በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማርስ ወደ ምድር ቀረብ አለች

ማርስ ወደ ምድር ቀረብ አለች

ማርስ ወደ ምድር ቀረብ አለች

በነሐሴ 2003፣ ማርስ መኖሪያችን ከሆነችው ፕላኔታችን ያላት ርቀት ወደ 56 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ዝቅ ያለ ሲሆን ይህም ወደ 60,000 በሚጠጉ ዓመታት ጊዜ ውስጥ በጣም ቀረብ ያለችበት ወቅት ነው። ይህ ርቀት በከዋክብት ጥናት ቀመር መሠረት ቀይዋን ፕላኔት በጓሯችን ያለች ያህል ያደርጋታል፤ ይህ ደግሞ ስለ ከዋክብትና ስለ ፕላኔት ለሚያጠኑ ሰዎች አስደሳች ዜና ነው።

በ2004 መጀመሪያ አካባቢ በርካታ ቁጥር ያላቸው የጠፈር መንኮራኩሮች ወደ ማርስ ተጓዙ። ከእነዚህ መንኮራኩሮች መካከል አንዳንዶቹ ፕላኔቷ ላይ በማረፍ የሚያጠኑ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ዙሪያዋን በመዞር አሰሳ ያካሂዳሉ። ይህ ጥናት ጎረቤታችን ስለሆነችው ፕላኔት ምን አስተምሮናል?

በቀይዋ ፕላኔት ላይ የተደረገ አሰሳ

ማርስ ግሎባል ሰርቪየር የተባለችው መንኮራኩር በ1997 ማርስ ላይ ደረሰች። ይህች መንኮራኩር ማርስ በአንድ ወቅት ኃይለኛ መግነጢሳዊ መስክ እንደነበራት አረጋግጣለች። በተጨማሪም መንኮራኩሯ የማርስን አጠቃላይ ገጽ ጥሩ አድርጎ የሚያሳይ ካርታ አንስታለች፤ እንዲሁም ከሰበሰበቻቸው መረጃዎች መካከል አንዱ ከፕላኔቷ ዝቅተኛ ቦታ አንስቶ እስከ ከፍተኛው ቦታ ያለው ርቀት ከ29 ኪሎ ሜትር እንደሚበልጥ ያሳያል። በምድር ላይ ግን ከዝቅተኛ ቦታ ተነስተን እስከ ከፍተኛ ቦታ ያለውን ርቀት ብንለካ ርቀቱ ከ19 ኪሎ ሜትር ጥቂት ከፍ የሚል ነው። *

በማርስ ላይ ያለው ዝቅተኛ ቦታ የሚገኘው ሔላስ ተብሎ በተሰየመው ሰፊ ሸለቆ ውስጥ ሲሆን ይህ ዝቅተኛ ቦታ የተፈጠረው ምናልባትም ፕላኔቷ በአንድ ግዙፍ አስትሮይድ በተመታችበት ጊዜ ሊሆን ይችላል። በማርስ ላይ የሚገኘው ከፍተኛ ቦታ ደግሞ በእሳተ ገሞራ የተፈጠረው ኦሊምፐስ ሞንስ የተባለው በጣም ግዙፍ ተራራ ሲሆን ከፍታውም 21 ኪሎ ሜትር ገደማ ነው። ማርስ ግሎባል ሰርቪየር በተባለችው መንኮራኩር ላይ የተገጠመው ካሜራ ከ18 ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸው ግዙፍ ቋጥኞችን፣ በየጊዜው ቦታቸውን የሚቀያይሩ የአሸዋ ክምሮችንና አዲስ የተፈጠሩ ቦዮችን ቀርጿል። ሌላኛው ሮቦት ደግሞ በፕላኔቷ ላይ ያሉት ድንጋዮች በእሳተ ገሞራ የተፈጠሩ እንደሆኑ አረጋግጧል።

ማርስ ግሎባል ሰርቪየር ከተባለችው መንኮራኩር ጋር ይደረግ የነበረው ግንኙነት ኅዳር 2006 የተቋረጠ ቢሆንም 2001 ማርስ ኦደሲ፣ ማርስ ኤክስፕረስና ማርስ ሪኮኒሰንስ ኦርቢተር የተባሉ ሌሎች ሦስት መንኮራኩሮች በቀይዋ ፕላኔት ላይ አሰሳ ማካሄዳቸውን ቀጥለዋል። * እነዚህ መንኮራኩሮች በጣም ዘመናዊ ካሜራዎችንና ጠቋሚ መሣሪዎችን በመጠቀም የማርስን ከባቢ አየርና ጠፈር ማጥናት ከመቻላቸውም በላይ በፕላኔቷ ሰሜናዊ ዋልታ አካባቢ በጣም ብዙ በረዶ እንዳለ ደርሰውበታል፤ አካባቢውንም ካርታ አንስተዋል።

ፎኔክስ ማርስ ላንደር የተባለች መንኮራኩር ግንቦት 25, 2008 ያለምንም ችግር ቀይዋ ፕላኔት ላይ ያረፈች ሲሆን ትኩረት ያደረገችውም በዚህ በረዶ ላይ ነበር። ይህች መንኮራኩር የፕላኔቷን ከባቢ አየርም ሆነ በዋልታዋ አካባቢ ያለውን በበረዶ የተጋገረ አፈር ወይም ፐርማፍሮስት ለመመርመር የሚያስችሉ የተራቀቁ መሣሪያዎች የተገጠሙላት ናት። ሳይንቲስቶች በዚህ በረዶ በሆነው አፈር ውስጥ ረቂቅ ተሕዋስያን ኖረው ያውቁ እንደሆነ ለመረዳት ጉጉት አላቸው። ይሁንና በዚህች ፕላኔት ላይ ሕይወት እንደነበረ ሌላው ቀርቶ ለሕይወት አመቺ ሁኔታ እንደነበር ለማወቅ ጥናት ማድረግ የተጀመረው ከዚህ ቀደም ብሎ ነው።

ስፕሪትና ኦፖርቹኒቲ የተባሉት አሳሽ ሮቦቶች

ስፕሪትና ኦፖርቹኒቲ የተባሉ ሁለት አሳሽ ሮቦቶች ጥር 2004 ማርስ ላይ የደረሱ ሲሆን የሚያርፉበት ቦታ የተመረጠው ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥናቶች ባሰባሰቡት መረጃ ላይ ተመሥርቶ ነው። ሮቦቶቹ የማርስን ከባቢ አየር አልፈው ያለምንም ችግር በላይዋ ላይ ማረፍ የቻሉት ሙቀት መከላከያ፣ ፓራሹትና ሮኬቶችን በመጠቀም ነው። እነዚህ ሮቦቶች መጠናቸው አራት ጎማ ያለው ጋሪ ያክላል። በ1997 ፕላኔቷ ላይ አርፋ እንደነበረችው ማርስ ፓዝፋይንደር የተባለች መንኮራኩር ሁሉ እነዚህ ርቦቶችም ያረፉት በአየር በተሞሉ ከረጢቶች ውስጥ ሆነው ነው። *

የማርስ ገጽ በምድር ላይ ካለው ደረቅ መሬት ጋር የሚመጣጠን ስፋት ስላለው በሮቦቶች አማካኝነት ምርምር ለማድረግ ሰፊ አጋጣሚ ፈጥሯል። ኦፓርቹኒቲ የተባለችው ሮቦት እንድታርፍበት የተመረጠው ሜሪዲያኒ ፕላኑም የተባለው ቦታ ሲሆን ይህ ሥፍራ ሂመታይት የተባለው በብረት የበለጸገ ማዕድን በብዛት የሚገኝባቸው ጥንታዊ ንብርብር አለቶች ያሉበት ነው። ስፕሪት የተባለችው ሮቦት ደግሞ ጉሲቭ በተባለ ሰፊ ጉድጓድ ላይ ጥናት ለማካሄድ በሌላኛው የማርስ ገጽ ላይ አርፋለች፤ አንዳንድ ተመራማሪዎች ይህ ቦታ በጥንት ጊዜ ሐይቅ እንደነበር ይገምታሉ። የእነዚህ ሁለት ጥናቶች ዓላማ “በአንድ ወቅት እርጥብና ለሕይወት አመቺ ሳይሆኑ አይቀሩም ተብለው የሚገመቱት አካባቢዎች ቀደም ሲል የነበራቸውን የአየር ጠባይ ማጥናት” እንደነበር ብሔራዊ የበረራና የሕዋ አስተዳደር ያዘጋጀው አንድ ጽሑፍ ይገልጻል።

በማርስ ላይ የሚገኙ “ጂኦሎጂስቶች”

ስፕሪት የተባለችው ሮቦት ጥር 4, 2004 የታቀደላት ቦታ ስትደርስ ያረፈችበት ቦታ ድንጋይ የሞላበት ጭው ያለ በረሃ ሲሆን ክብ ቅርጽ ያላቸው ሰርጎድ ያሉ ቦታዎችም በብዛት ይታዩበት ነበር። ይህች ሮቦት የተለያዩ የአፈር ዓይነቶችን፣ አለቶችንና የአካባቢውን አቀማመጥ በመመርመር ልክ እንደ አንድ ሰብዓዊ ጂኦሎጂስት በማርስ ገጽ ላይ ጥናት አካሂዳለች። ሮቦቷን የሚቆጣጠሩት ሳይንቲስቶች ያረፈችበት ቦታ በእሳተ ገሞራ ድንጋዮችና ሚቲዮራይትስ በፈጠሯቸው ጉድጓዶች የተሞላ መሆኑን አረጋግጠዋል። ስፕሪት በአንድ አካባቢ የሚገኙ ኮረብታዎችን ለማጥናት 2.6 ኪሎ ሜትር ተጉዛለች። እዚያም ለየት ያሉ አለቶችንና በእሳተ ገሞራ እንደተፈጠሩ የሚገመቱ ጠፍጣፋ ድንጋዮችን ማግኘት ችላለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጥር 25, 2004 ኦፖርቹኒቲ የተባለችው ሮቦት 456 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ተጉዛ የታለመላት ቦታ ለመድረስ 25 ኪሎ ሜትር ብቻ ሲቀራት አርፋለች። ይህችን ሮቦት ሸፍኗት የነበረው በአየር የተሞላ ከረጢት ሜሪዲያኒ በተባለ ሜዳማ አካባቢ ላይ ካረፈ በኋላ ተንከባሎ ወደ አንድ አነስተኛ ጎድጓዳ ሥፍራ ገባ። አንድ ሳይንቲስት ይህን ሁኔታ የጎልፍን ኳስ “በፕላኔት ላይ በሚገኝ ጉድጓድ ውስጥ” በአንድ ምት ከማስገባት ጋር አመሳስለውታል!

ኦፖርቹኒቲ፣ በሂመታይት ማዕድን የበለጸጉ ክብ ቅርጽ ያላቸው ንብርብር አለቶችን በያዙ በርካታ ጉድጓዶች ላይ ጥናት አካሂዳለች። እነዚህ ድንጋዮች ሰማያዊ እንጆሪዎች የሚል ቅጽል ስም ወጥቶላቸዋል። ምንም እንኳ እነዚህ ድንጋዮች ሰማያዊ ቀለም ባይኖራቸውም ይህን ስያሜ ያገኙት በዙሪያቸው ካለው ቀይ አፈርና ድንጋይ አንጻር ሲታዩ ያላቸው ግራጫ ቀለም ደመቅ ብሎ ስለሚታይ ነው። አንዳንዶቹ ንብርብር አለቶች ውኃ በሚወርድበት ቦታ ላይ እንዳለ ደለል አሸዋ ሞገድ የሚመስል ቅርጽ አላቸው። አንዳንድ ሳይንቲስቶች የአለቶቹን ቅርጽ ማየታቸው እንዲሁም በአለቶቹ ውስጥ ክሎሪንና ብሮማይን የተባሉ ማዕድናትን ማግኘታቸው በአንድ ወቅት በዚህ ቦታ ላይ ጨዋማ ውኃ እንደነበረ ይጠቁማል የሚል እምነት እንዲያድርባቸው አድርጓል።

ፎኔክስ ማርስ ላንደር 2008 የተባለችው መንኮራኩር የማርስን ገጽ በተለይም በረዶ የሚገኝበትን ክልል በተመለከተ በርካታ መረጃ ልካለች። በዚህች ሮቦት ላይ የተገጠመው እጅ ከፕላኔቷ ገጽ ላይ አፈርና በረዶ ዝቆ በማውጣት ፎኔክስ ቁጥር ሁለት ውስጥ ለሚገኘው “ቤተ ሙከራ” ናሙና ይልካል። ያም ሆኖ፣ ይህ ተልእኮ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ለአጭር ጊዜ እንዲቆይ የታቀደ ነበር፤ ሳይንስ መጽሔት ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጽ ላንደር ሥራዋን ከጨረሰች ከጥቂት ወራት በኋላ የሚመጣው የማርስ ክረምት ፎኔክስን “እንደ ወፍራም ብርድ ልብስ በሆነው የካርቦን ዳይኦክሳይድ ጭጋግ” እንድትሸፈን ያደርጋታል።

ሳይንቲስቶች በመቶ ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኙ ፕላኔቶች ላይ ጥናት ማካሄድ መቻላቸው፣ ሰዎች ለአንድ ዓላማ ተባብረው ከሠሩ ምን ሊያከናውኑ እንደሚችሉ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። እንዲህ ያለው ስኬት ሰዎች ምን ያህል ጥበብ እንዳላቸው ያሳያል። እርግጥ ነው የጠፈር ምርምር እንዲሁም በአጠቃላይ የሳይንስ ምርምር ስኬታማ ሊሆን የቻለው አጽናፈ ዓለምን የሚቆጣጠሩ ሕጎች ዝንፍ የማይሉና ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ በመሆናቸው ነው። እነዚህ ሕጎች እንዲሁ በራሳቸው የተገኙ አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ የጽንፈ ዓለምን ንድፍ ያወጣው ይሖዋ አምላክ የደነገጋቸው ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 ይህ 19 ኪሎ ሜትር፣ ፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ ካለው ማሪያና ትሬንች ከተባለው በጣም ዝቅተኛ ቦታ አንስቶ እስከ ኤቨረስት ተራራ ጫፍ ድረስ ያለውን ርቀት ያመለክታል።

^ አን.7 ማርስ ሪኮኒሰንስ ኦርቢተር እና 2001 ማርስ ኦደሲ የተባሉትን መንኮራኩሮች ወደ ማርስ ያመጠቀው ብሔራዊ የበረራና የሕዋ አስተዳደር (NASA) ሲሆን ማርስ ኤክስፕረስን ያመጠቀው ደግሞ የአውሮፓ የጠፈር ድርጅት ነው።

^ አን.10 በሰኔ 22, 1998 ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “ኤ ሮቦት ኤክስፕሎርስ ማርስ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በማርስ ላይ ሕይወት አለ?

ሰር ዊሊያም ኸርሸል እና ፐርሲቨል ሎዌል የተባሉ በ18ኛውና በ19ኛው መቶ ዘመን የኖሩት የከዋክብት ተመራማሪዎች ቀይዋ ፕላኔት በአንድ ወቅት የማሰብ ችሎታ ያላቸው ሕያዋን ፍጥረታት ይኖሩባት እንደነበረች የተናገሩ ሲሆን ይህ ደግሞ የዳርዊንን የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ የሚደግፍ ይመስላል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ ጽንሰ ሐሳቦች መላ ምት ብቻ ሆነው ቀርተዋል። የሳተላይት መረጃዎች፣ የማርስ ገጽ ጠፍ መሆኑንና ስስ የሆነው ከባቢ አየሯም በአብዛኛው በካርቦን ዳይኦክሳይድ የተሞላ እንደሆነ ያሳያሉ። ቫይኪንግ 1 ላንደር የተባለችው መንኮራኩር በ1976 ያደረገችው ምርምር በማርስ ላይ ምንም ሕይወት እንደሌለ አረጋግጧል። *

ያም ሆኖ ሳይንቲስቶች በማርስ ላይ ሕይወት እንደነበረ የሚጠቁሙ ምልክቶችን ለማግኘት ምርምር ማድረጋቸውን የቀጠሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ይህን ምርምር እያደረጉ ያሉት ፎኔክስ ማርስ ላንደር በተባለችው መንኮራኩር አማካኝነት ነው። ሳይንቲስቶች፣ ለሕይወት አመቺ ባልሆነው የምድር ክፍል ላይ አንዳንድ ረቂቅ ተሕዋስያን በሕይወት መቀጠል ስለቻሉ እነዚሁ ተሕዋስያን በማርስ አንዳንድ ቦታዎች ላይም ሊኖሩ እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። ማርስ ኤክስፕረስ ከተባለው መንኮራኩር ጋር ተያይዛ የነበረችው ቢግል 2 የተባለችው መንኮራኩር በማርስ አፈር ውስጥ ሕይወት ያላቸው ነገሮች መኖር አለመኖራቸውን ለመመርመር የሚያስችሉ መሣሪያዎች ተገጥመውላት ነበር፤ ሆኖም በ2003 መጨረሻዎቹ አካባቢ ይህችን መንኮራኩር ማርስ ላይ ለማሳረፍ የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀረ። በቀጣዩ ዓመት ሳይንቲስቶች በማርስ ከባቢ አየር ውስጥ ሜቴን የተባለ ጋዝ እንዳለ የሚያሳይ ፍንጭ ማግኘታቸው ይህ ጋዝ የተገኘው ሕይወት ካላቸው ነገሮች አሊያም ከእሳተ ገሞራ ነው የሚል ግምት እንዲያድርባቸው አደረገ።

በአጽናፈ ዓለም በየትኛውም ቦታ ሕይወት እንዲሁ በአጋጣሚ ሊገኝ ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ “የሕይወት ምንጭ ከአንተ [ከአምላክ] ዘንድ ነው” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 36:9) አዎ፣ ሕይወት ሊገኝ የሚችለው ሕይወት ካለው ነገር ብቻ ነው፤ የሕይወት ምንጭ ደግሞ ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 17:25

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.24 በሰኔ 2000 ንቁ! መጽሔት እትም ላይ የወጣውን “ቀይዋ ፕላኔት ዳግመኛ ስትጎበኝ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[ምንጭ]

NASA/JPL/Cornell

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መዛቂያ፣ መመርመሪያ መሣሪያና ካሜራ የተገጠመለት የፎኔክስ ማርስ ላንደር እጅ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ደመቅ እንዲሉ የተደረጉትን “ሰማያዊ እንጆሪዎች” የሚያሳይ ፎቶ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኦሊምፐስ ሞንስ የተባለው 21 ኪሎ ሜትር ከፍታ ያለው ጥፍ ገሞራ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስፕሪት የተባለችው አሳሽ ሮቦት የቦረቦረችውና የፋቀችው አለት

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከላይ በስተግራ፦ NASA/JPL-Caltech/University of Arizona/Texas A&M University; ከላይ በስተቀኝ፦ NASA/JPL/Malin Space Science Systems; ከታች በስተግራና በስተቀኝ፦ NASA/JPL/Cornell