በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የውኃ ሀብታችን እየተሟጠጠ ነው?

የውኃ ሀብታችን እየተሟጠጠ ነው?

የውኃ ሀብታችን እየተሟጠጠ ነው?

ኡዝቤካውያን “ውኃ ካጣህ ሕይወትህን አጣህ ማለት ነው” የሚል አባባል አላቸው። አንዳንድ ባለሞያዎች፣ ይህ አባባል ምሳሌያዊ አነጋገር ከመሆን አልፎ ትንቢት አዘል ይመስላል ይላሉ። በንጽሕና አጠባበቅ ጉድለትና በውኃ መበከል የተነሳ በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች ሕይወታቸውን የሚያጡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ሕፃናት ናቸው።

ውኃ የምታገኘው እንዴት ነው? ቤትህ ድረስ በተዘረጋ የቧንቧ መስመር ነው? ወይስ በአንዳንድ አገሮች እንደሚታየው ረጅም ርቀት መጓዝ፣ ወረፋ መጠበቅና ውኃውን ተሸክመህ ማምጣት ይጠይቅብሃል? ልብስና ዕቃ ለማጠብ እንዲሁም ምግብ ለማብሰል የሚያስፈልግህን በቂ ውኃ ለማግኘት በየዕለቱ ረጅም ሰዓት ይወስድብሃል? በብዙ አገሮች ውኃ ማግኘት ይህን ያህል አስቸጋሪና አድካሚ ነው! ዳያን ሬንስ ዋርድ፣ ዋተር ዎርስድራውት፣ ፍለድ፣ ፎሊ ኤንድ ዘ ፖለቲክስ ኦቭ ተርስት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ 40 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ “ውኃ ለማግኘት ወደ ወንዞች፣ ወደ ጉድጓዶች፣ ወደ ኩሬዎች ወይም የታቆረ ውኃ ወደሚገኙባቸው ቦታዎች መሄድ” እንደሚጠይቅበት ገልጸዋል። በአንዳንድ አገሮች፣ ሴቶች ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ውኃ ለመቅዳትና ተሸክመው ለማምጣት ስድስት ሰዓት ገደማ ሊወስድባቸው ይችላል፤ ውኃ ለማምጣት የሚጠቀሙበት ዕቃ ሙሉ ከሆነ ከ20 ኪሎ ግራም በላይ ሊመዝን ይችላል።

ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ የማግኘትና ቆሻሻን በተገቢው መንገድ የማስወገድ ከፍተኛ ችግር አለበት። በተለይ በአፍሪካ ችግሩ ይበልጥ አስከፊ ሲሆን ከ10 ሰዎች 6ቱ ጥሩ የሚባል መጸዳጃ ቤት የላቸውም፤ ይህ ደግሞ የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሠረት “በሰዎች ዓይነ ምድርና ሽንት ውስጥ የሚገኙ ባክቴሪያዎች፣ ቫይረሶችና ጥገኛ ተሕዋስያን ከሰው ወደ ሰው እንዲተላለፉ እንዲሁም . . . ውኃ፣ አፈርና ምግብ እንዲበከል” ያደርጋል። ሪፖርቱ አክሎ እንደገለጸው እንዲህ ያለው ብክለት “በታዳጊ አገሮች ውስጥ የብዙ ሕፃናትን ሕይወት በመቅጠፍ በሁለተኝነት ደረጃ ለሚጠቀሰው የተቅማጥ በሽታ ዋነኛ መንስኤ ሲሆን እንደ ኮሌራ፣ ቢልሃርዚያና ትራኮማ ያሉ ከባድ በሽታዎችንም ያስከትላል።”

ውኃ፣ ፈሳሽ ወርቅ ብሎም የ21ኛው መቶ ዘመን ነዳጅ ተብሎ ተጠርቷል። ይሁንና መንግሥታት ዋነኛ የሆኑት ወንዞቻቸው ደርቀው ወደ ባሕር የሚፈስ ውኃ እስኪጠፋ ድረስ ይህን ውድ ሀብት አላግባብ እየተጠቀሙበት ነው። የመስኖ ልማትና የውኃ ትነት በሚያሳድሩት ከፍተኛ ተጽዕኖ የተነሳ በምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘውን የኮሎራዶ ወንዝ፣ የቻይናውን ያንግዚ፣ የፓኪስታኑን ኢንደስ፣ የሕንዱን ጋንጀስና የግብፁን ናይል ጨምሮ ታዋቂ ወንዞች እየደረቁ ናቸው። ታዲያ ይህን ቀውስ ለማስወገድ ምን እየተደረገ ነው? ለዚህ ችግር ዘላቂው መፍትሔስ ምንድን ነው?

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የውኃ ሀብት አስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛል

“በመካከለኛው እስያ የሚገኘው የአራል ባሕር፣ በ1960 በዓለም ካሉት ሐይቆች በትልቅነቱ በአራተኝነት ደረጃ ላይ ይገኝ ነበር። በ2007 ግን የባሕሩ መጠን በፊት ከነበረው በጣም ቀንሶ የቀረው 10 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው።”—ሳይንቲፊክ አሜሪካን

ኢሪ፣ ሂውሮን፣ ሚሺገን፣ ኦንቴሪዮና ሱፒርየር የተባሉት አምስቱ የዩናይትድ ስቴትስና የካናዳ ትላልቅ ሐይቆች “በሚያስደነግጥ ፍጥነት” መጠናቸው እየቀነሰ ነው።—ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል

በዴኒሊኩዊን፣ አውስትራሊያ ይገኝ የነበረው የሩዝ መፈልፈያ ፋብሪካ በአንድ ወቅት ለ20 ሚሊዮን ሰዎች የሚበቃ ሩዝ ያመርት ነበር። ይሁን እንጂ የሩዝ ምርት 98 በመቶ በመቀነሱ ፋብሪካው በታኅሣሥ 2007 ተዘግቷል። ምክንያቱ ምን ነበር? “ለስድስት ዓመታት የዘለቀው ድርቅ ነው።”—ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ

[ሥዕል]

በአራል ባሕር ውኃ ከድቷት ተገትራ የቀረች መርከብ

[ምንጭ]

© Marcus Rose/Insight/Panos Pictures

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ካርታዎች]

‘ወንዞችና ጅረቶች እየደረቁ ነው’

“የጠፈር ተመራማሪዎች በአንድ ወቅት ከሕዋ ላይ በቀላሉ ያዩት የነበረውን በአፍሪካ የሚገኘውን የቻድ ሐይቅ አሁን አሁን መለየት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። [በካሜሩን፣] በቻድ፣ በኒጀርና በናይጄሪያ መካከል የሚገኘው . . . ይህ ሐይቅ ከ1960ዎቹ ዓመታት አንስቶ መጠኑ 95 በመቶ ቀንሷል። በአካባቢው ያለው መጠነ ሰፊ የሆነ የመስኖ ልማት፣ ለሐይቁ ሕልውና ወሳኝ የሆኑት ገባር ወንዞችና ጅረቶች እንዲደርቁ ምክንያት ሆኗል። በዚህም የተነሳ የቻድ ሐይቅ መጪዎቹ ትውልዶች የት ቦታ ላይ እንደነበር እንኳ መለየት እስኪያቅታቸው ድረስ ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ ይችላል።”በሌስተር ብራውን የተዘጋጀው፣ ፕላን ቢ 2.0—ሬስኪዊንግ ኤ ፕላኔት አንደር ስትረስ ኤንድ ኤ ሲቪላይዜሽን ኢን ትራብል

[ካርታዎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ውኃ

☒ ዕፅዋት

□ የብስ

1963

ኒጀር

ቻድ

ቻድ ሐይቅ

ናይጄሪያ

ካሜሩን

2007

ኒጀር

ቻድ

ቻድ ሐይቅ

ናይጄሪያ

ካሜሩን

[ምንጭ]

NASA/U.S. Geological Survey