ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
▪ በጀርመን፣ የገና ዋዜማ በጣም ጠቃሚ የሆነ ሃይማኖታዊ ገጽታ እንዳለው የሚቆጥሩት ከጠቅላላው ሕዝብ ውስጥ 8 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። በ1980 ይህ አኃዝ 47 በመቶ ነበር። —ቲቪ ኒውስ ቻነል ኤን24, ጀርመን
▪ “በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ100 ጎልማሳ አሜሪካውያን መካከል ከአንድ በላይ የሚሆን ሰው እሥር ቤት ውስጥ ይገኛል። . . . በመላ አገሪቱ በእስር ቤት ያለው ሕዝብ ብዛት 1.6 ሚሊዮን ገደማ ነው።”—ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ዩ ኤስ ኤ
▪ አንድ ጥናት እንዳመለከተው “ጥናቱ የተካሄደባቸው ስፔናውያን በሙሉ” በሰውነታቸው ውስጥ “ቢያንስ አንድ ዓይነት ፀረ ተባይ ኬሚካል” የተገኘባቸው ሲሆን እነዚህ ኬሚካሎች “በዓለም አቀፍ ደረጃ ለጤና ጎጂ ናቸው ተብለው የተፈረጁ ንጥረ ነገሮች” ናቸው።—የግራናዳ ዩኒቨርሲቲ፣ ስፔን
▪ “መረጃ ሊገኝ በቻለባቸው አገሮች እንደታየው ከትንባሆ ቀረጥ የሚገኘው ገቢ ትንባሆን ለመቆጣጠር ከሚውለው የገንዘብ መጠን ከ500 ጊዜ በላይ ይበልጣል።”—የዓለም ጤና ድርጅት፣ ስዊዘርላንድ
▪ በተከታዮች ብዛት የእስልምና ሃይማኖት፣ የሮማ ካቶሊክ ሃይማኖትን በልጧል። በ2006 የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ብዛት ከጠቅላላው የዓለም ሕዝብ ውስጥ 19.2 በመቶ የነበረ ሲሆን የሮማ ካቶሊክ ሃይማኖት ተከታዮች ብዛት ደግሞ 17.4 በመቶ ነበር።—ሮይተርስ የዜና አገልግሎት፣ ብሪታንያ
ሸራ መርከብ ለመንዳት ይረዳል
የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ በሄደበትና የአካባቢ መበከል አሳሳቢ እየሆነ በመጣበት በአሁኑ ጊዜ የመርከብ ባለቤቶች የነዳጅ ፍጆታንና የሚፈጠረውን ጭስ መቀነስ የሚቻልበትን መንገድ እያፈላለጉ ናቸው። ለዚህም ሲባል የድሮ አጋራቸው የሆነውን ነፋስን እየተጠቀሙ ነው። ቀደም ሲልም ጠቃሚነቱ ተፈትኖ የታየው አንድ አማራጭ መርከቡን ለመንዳት እንዲረዳቸው ሸራ መጠቀም እንደሆነ ፍራንክፈርተር አልጌማይነ ጻይቱንግ የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል። ሸራው አየር ላይ 300 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን ካፒቴኑ ነፋሱን በመቆጣጠር የመርከቡን ሞተር ኃይል እንዲቀንስ ያስችለዋል። በቅርቡ 160 ካሬ ሜትር የሆነ ሸራ አንድ የጭነት መርከብ የአትላንቲክ ውቅያኖስን ለማቋረጥ የሚያስችል ኃይል እንዲያገኝ ረድቷል።
ከድርቅ በሕይወት መትረፍ
“አንድ የአፍሪካ ዝንብ በዕጭነቱ ወቅት ከባድ ድርቅ ሲከሰት ይደርቅና ልክ እንደ ከረሜላ ጠጣር ሆኖ የድርቁን ዘመን ያሳልፋል” በማለት ሳይንስ ኒውስ ይናገራል። ፖሊፔዲለም ቫንደርፕላንኪ የተሰኘው የዚህ ዝንብ ዕጭ በሰውነቱ ውስጥ ያለው ፈሳሽ ሲያልቅ በፈሳሹ ምትክ ቀልጦ የደረቀ ስኳር የሚመስል መስታወት መሳይ ንጥረ ነገር ያዘጋጃል። ዕጩ ደረቅ ሆኖ በሚቆይበት ወቅት በውስጡ ይካሄድ የነበረው ምግብን ወደ ኃይል የመለወጥ ሂደት ሙሉ በሙሉ ይቆማል። ዕጩ እንደገና እንዲያንሰራራ የሚያስችለውን ዝናብ እስኪያገኝ ድረስ ለ17 ዓመታት ያህል “ያለምንም እንቅስቃሴ” በዚህ ሁኔታ ሊቆይ ይችላል።
ለሥነ ፈለክ ጥናት የሚመች ሥፍራ
አንድ ዓለም አቀፍ ቡድን ከባሕር ወለል በላይ 4,000 ሜትር ከፍታ ባለው በምሥራቅ አንታርክቲክ አምባ ላይ የመጨረሻው ከፍተኛ ቦታ በሆነው ዶም አርገስ በሚባለው ሥፍራ ላይ ሙሉ በሙሉ በሮቦት የሚሠራ የሥነ ፈለክ ምርምር ጣቢያ አቋቁሟል። ከደቡብ ዋልታ 1,000 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘው ይህ ሥፍራ በጣም ቀዝቃዛና አንዳንድ ጊዜም ከመጠን በላይ ጨለማ ነው። ሥፍራው በጣም ደረቅ ከመሆኑም ሌላ ጸጥ ያለ አየርና ለአራት ወራት የሚዘልቅ የሌሊት ወቅት አለው። ዶም አርገስ በምድር ላይ ካሉት ሥፍራዎች ሁሉ ይበልጥ ለሥነ ፈለክ ምርምር አመቺ እንደሆነ ይነገርለታል። የቻይና የአንታርክቲክ የሥነ ፈለክ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ሊፋን ዋንግ እዚህ ሥፍራ ባለ ቴሌስኮፕ አማካኝነት “ወደ ሕዋ ቴሌስኮፕ ማምጠቅ ከሚጠይቀው ወጪ በእጅጉ ባነሰ ዋጋ ሕዋ ላይ ሆኖ ከሚነሳው ጋር የሚወዳደር ጥራት ያለው ምስል ማግኘት ይቻላል” ሲሉ ተናግረዋል።