በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጓደኝነታችንን ማቆም ይኖርብን ይሆን?

ጓደኝነታችንን ማቆም ይኖርብን ይሆን?

የወጣቶች ጥያቄ

ጓደኝነታችንን ማቆም ይኖርብን ይሆን?

“ጓደኝነት ከጀመርን ሦስት ወራት ያለፉ ሲሆን ሁለታችንም ግንኙነታችን ሊቀጥል እንደሚችል ይሰማን ነበር። ቀሪውን ጊዜ አብረን ማሳለፋችን ሳይታለም የተፈታ ሐቅ ይመስል ስለ ወደፊቱ ሕይወታችን እናወራ ነበር።”—ጄሲካ *

“ልጁን በጣም ነበር የወደድኩት፤ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ እሱም ዓይኑን በእኔ ላይ መጣል ጀመረ! ሊንከባከበኝ የሚችል ከእኔ በዕድሜ የሚበልጥ የወንድ ጓደኛ መያዝ እመኝ ነበር።”—ካሮል

ጄሲካና ካሮል ከጊዜ በኋላ ከወንድ ጓደኞቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቁመዋል። ለምን? እነዚህን ከመሰሉ ልጆች ጋር የነበራቸውን ጓደኝነት ማቆማቸው ሞኝነት ነው?

ከአንድ ልጅ ጋር ጓደኝነት ከጀመርሽ አንድ ዓመት ገደማ ሆኖሻል እንበል። መጀመሪያ ላይ፣ “ከእሱ ሌላ ለእኔ የሚሆነኝ ሰው የለም” ብለሽ አስበሽ ይሆናል። * እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ፣ ጓደኝነት የጀመራችሁ ሰሞን ስለነበራችሁ የፍቅር ግንኙነት መለስ ብለሽ ታስቢ ይሆናል። አሁን ግን አንዳንድ ጥርጣሬዎች አድረውብሻል። እነዚህን ነገሮች በቸልታ ማለፍ ይኖርብሽ ይሆን? ጓደኝነታችሁን ማቆም ይኖርብሽ እንደሆነና እንዳልሆነስ እንዴት ማወቅ ትችያለሽ?

በቅድሚያ አንድን እውነታ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን አለብሽ፤ ይኸውም በጓደኝነት መቀጠል አደጋ እንደሚኖረው እያወቁ ችላ ማለት አንድ መኪና ችግር እንዳለው የሚጠቁሙ በዳሽ ቦርዱ ላይ የሚታዩትን የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ዝም ብሎ እንደማለፍ ይሆናል። በመካከላችሁ ያለውን ችግር ችላ ብሎ ማለፍ ሁኔታውን ያባብሰው ይሆናል እንጂ አያስወግደውም። ታዲያ በጓደኝነት መቀጠላችሁ አደጋ እንዳለው የሚጠቁሙና ትኩረት ልትሰጪያቸው የሚገቡ አንዳንድ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

በደንብ ሳንተዋወቅ በፍጥነት እየተቀራረብን ነው። የፍቅር ግንኙነት የጀመሩት ወጣቶች ጊዜ ወስደው በደንብ ሳይተዋወቁ በፍጥነት የሚቀራረቡ ከሆነ ችግሮች መፈጠራቸው አይቀርም። ካሮል እንዲህ ብላለች፦ “በኢንተርኔት መልእክት እንለዋወጥ እንዲሁም በስልክ እናወራ ነበር። በአካል ከመገናኘት ይልቅ በዚህ መንገድ መገናኘት በአጭር ጊዜ ውስጥ በጣም ሊያቀራርብ ይችላል!” ጊዜ ወስዳችሁ በደንብ ለመተዋወቅ ጥረት አድርጉ። ጓደኝነት ቶሎ አድጎ ወዲያው እንደሚጠፋ አረም ሳይሆን ለማደግ ጊዜ እንደሚያስፈልገው የሚያምር አትክልት መሆን አለበት።

የመንቀፍ ልማድ ያለው ከመሆኑም በላይ ያጣጥለኛል። አና የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “የወንድ ጓደኛዬ ሁልጊዜ ያጣጥለኝ ነበር፤ እኔ ግን ከእሱ መለየት አልፈልግም። በሌላ ጊዜ ቢሆን ኖሮ ችዬ ላሳልፋቸው እንደማልችል የሚሰሙኝን ነገሮች እንኳ በትዕግሥት አልፋቸው ነበር!” መጽሐፍ ቅዱስ “ስድብ” ተገቢ እንዳልሆነ ይናገራል። (ኤፌሶን 4:31) ሰዎችን የሚያንቋሽሹ ቃላት ሌላው ቀርቶ በእርጋታ የተነገሩ ቢሆኑም እንኳ በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ቦታ ሊኖራቸው አይገባም።—ምሳሌ 12:18

ግልፍተኛ ነው። ምሳሌ 17:27 ‘አስተዋይ ሰው መንፈሱ የረጋ ነው’ ይላል። ኤሪን የወንድ ጓደኛዋ በዚህ ረገድ ችግር እንዳለበት ታውቅ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “በመካከላችን አለመግባባት ከተፈጠረ ገፍትሮ ይጥለኛል። በዚህም የተነሳ አንዳንድ ጊዜ በሰውነቴ ላይ ጉዳት ይደርስብኛል።” መጽሐፍ ቅዱስ “የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት . . . ከእናንተ መካከል ይወገድ” በማለት ለክርስቲያኖች ምክር ይሰጣል። (ኤፌሶን 4:31) አንድ ሰው ራሱን የማይገዛ ከሆነ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት ለመጀመር ዝግጁ ነው ማለት አይቻልም።—2 ጢሞቴዎስ 3:1, 3, 5

ስለ ጓደኝነታችን ማንም እንዲያውቅ አይፈልግም። አንጄላ እንዲህ ብላለች፦ “የወንድ ጓደኛዬ መጠናናት እንደጀመርን ሌሎች እንዲያውቁ አይፈልግም። እየተጠናናን እንደሆነ አባቴ እንኳ በማወቁ ተበሳጭቷል!” እርግጥ ነው፣ በመጠናናት ላይ ያሉ ሰዎች ሁኔታውን በተወሰነ ደረጃ በሚስጥር መያዛቸው አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ስለ ግንኙነታችሁ ማወቅ ከሚገባቸው ሰዎች ጉዳዩን ሆን ብሎ ለመደበቅ መሞከር ችግር ሊያስከትል ይችላል።

የማግባት ሐሳብ የለውም። በክርስቲያኖች ዘንድ መጠናናት ክብር ያለውና በዓላማ የሚደረግ ነው፤ ይኸውም አንድ ወንድና አንዲት ሴት በትዳር አብረው መኖር ይችሉ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን የሚያስችል አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል። እርግጥ እንዲህ ሲባል ገና መጠናናት እንደጀመራችሁ ስለ ሠርጋችሁ እቅድ ማውጣት ያስፈልጋችኋል ማለት አይደለም። እንዲያውም ብዙ ሰዎች የሚጋቡት መጀመሪያ ላይ ሲጠናኑ ከነበረው ሰው ጋር አይደለም። አንድ ሰው ትዳር የሚያስከትልበትን ኃላፊነት ለመሸከም ዝግጁ ካልሆነ መጠናናት መጀመር የለበትም።

ጓደኝነታችን በተደጋጋሚ ይቋረጣል። ምሳሌ 17:17 “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው” በማለት ይናገራል። ይህ ሲባል ሁልጊዜ በመካከላችሁ ስምምነት ይኖራል ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ ጓደኝነታችሁ በየጊዜው የሚቋረጥ መሆኑ አና እንደተናገረችው መፍትሔ የሚያሻው አንድ ችግር እንዳለ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። እንዲህ ብላለች፦ “ከወንድ ጓደኛዬ ጋር የነበረን ግንኙነት በተደጋጋሚ ጊዜያት ይቋረጥ የነበረ ሲሆን ይህም ስሜቴን በጣም ጎድቶታል። ብዙውን ጊዜ ግንኙነታችን ከተቋረጠ በኋላ እንደገና ለማደስ ጥረት አደርግ ነበር፤ የተሻለ የሚሆነው ግን እንደተለያየን ብንቀር ነበር።”

የጾታ ግንኙነት እንድንፈጽም ጫና ያደርግብኛል። “የምትወጂኝ ቢሆን ታደርጊው ነበር።” “ግንኙነታችን አብሮ ጊዜ በማሳለፍ ብቻ መወሰን የለበትም።” “ቃል በቃል የጾታ ግንኙነት እስካልፈጸምን ድረስ በሌሎች መንገዶች ፍቅራችንን መግለጽ ችግር የለውም።” እነዚህ አባባሎች አንዳንድ ወንዶች፣ የጾታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ሴቶችን ለማሳመን የሚጠቀሙባቸው ማባበያዎች ናቸው። ያዕቆብ 3:17 “ከላይ የሆነው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጹሕ ነው” ይላል። ንጹሕ ሥነ ምግባር ያለውና ንጽሕናሽን ለመጠበቅ ስትዪ ያወጣሻቸውን ገደቦች የሚያከብርልሽ የወንድ ጓደኛ መምረጥ ይኖርብሻል። ካልሆነ ግን ይቅርብሽ!

ሌሎች ሰዎች ስለ እሱ አስጠንቅቀውኝ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “የሚሰጥህን ምክር የምታዳምጥ ከሆነ ይሳካልሃል፤ ካልሆነ ግን አይሳካልህም” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 15:22 ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርዥን) ጄሲካ እንዲህ ብላለች፦ “ግንኙነታችሁ ችግር እንዳለበት እየተሰማህ ጓደኝነታችሁ እንዲቀጥል እንደማታደርግ ሁሉ ቤተሰቦችህና የረጅም ጊዜ ጓደኞችህ የሚሰጡህን ሐሳብም በቸልታ ማለፍ አይኖርብህም። ሌሎች የሚሉትን ነገር ችላ ባልክ ቁጥር የበለጠ በራስህ ላይ ችግር ታመጣለህ።”

እስከ አሁን የተመለከትነው ከወንድ ጓደኛሽ ጋር ግንኙነታችሁን መቀጠላችሁ ችግር ሊኖረው እንደሚችል ከሚጠቁሙት ምልክቶች ጥቂቶቹን ብቻ ነው። * በመጠናናት ላይ ከሆንሽ የወንድ ጓደኛሽን ከላይ ከቀረቡት ሐሳቦች አንጻር ስትመዝኚው እንዴት ነው? የሚሰማሽን ነገር ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጻፊ።

․․․․․

ጓደኝነታችሁን ማቆም የምትችዪው እንዴት ነው?

ጓደኝነታችሁን ማቆሙ የተሻለ እንደሆነ ተሰምቶሻል እንበል። ታዲያ ይህን ማድረግ የምትችዪው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረግ የምትችዪባቸው በርካታ መንገዶች ቢኖሩም የሚከተሉትን ነጥቦች በአእምሮሽ መያዝሽ ጥሩ ይሆናል።

ደፋር ሁኚ። ትሪና የተባለች ወጣት “ያለ እሱ መኖር እንደማልችል ይሰማኝ ስለነበር ከእሱ መለየት በጣም ፈርቼ ነበር” በማለት ተናግራለች። ጓደኝነታችሁን ማቆሙ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ይህን ገልጾ መናገር ድፍረት ይጠይቃል። ስሜትሽን በግልጽ በመናገር አቋምሽን ማሳወቅሽ ተገቢ ነው። (ምሳሌ 22:3) እንዲህ ማድረግሽ ከአንድ ሰው ጋር በምትጠናኚበት ጊዜም ይሁን ወደፊት ትዳር ስትመሠርቺ መታገሥ የምትችያቸውንና የማትችያቸውን ነገሮች በተመለከተ ግልጽ አቋም እንዲኖርሽ ያስችልሻል።

ራስሽን በእሱ ቦታ አስቀምጪ። አንቺ በእሱ ቦታ ብትሆኚ ኖሮ ጓደኝነታችሁ መቆም እንዳለበት እንዴት እንዲነግርሽ ትመርጪ ነበር? (ማቴዎስ 7:12) ለወንድ ጓደኛሽ “ግንኙነታችን እዚህ ላይ ያበቃል!” የሚል አጭር መልእክት በኢሜይል ወይም በስልክ ከመላክ ያለፈ ነገር ማድረግ እንዳለብሽ የታወቀ ነው።

ለመነጋገር አመቺ የሆነ ቦታና ጊዜ ምረጪ። በአካል አግኝተሽው ማነጋገር ይኖርብሽ ይሆን ወይስ በስልክ? ደብዳቤ መጻፍ ያስፈልግሽ ይሆን ወይስ ተገናኝታችሁ መወያየት? አብዛኛውን ጊዜ ይህን የሚወስኑት ያሉት ሁኔታዎች ናቸው። ከወንድ ጓደኛሽ ጋር ለመነጋገር የምትመርጪው ጊዜና ቦታ ደኅንነትሽን አደጋ ላይ የሚጥል መሆን አይኖርበትም። እንዲሁም መጥፎ ምኞቶች ሊቀሰቀሱ ስለሚችሉ ገለል ባለ አካባቢ መሆን ጥበብ አይደለም።—1 ተሰሎንቄ 4:3

እውነቱን ንገሪው። ጓደኝነታችሁ መቆም እንዳለበት የተሰማሽ ለምን እንደሆነ በግልጽ ንገሪው። የወንድ ጓደኛሽ በምትፈልጊው መንገድ እንዳልያዘሽ ተሰምቶሽ ከሆነ ይህንኑ ንገሪው። አነጋገርሽ አንቺ የሚሰማሽን ስሜት ብቻ የሚያንጸባርቅ ይሁን። ለምሳሌ ያህል፣ “አንተ ሁልጊዜ ዝቅ አድርገህ ነው የምትመለከተኝ” ከማለት ይልቅ “. . . ስትል ዝቅ አድርገህ እንደምትመለከተኝ ይሰማኛል” ማለት ትችያለሽ።

አንቺም ለማዳመጥ ፈቃደኛ ሁኚ። በተሳሳተ መንገድ የተረዳሽው ነገር ይኖር ይሆን? በአንደበቱ እንዳይደልልሽ ግን ተጠንቀቂ። በሌላ በኩል ደግሞ ምክንያታዊ መሆንሽና ያሉትን ሁኔታዎች ግምት ውስጥ ማስገባትሽ አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ለክርስቲያኖች ‘ለመስማት የፈጠናችሁ፣ ለመናገር የዘገያችሁ ሁኑ’ የሚል ጥበብ ያዘለ ምክር ይሰጣል።—ያዕቆብ 1:19

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.6 ምንም እንኳ ይህ ትምህርት የተዘጋጀው ከሴቶች አንጻር ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቱ ለወንዶችም ይሠራል።

^ አን.16 ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የግንቦት 2007 ንቁ! መጽሔት ገጽ 18-20⁠ን ተመልከት።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

ለትዳር የምታስቢው ሰው ሊኖሩት ይገባል ብለሽ የምታስቢያቸውን ባሕርያት ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጻፊ። ․․․․․

ተገቢ እንዳልሆኑ የምታስቢያቸው ባሕርያት የትኞቹ ናቸው? ․․․․․

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የወንድ ጓደኛሽ እንዲሆን የምትመርጪው ሰው . . .

□ እምነትሽን የሚጋራ መሆን ይኖርበታል።—1 ቆሮንቶስ 7:39

□ የሥነ ምግባር ንጽሕናሽን ለመጠበቅ ስትዪ ያወጣሻቸውን ገደቦች የሚያከብርልሽ መሆን አለበት።—1 ቆሮንቶስ 6:18

□ ለአንቺም ሆነ ለሌሎች የሚያስብ ሊሆን ይገባል።—ፊልጵስዩስ 2:4

□ በሌሎች ዘንድ ጥሩ ስም ያተረፈ መሆን ይኖርበታል።—ፊልጵስዩስ 2:20

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በወንድ ጓደኛሽ ላይ የሚከተሉትን ነገሮች ካስተዋልሽ ጥንቃቄ አድርጊ፦

□ ሁልጊዜ እሱ የሚልሽን ብቻ እንድታደርጊ ጫና ያሳድርብሻል?

□ ጥፋተኛ እንደሆንሽና ዋጋ እንደሌለሽ እንዲሰማሽ የሚያደርጉ ነገሮችን በተደጋጋሚ ይፈጽማል?

□ ከጓደኞችሽና ከቤተሰቦችሽ እንድትርቂ ለማድረግ ይሞክራል?

□ የት ገባሽ የት ወጣሽ ማለት ያበዛል?

□ ከሌሎች ወንዶች ጋር ጥሩ ያልሆነ ቅርርብ እንዳለሽ በማሰብ መሠረተ ቢስ የሆነ ክስ ይሰነዝርብሻል?

□ ያስፈራራሻል አሊያም ይዝትብሻል?

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጓደኝነት መቀጠል አደጋ እንደሚኖረው እያወቁ ችላ ማለት አንድ መኪና ችግር እንዳለው የሚጠቁሙ በዳሽ ቦርዱ ላይ የሚታዩትን የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ዝም ብሎ እንደማለፍ ይሆናል

CHECK OIL