በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ የተወለደው መቼ ነበር?

ኢየሱስ የተወለደው መቼ ነበር?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ኢየሱስ የተወለደው መቼ ነበር?

“ክርስቶስ የተወለደበት ትክክለኛ ቀን አይታወቅም” በማለት ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ኧርሊ ክርስቺያኒቲ ይናገራል። ያም ሆኖ በምድር ዙሪያ የሚገኙ ክርስቲያን ነን የሚሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ታኅሣሥ 25 ላይ የኢየሱስን ልደት ያከብራሉ። * ይሁን እንጂ ይህ ቀን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። በእርግጥ ኢየሱስ የተወለደው በታኅሣሥ ወር ነበር?

ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የተወለደበትን ትክክለኛ ቀን ለይቶ ባይጠቅስም በታኅሣሥ እንዳልተወለደ የሚያሳይ ማስረጃ ይዟል። በተጨማሪም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ የሚገኙ ማስረጃዎችን ስንመረምር የኢየሱስን ልደት ለማክበር ታኅሣሥ 25 የተመረጠው ለምን እንደሆነ መረዳት እንችላለን።

የተወለደው በታኅሣሥ ሊሆን የማይችለው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ የተወለደው በይሁዳ ውስጥ በምትገኘው የቤተልሔም ከተማ ነው። የሉቃስ ወንጌል “በዚያው አገር በሌሊት መንጋቸውን ሲጠብቁ በሜዳ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ” ይላል። (ሉቃስ 2:4-8) እረኞች መንጎቻቸውን እየጠበቁ በሜዳ ላይ ማደራቸው ያልተለመደ ነገር አልነበረም። ዴይሊ ላይፍ ኢን ዘ ታይም ኦቭ ጂሰስ የተሰኘው መጽሐፍ “መንጎች በአብዛኛው የዓመቱ ክፍል በሜዳ ያድሩ ነበር” ይላል። ይሁን እንጂ እረኞች በጣም በሚበርደው የታኅሣሥ ወር መንጎቻቸውን ይዘው ሌሊቱን ከቤት ውጪ ሊያድሩ ይችላሉ? ይኸው መጽሐፍ በመቀጠል እንዲህ ብሏል፦ “መንጋዎቹ ክረምቱን የሚያሳልፉት በጉሮኗቸው ውስጥ ሆነው ነበር። እረኞች መንጋቸውን ሲጠብቁ በሜዳ ማደራቸውን ከሚናገረው የወንጌል ዘገባ አንጻር ሲታይ የገና በዓል ቅዝቃዜ በሚበረታባቸው ወራት መከበሩ ራሱ ቀኑ ፈጽሞ ትክክል እንዳልሆነ ያስገነዝባል።”

በሉቃስ ወንጌል ውስጥ የሚገኝ አንድ ዘገባ ይህን ሐሳብ ያጠናክርልናል፦ “በዚያን ዘመን፣ የዓለሙ ሁሉ ሕዝብ እንዲቈጠርና እንዲመዘገብ ከአውግስጦስ ቄሳር ትእዛዝ ወጣ። ይህም ቄሬኔዎስ የሶርያ ገዢ በነበረበት ጊዜ የተደረገ የመጀመሪያው የሕዝብ ቈጠራ ነበር። ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ለመመዝገብ ወደየራሱ ከተማ ሄደ።”—ሉቃስ 2:1-3

አውግስጦስ የሕዝብ ቆጠራ እንዲደረግ ያዘዘው ከግብር አከፋፈልና ከወታደራዊ ምልመላ ጋር በተያያዘ ጠቃሚ መረጃ ለማሰባሰብ ሳይሆን አይቀርም። ማርያም የመውለጃዋ ጊዜ ቢቃረብም በዓዋጁ መሠረት ከባሏ ከዮሴፍ ጋር በመሆን ከናዝሬት 150 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ወደ ቤተልሔም ተጓዘች። እስቲ አስበው፣ ከአካባቢው አስተዳደር ጋር ላለመጋጨት ይጠነቀቅ እንደነበረ የሚነገርለት አውግስጦስ፣ በሮማውያን ገዢዎቻቸው ላይ ለማመፅ በቋፍ ላይ የነበሩትን የአይሁድ ሕዝብ በክረምት እንዲህ ዓይነቱን ረዥም ጉዞ እንዲያደርጉ ያዝዛል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው?

አብዛኞቹ ታሪክ ጸሐፊዎችና የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን ታኅሣሥ 25ን የኢየሱስ የልደት ቀን አድርገው እንደማይቀበሉት ልብ ሊባል ይገባል። ማንኛውንም ኢንሳይክሎፒዲያ ብታነብ እንዲህ ዓይነቱን መረጃ እንደምታገኝ ጥርጥር የለውም። አወር ሰንዴይ ቪዚተርስ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ “ኢየሱስ የተወለደው ታኅሣሥ 25 እንዳልሆነ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል” ይላል።

ታኅሣሥ 25 የተመረጠበት ምክንያት

ኢየሱስ ከሞተ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ የልደቱን ቀን ለማክበር ታኅሣሥ 25 ተመረጠ። ለምን? በአሁኑ ጊዜ ገና የሚከበርበት ሰሞን ጥንት አረማዊ በዓላት የሚከበሩበት ወቅት እንደነበረ በርካታ ታሪክ ጸሐፊዎች ያምናሉ።

ለምሳሌ ያህል፣ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ብሏል፦ “ስለዚህ በዓል አጀማመር በሠፊው ተሠራጭቶ የሚገኘው ማብራሪያ፣ ታኅሣሥ 25 በሮማ ግዛት ውስጥ የፀሐይን እንደገና መታየት፣ የክረምቱን መውጣት እንዲሁም ፀደይና በጋ መግባቱን የሚያበስር ምልክት ነው ተብሎ ይከበር የነበረውን ዳይስ ሶሊስ ኢንቪክቲ ናቲ (‘ድል የማትነሳው ፀሐይ የልደት ቀን’) የሚባለውን ተወዳጅ በዓል የክርስቲያን በዓል ለማስመሰል የተደረገ ጥረት መሆኑን ያሳያል።”

ዚ ኢንሳይክሎፒድያ አሜሪካና እንደሚከተለው በማለት ይነግረናል፦ “ታኅሣሥ 25 የገና በዓል የሚከበርበት ቀን ሆኖ የተወሰነበት ምክንያት ግልጽ ባይሆንም ይህ ቀን የተመረጠው የቀኑ መርዘምና የክረምቱ ወራት ማለቅ በሚጀምርበት ጊዜ ከሚከበረው ‘የፀሐይ ዳግመኛ ልደት’ ጋር እንዲጋጠም ታስቦ እንደሆነ ይገመታል። . . . የሮማውያን የሳተርናልያም (የእርሻ አምላክ ለሆነው ለሳተርን እና ኃይሏን አድሳ ለምትመጣው ለፀሐይ ክብር ሲባል የሚከበረው በዓል) የሚከበረው በዚሁ ጊዜ ነበር።” አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቶቹን በዓላት የሚያከብሩ ሰዎች ልቅ የሆኑ የብልግና ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ሲሆን ገደብ የለሽና መረን የለቀቀ ባሕርይ ይታይባቸው ነበር። እንዲህ ዓይነቱ ባሕርይ በዛሬው ጊዜ በሚከበሩት በብዙዎቹ የገና በዓል ሥነ ሥርዓቶች ላይ ይታያል።

ክርስቶስን ማክበር የሚገባን በምን መንገድ ነው?

ክርስቶስ የተወለደበት ትክክለኛ ቀን ባይታወቅም አንዳንድ ሰዎች ክርስቲያኖች የኢየሱስን ልደት ማክበር እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች በዓሉ ክብር ባለው መንገድ እስከተከበረ ድረስ ለክርስቶስ ክብር ማምጣት የሚቻልበት አንዱ መንገድ እንደሆነ ያስባሉ።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የኢየሱስ መወለድ በእርግጥም ዓቢይ ክስተት እንደሆነ ተገልጿል። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በተወለደበት ዕለት በጣም ብዙ መላእክት በድንገት ተገልጠው “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም፣ ሰላምም እርሱ ለሚወዳቸው ሰዎች በምድር ይሁን!” ብለው አምላክን በደስታ እንዳወደሱት ይናገራል። (ሉቃስ 2:13, 14) ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የኢየሱስ ልደት መከበር እንዳለበት የሚጠቁም አንድም ፍንጭ አለመኖሩ ሊስተዋል ይገባል። በአንጻሩ ግን የይሖዋ ምሥክሮች በየዓመቱ እንደሚያደርጉት ሞቱን እንድናከብር የተሰጠ ግልጽ ትእዛዝ አለ። (ሉቃስ 22:19) ኢየሱስን ማክበር የሚቻልበት አንዱ መንገድ ይህ ነው።

ኢየሱስ ሰው ሆኖ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ “የማዛችሁን ብትፈጽሙ ወዳጆቼ ናችሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 15:14) በተጨማሪም “ብትወዱኝ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 14:15) በግልጽ ለማየት እንደምንችለው የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርቶች ከመማርና ተግባራዊ ከማድረግ የበለጠ እሱን ማክበር የሚቻልበት መንገድ የለም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 በአንዳንድ የኦርቶዶክስ አገሮች የኢየሱስ ልደት የሚከበረው ጥር 7 (በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ታኅሣሥ 29) ነው። የኢየሱስ ልደት በሚከበርበት ዕለት ላይ ልዩነት ሊፈጠር የቻለው እንዲህ ባሉ አገሮች ውስጥ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በዓሎቿን ለማክበር የጎርጎርዮስን አቆጣጠር ሳይሆን የጁሊያንን የቀን መቁጠሪያ ስለምትጠቀም ነው። በመሆኑም በጎርጎርዮስ አቆጣጠር ጥር 7 ማለት በጁልየስ አቆጣጠር ታኅሣሥ 25 ማለት ነው። በዚህም ምክንያት በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረበው ማብራሪያ ለጥር 7ም (እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ለታኅሣሥ 29) ይሠራል።

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ ኢየሱስ የተወለደው በታኅሣሥ ሊሆን የማይችለው ለምንድን ነው?—ሉቃስ 2:1-8

▪ ከአንድ ሰው የልደት ቀን ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምንድን ነው?—መክብብ 7:1

▪ ኢየሱስን ማክበር የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምንድን ነው?—ዮሐንስ 14:15

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በታኅሣሥ እንዳልተወለደ የሚያሳይ ማስረጃ ይዟል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በበረዶ ወራት እረኞች መንጎቻቸውን ይዘው ከቤት ውጪ ሊያድሩ ይችላሉ?

[ምንጭ]

Todd Bolen/Bible Places.com