በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሰሃራ ጨው አውጪዎች

የሰሃራ ጨው አውጪዎች

የሰሃራ ጨው አውጪዎች

በባለ ሁለት ዲፈረንሻል ተሽከርካሪያችን ስናልፍ ከዳር በኩል የተተከሉ አጫጭር ምሰሶዎች ይታዩናል። እነዚህ ምሰሶዎች፣ አሸዋ አዘል አቧራ መንገዱን በሚሸፍንበት ጊዜ ምልክት ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው። በእርግጥም አሸዋማ አውሎ ነፋሶች በዚህ በሰሃራ በረሃ የተለመዱ ናቸው።

በፍጥነት እየተጓዝንበት ያለው መንገድ ጥንታዊ የሆነ የግመል መመላለሻን ተከትሎ የተሠራ በሰሜናዊ ኒጀር የምትገኘውን የአጋዴዝ ከተማ ከአልጄሪያ ድንበር ጋር የሚያገናኝና ከዚያም አልፎ የሚሄድ ጎዳና ነው። መዳረሻችን ከአጋዴዝ ሰሜን ምዕራብ 200 ኪሎ ሜትር ላይ በጣም ርቃ የምትገኘው ቴግዊዳ-ን-ቴሱም የተባለች አነስተኛ መንደር ነች። በዚህች መንደር፣ ብዙ ዘመን ያስቆጠረውንና ከሰሃራ ሸክላማ አፈር ውድ የሆነ ጨው አጣርቶ የማውጣትን ዘዴ ተከትለው የሚሠሩ 50 ቤተሰቦች ይገኛሉ።

ሰው ሠራሽ ጉብታዎችና የሸክላ ኩሬዎች

ከፊት ለፊታችን ወደ መዳረሻችን መቅረባችንን የሚያበስሩ ትናንሽ ጉብታዎች ብቅ አሉ። የጉዞ መሪያችን መኪናችንን 10 ሜትር ከፍታ ካለው ጉብታ ሥር ካቆመ በኋላ ከመኪናው ወርደን ወደ ጉብታው አናት እንድንወጣና መንደሩን ቁልቁል እንድንመለከት ጋበዘን። አቀበቱን እያዘገምን ስንወጣ ይህ ጉብታም ሆነ እሱን የሚመስሉት ሌሎች ጉብታዎች ለበርካታ ዓመታት በአካባቢው ሲካሄድ ከነበረ ጨው የማውጣት ሥራ የተረፉ ዝቃጮች ውጤት የሆኑ ሰው ሠራሽ ጉብታዎች እንደሆኑ አስረዳን።

ከጉብታው ጫፍ ሆኖ የሚታየው ትዕይንት እጅግ በጣም ማራኪ ነው። ከበታቻችን ባለው መንደር የሚታየው ሁሉ፤ መሬቱ፣ ግድግዳዎቹ፣ ጣሪያዎቹ በሙሉ የተቃጠለ ሸክላ ቀለም ያላቸው ናቸው። ከዚህ የተለየ ቀለም ያላቸው በመንደሩ ጫፍና ጫፍ እንደ ዘበኛ ተገትረው በሚታዩት ሁለት ዛፎች ላይ ያሉት አረንጓዴ ቅጠሎች ብቻ ናቸው። አጥሮቹና ቤቶቹ ሳይቀሩ ከሸክላ የተሠሩ ናቸው። አንድ ዓይነት ቀለም ያላቸው ቤቶች በአቅራቢያው ከሚገኙት በመቶዎች የሚቆጠሩ የጨው ኩሬዎች ሸክላማ ቀለም ጋር ጥሩ ንጽጽር ፈጥረዋል። አካባቢው ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ደፋ ቀና ሲሉ የሚውሉበት ጥድፊያ የሚበዛበት ነው።

ያልተለመደ ጨው የማውጣት ዘዴ

ከመመልከቻ ጉብታው ላይ እየወረድን ሳለ የጉዞ መሪያችን መንደረተኞቹ የሚሠሩበትን ጥንታዊ ጨው ማውጫ ዘዴ አብራራልን። “ኩሬዎቹ ሁለት ዓይነት ብቻ ናቸው” አለን። “ሁለት ሜትር ያህል ስፋት ያላቸው ትላልቆቹ ኩሬዎች ጨው ተሸካሚ የሆነውን ውኃ ለማጥለል የሚያገለግሉ ናቸው። ትናንሾቹ ደግሞ የማትነኛ ኩሬዎች ናቸው። በአካባቢው ከሚገኙ 20 የሚያክሉ ምንጮች የሚቀዳው ውኃ በጣም ጨዋማ ነው። ቢሆንም ዋነኛው የጨው ምንጭ ውኃው ሳይሆን አፈሩ ነው። ይህን የጨው አወጣጥ ልዩ የሚያደርገውም ይኸው አፈር ነው።” ታዲያ ጨው ከአፈሩ የሚወጣው እንዴት ነው?

ከምንጭ በተቀዳ ውኃ በተሞላ ሠፊ ኩሬ ውስጥ አፈር የሚደፋ አንድ ሰው ተመለከትን። የወይን መጭመቂያ የሚረግጥ ይመስል በእግሩ በኃይል እየረገጠ አፈሩን ከውኃው ጋር ያደባልቃል። በበቂ መጠን ተለውሷል ብሎ ሲያምን ጨዋማው ጭቃ እንዲጠል ለበርካታ ሰዓታት ይተወዋል። ተመሳሳይ በሆነ ጨዋማ ጭቃ የተሞሉ ሰፋፊ ኩሬዎች ዙሪያውን ከበውታል። ጭቃው በሚዘቅጥበት ጊዜ የኩሬዎቹ መልክ ስለሚለወጥ በኩሬዎቹ ውስጥ የሚታየው ፈሳሽ ቡናማ ቢሆንም በድምቀቱና በዓይነቱ ይለያያል።

በአጠገቡ የሚገኝ ሌላ ሰው ጨዋማውን ውኃ ከቅል በተሠራ አንኮላ እየቀዳ ወደ ትናንሾቹ ኩሬዎች ይጨምራል። አብዛኛውን ጊዜ ይኸኛውን የሥራ ክፍል የሚያከናውኑት ወንዶች ናቸው። በተጨማሪም ለኩሬዎቹ ክትትልና እድሳት የማድረግ ኃላፊነት የሚወድቀው በወንዶቹ ላይ ነው። አንዳንዶቹ ኩሬዎች እንዲሁ በተፈጥሮ የተገኙ ረባዳ ቦታዎች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ የተቆፈሩ ዐለቶች ናቸው። መቆፈር በማይቻልባቸው ቦታዎች ወንዶቹ በድንጋያማ ቦታ ላይ ሸክላማ አፈር በቀለበት ቅርጽ ይቆልላሉ። በእጃቸው ከሸክላው ግድግዳ ከሠሩ በኋላ ጠንካራ እስኪሆን ድረስ ግድቡን በበትር ይደበድባሉ። እነዚህ ኩሬዎች በየዓመቱ መታደስ ወይም እንደገና መሠራት ይኖርባቸዋል።

ሴቶችስ ምን የሥራ ድርሻ አላቸው? በማንኛውም ጊዜ ለማጣሪያ የሚቀርብ ጨዋማ አፈር እንዳይታጣ የመሸከሙንና የማጓጓዙን ሥራ ያከናውናሉ። በተጨማሪም ከኩሬዎቹ ውስጥ የጨው ቅንጣቶችን ያስወግዳሉ። ከዚያ በኋላ ደግሞ ኩሬዎቹ ለሚቀጥለው የሥራ ሂደት ዝግጁ እንዲሆኑ ጥሩ አድርገው ያጸዷቸዋል።

በዚሁ ጊዜ ሕፃናቱ በትናንሾቹ ኩሬዎች ዙሪያ ይሯሯጣሉ። ሥራቸው የአደራረቁን ሂደት መከታተል ነው። ውኃው ከኩሬዎቹ ውስጥ በሚተንበት ጊዜ ከላይ ጠጣር የሆነ የጨው ንጣፍ ይፈጠራል። ይህ ንጣፍ ዝም ብሎ ከተተወ የመትነኑን ሂደት ያቆመዋል። በዚህ ምክንያት ልጆቹ የጨዉን ንጣፍ ለማፍረስና የጨው ቅንጣቶቹ ወደታች እንዲሰርጉ ለማድረግ ከላዩ ላይ ውኃ ያርከፈክፋሉ። ውድ የሆነው ጨው ብቻ እስኪቀር ድረስ ትነቱ ይቀጥላል።

ኩሬዎቹ ይህን የመሰለ የተለያየ የሚያምር ቀለም የኖራቸው ለምንድን ነው? የጉዞ መሪያችን እንዲህ ሲል አስረዳን፦ “በመሠረቱ በዚህ አካባቢ ያለው ሸክላ ወይም ጭቃ ሦስት ዓይነት ሲሆን ሁሉም ለውኃው ቀለም የተለያየ መሆን የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል። በተጨማሪም የውኃው ቀለም በውስጡ ካለው የጨው መጠን የተነሳ ይለያያል። ከዚህም በላይ በአንዳንዶቹ ኩሬዎች ውስጥ አልጌ ስለሚያድግ የውኃውን ቀለም ይለውጠዋል።” በተጨማሪም የምትፋጀው ፀሐይ ነጸብራቅ አቅጣጫ በሚለወጥበት ጊዜ ሁሉ የኩሬዎቹ ቀለምና ድምቀት እንደሚለወጥ አስተዋልን።

ጨው ገንዘብ ሆኖ ሲያገለግል

ሴቶች እርጥቡን ጨው ወደ መንደሩ ከወሰዱ በኋላ በቅርጽ በቅርጽ ጠፍጥፈው በጠራራ ፀሐይ ላይ በማስጣት ያደርቁታል። ጨዉን ስለማያጣሩት አሞሌዎቹ ቀለማቸው ቡናማ እንደሆነ ይቀራል። ሴቶቹ ጨዉን የሚጠፈጥፉት በሦስት መልክ ማለትም በሞላላ፣ በክብና በሦስት ማዕዘን ቅርጽ እንደሆነ አስተዋልን። ከሴቶቹ አንዷ ሞላላዎቹና ክብ ቅርጽ ያላቸው ጥፍጥፎች የሚሸጡ ሲሆኑ ባለ ሦስት ማዕዘኖቹ ግን በስጦታነት እንደሚሰጡ ነገረችን።

ይህን ጨው የሚገዛው ማነው? ዘላኖችና የጨው ነጋዴዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች በቴግዊዳ-ን-ቴሱም ሲያልፉ ጨዉን በምግብና በሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦች ይለውጣሉ። አብዛኛው ጨው የሚሸጠው በበረሃው ዳርቻዎች ባሉ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ ገበያዎች ነው። ከዚህ መንደር የሚገኘው ጥሬ ጨው ለሰው ምግብነት ላያገለግል ይችላል። ሆኖም በአብዛኛው ለቤት እንስሳት መኖነት ይውላል።

ወደ መኪናችን እየተመለስን ሳለን በአንድ ባዶ ኩሬ ውስጥ የቀረ አፈር እየዛቀ የሚያወጣ ሰው ተመለከትን። ጭቃውን ወደ መቆለያ ቦታው እያጓጓዘ በሰው ሠራሹ ጉብታ ላይ የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል። የመልስ ጉዟችንን በምናደርግበት ጊዜ እነዚህ ኮረብታዎች በቴግዊዳ-ን-ቴሱም ሲለፉና ሲደክሙ ኖረው ስላለፉ የጨው አውጪዎች ትውልድ የሚሰጡትን ምሥክርነት በአድናቆት አሰብን።—ተጽፎ የተላከልን

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ዋነኛው የጨው ምንጭ ውኃው ሳይሆን አፈሩ ነው። ይህን የጨው አወጣጥ ልዩ የሚያደርገውም ይኸው አፈር ነው”

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የሰሃራ በረሃ

ኒጀር

አጋዴዝ

ቴግዊዳ-ን-ቴሱም

[ምንጭ]

Based on NASA/Visible Earth imagery

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሰሃራ አፈር ውድ ጨው አጣርቶ ማውጣት

[ምንጭ]

© Victor Englebert

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የማትነኛ ኩሬዎቹ የተለያየ ቀለም አላቸው

[ምንጭ]

© Ioseba Egibar/age fotostock

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጠራራ ፀሐይ ላይ የደረቁ የጨው ጥፍጥፎች