በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጓደኛዬን ስህተት መናገር ይኖርብኛል?

የጓደኛዬን ስህተት መናገር ይኖርብኛል?

የወጣቶች ጥያቄ

የጓደኛዬን ስህተት መናገር ይኖርብኛል?

“ሁኔታው በጣም ከብዶኝ ነበር። ልጁ ጥሩ ጓደኛዬ ነበር።”—ጄምስ *

“መጀመሪያ ላይ ሁኔታዎቹ በጣም የሚያስጨንቁ ነበሩ። ጓደኞቼ ያደረጉትን ነገር ስለተናገርኩባቸው ሊያቀርቡኝ አልፈለጉም ነበር።”—አን

መጽሐፍ ቅዱስ “ከወንድም አብልጦ የሚቀርብ ጓደኛ አለ” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 18:24) እንዲህ ዓይነት ጓደኛ አለህ? ከሆነ አንድ ውድ ነገር አለህ ማለት ነው።

ይሁን እንጂ ክርስቲያን የሆነ አንድ ጓደኛህ ስህተት ቢሠራ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ለምሳሌ የጾታ ብልግና ቢፈጽም፣ ሲጋራ ቢያጨስ፣ ቢሰክር፣ አደንዛዥ ዕፅ ቢወስድ ወይም ሌላ ዓይነት ከባድ ስህተት ቢፈጽም ምን ታደርጋለህ? (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:9, 10) ያደረገውን ነገር እንዳወቅክበት ለራሱ ትነግረዋለህ? ለወላጆችህ ትነግራቸዋለህ? ለጓደኛህ ወላጆች ትናገራለህ? ወይስ ስለ ጉዳዩ ለአንድ የጉባኤ ሽማግሌ ትናገራለህ? * የሠራውን ስህተት ብትናገርበት ጓደኝነታችሁ ምን የሚሆን ይመስልሃል? ዝም ማለቱ የተሻለ ይሆን?

ልናገር ወይስ አልናገር?

ስህተት የማይሠራ ሰው የለም። መጽሐፍ ቅዱስም “ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” ይላል። (ሮሜ 3:23) ይሁንና አንዳንዶች ከባድ ኃጢአቶችን ይፈጽማሉ። ሌሎች ደግሞ ማስተካከያ ካላደረጉ ለተጨማሪ ችግር ሊዳርጋቸው የሚችል “የተሳሳተ እርምጃ” ይወስዳሉ። (ገላትያ 6:1 NW) እስቲ ቀጥሎ የቀረበውን እውነተኛ የሕይወት ታሪክ እንደ ምሳሌ ተመልከት።

ሱዛን የተባለች አንዲት ወጣት እንደ እሷው ክርስቲያን የሆነች ጓደኛዋ የጾታ ስሜት የሚቀሰቅሱ ፎቶዎችንና በብልግና ግጥሞች የተሞሉ ሙዚቃዎችን የያዘ ድረ ገጽ እንዳላት አወቀች።

እስቲ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ እኔ በሱዛን ቦታ ብሆን ኖሮ ምን አደርግ ነበር? አንድ ነገር አደርግ ነበር? ወይስ ጓደኛዬ በድረ ገጿ ውስጥ ያስቀመጠችው ነገር ራሷን እንጂ ሌላ ማንንም አይመለከትም ብዬ አስብ ነበር? ሱዛን ምክር ለመጠየቅ ወደ እኔ ብትመጣ ኖሮ ምን እላት ነበር?

․․․․․

ሱዛን ምን አደረገች? ሱዛን በጉዳዩ ላይ ካሰበችበት በኋላ ለጓደኛዋ ወላጆች ለመናገር ወሰነች። እንዲህ ብላለች፦ “ከወላጆቿ ጋርም በጣም ስለምንቀራረብ ሁኔታውን ለእነሱ ለመግለጽ ፈርቼ ነበር። መናገሩ በጣም ከብዶኝ ስለነበር ማልቀስ ጀመርኩ።”

ምን ይመስልሃል? ሱዛን ያደረገችው ነገር ትክክል ነው? ወይስ ዝም ብትል ይሻል ነበር?

በጉዳዩ ላይ እንድታስብበት የሚረዱ አንዳንድ ነጥቦች ቀጥሎ ቀርበዋል፦

እውነተኛ ጓደኛ ምን ማድረግ አለበት? ምሳሌ 17:17 “[እውነተኛ፣ NW] ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል” በማለት ይናገራል። አንድ ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ አካሄድ ሲከተል ግለሰቡ አወቀውም አላወቀው ‘ክፉ ቀን’ ውስጥ ገብቷል ወይም ችግር ላይ ወድቋል። ትናንሽ ነገሮችን አክብዶ በማየት “እጅግ ጻድቅ” መሆን ስህተት ቢሆንም እውነተኛ ጓደኛ ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ድርጊቶችን አይቶ እንዳላየ አይሆንም። (መክብብ 7:16) ሁኔታውን በቸልታ ማለፍ ፈጽሞ ተገቢ አይደለም።—ዘሌዋውያን 5:1

ወላጅ የሆንከው አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ይሰማህ ነበር? እስቲ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ወላጅ ብሆንና ልጄ የጾታ ስሜት የሚቀሰቅሱ ነገሮችን በድረ ገጹ ውስጥ ያስቀመጠ ቢሆን ስለ ሁኔታው ቢነገረኝ ደስ ይለኝ ነበር? ልጄ እያደረገ ያለውን ነገር የሚያውቅ ጓደኛ ቢኖረውና ይህ ጓደኛው ስለ ጉዳዩ ሳይነግረኝ ቢቀር ምን ይሰማኝ ነበር?’

የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መከተል አይኖርብህም? ይህ ወቅት ዝም የምትልበት ጊዜ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሠፈሩትን የአምላክ የሥነ ምግባር ሕጎች በጥብቅ መከተል ይኖርብሃል። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ትክክል ለሆነው ነገር አቋም ስትወስድ የፈጣሪህን ልብ ደስ ታሰኛለህ። (ምሳሌ 27:11) በተጨማሪም ለጓደኛህ የተሻለ ነገር እንዳደረግህለት ስለምታውቅ አንተም ጥሩ ስሜት ይኖርሃል።—ሕዝቅኤል 33:8

ለመናገር ጊዜ አለው’

መጽሐፍ ቅዱስ “ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:7) ብዙውን ጊዜ ትናንሽ ልጆች ከአንድ ሁኔታ ጋር በተያያዘ መወሰድ ያለበት ተገቢ የሆነ እርምጃ የትኛው እንደሆነ አያውቁም። አንድ ጓደኛቸው መጥፎ ነገር ሲያደርግ የሚያሳስባቸው ‘ጓደኛዬ ችግር እንዲደርስበት አልፈልግም’ ወይም ‘ከጓደኛዬ ጋር መጣላት አልፈልግም’ የሚለው ነው። ከግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው እነዚህ ነገሮች ብቻ ቢሆኑ ኖሮ “ዝም ለማለት” መምረጥ ያስኬድ ይሆናል።

ሆኖም እያደግህ ስትሄድ እንዲህ ያሉትን ጉዳዮች ብስለት በታከለበት መንገድ መመልከት ትጀምራለህ። ጓደኛህ ችግር ላይ እንደወደቀና እርዳታ እንደሚያስፈልገው ትገነዘባለህ፤ ምናልባትም እርዳታውን የሚያገኘው በአንተ አማካኝነት ይሆናል። ይሁን እንጂ ጓደኛህ የመጽሐፍ ቅዱስን ሕጎች ወይም መሠረታዊ ሥርዓቶች እንደጣሰ ብትሰማ ምን ማድረግ ትችላለህ?

በመጀመሪያ፣ የሰማኸው ነገር እውነት መሆኑን አጣራ። ምናልባትም ተራ አሉባልታ ይሆናል። (ምሳሌ 14:15) በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ ካቲ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ጓደኛዬ ስለ እኔ ውሸት ማውራት ጀመረች፤ የምቀርባቸው ሰዎች ደግሞ እሷ የተናገረችው ነገር እውነት እንደሆነ ተሰማቸው። ከአሁን በኋላ ማንም አያምነኝም የሚል ፍርሃት ነበረኝ!” መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ትንቢት ሲናገር “ጆሮውም እንደ ሰማ አይበይንም” ወይም ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን እንደተረጎመው “አሉባልታ አይሰማም” ይላል። (ኢሳይያስ 11:3) ከዚህ ምን ትምህርት ታገኛለህ? የሰማኸው ነገር ሁሉ እውነት ነው ብለህ ለመደምደም አትቸኩል። ሐቁን ለማወቅ ጥረት አድርግ። እስቲ ቀጥሎ የቀረበውን እውነተኛ የሕይወት ታሪክ ተመልከት።

በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰው ጄምስ የቅርብ ጓደኛው በአንድ ፓርቲ ላይ አደንዛዥ ዕፅ እንደወሰደ ሰማ።

እስቲ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ እኔ በጄምስ ቦታ ብሆን ኖሮ ምን አደርግ ነበር? የሰማሁት ነገር እውነት መሆን አለመሆኑን እንዴት ማረጋገጥ እችላለሁ?

․․․․․

ጄምስ ምን አደረገ? መጀመሪያ ላይ፣ ጄምስ ምንም እንዳልሰማና የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ለማስመሰል ሞክሮ ነበር። ጄምስ እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “ውሎ አድሮ ግን ሕሊናዬ እረፍት ይነሳኝ ጀመር። ስለ ጉዳዩ ጓደኛዬን ማናገር እንዳለብኝ አውቃለሁ።”

ምን ይመስልሃል? ክርስቲያናዊ ያልሆነ ድርጊት ፈጽሟል የተባለውን ሰው በቅድሚያ ቀርቦ ማነጋገሩ ምን ጥቅም ሊኖረው ይችላል?

․․․․․

ስለ ጉዳዩ ግለሰቡን ቀርበህ ማነጋገሩ ከከበደህ ማድረግ የምትችለው ሌላ ነገር ይኖር ይሆን?

․․․․․

የጄምስ ጓደኛ በፓርቲው ላይ አደንዛዥ ዕፅ መውሰዱን አመነ። ይሁንና ለማንም እንዳይናገርበት ጄምስን ለመነው። ጄምስ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ፈልጓል። ይሁን እንጂ ጓደኛውም ቢሆን ትክክል የሆነውን ነገር እንዲያደርግ ይፈልጋል። ስለዚህ ጉዳዩን በጉባኤው ላሉ ሽማግሌዎች እንዲናገር የአንድ ሳምንት ጊዜ እንደሚሰጠው ለጓደኛው ነገረው። እንዲህ የማያደርግ ከሆነ ግን ጄምስ ራሱ ለሽማግሌዎች እንደሚናገር ገለጸለት።

․․․․․

ጄምስ ያደረገው ነገር ትክክል ይመስልሃል? ‘አዎ’ ካልክ ለምን? ‘አይ፣ አይመስለኝም’ ካልክ ደግሞ ምክንያትህ ምንድን ነው?

․․․․․

የጄምስ ጓደኛ ጉዳዩን ለሽማግሌዎቹ ስላልተናገረ ጄምስ ራሱ ነገራቸው። ጓደኛው ድርጊቱ ስህተት መሆኑን ከጊዜ በኋላ ተገነዘበ። ሽማግሌዎቹ ንስሐ የመግባትንና ከይሖዋ ጋር የነበረውን ጥሩ ዝምድና መልሶ የማግኘትን አስፈላጊነት እንዲገነዘብ ረዱት።

አሳባቂ መሆንህ ነው?

ይሁን እንጂ ‘ጓደኛዬ የሠራውን ስህተት ብናገርበት ማሳበቅ አይሆንብኝም? ምንም እንደማያውቅ ሰው ብሆን አይሻልም?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ከሆንክ ምን ማድረግ ትችላለህ?

በመጀመሪያ ደረጃ፣ ለማድረግ ቀላል የሆነ ነገር ሁልጊዜ ፍቅር ይንጸባረቅበታል ማለት እንዳልሆነና ፍቅር የሚንጸባረቅበትን ነገር ማድረግ ደግሞ ሁልጊዜ ቀላል ሊሆን እንደማይችል ተረዳ። የጓደኛን መጥፎ ተግባር መናገር ድፍረት ይጠይቃል። ጉዳዩን አስመልክተህ ለምን ወደ ይሖዋ አትጸልይም? የሚያስፈልግህን ጥበብና ድፍረት እንዲሰጥህ ከጠየቅከው እንደሚረዳህ እርግጠኛ ሁን።—ፊልጵስዩስ 4:6

በሁለተኛ ደረጃ፣ የፈጸመውን መጥፎ ተግባር ለሽማግሌዎች መናገርህ ለጓደኛህ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝለት አስብ። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፦ ከጓደኛህ ጋር ቀጥ ያለ ድንጋያማ አቀበት እየወጣችሁ ነው እንበል። ጓደኛህ ያልሆነ ቦታ ላይ ረገጠና ተንሸራትቶ ወደቀ። ጓደኛህ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ በመውደቁ ሃፍረት ተሰምቶት አቀበቱን ራሱ ለመውጣት ጥረት እንደሚያደርግ ቢነግርህስ? በዚህ ሁኔታ ሕይወቱን አደጋ ላይ እንዲጥል ትፈቅድለታለህ?

አንድ ጓደኛ ከክርስቲያናዊ ጎዳና ሲደናቀፍም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ግለሰቡ ያለ ማንም እርዳታ በመንፈሳዊ ማገገም እንደሚችል ይሰማው ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ የሞኝነት አስተሳሰብ ነው። እውነት ነው፣ ጓደኛህ ባደረገው ነገር በተወሰነ መጠን ሃፍረት ይሰማው ይሆናል። ይሁን እንጂ ጓደኛህ እርዳታ እንዲያገኝ ‘የድረሱልኝ ጥሪ’ ማሰማትህ ሕይወቱን ሊያተርፍለት ይችላል።—ያዕቆብ 5:15

ስለዚህ ጓደኛህ መጥፎ ድርጊት ቢፈጽም ከመናገር ወደኋላ አትበል። በዚህ መንገድ ጓደኛህ የሚያስፈልገውን እርዳታ እንዲያገኝ የምታደርግ ከሆነ ለይሖዋ አምላክ ብቻ ሳይሆን ለጓደኛህም ጭምር ታማኝ መሆንህን እያሳየህ ነው፤ ጓደኛህ ላደረግህለት ፍቅራዊ እርዳታ አንድ ቀን ያመሰግንህ ይሆናል።

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.6 በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች ከባድ ኃጢአት ለፈጸመ ለማንኛውም ክርስቲያን መንፈሳዊ እርዳታ ይሰጣሉ።—ያዕቆብ 5:14-16

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ የጓደኛህን መጥፎ ተግባር መናገርህ ለእሱ ታማኝ መሆንህን የሚያሳየው እንዴት ነው?

▪ ለጓደኛቸው ታማኝ የመሆን ፈተና ያጋጠማቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎችን ማስታወስ ትችላለህ? ከእነሱ ምን ልትማር ትችላለህ?

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጓደኛህ ከክርስቲያናዊ ጎዳና ከተደናቀፈ እርዳታ እንዲያገኝ ማድረግ ያስፈልግሃል