በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስከሬን ማቃጠል ተገቢ እንዳልሆነ ይሰማሃል?

አስከሬን ማቃጠል ተገቢ እንዳልሆነ ይሰማሃል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አስከሬን ማቃጠል ተገቢ እንዳልሆነ ይሰማሃል?

አንዳንድ ሰዎች፣ አስከሬን ማቃጠል ለሟቹ አካል አክብሮት አለማሳየት ከመሆኑም ሌላ የሞተው ሰው ጨርሶ እንዳይታወስ ያደርጋል ብለው ያስባሉ። ‘ይህ ልማድ ከአረማውያን የመጣ ስለሆነ አምላክን እናመልካለን የሚሉ ሰዎች እንዲህ ማድረግ የለባቸውም’ በማለት ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ አስከሬን ማቃጠል ተቀባይነት ያለው እንደሆነና የሟቹንም ክብር ዝቅ እንደማያደርግ ያምናሉ። አንተስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማሃል?

በጥንት ዘመን፣ የሞቱ ሰዎችን መቅበር የተለመደ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አብርሃም ሚስቱ ሣራ ስትሞት ዋሻ ውስጥ ቀብሯታል። በተጨማሪም የኢየሱስ አስከሬን ያረፈው ከዐለት ተፈልፍሎ በተሠራ መቃብር ውስጥ ነበር። (ዘፍጥረት 23:9፤ ማቴዎስ 27:60) ይሁን እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ሲታይ የሰዎችን አስከሬን ከመቅበር ውጪ ተቀባይነት ያለው ሌላ ምንም መንገድ የለም ማለት ነው? የጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች፣ የሞቱ ሰዎችን መቅበራቸው አስከሬንን ማቃጠል ተገቢ እንዳልሆነ ይሰማቸው እንደነበር ይጠቁማል?

መለኮታዊ ተቀባይነት አለማግኘትን የሚጠቁም ነው?

አንዳንድ ጥቅሶች፣ ጠለቅ ብለን ካልመረመርናቸው በጥንት ዘመን አስከሬናቸው የተቃጠለው የአምላክን ሞገስ ያጡ ሰዎች ብቻ እንደሆኑ የሚጠቁሙ ሊመስሉ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋን ከሚያገለግሉ ካህናት መካከል አንዱ ሴት ልጁ ዝሙት አዳሪ ብትሆን መገደልና አስከሬኗ ‘በእሳት መቃጠል’ እንዳለበት የሙሴ ሕግ ያዝ ነበር። (ዘሌዋውያን 20:10፤ 21:9) አካንና ቤተሰቡ ታዛዥ ሳይሆኑ መቅረታቸው እስራኤላውያን በጋይ በተደረገው ጦርነት እንዲሸነፉ ምክንያት ሆኖ ነበር፤ በመሆኑም እስራኤላውያን አካንንና ቤተሰቡን በድንጋይ ወግረው ከገደሏቸው በኋላ “በእሳት አቃጠሏቸው።” (ኢያሱ 7:25) አንዳንድ ምሁራን፣ አሳፋሪ ድርጊት የፈጸሙ ሰዎች አስከሬን ይቃጠል እንደነበር ይናገራሉ፤ በመሆኑም ክፉ ሰዎች በብዙዎች ዘንድ ክብር እንዳለው ተደርጎ በሚታሰበው መንገድ አይቀበሩም ነበር የሚል ሐሳብ ይሰነዝራሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ንጉሥ ኢዮስያስ፣ ይሁዳን ከጣዖት አምልኮ ለማጽዳት እርምጃ በወሰደበት ወቅት ለበኣል ይሠዉ የነበሩትን ካህናት አጥንት ከመቃብር አውጥቶ በመሠዊያዎቻቸው ላይ አቃጥሎ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 34:4, 5) ታዲያ እነዚህ ታሪኮች የአምላክን ሞገስ ያጡ ሰዎች አስከሬን መቃጠል እንዳለበት የሚጠቁሙ ናቸው? አይደሉም፤ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይህን ያረጋግጥልናል።

ፍልስጥኤማውያን የእስራኤል ንጉሥ የነበረውን ሳኦልን በውጊያ ድል ባደረጉበት ወቅት የእሱንና የሦስት ወንዶች ልጆቹን አስከሬን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በቤትሳን ግንብ ላይ አንጠልጥለውት ነበር። ይሁንና በኢያቢስ ገለዓድ የሚኖሩ እስራኤላውያን በሳኦልና በልጆቹ ላይ የተደረገውን መጥፎ ነገር በሰሙ ጊዜ አስከሬኖቹን ከግንቡ ላይ አውርደው አቃጠሏቸው፤ ከዚያም አጥንቶቹን ቀበሯቸው። (1 ሳሙኤል 31:2, 8-13) ይህን ዘገባ እንዲሁ ላይ ላዩን ካየነው የመጥፎ ሰዎችን አስከሬን ማቃጠል ተገቢ እንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃ ሊመስል ይችላል። ደግሞም ሳኦል፣ ይሖዋ የቀባውን ዳዊትን ያሳደደና የአምላክን ሞገስ አጥቶ የሞተ ክፉ ሰው ነበር።

ይሁን እንጂ ከሳኦል ጋር ከተገደሉትና አስከሬናቸው በግንብ ላይ ከተሰቀለው ልጆቹ መካከል ዮናታንም እንደሚገኝበት ልብ በል። ዮናታን መጥፎ ሰው አልነበረም። እንዲያውም የዳዊት የቅርብ ወዳጅና ረዳት ነበር። ከዚህም ሌላ እስራኤላውያን፣ ዮናታን ነገሮችን ‘የሚያደርገው በአምላክ እርዳታ’ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። (1 ሳሙኤል 14:45) ዳዊት የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ያደረጉትን ሲሰማ ‘በእንዲህ ዐይነት ሁኔታ ለጌታችሁ ለሳኦል በጎነት አሳይታችኋልና ይሖዋ ይባርካችሁ’ በማለት ላከናወኑት ነገር አመስግኗቸዋል። ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የሳኦልና የዮናታን አስከሬን መቃጠል ዳዊትን እንዲያዝን አላደረገውም።—2 ሳሙኤል 2:4-6

ለትንሣኤ እንቅፋት አይፈጥርም

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ አምላክ በአሁኑ ጊዜ በሞት ያንቀላፉ በርካታ ሰዎችን መልሶ እንደሚያስነሳቸው በግልጽ ይናገራል። (መክብብ 9:5, 10፤ ዮሐንስ 5:28, 29) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ፣ ሙታን የሚነሱበትን ጊዜ አስመልክቶ ሲናገር “ባሕርም በውስጡ ያሉትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና ሔዲስም በውስጣቸው ያሉትን ሙታን ሰጡ” ይላል። (ራእይ 20:13) አንድ ሰው ቢቀበር፣ ቢቃጠል፣ ባሕር ውስጥ ሰምጦ ቢሞት አሊያም የዱር አራዊት ቢበላው ሌላው ቀርቶ በአቶሚክ ቦንብ ፍንዳታ አማካኝነት ቢተን እንኳ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በትንሣኤ እንዳያስነሳው እንቅፋት አይሆንበትም።

መጽሐፍ ቅዱስ አስከሬን ምን መደረግ እንዳለበት ግልጽ መመሪያ አይሰጥም። ይሖዋ አስከሬን ማቃጠልን አያወግዝም። ሆኖም የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ክብር የተላበሱ መሆን እንዳለባቸው ግልጽ ነው።

አንድ ሰው የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዴት መካሄድ እንዳለበት ለመወሰን የአካባቢው ሰዎች ለቀብር ሥነ ሥርዓት ያላቸውን አመለካከት ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚከተሉ ሰዎች በዚህ ረገድ የአካባቢያቸውን ነዋሪዎች ቅር ሊያሰኝ የሚችል ምንም ነገር ማድረግ እንደማይፈልጉ ጥርጥር የለውም። ነፍስ አትሞትም እንደሚሉት ባሉ የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች የምናምን በሚያስመስሉ አንዳንድ ድርጊቶች መካፈልም ተገቢ አይደለም። ያም ሆነ ይህ አንድ ሰው ራሱም ሆነ ሌላ ሰው ሲሞት አስከሬኑ ምን መደረግ እንዳለበት መወሰን የራሱ የግለሰቡ ወይም የቤተሰቡ ኃላፊነት ነው።

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስከሬኑ እንደተቃጠለ የተጠቀሰው ታማኝ አገልጋይ ማን ነው?—1 ሳሙኤል 31:2, 12

▪ ዳዊት የሳኦልን አስከሬን ስላቃጠሉት ሰዎች ምን ተሰምቶት ነበር?—2 ሳሙኤል 2:4-6

▪ አንድ ሰው አስከሬኑ መቃጠሉ ትንሣኤ እንዳያገኝ እንቅፋት እንደማይሆንበት የሚያሳየው ምንድን ነው?—ራእይ 20:13

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

መጽሐፍ ቅዱስ አስከሬን ምን መደረግ እንዳለበት ግልጽ መመሪያ አይሰጥም