ስንፈልገው የነበረውን ነገር አገኘን
ስንፈልገው የነበረውን ነገር አገኘን
በርት ቶልማን እንደተናገረው
የብለድ ጎሳ ተወላጅ ስሆን በልጅነቴ ስላሳለፍኩት ሕይወት ሳስብ ልቤ በደስታ ይሞላል፤ የብለድ ጎሳ በአልበርታ፣ ካናዳ ውስጥ የሚገኘው የብላክፉት ብሔር አንዱ ክፍል ነው። የምንኖረው ካናዳ ውስጥ በሚገኙት ዐለታማ የሆኑ ተራሮች አካባቢ ሲሆን በአቅራቢያችንም ሉዊዝ የተባለ ደስ የሚል ሐይቅ አለ።
በቤተሰባችን ውስጥ ሰባት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆች ነበርን። እኔም ሆንኩ ወንድሞቼና እህቶቼ አብዛኛውን ጊዜያችንን የምናሳልፈው አያታችን ቤት ነበር። አያታችን ጠንካራ ሠራተኛ የነበረች ሲሆን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የብላክፉት ሕዝቦች ባሕል ታስተምረን ነበር። የጫካ ቤሪዎችን መልቀም፣ ባሕላዊ ምግቦችን ማዘጋጀትና አትክልቶችን መትከል ተምረናል። ወንድ አያቴና አባቴ ለአደን እንዲሁም ዓሣ ለማጥመድ ሲወጡ ይዘውኝ ይሄዱ ነበር። አጋዘን የሚመስሉ የተለያዩ እንስሳትን በማደን ለምግብነት የምንጠቀምባቸው ሲሆን ቆዳቸውንም ለተለያየ ዓላማ እናውለው ነበር። ወላጆቻችን ትጉህ ሠራተኞች የነበሩ ከመሆኑም ሌላ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማቅረብ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጉ ነበር። የብለድ ሕዝቦች በሚኖሩበት አካባቢ ያሳለፍኩት ሕይወት በእርግጥም በጣም አስደሳች ነው።
ይሁንና አያቴ በ1963 ስትሞት ነገሮች ሁሉ ተለዋወጡ። በወቅቱ የአምስት ዓመት ልጅ ስለነበርኩ በተፈጠረው ሁኔታ ግራ ተጋባሁ። የምሰማው ነገር ሁሉ ምንም ሊያጽናናኝ አልቻለም። በዚያ ዕድሜዬ እንኳ ‘ፈጣሪ ካለ ታዲያ የት አለ? ሰዎች የሚሞቱት ለምንድን ነው?’ እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎቹ ስለሚያበሳጩኝ እነጫነጭ ነበር። ወላጆቼ ምን ሆኜ እንደሆነ ሲጠይቁኝ ትንሽ እንዳመመኝ እነግራቸዋለሁ።
ከነጮች ጋር የነበረን ግንኙነት
አያቴ ከመሞቷ በፊት ከነጮች ጋር እምብዛም አንቀራረብም ነበር። ነጮቹን ባየናቸው ቁጥር “እዩት ደግሞ ይሄን ክፉ፣ ስግብግብ፣ ርኅራኄ የሌለው። እነዚህ እኮ ሰው አይደሉም” እንደሚሉት ያሉ ሐሳቦች ሲሰነዘርባቸው እሰማ ነበር። ከነጮች መካከል ጥሩ ሰው የሚባሉት በጣት የሚቆጠሩ እንደሆኑና እነሱም ቢሆኑ ሊታመኑ እንደማይችሉ ይነገረኝ ነበር። ስለ እነዚህ ሰዎች ለማወቅ ጉጉት ቢኖረኝም በአካባቢያችን የነበሩት ነጮች አብዛኛውን ጊዜ ያፌዙብንና ያንቋሽሹን ስለነበር እነሱን ለመቅረብ አልደፈርኩም።
አያቴ ከሞተች በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወላጆቼ ከልክ በላይ የአልኮል መጠጥ መጠጣት ጀመሩ፤ ይህ ጊዜ በሕይወቴ በጣም ካዘንኩባቸው ወቅቶች አንዱ ነው። የስምንት ዓመት ልጅ ሳለሁ የሞርሞን እምነት ተከታይ የሆኑ ሁለት ሰዎች ቤታችን መምጣት ጀመሩ። ሲታዩ ጥሩ ሰዎች ይመስላሉ። እነዚህ ሰዎች ነጮች፣ የብለድ ጎሳ ተወላጅ የሆኑ ልጆችን በጉዲፈቻ የማሳደግ እቅድ እንዳላቸው ለወላጆቼ የነገሯቸው ሲሆን እነሱም በሐሳቡ ተስማሙ። እንደገባኝ ከሆነ እቅዳቸው በአካባቢያችን የሚገኙት ልጆች ከነጮች ጋር አብረው እንዲኖሩ በማድረግ አመለካከታቸውን መቀየር ነበር። ወላጆቼ ከሌላ ቤተሰብ ጋር መኖሬ የተሻለ እንደሚሆን የተሰማቸው በወቅቱ በቤተሰባችን ውስጥ ያለው ሁኔታ ጥሩ ስላልነበር እንደሆነ ተገነዘብኩ። ወላጆቼ ነጮች ሊታመኑ እንደማይችሉ ሲናገሩ እሰማ ስለነበር በሐሳቡ መስማማታቸው ያስደነገጠኝ ከመሆኑም በላይ አበሳጨኝ። ከወላጆቼ ላለመለየት ስል ማምለጫ መንገድ መፈለግ ጀመርኩ። በመጨረሻ ግን ወላጆቼ፣ ታላቅ ወንድሜ አብሮኝ እንደሚሆን ሲነግሩኝ ለመሄድ ተስማማሁ።
ይሁን እንጂ የወሰዱን ሰዎች በብሪትሽ ኮሎምቢያ ወደምትገኘው ቫንኩቨር ከተማ ስንደርስ ከወንድሜ ጋር ለያዩንና
እኔን 100 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ወደሚገኝ አካባቢ ይዘውኝ ሄዱ። በዚህ ጊዜ ሁሉ ነገር ጨለመብኝ! የተቀበለኝ ቤተሰብ ጥሩ ቢሆንም አጠቃላይ ሁኔታው ደስ የማይል ስለነበር ፈራሁ። ከአሥር ወር ገደማ በኋላ ወደ ቤተሰቦቼ ተመለስኩ።ከወላጆቼ ጋር አብሬ መኖር ጀመርኩ
በቤተሰባችን ውስጥ የነበረው ሁኔታ ያን ያህል ባይለወጥም ተመልሼ መምጣቴ ግን አስደሰተኝ። የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ ወላጆቼ አልኮል መጠጣታቸውን አቆሙ። ይህ ትልቅ እፎይታ ያስገኘ ቢሆንም እኔ ግን አደንዛዥ ዕፅ መውሰድና አልኮል መጠጣት በመጀመሬ ሕይወቴ ተበላሽቶ ነበር። ወላጆቼ ያልተገሩ ፈረሶችንና ወይፈኖችን የመጋለብ ትርዒት እንደማሳየት ባሉ እንቅስቃሴዎች እንድካፈል ያበረታቱኝ ነበር፤ ይህን ስፖርት ደግሞ በጣም እወደዋለሁ። እንዲህ ያለውን ትርዒት ማሳየት ከፍተኛ ድፍረት ይጠይቃል። በወይፈኑ ሆድ ላይ የታሰረውን ገመድ በአንድ እጅ ብቻ በመያዝ፣ ከሚዘለው ወይፈን ላይ ሳልወድቅ ቢያንስ ለስምንት ሴኮንድ መጋለብ ችዬ ነበር።
በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለሁ በአካባቢያችን የሚገኙ የጎሳ ሽማግሌዎች ከጥንት ጀምሮ ብሔሩ ይከተለው ስለነበረው ሃይማኖት ያስተምሩኝ ነበር። ‘ለነጮች ሃይማኖት’ ንቀት ስለነበረኝ የሃይማኖት አባቶቹ ያስተማሩኝ ነገር ትኩረቴን በእጅጉ ሳበው። የብላክፉት ባሕል፣ ሰዎች በበርካታ “የክርስትና” ሃይማኖቶች ውስጥ የማይታየውን የደግነትና የፍትሕ ባሕርይ እንዲያንጸባርቁ ያበረታታል የሚል አስተሳሰብ ነበረኝ። የብላክፉት ብሔር ተወላጅ የሆኑ ቤተሰቦችና ጓደኛሞች እርስ በርስ የሚቀራረቡና ተጫዋች በመሆናቸው ከእነሱ ጋር ስሆን ደስ ይለኛል።
በዚህ ጊዜ፣ በአካባቢያችን ያሉት ሰዎች ለዘመናት ኢፍትሐዊ የሆነ ድርጊት ሲፈጸምባቸው እንደኖረም ሰማሁ። ነጮች በሕዝቡ መካከል በሽታ እንዳዛመቱና በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ከፍተኛ አገልግሎት ይሰጡን የነበሩትን ጎሾች እንዳጠፉ አወቅሁ። የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሠራዊት አባል የሆኑት ኮሎኔል ሪቻርድ ኧርቪንግ ዶጅ “በተቻላችሁ መጠን ሁሉንም ጎሾች አጥፏቸው፤ ጎሾቹን ገደላችሁ ማለት [የአሜሪካ] ሕንዶችን አጠፋችሁ ማለት ነው” እንዳሉ ይነገራል። ይህ አባባል የብላክፉት ሕዝቦች ቅስማቸው እንዲሰበርና ተስፋ ቢስ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ማድረጉን ተረዳሁ።
ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ከሃይማኖት መሪዎች ጋር በመተባበር ኋላ ቀር እንደሆኑ አድርገው የሚመለከቷቸውን የአካባቢውን ሕዝቦች ከነጮች ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩ በማድረግ እነሱን ለመለወጥ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ባለ ሥልጣናቱም ሆኑ የሃይማኖት መሪዎቹ የአካባቢው ሕዝቦች ባሕላቸውን፣ እምነታቸውን፣ ባሕርያቸውንና ቋንቋቸውን ጨምሮ ሁሉ ነገራቸውን በመለወጥ የነጮችን የአኗኗር መንገድ መከተል እንደሚያስፈልጋቸው ይሰማቸው ነበር። በካናዳ በሚገኙ ሃይማኖታዊ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በሚማሩ የብለድ ጎሳ ተወላጅ የሆኑ አንዳንድ ልጆች ላይ በደል ተፈጽሞባቸዋል። ሌሎች ደግሞ አደንዛዥ ዕፅ ይወስዱ፣ ከመጠን በላይ የአልኮል መጠጥ ይጠጡና በዓመጽ ድርጊቶች ይካፈሉ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ራሳቸውን ያጠፉም ነበሩ። እንዲህ ያሉ ችግሮች የብለድ ጎሳ ተወላጆች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች አሁንም ድረስ ይስተዋላሉ።
አንዳንዶች ከሚደርስባቸው ጫና ለማምለጥ ሲሉ የብላክፉትን ባሕል ለመተው ወስነዋል። እነዚህ ሰዎች ከልጆቻቸው ጋር ሲነጋገሩ ከብላክፉት ቋንቋ ይልቅ በእንግሊዝኛ ለመጠቀም የመረጡ ሲሆን የነጮችን አንዳንድ ባሕሎች ለመከተልም ሞክረዋል። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ይህ ድርጊታቸው ተቀባይነት እንዲያገኙ ከማድረግ ይልቅ በአንዳንድ ነጮች አልፎ ተርፎም በብላክፉት ተወላጆች ዘንድ እንዲሾፍባቸው አድርጓቸዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች እነዚህን ሰዎች፣ መልካቸው ሲታይ ቀይ ድርጊታቸው ግን እንደ ነጮች ስለሆነ “አፕል ሕንዳውያን” በማለት ይጠሯቸው ነበር።
የብላክፉት ሕዝቦች በብዙ መንገድ ሥቃይ ሲደርስባቸው ማየት በእርግጥም የሚያሳዝን ነው። በአካባቢያችንም ሆነ በካናዳና በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ የብላክፉት ሕዝቦች የተሻለ ነገር እንዲያገኙ እመኛለሁ።
ለጥያቄዎቼ መልስ ለማግኘት እጓጓ ነበር
በነጮች ዘንድ ፈጽሞ ተቀባይነት እንደማላገኝ አስብ ስለነበር በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ እያለሁ ይሰማኝ የነበረው የበታችነት ስሜት ብዙውን ጊዜ ቶሎ እንድቆጣና እንድበሳጭ ያደርገኝ ነበር። እንዲያውም ለነጮች ከፍተኛ ጥላቻ እያደረብኝ መጣ። ይሁንና ወላጆቼም ሆኑ አክስቴ የጥላቻና የበቀል ስሜት በውስጤ ማሳደር እንደሌለብኝ ይነግሩኝ ነበር። ከዚህ በተቃራኒ ይቅር ባይና አፍቃሪ እንድሆን እንዲሁም ሰዎች በጭፍን ቢጠሉኝም ችላ ብዬ እንዳልፋቸው ያበረታቱኝ ነበር። እነዚህ ምክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር የሚስማሙ እንደሆኑ ከጊዜ በኋላ ተማርኩ። ያም ሆኖ ከልጅነቴ ጀምሮ ያስጨንቁኝ ለነበሩት ጥያቄዎች መልስ የማግኘት ከፍተኛ ጉጉት ነበረኝ። በተጨማሪም ‘የተፈጠርነው
ለምንድን ነው? የፍትሕ መጓደል የማይወገደውስ ለምንድን ነው?’ በማለት መጠየቅ ጀመርኩ። የሰው ልጅ የተፈጠረው ለአጭር ጊዜ ብቻ ኖሮ እንዲሞት ነው የሚለው ሐሳብ ምክንያታዊ መስሎ አልታየኝም። በመሆኑም ግራ ተጋባሁ።የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችን ሲመጡ በር እንድከፍትላቸው የምታዘዘው እኔ ነበርኩ። ለሰዎች ጭፍን ጥላቻ ስለሌላቸው ምንጊዜም ቢሆን ለእነሱ አክብሮት ነበረኝ። ጥያቄዎቼን በጥሩ ሁኔታ አቀናብሬ የመግለጽ ችግር ቢኖርብኝም ጥሩ ውይይት እናደርግ ነበር። ጆን ብሩስተር እና ሃሪ ካለሁ ከተባሉ የብላክፉት ተወላጅ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያደረግነውን ውይይት መቼም አልረሳውም። በሣር በተሸፈነው ሜዳ ላይ እየተንሸራሸርን ረጅም ውይይት አደረግን። የይሖዋ ምሥክሮቹ አንድ መጽሐፍ የሰጡኝ ሲሆን ግማሹን ያህል እንዳነበብኩት የት እንደገባ ጠፋብኝ።
የግልቢያ ትርዒት ማሳየት ጀመርኩ
በአካባቢያችን የሚገኙ አረጋውያን ምክር እንዲሰጡኝ ጠይቄ ነበር። የሰጡኝን ጠቃሚ ምክር ባደንቅም ሕይወትን አስመልክቶ ለነበሩኝ ጥያቄዎች ግን አጥጋቢ መልስ አላገኘሁም። አሥራ ስድስት ዓመት ገደማ ሲሆነኝ ከቤት የወጣሁ ሲሆን መላ ሕይወቴም በግልቢያ ውድድሮች ላይ ብቻ ያተኮረ ሆነ። የግልቢያ ውድድር ከተካሄደ በኋላ በሚኖሩት ግብዣዎች ላይ እገኝ ነበር፤ በእነዚህ ዝግጅቶች ላይ ከልክ በላይ አልኮል መጠጣትና አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ የተለመደ ነው። እያደረግኩት ያለሁት ነገር ስህተት እንደሆነና አምላክም እንደማይደሰትበት ስለሚሰማኝ ሕሊናዬ ይወቅሰኝ ነበር። ትክክለኛ የሆነውን ነገር ማድረግና ለሚያስጨንቁኝ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት እንድችል እንዲረዳኝ አዘውትሬ ወደ ፈጣሪ እጸልይ ነበር።
በ1978 በካልገሪ እያለሁ ሮዝ ከተባለች ወጣት ጋር ተዋወቅሁ። ሮዝ በእናቷ ብላክፉት በአባቷ ደግሞ ክሪ ነች። አመለካከታችን ተመሳሳይ ስለነበረ ከእሷ ጋር በግልጽና በነፃነት መግባባት ችዬ ነበር። ከሮዝ ጋር ተዋደድንና በ1979 ተጋባን። ከጊዜ በኋላ ካርማ የተባለች ሴት ልጅና ጄረድ የተባለ ወንድ ልጅ ወለድን። ሮዝ ጥሩ ረዳት የሆነችልኝ ከመሆኑም ሌላ ለትዳሯ ታማኝና አሳቢ እናት ነች። ከቤተሰቤ ጋር ሆኜ ታላቅ ወንድሜን ለመጠየቅ በሄድኩበት ወቅት በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ * የተባለ መጽሐፍ አገኘሁ። መጽሐፉ ትኩረቴን የሳበው ሲሆን በውስጡ ያሉት ሐሳቦችም ምክንያታዊ እንደሆኑ ተሰማኝ። መጽሐፉን በማነብበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት እየተረዳሁ መጣሁ፤ ይሁንና የሆነ ቦታ ላይ ስደርስ መጽሐፉ የተወሰኑ ገጾች እንደጎደሉት አወቅሁ። እኔና ሮዝ የጎደሉትን ገጾች ለማግኘት ያላደረግነው ነገር የለም፤ ይሁን እንጂ ሊሳካልን አልቻለም። አምላክ እንዲረዳኝ መጸለዬን ግን አላቋረጥኩም።
ወደ አንድ ቄስ ሄድን
በ1984 የጸደይ ወቅት ሮዝ ሦስተኛ ልጃችንን የወለደች ሲሆን ይህችን ቆንጆ ልጅ ኬለ ብለን ጠራናት። ይሁን እንጂ ኬለ ከሁለት ወር በኋላ በልብ በሽታ ሞተች። በልጃችን ሞት ቅስማችን የተሰበረ ሲሆን ሮዝን እንዴት ማጽናናት እንዳለብኝም ግራ ገብቶኝ ነበር። ሮዝ ማጽናኛና ለጥያቄዎቻችን መልስ ለማግኘት በአካባቢያችን ወደሚገኙ አንድ የካቶሊክ ቄስ አብሬያት እንድሄድ አግባባችኝ።
ቄሱን ልጃችን ለምን እንደሞተችና ወዴት እንደሄደች ጠየቅናቸው። እሳቸውም አምላክ፣ ኬለን የወሰዳት ተጨማሪ መልአክ ስላስፈለገው እንደሆነ ነገሩን። ‘አምላክ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ ከሆነ መልአክ እንድትሆን ልጃችንን መውሰድ ለምን አስፈለገው? ደግሞስ ይህቺ ጨቅላ ሕፃን ምን ትጠቅመዋለች?’ ብዬ አሰብኩ። ቄሱ ከእኛ ጋር ሲነጋገሩ አንዴም መጽሐፍ ቅዱስ ገልጠው አላነበቡልንም። እኛም ምንም ሳንጽናና ወደ ቤታችን ተመለስን።
ከጸሎት ትልቅ እርዳታ አግኝተናል
በኅዳር ወር 1984 መገባደጃ አካባቢ ሰኞ ቀን ጠዋት ላይ ወደ አምላክ ረጅም ጸሎት በማቅረብ ጥሩ ሰው እንድሆን፣ ችግሮች የሚደርሱበትን ምክንያት እንድረዳና የሕይወትን ዓላማ እንዳውቅ እንዲረዳኝ ተማጸንኩት። በዚያኑ ቀን ጠዋት፣ ዳያና ቤሌሚ እና ኬረን ስኮት የተባሉ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች በራችንን አንኳኩ። ቅንና ደግ የነበሩት እነዚህ ሴቶች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለእኛ ለማካፈል ጉጉት ነበራቸው። መልእክታቸውን ያዳመጥኩ ሲሆን እነሱም መጽሐፍ ቅዱስና በሕይወት ተርፎ ወደ አዲስ ምድር መግባት * የተባለውን መጽሐፍ ሰጡኝ፤ እንዲሁም ዳያና እና ባለቤቷ ዴረል በዚያው ሳምንት ተመልሰው መጥተው እንዲያነጋግሩኝ ፈቃደኛ መሆኔን ገለጽኩ።
የእነዚህ ሰዎች መምጣት የጸሎቴ መልስ እንደሆነ ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀብኝም። በጣም ከመደሰቴ የተነሳ ሮዝ ከሥራ ተመልሳ ስለ ሁኔታው እስክነግራት ድረስ ስላላስቻለኝ ተንቆራጠጥኩ። የሚገርመው ሮዝ ሰዎቹ ከመምጣታቸው በፊት በነበረው ምሽት ላይ እውነተኛውን ሃይማኖት ማግኘት እንድትችል እንዲረዳት ወደ አምላክ ጸልያ እንደነበር ነገረችኝ። በዚያው ሳምንት አርብ ቀን ሁለታችንም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርን። ኬረንና ዳያና በመጀመሪያ ቤታችን በመጡበት ዕለት የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለማድረስ ያሰቡት ለሌሎች ቤቶች እንደነበረና ሆኖም ቦታው ስለጠፋባቸው
ዝም ብለው ከሚሄዱ የእኛን ቤት እንዳንኳኩ ከጊዜ በኋላ አወቅን።በመጨረሻ ለጥያቄዎቼ መልስ አገኘሁ!
ቤተሰቦቻችንና ወዳጆቻችን መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ስንጀምር ግራ የተጋቡ ሲሆን ለእኛም ጥሩ አመለካከት አልነበራቸውም። በመሆኑም ሕይወታችንን እያበላሸነው እንዳለ እንዲሁም ያለንን ተሰጥኦና ችሎታ በሚገባ እንዳልተጠቀምንበት በመናገር ጥናታችንን እንድንተው ጫና ያደርጉብን ነበር። ሆኖም ለአዲሱ ወዳጃችን ማለትም ለፈጣሪያችን ለይሖዋ ጀርባችንን ላለመስጠት ቆርጠን ነበር። በተጨማሪም ውድ የሆኑ ነገሮችን ይኸውም የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ድንቅ እውነቶችና ቅዱስ ሚስጥሮች ማወቅ ችለን ነበር። (ማቴዎስ 13:52) በታኅሣሥ ወር 1985 እኔና ሮዝ ተጠምቀን የይሖዋ ምሥክሮች ሆንን። ዘመዶቻችን ከተጠመቅን በኋላ በሕይወታችን ውስጥ ያደረግናቸውን አንዳንድ ለውጦች ስለተመለከቱ በአሁኑ ጊዜ ለይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ አክብሮት አላቸው።
አዎን፣ ስፈልገው የነበረውን ነገር አግኝቻለሁ! መጽሐፍ ቅዱስ አስፈላጊ ለሆኑ ጥያቄዎች ቀላልና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መልስ ይሰጣል። የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ፣ ለምን እንደምንሞት እንዲሁም ከልጃችን ከኬለ ጋር በድጋሚ ተገናኝተን ፍጹም በሆነ ዓለም ውስጥ አብረን እንደምንኖር አምላክ ቃል መግባቱን ማወቄ አስደስቶኛል። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 21:4) በተጨማሪም ሰውነታችንን ማርከስ እንደሌለብን፣ ለሕይወት አክብሮት ማሳየት እንዳለብንና የፉክክር መንፈስ ማስወገድ እንደሚኖርብን ከጊዜ በኋላ ተማርኩ። (ገላትያ 5:26) ምንም እንኳ ለመወሰን አስቸጋሪ ቢሆንም አምላክን ለማስደሰት ስል በግልቢያ ውድድር መካፈሌን አቆምኩ።
በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች አንድ ጉጉት ቤታቸው ላይ ካረፈች አሊያም አንድ ውሻ የሚያላዝን ከሆነ ከቤተሰባቸው አባላት መካከል አንዱ እንደሚሞት ይገልጻሉ። ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ማግኘታችን ብዙዎችን አንቆ ከያዘው ይህን ከመሰለው አጉል እምነት ነፃ አውጥቶናል። ሕይወት ባላቸው ፍጥረታትም ሆነ ሕይወት በሌላቸው ነገሮች ውስጥ አሉ የሚባሉት በዓይን የማይታዩ መናፍስት ጉዳት ያደርሱብናል ብለን አንፈራም። (መዝሙር 56:4፤ ዮሐንስ 8:32) በአሁኑ ጊዜ፣ ግሩም ለሆኑት የይሖዋ ፍጥረታት አድናቆት አለን። ወንድሞቼና እህቶቼ በማለት የምጠራቸው የተለያየ ዜግነት ያላቸው በርካታ ወዳጆች አሉኝ። እነሱም እኛን ዝቅ አድርገው የማይመለከቱን ከመሆኑም ሌላ የእምነት አጋሮቻቸው እንደሆንን አድርገው ተቀብለውናል። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ሰዎችን በሚማርክ መንገድ ለማካፈል ሲሉ ባሕላችንንና አስተሳሰባችንን ለማወቅ እንዲሁም የብላክፉትን ቋንቋ ለመማር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው።
በአሁኑ ጊዜ ከቤተሰቤ ጋር የምኖረው በደቡባዊ አልበርታ የብለድ ጎሳዎች በሚገኙበት አካባቢ ነው። በዚያም አነስተኛ የሆነ የከብት እርባታ አለን። ባሕላዊ ምግባችንን፣ ሙዚቃችንንና ጭፈራችንን ጨምሮ አጠቃላይ ባሕላችንን አሁንም እንወደዋለን። ሰዎች አንዳንዴ ፓዋ ብለው በሚጠሯቸው ባሕላዊ ጭፈራዎች ላይ ብዙውን ጊዜ ባንሳተፍም ከእኛ ሁኔታ ጋር የሚስማማ ሲሆን መመልከት ያስደስተናል። በተጨማሪም ልጆቻችን ባሕላችንን እንዲሁም የብላክፉት ሕዝቦች ከሚናገሯቸው ቋንቋዎች መካከል አንዳንዶቹን እንዲያውቁ አስተምራቸዋለሁ። አብዛኞቹ የአካባቢያችን ነዋሪዎች እንደ ደግነትና ትሕትና ያሉ ግሩም ባሕርያትን በማሳየት የሚታወቁ ከመሆናቸውም ባሻገር ለቤተሰቦቻቸውና ለጓደኞቻቸው አሳቢ ናቸው። በተጨማሪም በእንግዳ ተቀባይነታቸው የታወቁ ሲሆን የተለያየ ዘርና አስተዳደግ ያላቸውን ጨምሮ ለሁሉም ሰዎች አክብሮት አላቸው። ለእነዚህ ነገሮች አሁንም ድረስ ከፍተኛ አድናቆት አለኝ።
ጊዜያችንንና ያለንን ነገር ተጠቅመን ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲማሩና እሱን እንዲወዱት መርዳት መቻላችን ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶልናል። ልጃችን ጄረድ በቶሮንቶ አቅራቢያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በፈቃደኝነት እያገለገለ ነው። እኔ ደግሞ በአካባቢያችን በሚገኘው ማክላውድ በሚባል ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ እንዲሁም የዘወትር አቅኚ ማለትም የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኜ የማገልገል መብት አግኝቻለሁ፤ ሮዝና ካርማም የዘወትር አቅኚዎች ናቸው። የአፍ መፍቻ ቋንቋችን በሆነው በብላክፉት ቋንቋ መስበክ መቻል የሚያስደስት ነገር ነው። ሰዎች ስለ ፈጣሪና ስለ ዓላማው እውነቱን አውቀው ጥሩ ምላሽ ሲሰጡ መመልከት ያስደስታል።
መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን አስመልክቶ ሲናገር “ከፈለግኸው ታገኘዋለህ” ይላል። (1 ዜና መዋዕል 28:9) ይሖዋ የገባውን ቃል በመጠበቅ እኔም ሆንኩ ቤተሰቤ ስንፈልገው የነበረውን ነገር እንድናገኝ ስለረዳን አመስጋኝ ነኝ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.22 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን መታተም አቁሟል።
^ አን.27 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን መታተም አቁሟል።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
‘ፈጣሪ ካለ ታዲያ የት አለ? ሰዎች የሚሞቱት ለምንድን ነው?’
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
‘አብዛኞቹ የአካባቢያችን ነዋሪዎች እንደ ደግነትና ትሕትና ያሉ ግሩም ባሕርያትን በማሳየት የሚታወቁ ናቸው’
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አያቴ የብላክፉትን ባሕል ታስተምረኝ ነበር
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መላ ሕይወቴ በግልቢያ ውድድሮች ላይ ብቻ ያተኮረ ሆነ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“በፈጣሪ ላይ እምነት መጣል ትችላለህ” የተባለው ልዩ ትራክት በብላክፉትና በሌሎች ቋንቋዎች ይገኛል
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአሁኑ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት ለሌሎች ማካፈል የሚያስገኘውን ደስታ እያጣጣምኩ ነው
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሬው ጊዜ ከቤተሰቤ ጋር