ለሰው ልጆች የተደረገ ልዩ ዝግጅት
ለሰው ልጆች የተደረገ ልዩ ዝግጅት
የሰው ልጆች የሚያስፈልጋቸው አየር፣ ምግብና ውኃ ብቻ አይደለም። እውነተኛ ደስታ እንዲኖረን መንፈሳዊ ፍላጎታችን መሟላት አለበት። የሕይወትን ዓላማ ማለትም የተፈጠርንበትን ምክንያት ማወቅ ያስፈልገናል። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው” ብሏል።—ማቴዎስ 5:3
አምላክ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት በዓለም ዙሪያ በስፋት የተሰራጨውን ቅዱስ መጽሐፍ ሰጥቶናል፤ መጽሐፍ ቅዱስ በአሁኑ ጊዜ በሙሉ ወይም በከፊል በ2,400 ቋንቋዎች ገደማ ይገኛል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ አጽናፈ ዓለምንም ሆነ በምድር ላይ ያለውን ሕይወት በሙሉ እንደፈጠረ ይነግረናል። (ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 እና 2) ሌላው ቀርቶ አምላክ የፍጥረት ሥራውን ምሳሌያዊ በሆኑ ስድስት “ቀናት” ወይም የተወሰኑ ጊዜያት እንደከፋፈላቸው የሚነግረን ሲሆን የአከፋፈሉ ቅደም ተከተል ሳይንቲስቶች ከምድር አፈጣጠር ጋር በተያያዘ ከሚሰጡት ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነው።
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ይገልጻል። ይህ ዓላማ በመዝሙር 37:29 ላይ እንደሚከተለው በማለት ተገልጿል፦ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።” እዚህ ጥቅስ ላይ ጻድቃን ማለትም በሥነ ምግባርም ሆነ በመንፈሳዊ ንጹሕ የሆኑ ሰዎች በሰማይ ሳይሆን በምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ እንደተባለ ልብ በል። እርግጥ ነው፣ ምድር አሁን እንደምንመለከታት የተበከለች ፕላኔት አትሆንም። ከዚህ ይልቅ መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች።—መዝሙር 104:5፤ ሉቃስ 23:43
ወደ ሕይወት የሚመራ እውቀት
ምድር በሁለት መንገድ ገነት ትሆናለች፤ ይኸውም ግዑዟ ምድር ቃል በቃል ወደ ገነትነት የምትለወጥ ከመሆኑም ሌላ ሰዎች ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ስለሚኖራቸው በመንፈሳዊም ገነት ትሆናለች። ኢሳይያስ 11:9 “ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን፣ ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] በማወቅ ትሞላለች” ይላል። በሰዎች ልብ ላይ የሚጻፈው ይህ እውቀት በአሁኑ ጊዜም ቢሆን እውነተኛ ክርስቲያኖች እርስ በርስ በሰላም ተስማምተው እንዲኖሩ አስችሏል። ከዚህም በላይ እነዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ኢየሱስ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ በቁም ነገር ይመለከቱታል፦ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ስለሆንከው ስለ አንተና ስለላክኸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል አለባቸው።”—ዮሐንስ 17:3
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተገለጸው ተስፋ የበለጠ ማወቅ ከፈለግህ የይሖዋ ምሥክሮች ያለምንም ክፍያ ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው። *
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.7 www.watchtower.org በዚህ ድረ ገጽ አማካኝነትም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘት ትችላለህ።