነው

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአዲስ ዓለም ትርጉም አንዳንድ ገጽታዎች፦

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ4ኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተዘጋጀው ኮዴክስ ሳይናይቲከስ ላይ የሚገኘው 1 ጢሞቴዎስ 3:16

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የግሪክኛውን በኩረ ጽሑፍ ቀላልና ዘመናዊ በሆነ ቋንቋ፣ በተቻለ መጠን ቃል በቃልና በትክክል ለመተርጎም ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቁልጭ ባለ መንገድ የተጻፈ መሆኑ ለማንበብ ይጋብዛል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በገጾቹ አናት ላይ የሚገኙ ጠቋሚ ሐሳቦች የታወቁ ጥቅሶችን በቀላሉ ለማውጣት ይረዳሉ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ካርታዎቹ አንባቢዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱ መልክዓ ምድሮችን በተመለከተ ያላቸው ግንዛቤ እንዲጨምር ያደርጋሉ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“አዲስ ዓለም ትርጉም” ግልጽ በሆነ መንገድ መተርጎሙ ለክርስቲያናዊ አገልግሎት ከፍተኛ ጥቅም ያበረክታል