የተሻሉ ጓደኞች ያስፈልጉኝ ይሆን?
የወጣቶች ጥያቄ
የተሻሉ ጓደኞች ያስፈልጉኝ ይሆን?
“ስናደድ ስሜቴን አውጥቼ የምነግረው ሰው እፈልጋለሁ። ሳዝን የሚያጽናናኝ ሰው እፈልጋለሁ። ስደሰት ደግሞ ደስታዬን የማካፍለው ሰው እፈልጋለሁ። እኔ ያለ ጓደኛ መኖር አልችልም።”—ብሪተኒ
ትንንሽ ልጆች አብረዋቸው የሚጫወቱ ልጆች፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ደግሞ ጓደኞች እንደሚያስፈልጓቸው ይነገራል። ልዩነቱ ምንድን ነው?
አብሮህ የሚጫወት ልጅ ሲባል አብሮህ ጊዜ የሚያሳልፍ ማለት ነው።
ጓደኛ ሲባል ግን የአንተ ዓይነት የሥነ ምግባር አቋም ያለው ሰው ማለት ነው።
ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል” ይላል። (ምሳሌ 17:17) ይህ ዓይነቱ ጓደኝነት አብረህ ከምትጫወተው ልጅ ጋር ከሚኖርህ ቅርርብ ይበልጥ የጠነከረን ወዳጅነት የሚያመለክት ነው።
እውነታው፦ ዕድሜህ እየጨመረ ሲሄድ
(1) ጥሩ ባሕርያት ያሏቸው፣
(2) ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው የሚኖሩ እንዲሁም
(3) በአንተ ላይ ጥሩ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ጓደኞች ያስፈልጉሃል።
ጥያቄ፦ ጓደኞችህ እነዚህን ብቃቶች እንደሚያሟሉ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? እስቲ እነዚህን ነጥቦች አንድ በአንድ እንመልከት።
የመጀመሪያው ነጥብ—ጥሩ ባሕርያት
ልታውቀው የሚገባ ጉዳይ። ጓደኛ ነኝ የሚል ሁሉ እውነተኛ ጓደኛ ሊሆን አይችልም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ወዳጅነታቸው እንደሚፍረከረክ የሚያስታውቅ ጓደኛሞች አሉ” ይላል። (ምሳሌ 18:24 NW) በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው ሐሳብ በጣም የተጋነነ ሊመስል ይችላል። እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ቆም ብለህ አስብባቸው፦ መጠቀሚያ ሊያደርግህ የሞከረ “ጓደኛ” ኖሮህ ያውቃል? የሚያማህ ወይም ስለ አንተ የሐሰት ወሬ የሚያሰራጭ ጓደኛስ ነበረህ? እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ከነበረ በጓደኞችህ ላይ እምነት ለመጣል ትቸገር ይሆናል። * መጥፎ ባሕርይ ያላቸው ብዙ ጓደኞች ከሚኖሩህ ይልቅ ጥሩ ባሕርይ ያላቸው ጥቂት ጓደኞች ቢኖሩህ የተሻለ መሆኑን ሁልጊዜ አስታውስ።
ማድረግ የምትችለው ነገር። ልትኮርጀው የሚገባ ጥሩ ባሕርይ ያላቸውን ጓደኞች ምረጥ።
“ሁሉም ሰው ፋዮና ለተባለችው ጓደኛዬ ጥሩ አመለካከት አለው። ሰዎች ለእኔም ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው እፈልጋለሁ። የእሷ ዓይነት ስም ባተርፍ ደስ ይለኛል። ለእኔ ይህ ጥሩ ነገር ነው።”—የ17 ዓመቷ ኢቬት
ይህን ለማድረግ ሞክር።
1. ገላትያ 5:22, 23ን አንብብ።
2. ‘ጓደኞቼ “የመንፈስ ፍሬ” ገጽታዎች የሆኑትን ባሕርያት ያንጸባርቃሉ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።
3. በጣም የምትቀርባቸውን ጓደኞችህን ስም ከዚህ በታች ጻፍ። ከእያንዳንዱ ስም ጎን ግለሰቡን በተሻለ ሁኔታ ይገልጸዋል የምትለውን ባሕርይ ጥቀስ።
ስም ባሕርይ
․․․․․ ․․․․․
․․․․․ ․․․․․
․․․․․ ․․․․․
ፍንጭ፦ ስለ ጓደኞችህ ስታስብ ወደ አእምሮህ የሚመጣው መጥፎ ባሕርያቸው ብቻ ከሆነ የተሻሉ ጓደኞች መምረጥ ያስፈልግህ ይሆናል!
ሁለተኛው ነጥብ—ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ መኖር
ልታውቀው የሚገባ ጉዳይ። ጓደኞች ለማግኘት ከመጠን በላይ የምትጓጓ ከሆነ ከመጥፎ ጓደኞች ጋር የመወዳጀት አጋጣሚህ ሰፊ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል” ይላል። (ምሳሌ 13:20) “ተላሎች” ወይም ሞኞች የሚለው ቃል የማሰብ ችግር ያለባቸውን ሰዎች የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሚሰጣቸውን አሳማኝ የሆነ ምክር ችላ በማለት ከሥነ ምግባር አኳያ ማስተዋል የጎደለው አካሄድ የሚከተሉ ሰዎችን የሚያመለክት ነው፤ እንዲህ ያሉ ጓደኞች ደግሞ አያስፈልጉህም!
ማድረግ የምትችለው ነገር። የቀረበህን ሰው ሁሉ ጓደኛ ከማድረግ ይልቅ ሰው መለየት ይኖርብሃል። (መዝሙር 26:4) እንዲህ ሲባል ግን ጭፍን ጥላቻ ሊኖርህ ይገባል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሰውን መለየት ይኖርብሃል ሲባል “በጻድቁና በኀጢአተኛው መካከል፣ እግዚአብሔርን በሚያገለግለውና በማያገለግለው መካከል ያለውን ልዩነት” ማስተዋል መቻል አለብህ ማለት ነው።—ሚልክያስ 3:18
አምላክ አያዳላም፤ ሆኖም ‘በድንኳኑ ውስጥ’ በእንግድነት የሚቀበለው ሁሉንም ሰው አይደለም። (መዝሙር 15:1-5) አንተም እንዲህ ማድረግ ትችላለህ። አምላክ ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር ተስማምተህ የምትኖር ከሆነ እነዚህን መሥፈርቶች ለመከተል ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች ሊቀርቡህ ይችላሉ። የተሻሉ ጓደኞች ሊሆኑህ የሚችሉት ደግሞ እንዲህ ያሉ ሰዎች ናቸው!
“ወላጆቼ በእኔ የዕድሜ ክልል ያሉ ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ያላቸው ጓደኞች እንዳገኝ ስለረዱኝ አመሰግናቸዋለሁ።”—የ13 ዓመቱ ክሪስተፈር
ይህን ለማድረግ ሞክር።
ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ስጥ፦
▪ ከጓደኞቼ ጋር ስሆን ትክክል እንዳልሆነ የማውቀውን ነገር
እንድፈጽም ተጽዕኖ ሊያሳድሩብኝ ይችላሉ ብዬ እጨነቃለሁ?□ አዎ □ አልጨነቅም
▪ ወላጆቼ በጓደኛ ምርጫዬ ላይስማሙ ይችሉ ይሆናል በሚል ፍራቻ ጓደኞቼን ለእነሱ ከማስተዋወቅ ወደኋላ እላለሁ?
□ አዎ □ ወደኋላ አልልም
ፍንጭ፦ ከላይ ላሉት ጥያቄዎች አዎ የሚል መልስ ከሰጠህ ላቅ ያሉ መሥፈርቶችን የሚከተሉ ጓደኞች መፈለግ ይኖርብሃል ማለት ነው። በዕድሜ ከአንተ ትንሽ ከፍ ከሚሉና በክርስቲያናዊ አኗኗራቸው ጥሩ ምሳሌ ከሚሆኑ ሰዎች ጋር ለምን ጓደኝነት አትጀምርም?
ሦስተኛው ነጥብ—ጥሩ ተጽዕኖ
ልታውቀው የሚገባ ጉዳይ። መጽሐፍ ቅዱስ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል” በማለት ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ሎረን የተባለች ወጣት እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “አብረውኝ የሚማሩ ልጆች እንደ ጓደኛቸው አድርገው የሚያዩኝ እነሱ የሚሉትን እስካደረግኩ ድረስ ብቻ ነው። ብቸኝነት ይሰማኝ ስለነበር በእነሱ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ስል እነሱ የሚያደርጉትን ነገር ማድረግ ጀመርኩ።” ሎረን መገንዘብ እንደቻለችው አንተም ከሌሎች ሰዎች መሥፈርቶች ጋር ተስማምተህ ለመኖር የምትሞክር ከሆነ በቼዝ መጫወቻ ላይ እንዳለ ወታደር እንደፈለጉ ያሽከረክሩሃል። ሆኖም ይህ ሊሆን አይገባም!
ማድረግ የምትችለው ነገር። የእነሱን የአኗኗር ዘይቤ እንድትከተል ተጽዕኖ ከሚያሳድሩብህ ሰዎች ጋር ያለህን ግንኙነት ማቆም ይኖርብሃል። ይህን እርምጃ ከወሰድክ ስለ ራስህ ጥሩ አመለካከት የሚኖርህ ከመሆኑም ሌላ ጥሩ ተጽዕኖ ሊያሳድርብህ የሚችል የተሻለ ጓደኝነት ለመመሥረት የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍትልሃል።—ሮም 12:2
“የቅርብ ጓደኛዬ የሆነው ክሊንት ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያለው ከመሆኑም በተጨማሪ የሌሎችን ስሜት ይረዳል፤ በመሆኑም ጥሩ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል።”—የ21 ዓመቱ ጄሰን
ይህን ለማድረግ ሞክር።
የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራስህን ጠይቅ፦
▪ ጓደኞቼን ለማስደሰት ስል በአለባበሴ፣ በአነጋገሬ አሊያም በማደርገው ነገር እነሱን ለመምሰል እሞክራለሁ?
□ አዎ □ አልሞክርም
▪ ለጓደኞቼ ስል ብቻ በሥነ ምግባር አጠያያቂ ወደሆኑ ቦታዎች እሄዳለሁ?
□ አዎ □ አልሄድም
ፍንጭ፦ ከላይ ላሉት ጥያቄዎች አዎ የሚል መልስ ከሰጠህ ከወላጆችህ ወይም ከጎለመሰ ሰው ምክር ለማግኘት ሞክር። የይሖዋ ምሥክር ከሆንክ ደግሞ ወደ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ቀርበህ ጥሩ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብህ የሚችሉ ጓደኞችን በመምረጥ ረገድ እንዲረዳህ ልትጠይቀው ትችላለህ።
www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.14 እርግጥ ነው፣ ሁሉም ሰው ስህተት ይሠራል። (ሮም 3:23) ስለሆነም ጓደኛህ ቢያስቀይምህና ባደረገው ነገር ተጸጽቶ ከልቡ ይቅርታ ቢጠይቅህ “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል” የሚለውን ጥቅስ አስታውስ።–1 ጴጥሮስ 4:8
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
▪ ጓደኛ እንዲሆንህ የምትፈልገው ሰው ይበልጥ እንዲኖረው የምትፈልገው ባሕርይ የትኛው ነው? ለምንስ?
▪ የተሻልክ ጓደኛ መሆን እንድትችል የትኞቹን ባሕርያት ማዳበር ይኖርብሃል?
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
እኩዮችህ ምን ይላሉ?
“ወላጆቼ ከአንዳንድ ጓደኞቼ እንድርቅ ሲነግሩኝ መቀራረብ የምፈልገው ከእነሱ ጋር ብቻ ነው ብዬ አስቤ ነበር። ሆኖም እነሱ የሰጡኝ ምክር ጠቃሚ ነበር፤ የሰጡኝን ምክር በጥሞና ሳስብበት በርካታ የተሻሉ ጓደኞች እንዳሉ ተገነዘብኩ።”—ኮል
“በክርስቲያናዊ አገልግሎት መካፈሌ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ለማወቅ የሚያስችል የተሻለ አጋጣሚ ፈጥሮልኛል። በዚህ መንገድ ወጣቶችንም ሆነ ትልልቅ ሰዎችን ጨምሮ ከተለያዩ ሰዎች ጋር መቀራረብ ችያለሁ። ከዚህም በተጨማሪ ጊዜዬን የማሳልፈው ይሖዋን ከሚወዱ ሰዎች ጋር ነው።”—ኢቬት
“ጓደኞች ለማግኘት እጸልይ የነበረ ቢሆንም በበኩሌ ምንም ያደረግኩት ጥረት እንደሌለ ተገነዘብኩ። በመሆኑም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ራሴ ቅድሚያውን በመውሰድ ሰዎችን ለመቅረብ ጥረት ማድረግ ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ በርካታ አዳዲስ ጓደኞች አገኘሁ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ብቸኝነት ተሰምቶኝ አያውቅም ማለት እችላለሁ።”—ሳም
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የሚከተሉትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር
ጓደኝነትን በተመለከተ ወላጆችህን አማክራቸው። ወላጆችህ በአንተ ዕድሜ በነበሩበት ወቅት ምን ዓይነት ጓደኞች እንደነበሯቸው ጠይቃቸው። ለጓደኝነት የመረጧቸውን ሰዎች በተመለከተ የሚቆጩበት ነገር አለ? ካለ የሚቆጩት ለምንድን ነው? እነሱ የገጠሟቸው አንዳንድ ችግሮች አንተም ላይ እንዳይደርሱ ምን ማድረግ እንደምትችል ጠይቃቸው።
ጓደኞችህን ከወላጆችህ ጋር አስተዋውቃቸው። ይህን ለማድረግ የምታመነታ ከሆነ ‘እንዲህ ማድረግ የከበደኝ ለምንድን ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ጓደኞችህ በሚያደርጓቸው አንዳንድ ነገሮች ወላጆችህ እንደማይደሰቱ ይሰማሃል? ከሆነ ጓደኞች በመምረጥ ረገድ ይበልጥ ጠንቃቃ መሆን ሊያስፈልግህ ይችላል።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ጥሩ ከሆኑ ጓደኞችህ ጋር የመሠረትከው ወዳጅነት ዘላቂ እንዲሆን የሚረዱ ሦስት መንገዶች
▪ ጥሩ አድማጭ ሁን። ጓደኞችህ ለሚያሳስቧቸውና ለሚያስጨንቋቸው ጉዳዮች ትኩረት ስጥ።—ፊልጵስዩስ 2:4
▪ ይቅር ባይ ሁን። ከጓደኞችህ ፍጽምና አትጠብቅ። “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን።”—ያዕቆብ 3:2
▪ መፈናፈኛ አታሳጣቸው። ጓደኞችህ ላይ ሙጭጭ ማለት ተገቢ አይደለም። እውነተኛ ጓደኞች በምትፈልጋቸው ጊዜ ሁሉ ከጎንህ ይሆናሉ።—መክብብ 4:9, 10
[በገጽ 18 እና 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሌሎች ሰዎች መሥፈርቶች ጋር ተስማምተህ ለመኖር የምትሞክር ከሆነ በቼዝ መጫወቻ ላይ እንዳለ ወታደር እንደፈለጉ ያሽከረክሩሃል