ከወንድ ጓደኛዬ ጋር መለያየቴ ያስከተለብኝን ሐዘን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
የወጣቶች ጥያቄ
ከወንድ ጓደኛዬ ጋር መለያየቴ ያስከተለብኝን ሐዘን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
“ለአምስት ዓመት ጓደኛሞች የነበርን ሲሆን ለስድስት ወራት ያህል ደግሞ ስንጠናና ቆይተናል። ከእኔ ጋር የነበረውን ግንኙነት ለማቆም በወሰነበት ወቅት ፊት ለፊት ሊነግረኝ እንኳ አልፈለገም። ጭራሽ ዘጋኝ፤ ቅስሜ ተሰበረ። የደረሰብኝን ሐዘን መቋቋም አልቻልኩም። ‘ምን አድርጌው ይሆን?’ እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር።”—ሪቼል *
ከወንድ ጓደኛሽ ጋር የነበረሽ ግንኙነት ሲቋረጥ ደስታሽ ሁሉ ጠፍቶ በከባድ ሐዘን ልትዋጪ ትችያለሽ። ለምሳሌ ያህል፣ ለሁለት ዓመት ያህል ሲጠናኑ የቆዩትን የጄፍንና የሱዛንን ሁኔታ እንመልከት። በእነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ ጄፍና ሱዛን በጣም ተዋደው ነበር። ጄፍ በቀን ውስጥ በተደጋጋሚ የፍቅር መግለጫዎች የያዙ መልእክቶችን በሞባይል ይልክላት ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ፍቅሩን ለመግለጽ በየጊዜው ስጦታዎች ይሰጣት ነበር። ሱዛን እንዲህ ብላለች፦ “ጄፍ ትኩረት ሰጥቶ ያዳምጠኝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ስሜቴን ይረዳልኝ ነበር፤ እንዲሁም ተወዳጅ ሰው እንደሆንኩ ሆኖ እንዲሰማኝ ያደርገኝ ነበር።”
ብዙም ሳይቆይ ጄፍና ሱዛን ትዳር ስለ መመሥረት ብሎም ከተጋቡ በኋላ ስለሚኖሩበት ቦታ ማውራት ጀመሩ። ሌላው ቀርቶ ጄፍ ለሱዛን ቀለበት ሊሰጣት አስቦ ነበር። ይሁንና ጄፍ በድንገት ከእሷ ጋር የነበረውን ግንኙነት አቆመ! በዚህ ጊዜ ሱዛን በሐዘን ልቧ ተሰበረ። ስሜቷ በጣም ከመጎዳቱ የተነሳ የዕለት ተዕለት ተግባሯን ታከናውን የነበረው በደመ ነፍስ ነበር። “አእምሮዬም ሆነ ሰውነቴ በጣም ዝሎ ነበር” በማለት ተናግራለች። *
ስሜታቸው በጣም የሚጎዳው ለምንድን ነው?
አንቺም በሱዛን ላይ የደረሰው ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞሽ ከሆነ ‘የደረሰብኝን ሐዘን ተቋቁሜ እንደ ቀድሞው መሆን እችል ይሆን?’ ብለሽ ራስሽን ትጠይቂ ይሆናል። (መዝሙር 38:6) እንዲህ ያለ ጭንቀት ቢሰማሽ ምንም አያስገርምም። ከጓደኛሽ ጋር መለያየትሽ በሕይወትሽ ውስጥ ከባድ ሥነ ልቦናዊ ቀውስ አስከትሎብሽ ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲደርስባቸው በቁማቸው የሞቱ ያህል ሆኖ ይሰማቸዋል። እንዲያውም አንድ ሰው የሚወደውን ሰው በሞት ሲያጣ የሚሰሙት ስሜቶች ሊፈራረቁብሽ ይችላሉ። ከእነዚህ ስሜቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
እውነታውን አምኖ አለመቀበል። ‘በፍጹም፤ ይህ ሊሆን አይችልም! ከጥቂት ቀን በኋላ ሐሳቡን መቀየሩ አይቀርም።’
ንዴት። ‘እንዴት እንዲህ ያደርገኛል? ዓይኑን ማየት አልፈልግም!’
የመንፈስ ጭንቀት። ‘እኔ የምወደድ ሰው አይደለሁም። ከእንግዲህ እኔን ማንም ሊወደኝ አይችልም።’
እውነታውን አምኖ መቀበል። ‘የማያልፍ ነገር የለም። ግንኙነታችን መቋረጡ ስሜቴን የጎዳው ቢሆንም አሁን እያገገምኩ ነው።’
ደግነቱ ሁሉም ነገር አልፎ እውነታውን አምነሽ ወደመቀበል ደረጃ መድረስ ትችያለሽ። እርግጥ ነው፣ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚወስድብሽ ጊዜ እንደ ሁኔታው ይለያያል፤ በጓደኝነት ብዙ ጊዜ የቆያችሁ ከሆነና ግንኙነታችሁ በጣም ጠንክሮ ከነበረ እውነታውን አምነሽ ለመቀበል ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድብሽ ይችላል። ታዲያ የተሰማሽን ከባድ ሐዘን ለመቋቋም ምን ልታደርጊ ትችያለሽ?
ልትወስጃቸው የሚገቡ እርምጃዎች
አንዳንድ ሰዎች፣ በጊዜ ሂደት ማንኛውም ቁስል መዳኑ አይቀርም ብለው ሲናገሩ ሰምተሽ ይሆናል። መጀመሪያ ላይ ይህ አባባል ብዙም ትርጉም አይሰጥሽ ይሆናል። ምክንያቱም ጊዜ ብቻውን መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ ነገር ሲቆርጥሽ ቁስሉ ከጊዜ በኋላ የሚድን ቢሆንም ለጊዜው ማመሙ አይቀርም። በመሆኑም እየፈሰሰ ያለውን ደም እንዲቆም ማድረግና ህመሙን ማስታገስ ይኖርብሻል። በተጨማሪም ቁስሉ እንዳይመረዝ ጥንቃቄ ማድረግ አለብሽ። ከስሜት ቁስል ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። መጀመሪያ ላይ ሥቃይ ማስከተሉ አይቀርም። ይሁንና ሥቃዩን ለማስታገስ እንዲሁም ቁስሉ በጥላቻ ስሜት እንዳይመረዝ ለማድረግ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርብሻል። ጊዜ የራሱን ሚና መጫወቱ አይቀርም፤ ታዲያ አንቺ የበኩልሽን ድርሻ መወጣት የምትችይው እንዴት ነው? የሚከተሉትን ነገሮች ማድረግ ትችያለሽ፦
▪ ስሜትሽን አምቀሽ አትያዢ። የተሰማሽ ሐዘን እንዲወጣልሽ ብለሽ ብታለቅሺ ምንም ስህተት የለውም። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን ‘ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ ለሐዘንም ጊዜ አለው’ ይላል። (መክብብ 3:1, 4) ማልቀስ የድክመት ምልክት አይደለም። ደፋር ተዋጊ የነበረው ዳዊትም እንኳ ሳይቀር ስሜቱ በጣም ተጎድቶ በነበረበት ወቅት “ሌሊቱን ሁሉ በልቅሶ ዐልጋዬን አርሳለሁ፤ መኝታዬንም በእንባዬ አሾቃለሁ” ሲል ተናግሯል።—መዝሙር 6:6
▪ ጤንነትሽን ተንከባከቢ። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ ስሜትሽ በጣም በተጎዳበት ወቅት ያጣሽውን ኃይል መልሰሽ መተካት እንድትችይ ይረዳሻል። መጽሐፍ ቅዱስ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ . . . ይጠቅማል” ይላል።—1 ጢሞቴዎስ 4:8
ከጤንነትሽ ጋር በተያያዘ ትኩረት ልትሰጫቸው የሚገቡ ምን ጉዳዮች አሉ?
․․․․․
▪ በተለያዩ ነገሮች ራስሽን አስጠምጂ። የሚያስደስቱሽን ነገሮች ከማድረግ አትቆጠቢ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ራስሽን አታግልዪ። (ምሳሌ 18:1) ከሚያስቡልሽ ሰዎች ጋር መቀራረብሽ አዎንታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንድታተኩሪ ይረዳሻል።
ራስሽን በተለያዩ ነገሮች ለማስጠመድ ምን ግቦች ልታወጪ ትችያለሽ?
․․․․․
▪ የሚሰማሽን ነገር በጸሎት ለአምላክ ንገሪው። ምናልባት ይህን ማድረግ ቀላል ላይሆን ይችላል። እንዲያውም አንዳንዶች ከጓደኛቸው ጋር ሲለያዩ አምላክ እንደተዋቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። ‘የወንድ ጓደኛ ለማግኘት በተደጋጋሚ ጸልያለሁ፤ አሁን ግን ምን እንደደረሰብኝ ተመልከቱ!’ ይላሉ። (መዝሙር 10:1) ይሁንና አምላክ የትዳር ፈላጊዎች አገናኝ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ተገቢ ነው? በፍጹም ተገቢ አይደለም፤ ደግሞም አንደኛው ወገን ግንኙነቱን ለመቀጠል ፈቃደኛ ባይሆን አምላክ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም። ይሁን እንጂ ይሖዋ ‘ስለ አንቺ እንደሚያስብ’ እርግጠኞች ነን። (1 ጴጥሮስ 5:7) በመሆኑም የሚሰማሽን ሁሉ በጸሎት ንገሪው። መጽሐፍ ቅዱስ “ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል” በማለት ይናገራል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
ከጓደኛሽ ጋር መለያየትሽ ያስከተለብሽን የስሜት ቀውስ ለመቋቋም በምታደርጊው ጥረት ይሖዋ እንዲረዳሽ ምን ነገሮችን ለይተሽ በጸሎት መጥቀስ ትችያለሽ?
․․․․․
ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማሰብ
ከደረሰብሽ የስሜት ሥቃይ በሚገባ ካገገምሽ በኋላ ከጓደኛሽ ጋር የነበረሽን ግንኙነት መለስ ብለሽ በጥሞና ማሰብሽ ሊጠቅምሽ ይችላል። ይህን ለማድረግ የምትችይበት ደረጃ ላይ እንደደረስሽ ከተሰማሽ ለሚከተሉት ጥያቄዎች የምትሰጪያቸውን መልሶች በጽሑፍ ማስፈርሽ ይረዳሻል።
▪ ከአንቺ ለመለየት የወሰነበትን ምክንያት ነግሮሻል? ነግሮሽ ከሆነ ያቀረበልሽ ምክንያት አሳማኝ ሆነም አልሆነ ጻፊው።
․․․․․
▪ ጓደኝነታችሁ እንዲቋረጥ ምክንያት የሆኑ ሌሎች ነገሮች ይኖራሉ?
․․․․․
▪ የተፈጠረውን ሁኔታ መለስ ብለሽ ስታስቢ ግንኙነቱ እንዳይቋረጥ ልታደርጊ ትችይው የነበረ ነገር እንዳለ ይሰማሻል? ካለ ጻፊው።
․․․․․
▪ እንዲህ ያለ ሁኔታ መከሰቱ በስሜታዊም ይሁን በመንፈሳዊ ማሻሻያ ልታደርጊባቸው የሚገቡ አቅጣጫዎችን ጠቁሞሻል?
․․․․․
▪ ወደፊት መጠናናት ብትጀምሪ ልታሻሽዪው የሚገባ ነገር አለ?
․․․․․
ከጓደኛሽ ጋር የመሠረትሽው ግንኙነት መጨረሻው ያማረ እንዲሆን ትመኚ እንደነበር ጥርጥር የለውም። ከባድ ዝናብ እየጣለ ባለበት ወቅት ትኩረታችን በአብዛኛው የሚያርፈው በጠቆረው ሰማይና እየወረደ ባለው ዝናብ ላይ እንደሚሆን አትርሺ። ሆኖም ከጊዜ በኋላ ዝናቡ ማቆሙና ሰማዩ ጥርት ማለቱ አይቀርም። ቀደም ሲል በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ወጣቶች በጊዜ ሂደት ሙሉ በሙሉ ማገገም ችለዋል። አንቺም ካጋጠመሽ የስሜት ሥቃይ ማገገም እንደምትችይ ፈጽሞ አትጠራጠሪ!
www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.5 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት፣ ሴቶች ቢሆኑም መሠረታዊ ሥርዓቱ ለወንዶችም ይሠራል።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
▪ ቀደም ሲል ከጓደኛሽ ጋር የነበረሽ ግንኙነት ስለ ራስሽ ምን አስተምሮሻል?
▪ ስለ ተቃራኒ ጾታ ምን ትምህርት አግኝተሻል?
▪ ከጓደኛሽ ጋር የነበረሽ ግንኙነት መቋረጡ ያስከተለብሽ ሐዘን በጣም ከከበደሽ ስሜትሽን ለማን አውጥተሽ መግለጽ ትችያለሽ?
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
እንዲህ ብታደርጊ ጥሩ ነው፦
ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሱዛን የተወሰኑ ጥቅሶችን ጽፋ የያዘች ሲሆን ስሜቷ በጣም በሚረበሽበት ጊዜ አውጥታ ታነባቸዋለች። አንቺም በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱትን አንዳንድ ጥቅሶች በመጻፍ እንደ ሱዛን ማድረግ ትችያለሽ።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከጓደኛሽ ጋር መለያየትሽ የሚፈጥርብሽ ስሜት ከቁስል ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ በጣም ቢያምም በጊዜ ሂደት መዳኑ አይቀርም