በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ችግሮች የሚደርሱብህ አምላክ እየቀጣህ ስለሆነ ነው?

ችግሮች የሚደርሱብህ አምላክ እየቀጣህ ስለሆነ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ችግሮች የሚደርሱብህ አምላክ እየቀጣህ ስለሆነ ነው?

በ50ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ የምትገኝ አንዲት ሴት ካንሠር እንደያዛት ስታውቅ “እየተቀጣሁ እንዳለ ሆኖ ይሰማኛል” በማለት ተናግራለች። ይህች ሴት ከበርካታ ዓመታት በፊት የሠራችውን ስህተት በማስታወስ “አምላክ ኃጢአት መሥራቴን በዚህ መንገድ እየነገረኝ መሆን አለበት” የሚል መደምደሚያ ላይ ደረሰች።

ብዙ ሰዎች፣ መከራ ሲደርስባቸው አምላክ ከዚህ በፊት ለሠሩት ስህተት እየቀጣቸው እንደሆነ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች በድንገት ችግሮች ሲያጋጥሟቸው “ለምን በእኔ ላይ ደረሰ? ምን በድዬ ነው?” በማለት በምሬት ሲናገሩ ይደመጣል። ችግሮች የሚደርሱብን አምላክ ስላዘነብን እንደሆነ አድርገን መደምደም ይኖርብናል? በግለሰብ ደረጃ መከራ የሚደርስብን በእርግጥ አምላክ እየቀጣን ስለሆነ ነው?

ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች መከራ ደርሶባቸዋል

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢዮብ ስለተባለ ሰው ሲናገር ምን እንደሚል ተመልከት። ይህ ሰው በድንገት ሀብቱን አጣ። ቀጥሎ አሥሩም ልጆቹ በታላቅ አውሎ ነፋስ ሞቱ። ብዙም ሳይቆይ አስከፊ በሆነ በሽታ ተያዘ። (ኢዮብ 1:13-19፤ 2:7, 8) እነዚህ መከራዎች ኢዮብን “የእግዚአብሔር እጅ መታኛለች” በማለት እንዲናገር አድርገውታል። (ኢዮብ 19:21) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው በዛሬው ጊዜ እንዳሉ ብዙ ሰዎች ሁሉ ኢዮብም አምላክ እየቀጣው እንዳለ ተሰምቶት ነበር።

ይሁንና በኢዮብ ላይ መከራ ከመድረሱ በፊት አምላክ ራሱ፣ ኢዮብ “ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ሰው” መሆኑን እንደተናገረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ኢዮብ 1:8) ኢዮብ በአምላክ ፊት ሞገስ ያገኘ ሰው መሆኑን ከሚያረጋግጠው ከዚህ ሐሳብ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ኢዮብ መከራ የደረሰበት አምላክ እየቀጣው ስለሆነ አይደለም።

መጽሐፍ ቅዱስ በግለሰብ ደረጃ መከራ የደረሰባቸውን የበርካታ ቅን ሰዎች ታሪክ ይዟል። ዮሴፍ የአምላክ ታማኝ አገልጋይ ቢሆንም ፍትሕ በጎደለው መንገድ ለዓመታት ታስሯል። (ዘፍጥረት 39:10-20፤ 40:15) ታማኝ ክርስቲያን የሆነው ጢሞቴዎስ ‘በተደጋጋሚ ይታመም’ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 5:23) ምንም ዓይነት ስህተት ያልሠራው ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ ተሠቃይቶ ከመሞቱ በፊት ጭካኔ በተሞላበት መንገድ እንግልት ደርሶበት ነበር። (1 ጴጥሮስ 2:21-24) በመሆኑም መከራ የሚደርስብን አምላክ ስላዘነብን እንደሆነ አድርጎ መደምደም ስህተት ነው። ታዲያ መከራ የሚያመጣብን አምላክ ካልሆነ ለዚህ ተጠያቂው ማን ነው?

የችግሮቻችን መንስኤዎች

መጽሐፍ ቅዱስ በኢዮብ ላይ ለደረሰው መከራ መንስኤው ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ ይናገራል። (ኢዮብ 1:7-12፤ 2:3-8) ከዚህም በላይ በዛሬው ጊዜ ለሚደርሱብን ችግሮች ዋነኛ ተጠያቂው ሰይጣን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዷል።” (ራእይ 12:12) ሰይጣን “የዚህ ዓለም ገዥ” እንደመሆኑ መጠን፣ ይህ ነው የማይባል ችግርና ሐዘን የሚያስከትሉ መጥፎ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ በብዙ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።—ዮሐንስ 12:31፤ መዝሙር 37:12, 14 *

ይሁን እንጂ ለሚደርሱብን መከራዎች በሙሉ ዲያብሎስን ተወቃሽ ለማድረግ መቸኮል አይኖርብንም። ኃጢአት በመውረሳችንና ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን ችግር ሊያስከትሉብን የሚችሉ ጥበብ የጎደላቸው ውሳኔዎችን የማድረግ ዝንባሌ አለን። (መዝሙር 51:5፤ ሮም 5:12) ለምሳሌ ያህል፣ በተገቢው መንገድ መመገብ እንዲሁም በቂ እረፍት ማድረግ እንዳለበት ቢያውቅም እንዲህ የማያደርግ አንድ ሰው አለ እንበል። ይህ ልማዱ ከጊዜ በኋላ ለከፋ የጤና ችግር ቢዳርገው ግለሰቡ ዲያብሎስን ተወቃሽ ማድረግ ይኖርበታል? በፍጹም፤ ሰውየው ያጨደው ማስተዋል የጎደለው ነገር ማድረጉ ያስከተለበትን መዘዝ ነው። (ገላትያ 6:7) ይህ ዓይነቱ ሁኔታ “ሰው በራሱ ተላላነት ሕይወቱን ያበላሻል” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ እንደተናገረው መሆኑ ነው።—ምሳሌ 19:3

በመጨረሻም፣ “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” በሚያመጧቸው ነገሮች የተነሳ በርካታ ችግሮች ሊደርሱብን እንደሚችሉ ልብ ሊባል ይገባል። (መክብብ 9:11 NW) መንገድ ላይ ድንገት ኃይለኛ ዝናብ የያዘውን አንድ ሰው እንደ ምሳሌ እንመልከት። ይህ ሰው ዝናቡ ሲጀምር ቶሎ መጠለያ ሊያገኝ የሚችልበት ቦታ ላይ ከነበረ ብዙ ሳይመታው ሊያመልጥ ይችላል። አጉል ቦታ ላይ ካለ ግን በጣም ሊበሰብስ ይችላል። በተመሳሳይም ‘ለመቋቋም የሚያስቸግርና በዓይነቱ ልዩ በሆነው’ በዚህ ዘመን አንዳንድ ሁኔታዎች በቅጽበት መልካቸው ተቀይሮ የመከራ ዶፍ ሊወርድብን ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በግለሰብ ደረጃ ችግሩ የሚነካን እስከ ምን ድረስ ነው የሚለው ጉዳይ በአብዛኛው የተመካው በጊዜና በሁኔታዎች ላይ ነው፤ የሚያጋጥሙንን ሁኔታዎች በተወሰነ ደረጃ ልንቆጣጠራቸው አሊያም ፈጽሞ ከቁጥጥራችን ውጪ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ ሲባል ግን ሁልጊዜ መከራ እየደረሰብን እንኖራለን ማለት ነው?

መከራ በሙሉ በቅርቡ ይወገዳል

ደስ የሚለው፣ ይሖዋ አምላክ መከራን በሙሉ በቅርቡ ያስወግዳል። (ኢሳይያስ 25:8፤ ራእይ 1:3፤ 21:3, 4) በጉጉት የምንጠብቀው ይህ አስደናቂ ተስፋ ፍጻሜውን እስከሚያገኝ ድረስ አምላክ የሚደርሱብንን መከራዎች መቋቋም እንድንችል ‘ትምህርት’ እና ‘በቅዱሳት መጻሕፍት አማካኝነት ማጽናኛ’ በመስጠት በእርግጥ እንደሚያስብልን እያሳየ ነው። (ሮም 15:4፤ 1 ጴጥሮስ 5:7) አምላክ የሰጠው ተስፋ ፍጻሜውን ሲያገኝ በእሱ ፊት ቅን የሆኑ ሰዎች ሁሉ ምንም ዓይነት መከራ በሌለበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም ይኖራሉ።—መዝሙር 37:29, 37

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 በየካቲት 2001 ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “ሰይጣን ማን ነው? በእርግጥ እውን አካል ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ መከራ የሚደርስባቸው መጥፎ ነገር የሠሩ ሰዎች ብቻ ናቸው?—ኢዮብ 1:8

▪ ለሚደርሱብን ችግሮች ሁሉ ተወቃሹ ዲያብሎስ ነው?—ገላትያ 6:7

▪ መከራ ለሁልጊዜ ይቀጥላል?—ራእይ 21:3, 4

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ሁሉም መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች ያጋጥሟቸዋል።”—መክብብ 9:11 NW