በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትንሿ ሮዝ መጽሐፌ

ትንሿ ሮዝ መጽሐፌ

ትንሿ ሮዝ መጽሐፌ

ሲንቲያ ኑኤል እንደተናገረችው

የሰባት ዓመት ልጅ ሳለሁ ወደ ትምህርት ቤት በሚወስደን አውቶቡስ ላይ አብራኝ የምትጓዝ አንዲት ልጅ ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥ የሚል ርዕስ ያላት ትንሽ ሮዝ መጽሐፍ አሳየችኝ። ልጅቷ መጽሐፏን 50 ሳንቲም ከፍዬ ልወስዳት እንደምችል ነገረችኝ። በመሆኑም አብረን ወደ ቤት ሄድንና 50 ሳንቲሙን ሰጠኋት። በወቅቱ የምንኖረው በሽሪቭፖርት፣ ሉዊዚያና፣ ዩናይትድ ስቴትስ ነበር።

ሮዝ ቀለም ያላትን ያችን ትንሽ መጽሐፍ በጣም እወዳት ነበር። መጽሐፏን ካገኘሁ ብዙም ሳይቆይ ታምሜ ሆስፒታል ገባሁ። ቤተሰቦቼ እኔን ለማበረታታት ሲሉ ያችን የምወዳትን መጽሐፍ ያነቡልኝ ነበር። መጽሐፏ በዋነኝነት የተዘጋጀችው ለልጆች በመሆኑ እያደግኩ ስሄድ እንደቀድሞው አዘውትሬ ማንበቤን ተውኩ። ከመጽሐፏ ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶችን ብቀስምም ጥልቀት ያለው እውቀት ማግኘት እፈልግ ነበር። በአእምሮዬ ለሚመላለሱት ጥያቄዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ መልሶችን ለማግኘት ስል በየሳምንቱ ወደተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖች ለመሄድ ወሰንኩ። ይሁን እንጂ አጥጋቢ መልስ ማግኘት አልቻልኩም።

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስገባ ለሃይማኖት ግድ የለሽ ሆንኩ፤ ያም ቢሆን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ እጓጓ የነበረ ከመሆኑም በላይ መጽሐፍ ቅዱሴን አዘውትሬ አነብብ ነበር። አንድ ቀን አብራኝ የምትማር አንዲት ልጅ አገራችንን በታማኝነት እንደምንደግፍ በምንገልጽበት ሥነ ሥርዓት ላይ እንደማትካፈል አስተዋልኩ። ስለ ሁኔታው ስጠይቃት እንዲህ አለችኝ፦ “ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ቃል ገብቻለሁ፤ ታዲያ ለሁለት ነገሮች ማለትም ለአምላክ እና ለሰንደቅ ዓላማው እንዴት ታማኝ መሆን እችላለሁ?” የሰጠችኝ መልስ ምክንያታዊ እንደሆነ ተሰማኝ። ‘ይሁንና ይሖዋ ማን ነው?’ በማለት አሰብኩ።

ልጅቷ ላነሳኋቸው ጥያቄዎች በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ እያወጣች መልስ ሰጠችኝ። ‘ይህን ሁሉ እንዴት አወቀች? እኩያሞች ብንሆንም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ነገር ታውቃለች!’ ብዬ አሰብኩ። እሷም “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የተማርኩት በመንግሥት አዳራሽ ነው” አለችኝ። እሁድ በሚደረገው ስብሰባ ላይ እንድገኝ ያቀረበችልኝን ግብዣ በደስታ ተቀበልኩ። በከተማ ውስጥ ያሉትን ቤተ ክርስቲያኖች ሁሉ ያዳረስኩ ቢሆንም የይሖዋ ምሥክሮችን የመንግሥት አዳራሽ ግን አላውቀውም ነበር። የዚያን ዕለት ስብሰባ ላይ ስገኝ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ትምህርት የሚሰጥበትን ቦታ እንዳገኘሁ ተገነዘብኩ።

ስብሰባው ካለቀ በኋላ ጽሑፎች ወደተደረደሩበት ቦታ ስሄድ ከላይ ከተቀመጡት ጽሑፎች መካከል ትንሿን ሮዝ መጽሐፌን አየኋት! ትንሿ ልጅ ይህችን መጽሐፍ ከሰጠችኝ አሥር ዓመት አልፎ ስለነበር መጽሐፉን ማን እንደሰጠኝ እንኳ ረስቼው ነበር። አሁን ግን ሁኔታው ሁሉ ትዝ አለኝ፤ መጽሐፉን የሰጠችኝ ወደዚህ ስብሰባ የጋበዘችኝ ልጅ ራሷ ናት! ልጅቷ ናንሲ ትባላለች።

ከዚያ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በየሳምንቱ ማጥናት የጀመርኩ ሲሆን ፈጣን እድገት አደረግኩ። ከትንሿ መጽሐፌ ብዙ ነገር ስለተማርኩ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የማጠናውን ነገር ለመረዳት ብዙ ጊዜ አልወሰደብኝም። ብዙም ሳይቆይ ራሴን ለይሖዋ ወሰንኩና በ1985 በ18 ዓመቴ ተጠመቅኩ። በዚህ መሃል ናንሲ ወደ ፍሎሪዳ ስለተዛወረች ተጠፋፋን።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ ትዳር መሠረትኩ። በ1991 እኔና ባለቤቴ ድሩ በምሥራቅ ቴክሳስ በምትገኝ አንዲት አነስተኛ ከተማ ውስጥ አቅኚዎች ሆነን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ጀመርን። ናንሲስ የት ደርሳ ይሆን? ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም። አንድ ምሽት የታኅሣሥ 1, 1992 መጠበቂያ ግንብ ሳነብ “ናንሲን አገኘኋት! ናንሲን አገኘኋት!” ብዬ በደስታ ጮኽኩ። በቅርቡ የተመረቁትን የጊልያድ ተማሪዎች በሚያሳየው ፎቶግራፍ ላይ እሷም ነበረች። ናንሲና ባለቤቷ ኒክ ሳይሞኔሊ በደቡብ አሜሪካ በምትገኘው በኢኳዶር እንዲያገለግሉ ተመድበው ነበር።

በ2006 እኔና ባለቤቴ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያከናውኗቸው ዓለም አቀፍ የግንባታ ሥራዎች ላይ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነን ለማገልገል አመለከትን። የመጀመሪያ ምድባችን በኢኳዶር የሚገኘውን ቅርንጫፍ ቢሮ በማስፋቱ ሥራ መካፈል እንደሆነ ስናውቅ ምን ያህል እንደተደሰትን መገመት አያዳግትም! በኢኳዶር ቅርንጫፍ ቢሮ በደረስንበት ቀን ናንሲን አገኘኋት! በዚያ ዕለት በአጋጣሚ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው መጥታ ነበር። ተቃቅፈን ሰላም ተባባልን፤ ይህ የሆነው ትንሿን መጽሐፍ ከሰጠችኝ ከ32 ዓመታት በኋላ ነበር! ያችን መጽሐፍ በማግኘቴ ይሖዋንም ሆነ መጽሐፏን የሰጠችኝን ትንሿን ልጅ በጣም አመሰግናቸዋለሁ!

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ለውጠዋል

ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥ የተባለው መጽሐፍ ከታተመ ከ32 ዓመታት በኋላ መጽሐፉ በ2003 ተሻሽሎ በድጋሚ ወጣ። አዲሱ መጽሐፍ ከታላቁ አስተማሪ ተማር የሚል ርዕስ አለው። ኢየሱስ ስላስተማራቸው ነገሮች የሚናገሩት እነዚህ ሁለት መጻሕፍት እስከዛሬ ድረስ በአጠቃላይ ከ65 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ ቅጂዎችና ከ100 በሚበልጡ ቋንቋዎች ታትመዋል። ከታላቁ አስተማሪ ተማር የተባለውን መጽሐፍ በአካባቢህ ከሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች ማግኘት ትችላለህ።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ትናንሾቹ ፎቶዎች፦ ልጆች እያለን

ሲንቲያ

ናንሲ

ትልቁ ፎቶ፦ ከዓመታት በኋላ በኢኳዶር ቅርንጫፍ ቢሮ