በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዲስሌክሲያ ግቤ ላይ ከመድረስ አላገደኝም

ዲስሌክሲያ ግቤ ላይ ከመድረስ አላገደኝም

ዲስሌክሲያ ግቤ ላይ ከመድረስ አላገደኝም

ማይካል ሄንቦ እንደተናገረው

ዲስሌክሲያ የተባለ የማንበብ ችግር ያለብኝ ሲሆን አባቴ፣ እናቴና ሦስት ታናናሽ ወንድሞቼም ይህ የጤና እክል አለባቸው። ይህ ችግር የአፍ መፍቻ ቋንቋዬ በሆነው በደች ቋንቋ ማንበብ ከባድ እንዲሆንብኝ ከማድረጉም በላይ ትምህርት መከታተልም ቢሆን ለእኔ ተፈታታኝ ነበር። ይሁንና ከቤተሰቦቼ ከፍተኛ እርዳታና ማበረታቻ አግኝቻለሁ።

ከቅድመ አያቶቼ ጀምሮ ቤተሰቦቼ የይሖዋ ምሥክሮች ሲሆኑ በተለይ መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ማንበብ በቤተሰባችን ውስጥ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ነገር ነበር። እኔና ታናሽ ወንድሜ ፍሌሚንግም ከአባታችን ጋር በክርስቲያናዊ አገልግሎት እንካፈል ነበር፤ ይህም ጥሩ አድርጎ የማንበብንና የመጻፍን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ አድርጎናል።

ልጅ እያለሁ እያንዳንዱን የመጠበቂያ ግንብና የንቁ! መጽሔት እትም አነብብ የነበረ ሲሆን አንድ መጽሔት አንብቤ ለመጨረስ እስከ 15 ሰዓት ይፈጅብኝ ነበር! በተጨማሪም መላውን መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ጀመርኩ። በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ በሚካሄደው የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤትም ተመዘገብኩ። ይህ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በደንብ ማንበብና መናገር እንዲሁም በሰዎች ፊት ንግግር መስጠት እንዲችሉ ያሠለጥናል። እነዚህ ሁሉ ዝግጅቶች በዲስሌክሲያ ምክንያት ያለብኝን ችግር እንድቋቋም ረድተውኛል። ይሁን እንጂ ወደፊት ገና ብዙ ተፈታታኝ ችግሮች እንደሚጠብቁኝ አልተገነዘብኩም ነበር። ይህ የሆነበትን ምክንያት እስቲ ላጫውታችሁ።

እንግሊዝኛ መማር

በ1988፣ በ24 ዓመቴ አቅኚ ማለትም የምሥራቹ የሙሉ ጊዜ ሰባኪ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ዴንማርክ ከተለያዩ አገሮች በስደት የመጡ ሰዎች የሚኖሩባት ከተማ ስለሆነች ለእነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የመስበክ ፍላጎት አደረብኝ። ይሁን እንጂ ይህንን ለማድረግ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መማር ያስፈለገኝ ሲሆን ቋንቋውን መማር ደግሞ ለእኔ ከባድ ፕሮጀክት ነበር። ተስፋ ሳልቆርጥ ባደረግኩት ጥረትና በግል በተሰጠኝ እርዳታ እንግሊዝኛ ቋንቋዬን ያሻሻልኩ ሲሆን ከጊዜ በኋላ በተወለድኩባት ከተማ በኮፐንሃገን ለሚኖሩ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ለሆኑ የውጪ አገር ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች መስበክ ጀመርኩ። ቋንቋውን ስናገር በርካታ ጊዜ እሳሳት የነበረ ቢሆንም ይህ ግን ቋንቋውን ከመማርና ከመስበክ ወደኋላ እንድል አላደረገኝም።

የእንግሊዝኛ ቋንቋ መማሬ የይሖዋ ምሥክሮች በተለያዩ አገሮች ውስጥ በሚያካሂዷቸው የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆኜ እንዳገለግል ረድቶኛል። መጀመሪያ ግሪክ የተመደብኩ ሲሆን በኋላም በማድሪድ ስፔን የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ሲገነባ ረድቻለሁ።

በስብከቱ ሥራ የማደርገውን ተሳትፎ ከፍ ማድረግ ስለፈለግሁ በይሖዋ ምሥክሮች በተቋቋመው የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ገብቼ ለመማር አመለከትኩ። ይህ ትምህርት ቤት የምሥራቹ አገልጋዮች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው ለማገልገል ፈቃደኛ ለሆኑ ያላገቡ ክርስቲያን ወንዶች ስምንት ሳምንታት የሚፈጅ ልዩ ሥልጠና ይሰጣል። (ማርቆስ 13:10) በስዊድን አገር በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚሰጠው የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት እንድካፈል ተጋበዝኩ።

እኔ የተካፈልኩበት ሥልጠና የጀመረው መስከረም 1, 1994 ነበር። እኔም ለትምህርቱ ጥሩ ዝግጅት ለማድረግ ስል ለስምንት ወራት በየቀኑ ለአራት ሰዓታት እንግሊዝኛ አጠና የነበረ ሲሆን በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤም እሰበሰብ ነበር። ትምህርት ቤቱ ከተጀመረም በኋላ ላለብኝ ችግር እጄን አልሰጠሁም። ለምሳሌ ያህል፣ አስተማሪው ጥያቄ ሲጠይቅ መጠቀም ያለብኝን ትክክለኛ ቃላት ባላውቅም እንኳ አብዛኛውን ጊዜ መልስ ለመስጠት እጄን አወጣ ነበር። ከትምህርት ቤቱ ከተመረቅሁ በኋላ በኮፐንሃገን አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። እንግሊዝኛ ቋንቋ መማር በጣም ተፈታታኝ ቢሆንብኝም ከዚህ የበለጠ ከባድ ቋንቋ መማር ገና ይጠብቀኝ ነበር።

የታሚል ቋንቋ መማር

ታኅሣሥ 1995፣ ኸርኒግ በተባለች የደች ከተማ ውስጥ በሚገኝ በታሚል ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ እንዳገለግል ተመደብኩ። የታሚል ቋንቋ በዓለም ላይ ካሉት ለመማር አስቸጋሪ ከሆኑ ቋንቋዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ይሰማኛል። ይህ ቋንቋ 31 ሆሄያትን እንዲሁም ተነባቢና አናባቢ ሆሄያትን አንድ ላይ በማጣመር የሚፈጠሩ ሌሎች ፊደላትን ጨምሮ ወደ 250 ገደማ የሚሆኑ ፊደላት አሉት!

መጀመሪያ ላይ ለጉባኤው ንግግር አቀርብ የነበረው በደች ቋንቋ ሲሆን ወደ ታሚል ቋንቋ ይተረጎም ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ በታሚል ቋንቋ ንግግር ባቀረብኩበት ወቅት ንግግሩ የገባው ሰው ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ። ብዙዎቹ ግራ የገባቸው ቢመስሉም በአክብሮት ያዳምጡኝ ነበር። ይህን ቋንቋ በፍጥነት መማር ስለፈለግሁ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የታሚል ቋንቋ ተናጋሪዎች ወዳሉባት ወደ ስሪላንካ ለመሄድ ወሰንኩ።

ጥቅምት 1996፣ ስሪላንካ ስደርስ አገሪቱ በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች ነበር። ለተወሰነ ጊዜ በሁለቱ ተዋጊ አንጃዎች መሃል በምትገኝ ቫቩቢያ በተባለች ከተማ ተቀምጫለሁ። በዚያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ቁሳዊ ነገር ባይኖራቸውም የሚያሳዩት ፍቅርና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አስገራሚ ነበር፤ እኔን የታሚል ቋንቋ ለማስተማር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች በዚያ አካባቢ ካሉ ምዕራባውያን ሰዎች ሁሉ እነሱን በቋንቋቸው ለማናገር ጥረት የማደርገው እኔ ብቻ ስለነበርኩ ይገረሙ ነበር። የአገሩ ሰዎች አድናቂዎችና ትሑቶች ስለሆኑ እነሱን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማናገር አይከብደኝም ነበር።

ጥር 1997 የግድ ወደ ዴንማርክ መመለስ ነበረብኝ፤ ከዚያም በቀጣዩ ዓመት ካሚላ የተባለች አቅኚ አገባሁ። የስሪላንካ ነገር ልቤ ውስጥ ገብቶ ስለነበር ታኅሣሥ 1999 ወደዚች አገር ከባለቤቴ ጋር ተመልሼ ሄድኩ። በአጭር ጊዜ ውስጥ የተለያዩ ቤተሰቦችንና ግለሰቦችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት የጀመርን ሲሆን በዚያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በጥናቶቻቸው ላይ እንድንገኝ ይጋብዙን ነበር። ቋንቋውን በማጥናትም ሆነ በስብከቱ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠምደን ነበር።

ይሁን እንጂ መጋቢት 2000 ወደ ዴንማርክ መመለስ ነበረብን። ወንድሞችንም ሆነ ጥናቶቻችንን በጣም ስለምንወዳቸው ከእነሱ መለየት ከብዶን ነበር። ሆኖም ሌላ ቋንቋ መማርን የሚጠይቅ ተጨማሪ ሥራ ከፊታችን ይጠብቀን ነበር።

ከታሚል ቋንቋ ወደ ላትቪያ ቋንቋ

እኔና ካሚላ በተጋባን በአራት ዓመታችን ማለትም ግንቦት 2002 ከዴንማርክ በስተ ምሥራቅ በምትገኘው ላትቪያ በምትባል አንዲት አውሮፓዊት አገር ሚስዮናውያን ሆነን እንድናገለግል ግብዣ ቀረበልን። ካሚላ የላትቪያን ቋንቋ በአጭር ጊዜ በመማር በስድስት ሳምንታት ውስጥ ከሰዎች ጋር መግባባት ቻለች! እኔ ግን እንደ እሷ በቶሎ ቋንቋውን መማር አልቻልኩም። እርግጥ ነው፣ ቋንቋውን እንድማር ብዙ እገዛ የተደረገልኝ ቢሆንም አሁንም ቢሆን የሚፈለግብኝን ያህል መሻሻል እንዳላደረግሁ ይሰማኛል። ሆኖም ተስፋ ሳልቆርጥ ጥረት ማድረጌን እቀጥላለሁ። *

ካሚላ ጥሩ ድጋፍ እየሰጠችኝ ሲሆን ሁለታችንም በሚስዮናዊነት አገልግሎታችን ደስተኞች ነን። ደግሞም አድናቆት ያላቸውን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እያስጠናን ነው። በዚያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቃላቶች ሲጠፉኝ ወይም ትክክል ያልሆነ ሰዋሰው ስጠቀም ለማለት የፈለግሁትን ነገር ለመረዳትና እኔን ለማገዝ ይሞክራሉ። ይህ ደግሞ ለሰዎች ስሰብክም ሆነ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ንግግር ስሰጥ እንዳልሸማቀቅ ረድቶኛል።

ለእኔ ቋንቋ መማር ከባድ ትግል የሚጠይቅብኝ ሆኖ ሳለ ተጨማሪ ቋንቋ ለመማር የወሰንኩት ለምንድን ነው? በአጭሩ ለመናገር ያህል ለቋንቋ ሳይሆን ለሰዎች ፍቅር ስላለኝ ነው። አንድን ሰው ስለ እውነተኛው አምላክ ስለ ይሖዋ እንዲያውቅና ወደ እሱ እንዲቀርብ መርዳት ታላቅ መብት ነው። ከበርካታ ሚስዮናውያን ተሞክሮ እንደታየው ደግሞ ይህን ሥራ ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ማከናወን የሚቻለው ሰዎችን በራሳቸው ቋንቋ ማናገር ሲቻል ነው።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ እኔና ባለቤቴ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲያውቁ መርዳት ችለናል። ይሁን እንጂ ላገኘነው ጥሩ ውጤት ሊመሰገን የሚገባው ይሖዋ እንጂ እኛ አይደለንም፤ ለዚህ ደግሞ ይሖዋን እናመሰግነዋለን። እኛ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተከልን እንዲሁም ውኃ ያጠጣን ቢሆንም የሚያሳድገው ግን አምላክ ነው።—1 ቆሮንቶስ 3:6

ያለብኝ ችግር ያስገኘልኝ ጥቅም

ምንም እንኳ ዲስሌክሲያ አንዳንድ እንቅፋቶች ቢፈጥርብኝም ያስገኘልኝ ጥቅምም አለ። እንዲህ የምለው ለምንድን ነው? ለምሳሌ ያህል በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ንግግር ስሰጥ የያዝኩትን ማስታወሻ ብዙም ስለማልመለከት አድማጮቼን እያየሁ ለመናገር አስችሎኛል። በተጨማሪም ለማስታወስ ቀላል የሆኑ ምሳሌዎችን እንድጠቀም ረድቶኛል። በመሆኑም ያለብኝ ችግር በአንዳንድ የንግግር ባሕርይዎች ረገድ የማስተማር ችሎታዬን እንዳሳድግ ረድቶኛል።

ክርስቲያን የሆነው ሐዋርያው ጳውሎስ አምላክ “ብርቱውንም ነገር ያሳፍር ዘንድ የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ” በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 1:27) ያለብኝ የጤና ችግር በአንዳንድ መንገዶች “ደካማ ነገር” እንድሆን አድርጎኛል። እኔም ሆንኩ ሌሎች ብዙ ሰዎች ይሖዋ ያለብንን ማንኛውንም ጉደለት እንደሚሸፍንልን ተገንዝበናል። ከእኛ የሚጠበቀው ነገር ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦችን ማውጣት፣ ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ምክንያታዊ መሆን፣ የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ለማግኘት መጸለይ እንዲሁም ማከናወን የምንፈልገውን ለመፈጸም ጥረት ማድረግ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.18 ወንድም ማይካልና ባለቤቱ ለስድስት ዓመት በላትቪያ ካገለገሉ በኋላ በአሁኑ ወቅት በጋና በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ስለ ዲስሌክሲያ ይህን ታውቅ ኖሯል?

ዲስሌክሲያ ምንድን ነው? “ዲስሌክሲያ” የሚለው ቃል የተገኘው ከግሪክኛ ሲሆን “መንተባተብ” የሚል ትርጉም አለው። ዲስሌክሲያ አንድ ሰው የትኛውንም ዓይነት ቋንቋ ለመማር ከሚያደርገው ጥረት በተለይም ከማንበብ ጋር በተያያዘ ዕድሜ ልክ የማይተው እክል ነው። ዲስሌክሲያ ያለባቸው ሰዎች በሆሄያትና ሆሄያቱ ባላቸው ድምፅ መካከል ያለውን ግንኙነት መረዳት ይከብዳቸዋል። ይሁንና የዚህ ችግር አንዳንድ ምልክቶች ከሰው ወደ ሰው ሊለያዩ ይችላሉ።

የዲስሌክሲያ መንስኤ ምንድን ነው? ይህ ችግር በዘር የሚተላለፍ ቢሆንም እንኳ ትክክለኛ መንስኤው በውል አይታወቅም። ምንም እንኳ ዲስሌክሲያ ትክክለኛ ያልሆነ የአንጎል እድገትና የአእምሮ አሠራር መዛባት እንደሆነ ጥናቶች ቢያመለክቱም ይህ ችግር ከማሰብ ችሎታ ወይም የመማር ፍላጎት ከማጣት ጋር የሚያያዝ አይደለም። እንዲያውም ይህ ችግር ያለባቸው ሰዎች ከፍተኛ የቋንቋ ችሎታ በማይጠይቁ ሥራዎች ረገድ የተዋጣላቸው ናቸው።

ዲስሌክሲያ በሕክምና ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው? ይህ ችግር ያለበት ሰው ችግሩ ቶሎ ከታወቀለት ጥሩ ነው። አንድ ሰው የቋንቋ ችሎታውን እንዲያሻሻል ለመርዳት የሚሰጠው ሥልጠና ውጤታማ እንዲሆን የስሜት ሕዋሳትን በተለይም መስማትን፣ ማየትንና መዳሰስን ማካተት ይኖርበታል። በመሆኑም እያንዳንዱ ተማሪ በራሱ የመረዳት ችሎታ መጠን እድገት እንዲያደርግ ከተፈለገ በግል እርዳታ ሊሰጠው ይገባል። ይህ ችግር ያለባቸው ልጆች በትምህርት ቤት ከሚያጋጥማቸው ስሜታቸውን የሚጎዳ ሁኔታ ጋር በተያያዘ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ዲስሌክሲያ ያለባቸው ተማሪዎች ጥሩ ሥልጠና ከተሰጣቸው እንዲሁም ጥረት ከተደረገላቸው በደንብ ማንበብና መጻፍ ሊማሩ ይችላሉ። *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.31 ከላይ የቀረበው ሐሳብ ከኢንተርናሽናል ዲስሌክሲያ አሶሴሽን በተገኘው መረጃ ላይ የተመሠረተ ነው። በተጨማሪም በጥር 2009 ንቁ! መጽሔት ላይ “ትምህርት የመቀበል ችግር ያለባቸውን ልጆች መርዳት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስሪላንካ ውስጥ ከአንድ ወንድም ጋር

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በላትቪያ ከካሚላ ጋር