በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የደቡብ ባሕሮች የተረሱ ባሮች

የደቡብ ባሕሮች የተረሱ ባሮች

የደቡብ ባሕሮች የተረሱ ባሮች

ፊጂ የሚገኘው የንቁ! ጸሐፊ እንዳዘጋጀው

ው የማይደርስበት ወደሚመስለው የፓስፊክ ደሴት ሁለት መርከቦች መቃረባቸውን ሲመለከቱ በዚያ የተሰበሰቡት ሰዎች በደስታ ስሜት ተዋጡ። ከበርካታ ዓመታት በፊት ከመርከብ አደጋ የተረፈ አንድ ሰው ከራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የቀደዳቸውን ገጾች በዚያ ለነበረ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ አድሎ ነበር። እነዚህ ትሑት ሰዎች ያገኟቸውን ገጾች በጉጉት ካነበቡ በኋላ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ክርስቲያን አስተማሪ ለማግኘት በታላቅ ጉጉት ሲጠብቁ ኖረዋል።

አሁን እነዚህ ባሕረኞች ለሰዎቹ ስለ አምላክ ተጨማሪ እውቀት ሊያገኙ ወደሚችሉበት ቦታ እንደሚወስዷቸው ቃል እየገቡላቸው ነው። ሁለት መቶ ሃምሳ የሚያክሉ ያልጠረጠሩ ወንዶችና ሴቶች፣ ብዙዎቹ ያችን እንደ ውድ ንብረት የሚቆጥሯትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሙጥኝ ብለው በእጃቸው እንደያዙ መርከቡ ላይ ተሳፈሩ።

ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች የረቀቀ የማታለያ ዘዴ ሰለባዎች ነበሩ። መርከቡ ላይ እንደተሳፈሩ ታስረው ወደ መርከቡ ታችኛ ክፍል ከተወረወሩ በኋላ በደቡብ አሜሪካ ወደሚገኘው የከያኦ ወደብ ረዥም ጉዞ ጀመሩ። በጉዞ ላይ እንዳሉ በንጽሕና ጉድለት ብዙዎች ሞቱ። ወሲባዊ ጥቃት እጅግ የተስፋፋ ነበር። ከሞት ተርፈው ወደብ የደረሱት በእርሻዎችና በማዕድን ማውጫዎች እንዲሠሩ እንዲሁም የቤት አገልጋዮች እንዲሆኑ ዳግም ወደ ትውልድ አገራቸው ላይመለሱ ለባርነት ተሸጡ።

የባሪያ ፍንገላ መስፋፋት

የደቡብ ፓስፊክ ደሴቶች ነዋሪዎች በ19ኛው መቶ ዘመንና በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በግድ ታፍነው እየተወሰዱ ለባርነት ይሸጡ ነበር። በ1860ዎቹ መጀመሪያ ላይ በደሴቶቹ ላይ የሚኖሩ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በዚህ የባሪያ ፍንገላ እንቅስቃሴ ወደ ደቡብ አሜሪካ ተጋዙ። ከዚያ ቀጥሎ በነበረው አሥር ዓመት የትኩረት አቅጣጫው ወደ ምዕራብ በመዞሩ የደሴቶቹ ነዋሪዎች ወደ አውስትራሊያ ይወሰዱ ጀመር። በ1867፣ ቀድሞ የሮያል ባሕር ኃይል ባልደረባ የነበሩት ሮስ ሉወን “ከደሴቶቹ የመጡትን ምርጥና የተሻለ አገልግሎት የሚሰጡ ሠራተኞችን፣ አንዱን 7 ፓውንድ በመክፈል ማግኘት” እንደሚቻል ለሸንኮራና ለጥጥ አምራቾች እስከማስታወቅ ደርሰው ነበር።

የብሪታንያ የቅኝ አገዛዝ ቢሮ የባሪያ ፍንገላን ለማስቆም ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀረ። ይህ የሆነበት አንደኛው ምክንያት የባዕድ አገር ዜጎች በሆኑ ሰዎች ላይ የብሪታንያን ሕግ ተፈጻሚ ማድረግ አለመቻሉ ሲሆን ሌላው ምክንያት ደግሞ የእንግሊዝ ሕግ ባርነትን በተመለከተ አንድ ወጥ የሆነና ለሁሉም ሁኔታ የሚሠራ ፍቺ አለመስጠቱ ነበር። በዚህ የተነሳ ባሪያ ፈንጋዮች ተከሰው ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ጊዜ እነዚህ የደሴት ነዋሪዎች ተታልለውና ተገድደው የተወሰዱ ቢሆኑም ደመወዝ የሚከፈላቸውና ውሎ አድሮ ወደ አገራቸው የሚመለሱ የውል ግዴታ ያለባቸው የጉልበት ሠራተኞች እንጂ ባሮች አይደሉም ብለው በመከራከር ይረቱ ነበር። እንዲያውም አንዳንዶቹ እነዚህን አረመኔ የነበሩ ሰዎች በብሪታንያ ሕግ ሥር እንዲጠለሉ በማድረጋቸውና ሥራ በማስተማራቸው ውለታ እንደዋሉላቸው እስከመናገር ደርሰው ነበር! በዚህ የተነሳ ለጊዜውም ቢሆን የባሪያ ፍንገላ እየተስፋፋ ሄደ።

ሁኔታው መቀልበስ ጀመረ

ፍትሐዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ባሪያ ፍንገላን የሚቃወም ድምፅ ማሰማት በመቀጠላቸው ሁኔታው መቀልበስ ጀመረ። አንዳንድ የደሴቶቹ ነዋሪዎች በገዛ ፈቃዳቸው ቢመለመሉም እንኳ አስገድዶ መያዝ ግን በዝምታ የሚታለፍ ነገር መሆኑ አበቃ። እንደ መግረፍና ሰውነትን እንደመተኮስ ያሉ አሰቃቂ ግፎችም ሆኑ የጉልበት ሠራተኞቹ ይኖሩባቸውና ይሠሩባቸው የነበሩት አስከፊ ሁኔታዎች ችላ ተብለው ሊታለፉ አልቻሉም።

የባሪያ ፍንገላ ጠንካራ ተቃዋሚ የነበሩት የአንግሊካኑ ጳጳስ ጆን ኮሌሪጅ ፓተሰን ጥብቅና በቆሙላቸው የደሴቶቹ ነዋሪዎች ከተገደሉ በኋላ ሁኔታው በጣም ተፋፋመ። ባሪያ ፈንጋዮች ብዙ ጊዜ ይሠሩበት የነበረውን የማታለያ ዘዴ በመጠቀም ሆን ተብሎ የፓተሰንን መርከብ እንዲመስል በተደረገ መርከብ ከፓተሰን ቀድመው ወደ አንድ ደሴት ደርሰው ነበር። በዚህ ጊዜ የአካባቢው ሰዎች ወደ መርከቢቱ ገብተው ከጳጳሱ ጋር እንዲነጋገሩ ተጋበዙ። መርከቡ ውስጥ የገቡት ሰዎች ከዚያ በኋላ የውኃ ሽታ ሆነው ቀሩ። እውነተኛው ፓተሰን በመጡ ጊዜ በቁጣ በግኖ የነበረ ብዙ ሕዝብ አገኛቸውና በተሳሳተ የበቀል እርምጃ ተገደሉ። ከዚህ ክስተት የተነሳ እንዲሁም የሕዝብ ጩኸት እየጠነከረ በመምጣቱ ምክንያት የብሪታንያና የፈረንሳይ ባሕር ኃይል መርከቦች እንዲህ ያለውን ግፍ እንዲያስቆሙ ታዘው በፓስፊክ ውቅያኖስ እንዲሰፍሩ ተደረገ።

በአውስትራሊያ የኒው ሳውዝ ዌልስና የክዊንስላንድ ክልላዊ መንግሥታት የግፍ ተግባራትን የሚያስቆምና የኮንትራት የጉልበት ሠራተኞችን ንግድ የሚቆጣጠር ሕግ በማውጣት ኃይላቸውን ከቅኝ ግዛት ቢሮ ጋር አስተባበሩ። ለምልመላ ሥራ በሚያገለግሉ መርከቦች ላይ ተቆጣጣሪዎች የተመደቡ ከመሆኑም ሌላ የመንግሥት ተወካዮችም እንዲሳፈሩ ተደረገ። ፋይዳ ቢስ በሆነው የፀረ ባርነት ሕግ ሳይሆን በጠለፋና በግድያ ወንጀል ከስሶ ማስቀጣት በመቻሉ እነዚህ ትጋት የተሞላባቸው ጥረቶች ውጤት አስገኙ። በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ በደቡብ ባሕሮች ላይ ለወጥ ያለ ሁኔታ መታየት ጀመረ። የባሪያ ፍንገላ በአብዛኛው የቆመ ሲሆን በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ደግሞ የአዳዲስ “ምልምሎች” ቁጥር በጣም ተመናመነ።

በ1901 ኮመንዌልዝ ኦቭ አውስትራሊያ በሚል ስያሜ የተቋቋመው አዲስ ብሔራዊ ምክር ቤት የመላ አገሪቱን ኢምግሬሽን በራሱ ቁጥጥር ሥር አደረገ። የዚህ ምክር ቤት ፖሊሲ በጊዜው ሰፍኖ የነበረውን፣ የውጭ አገር ሠራተኞች ለአገሬው ሕዝብ የሥራ እድል ያሳጣሉ ከሚል ሥጋት የመነጨውን የአብዛኛውን ሕዝብ የውጭ አገር ሠራተኛ ጥላቻ የሚያንጸባርቅ ነበር። የደቡብ ባሕር ደሴት ተወላጆች የኮንትራት ሠራተኞች ሆኑም አልሆኑ ተቀባይነታቸውን አጡ። በሺህ የሚቆጠሩት ተገድደው ወደየአገራቸው እንዲመለሱ ተደረገ። በዚህም ምክንያት ተደላድለው መኖር ከጀመሩበት ቦታ እንዲፈናቀሉ በመደረጋቸውና ካፈሯቸው ወዳጅ ዘመዶች ለመነጠል በመገደዳቸው ሌላ ከባድ ግፍ ተፈጸመ።

ተረስተው የነበሩ ባሮች ተዘከሩ

በመስከረም 2000 የክዊንስላንድ ክልላዊ መንግሥት በቋሚነት ለሕዝብ የሚታይ መግለጫ አወጣ። የደቡብ ባሕሮች ደሴት ነዋሪዎች ለክዊንስላንድ ኤኮኖሚያዊ፣ ባሕላዊና አካባቢያዊ እድገት ላደረጉት አስተዋጽኦ እውቅና የሚሰጥ መግለጫ ነበር። በተጨማሪም መንግሥት በእነዚህ ሰዎች ላይ በተፈጸመው ግፍ እጅግ እንደሚያዝን ገልጿል።

በታሪክ ዘመናት ሁሉ በሌሎች ሕይወትና ነፃነት ተረማምደው ራሳቸውን ለማበልጸግ ባገኙት አጋጣሚ የተጠቀሙ ግለሰቦች ብዙ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንግሥት ውስጥ እንዲህ ያለ ግፍ ፈጽሞ እንደማይኖር የሚገልጽ ተስፋ ይዟል። እንዲያውም የዚህ ሰማያዊ መንግሥት ምድራዊ ዜጋ ሆኖ የሚኖር “እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም።”—ሚክያስ 4:4

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ወደ አውስትራሊያና ወደ ደቡብ አሜሪካ የሚያመሩ የባሪያ ማጓጓዣ መስመሮች

ፓስፊክ ውቅያኖስ

ማይክሮኔዥያ

የማርሻል ደሴቶች

ኒው ጊኒ

የሰለሞን ደሴቶች

ቱቫሉ

አውስትራሊያ ኪሪባቲ

ክዊንስላንድ ቫኑዋቱ

ኒው ሳውዝ ዌልስ ኒው ካሊዶንያ ደቡብ አሜሪካ

ሲድኒ ← ፊጂ → ከያኦ

ሳሞአ

ቶንጋ

የኩክ ደሴቶች

የፈረንሳይ ፖሊኔዥያ

ኢስተር ደሴት

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

National Library of Australia, nla.pic-an11279871