ቢላዋ የሚስለው ብስክሌት
ቢላዋ የሚስለው ብስክሌት
ታንዛኒያ የሚገኘው የንቁ! ጸሐፊ እንዳዘጋጀው
▪ በአንድ ብስክሌት ላይ ፊቱን አዙሮ የተቀመጠ አንድ ሰው የብስክሌቱን ፔዳል በኃይል እየመታው ቢሆንም ብስክሌቱ ከቦታው ንቅንቅ አላለም፤ እንዲህ ያለ ሁኔታ ብታይ ምን ትላለህ? በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ለምሳሌ በምሥራቅ አፍሪካ፣ ለአካባቢው ኅብረተሰብ በዚህ መልኩ ቢላዋ በመሳል የሚተዳደር ሰው ተመልክተህ ይሆናል።
ይህ ሰው ቢላዋ ለመሳል የሚጠቀምበት ብስክሌት፣ እንደማንኛውም ብስክሌት ቢሆንም አንዳንድ አስፈላጊ ለውጦች ተደርጎበታል። በብስክሌቱ የዕቃ መጫኛ ላይ ለመሳል የሚያገለግል ክብ ድንጋይ ተገጥሟል። የናይለን ሲባጎ የሆነው ማሽከርከሪያው ከብስክሌቱ የኋላ ጎማ ጋር በተበየደው ለሁለት የተሰነጠቀ ሌላ የብስክሌት ቸርኬ ዙሪያ ተጠምጥሟል።
አስደናቂ የሆነው ይህ የቢላዋ መሳያ ወደ አፍሪካ የገባው እንዴት እንደሆነ በእርግጠኝነት አይታወቅም። ከ1985 ጀምሮ በዚህ መንገድ ቢላዋ በመሳል እየተዳደረ ያለው አንድሪያ እንዲህ ብሏል፦ “እነዚህ ብስክሌቶች፣ እኔ በምኖርባት በሞሺ ከተማ አገልግሎት መስጠት ከመጀመራቸው በፊት የታንዛኒያ ዋና ከተማ በሆነችው በዳሬ ሰላም ይሠራባቸው እንደነበር ሰምቻለሁ።” አክሎም “ብስክሌቱ በዚህ ከተማ አገልግሎት ላይ የዋለው በ1982 ነው” ብሏል።
አንድ ሰው፣ ቢላዋ የሚስል ብስክሌት ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው? አንድሪያ “ወደ ፈንዲ (በስዋሂሊ ‘የእጅ ሞያተኛ’ ማለት ነው) እንሄድና ብስክሌታችንን በምንፈልገው መሠረት እንዲሠራልን እንነግረዋለን” በማለት ገልጿል። አብዛኛውን ጊዜ ይህን ለመሥራት አንድ ወይም ሁለት ቀን ይፈጃል።
የእሳት ፍንጣሪዎች እና ላብ!
አንድሪያ የዕለቱን ውሎ የሚጀምረው ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ገደማ ነው፤ በዚህ ጊዜ ብስክሌቱን እየነዳ ሕዝብ ወደሚበዛበት አካባቢ ይሄዳል። እዚያም ሲደርስ ድምፁን ከፍ አድርጎ “የሚሳል ቢላዋ ያለው! የሚሳል ቢላዋ ያለው!” ይላል። በተጨማሪም የብስክሌቱን ደወል ይደውላል። ብዙም ሳይቆይ አንዲት የቤት እመቤት በመስኮት ብቅ ብላ አንድሪያን ትጠራውና የደነዙ ሁለት ቢላዎችን ትሰጠዋለች። የሴትየዋ ጎረቤት ቆንጨራ ስታመጣ፤ አንድ የፀጉር አስተካካይ ደግሞ መቀሶቹን ይሰጠዋል። አንድሪያ ዶማዎችን፣ መሰርሰሪያዎችንና ስለት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ይስላል።
አንድሪያ ሥራውን ለመጀመር ሲዘጋጅ ደልዳላ መሬት ይፈልግና የብስክሌቱን ማቆሚያ አውርዶ የኋላውን ጎማ ከፍ በማድረግ ያቆመዋል። ከዚያም የናይለን ማሽከርከሪያውን ካያያዘ በኋላ ፊቱን አዙሮ ይቀመጣል። አንድሪያ ስለት ያላቸውን የተለያዩ ነገሮች በሚስልበት ጊዜ የእሳት ፍንጣሪዎች የሚፈጠሩ ከመሆኑም ሌላ ላብ በላብ ይሆናል። በዚህ መንገድ ከምሽቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ገደማ የዕለት ሥራውን ይጨርሳል።
ይህ ዘገባ፣ ማንኛውም ‘ትጉ’ የሆነ ሰው አስቸጋሪ በሆኑ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ሥር እንኳ ሳይቀር የፈጠራ ችሎታውን ተጠቅሞና በሐቅ ሠርቶ መተዳደሪያ የሚያገኘው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው።—ምሳሌ 13:4