ሕይወት የሚያስገኝ ውኃ
ሕይወት የሚያስገኝ ውኃ
ኢየሱስ ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን በምትገኘው በሰማርያ በኩል እየተጓዘ ነበር። በጣም ደክሞትና ውኃ ጠምቶት ነበር። በአንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠና አንዲትን ሳምራዊት ሴት ውኃ እንድትሰጠው ጠየቃት። ይህች ሴት አንድ አይሁዳዊ ሰው ውኃ እንድትሰጠው መጠየቁ በጣም አስገረማት፤ ምክንያቱም በመጀመሪያው መቶ ዘመን በአይሁዳውያንና በሳምራውያን መካከል ጥላቻ ነበር።
በሁኔታው ግራ የተጋባችው ይህች ሴት ኢየሱስን “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ ሳለ እኔን ሳምራዊቷን ሴት እንዴት የምጠጣው ውኃ ስጪኝ ትለኛለህ?” በማለት ጠየቀችው።
ኢየሱስም እንዲህ በማለት መለሰላት፦ “የአምላክን ነፃ ስጦታ ብታውቂና ‘የምጠጣው ውኃ ስጪኝ’ የሚልሽ ማን መሆኑን ብትረጂ ኖሮ አንቺ ራስሽ ትጠይቂው ነበር፤ እሱም ሕያው ውኃ ይሰጥሽ ነበር።”
በተጨማሪም ኢየሱስ እንዲህ አላት፦ “ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማል። እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ፈጽሞ አይጠማም፤ ከዚህ ይልቅ እኔ የምሰጠው ውኃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ የውኃ ምንጭ ይሆናል።”—ዮሐንስ 4:1-15
እዚህ ላይ ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው ስለ ምን ዓይነት ውኃ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈጣሪ የሆነውን ይሖዋ አምላክን “ሕያው የውሃ ምንጭ” በማለት ይጠራዋል። (ኤርምያስ 2:13) ሕይወት የአምላክ ስጦታ ሲሆን በሕይወት ለመቀጠል ከእሱ የምናገኘውን ውኃ በሚገባ መጠጣት አለብን። ይህ ደግሞ ለሥጋዊ አካላችን የሚያስፈልገውን ውኃ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ የሆነውን ውኃ መጠጣትን ይጨምራል።
መንፈሳዊ መመሪያ የአሁኑን ያህል አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ የለም። በእርግጥም፣ ምድራችን በመንፈሳዊ ድርቅ ተጠቅታለች ሊባል ይችላል። ሰዎች ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ይጓጓሉ፦ ሙታን የት ናቸው? ከእነሱ ጋር ዳግመኛ የመገናኘት ተስፋ አለን? አምላክ መከራና ሥቃይ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? ጦርነት፣ ወንጀል፣ ረሃብና በሽታ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? የይሖዋ ምሥክሮች፣ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው “ውኃ” ወይም እውነት ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ እንደሚሰጥ ያምናሉ።
ኢየሱስ ሳምራዊቷን ሴት በውኃ ጉድጓድ አጠገብ ባነጋገራት ራእይ 22:17
ወቅት የጠቀሰው ከአምላክ ቃል የሚገኘውን ሕይወት ሰጪ የሆነ የእውነት ውኃ ነው። የይሖዋ ምሥክሮችም የጠራውን የእውነት ውኃ እንድትጠጣ ይጋብዙሃል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የመጨረሻው መጽሐፍ ይህን ግብዣ እንዲህ በማለት ገልጾታል፦ “የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግ ሁሉ የሕይወትን ውኃ በነፃ ይውሰድ።”—የአምላክ መንግሥት ለሰው ልጆች በረከት የሚያመጣው እንዴት እንደሆነ ይበልጥ ለማወቅ የምትፈልግ ከሆነ በአካባቢህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን ማነጋገር ወይም በዚህ መጽሔት ገጽ 5 ላይ ከሚገኙት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው መጻፍ ትችላለህ። በተጨማሪም www.watchtower.org የተባለውን ድረ ገጽ መመልከት ትችላለህ።
[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሃይማኖት የሰው ልጆችን ጥም ማርካት ችሏል?
አንድ ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን ስለሄደ ወይም ሃይማኖተኛ ነኝ ስላለ ብቻ አርኪ የሆነውን የእውነት ውኃ ማግኘት አይችልም። እንዲያውም በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ ሃይማኖቶች የሰውን ልጅ ችግሮች ከመፍታት ይልቅ እንዲባባሱ አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በጦርነት ወቅት ካቶሊኮች ካቶሊኮችን፣ ፕሮቴስታንቶች ደግሞ ፕሮቴስታንቶችን ገድለዋል፤ በሁለቱም ጎራ የተሰለፉ ሰዎች አምላክ ድል እንዲሰጣቸው ይለምኑ ነበር!
ከዚህም በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸሙ ቅሌቶችን በተመለከተ በርካታ ዘገባዎች ይወጣሉ፤ ቀሳውስት የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉ ከመሆኑም ሌላ ልጆችን ያስነውራሉ። በእርግጥም አብዛኞቹ ሃይማኖቶች ምእመናኖቻቸውን የሚያጠጡት የተበከለ ውኃ ነው። (ራእይ 17:4-6፤ 18:1-5) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሁኔታ በቲቶ 1:16 ላይ ሲገልጽ “አምላክን እንደሚያውቁ በይፋ ይናገራሉ፤ ሆኖም በሥራቸው ይክዱታል” ይላል። በአብዛኛው ሲታይ መንፈሳዊ ድርቅ በተስፋፋበት በዚህ ዘመን ሃይማኖት የሰውን ልጅ ጥም ለማርካት ምንም ያደረገው ነገር የለም ሊባል ይችላል።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው 19 ምዕራፎችና 224 ገጾች ያሉት መጽሐፍ እንደሚከተሉት ላሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ ይዟል፦
“አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?”
“ሙታን የት ናቸው?”
“የምንኖረው ‘በመጨረሻው ዘመን’ ውስጥ ነው?”
“አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው?”
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ ‘የእውነትን ውኃ’ ማግኘት ትችላለህ