በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

ብዙ ሰዎች፣ የትዳር ጓደኛሞች በጾታ ግንኙነት ረገድ አንዳቸው ለሌላው ታማኝ መሆን እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። ይህ አመለካከት “ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር፣ መኝታውም ከርኩሰት የጸዳ ይሁን” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር ይስማማል።—ዕብራውያን 13:4

ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆን ሲባል ከትዳር ጓደኛ ውጭ የጾታ ግንኙነት አለመፈጸምን ብቻ የሚያመለክት ነው? የትዳር ጓደኛህ ካልሆነ ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት ስለ መፈጸም ማውጠንጠንን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ከተቃራኒ ጾታ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት “ታማኝነት ማጉደል” እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል?

ስለ ጾታ ግንኙነት ማውጠንጠን ስህተት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ በተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸም የጾታ ግንኙነት ተፈጥሯዊና ምንም ስህተት እንደሌለው ብሎም ለባልም ሆነ ለሚስት ደስታና እርካታ እንደሚያስገኝ ይገልጻል። (ምሳሌ 5:18, 19) ይሁንና በዘመናችን ያሉ በርካታ ምሁራን፣ የተጋቡ ሰዎች የትዳር ጓደኛቸው ካልሆነ ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት ስለ መፈጸም ማውጠንጠናቸው ተቀባይነት ያለውና ምንም ችግር የሌለው ድርጊት መሆኑን ያምናሉ። ታዲያ አንድ ሰው የጾታ ግንኙነት እስካልፈጸመ ድረስ ስለዚህ ጉዳይ ማውጠንጠኑ ምንም ስህተት የለውም ማለት ነው?

ስለ ጾታ ግንኙነት ማውጠንጠን በዋነኝነት ያተኮረው የራስን ደስታ በማርካት ላይ ነው። ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት እንዲህ ያለው ባሕርይ መጽሐፍ ቅዱስ ለተጋቡ ሰዎች ከሚሰጠው ምክር ጋር ይቃረናል። የአምላክ ቃል የጾታ ግንኙነትን በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “ሚስት በራሷ አካል ላይ ሥልጣን የላትም፤ ሥልጣን ያለው ባሏ ነው፤ በተመሳሳይም ባል በራሱ አካል ላይ ሥልጣን የለውም፤ ሥልጣን ያላት ሚስቱ ናት።” (1 ቆሮንቶስ 7:4) አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መከተሉ፣ ስለ ጾታ ግንኙነት በማውጠንጠን በራስ ወዳድነት ስሜት ተነሳስቶ ፍላጎቱን ለማርካት ከማሰብ እንዲቆጠብ ያደርገዋል። ይህም ለሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ከፍተኛ ደስታ ያስገኝላቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35፤ ፊልጵስዩስ 2:4

የትዳር ጓደኛ ካልሆነ ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት ስለ መፈጸም ማውጠንጠን የሌላውን የትዳር አጋር ስሜት በእጅጉ የሚጎዳ ነገር ለማድረግ መዘጋጀት ማለት ነው። አንድ ሰው ስለ ጾታ ግንኙነት ማውጠንጠኑ ምንዝር ወደ መፈጸም ሊመራው ይችላል? በአጭሩ መልሱ አዎን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ነገር በማሰብና በማድረግ መካከል ያለውን ግንኙነት ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል። ከዚያም ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች።”—ያዕቆብ 1:14, 15

ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የፆታ ስሜቱ እስኪቀሰቀስ ድረስ አንዲትን ሴት በምኞት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል።” (ማቴዎስ 5:28) ምንዝር የመፈጸምን ሐሳብ ከማውጠንጠን በመራቅ ‘ልብህን መጠበቅና’ ትዳርህን ከመፍረስ መታደግ ትችላለህ።—ምሳሌ 4:23

በስሜት ታማኝ መሆን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ትዳርህ የሰመረ እንዲሆን ለትዳር ጓደኛህ ‘ሙሉ በሙሉ ማደር’ ይኖርብሃል። (ማሕልየ መሓልይ 8:6 NW፤ ምሳሌ 5:15-18) ይህ ምን ማለት ነው? ከትዳር አጋርህ ውጭ የወንድና የሴት ወዳጆች ሊኖሩህ ቢችሉም በዋነኝነት ጊዜህንና ትኩረትህን መስጠት እንዲሁም የስሜት ድጋፍ ማድረግ ያለብህ ለትዳር ጓደኛህ ነው። ከአንድ ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት ባትፈጽምም እንኳ ለትዳር ጓደኛህ ብቻ የሚገባውን ነገር ለዚህ ሰው መስጠት “ታማኝነት ማጉደል” እንደሆነ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። *

እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊፈጠር የሚችለው እንዴት ነው? የትዳር ጓደኛህ ያልሆነ ሰው ከትዳር አጋርህ የበለጠ ማራኪ ወይም አሳቢ መስሎ ሊታይህ ይችላል። ከዚህ ግለሰብ ጋር በሥራ ቦታ ወይም በሌሎች አጋጣሚዎች አብረህ ጊዜ ማሳለፍህ በትዳርህ ውስጥ ያጋጠሙህን ችግሮች ወይም አሳዛኝ ሁኔታዎች ጨምሮ ሌሎች የግል ጉዳዮችን ለመጨዋወት አጋጣሚ ሊከፍት ይችላል። ይህ ደግሞ ስሜታዊ ድጋፍ ለማግኘት ስትል ሁልጊዜ ወደዚህ ግለሰብ እንድትሄድ ሊገፋፋህ ይችላል። ከግለሰቡ ጋር በአካል ተገናኝቶ ማውራት፣ በስልክ መነጋገር አሊያም በኢንተርኔት አማካኝነት መልእክት መለዋወጥ ሚስጥራዊ የሆኑ ጉዳዮችን ወደ መወያየት ሊመራህ ይችላል። ባልና ሚስት በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ መወያየት ያለባቸው ሁለቱ ብቻ እንደሆኑና የተነጋገሩባቸውን ‘ሚስጥራዊ’ ነገሮችም ሌላ ሰው መስማት እንደሌለበት ይሰማቸው ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ተገቢ ነው።—ምሳሌ 25:9

ለሌላ ሰው የፍቅር ስሜት አድሮብህ እያለ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ለማስመሰል ከመሞከር ተቆጠብ! ኤርምያስ 17:9 ‘የሰው ልብ ተንኰለኛ ነው’ ይላል። ከተቃራኒ ጾታ ጋር የተቀራረበ ግንኙነት ካለህ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ከዚህ ሰው ጋር ያለኝን ግንኙነት በተመለከተ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ለማስመሰል ሰበብ እደረድራለሁ? ሌላ ሰው ስለ ግንኙነታችን እንዳያውቅ ለማድረግስ እሞክራለሁ? ከዚህ ግለሰብ ጋር የማወራውን ነገር የትዳር ጓደኛዬ ቢያውቅ ምን ይሰማኛል? የትዳር ጓደኛዬ እንዲህ ዓይነት ጓደኝነት ቢመሠርት ምን ይሰማኛል?’—ማቴዎስ 7:12

ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተገቢ ያልሆነ ቅርርብ መመሥረት ትዳርን ሊያፈርስ ይችላል፤ ምክንያቱም ይህ ዓይነቱ ወዳጅነት ስሜታዊ ቅርርብ እንዲፈጠር ስለሚያደርግ ውሎ አድሮ የጾታ ግንኙነት ወደ መፈጸም ይመራል። ኢየሱስ ‘ምንዝር ከልብ ይወጣል’ በማለት አስጠንቅቆ ነበር። (ማቴዎስ 15:19) ምንዝር ወደ መፈጸም ደረጃ ባትደርስም እንኳ የትዳር ጓደኛህን አመኔታ መልሰህ ማግኘት በጣም ከባድ ነው። ካረን * የተባለች አንዲት ባለትዳር እንዲህ ብላለች፦ “ማርክ በየቀኑ በተደጋጋሚ ከአንዲት ሴት ጋር በድብቅ በስልክ እንደሚያወራ ሳውቅ ቅስሜ ተሰበረ። የጾታ ግንኙነት አልፈጸመም ብዬ ማመን ያዳግተኛል። ከአሁን በኋላ መቼም ቢሆን የማምነው አይመስለኝም።”

ተቃራኒ ጾታ ካላቸው ሰዎች ጋር ያለህ ግንኙነት ገደብ ልታበጅለት ይገባል። ተገቢ ያልሆነ ስሜት ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ ያለብህ ከመሆኑም ሌላ መጥፎ ዝንባሌዎችን ለመሸፋፈን ሰበብ አስባብ ማቅረብ አይኖርብህም። ከተቃራኒ ጾታ ጋር ያለህ ቅርርብ በትዳርህ ላይ ችግር እንደሚፈጥር ከተሰማህ ገደብ ለማበጀት ወይም ጨርሶ ለማቆም ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል” ይላል።—ምሳሌ 22:3

ትዳራችሁን ታደጉ

ፈጣሪያችን ጋብቻን ያቋቋመው በሁለት ሰዎች መካከል ከሚፈጠሩት ዝምድናዎች ሁሉ እጅግ የጠበቀ እንዲሆን አድርጎ ነው። አምላክ ባልና ሚስት “አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ብሏል። (ዘፍጥረት 2:24) አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለው አባባል ከጾታ ግንኙነት ያለፈ ወዳጅነትን ያመለክታል። ይህም የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ፣ እምነት በመጣልና እርስ በርስ በመከባበር ይበልጥ እየዳበረ የሚሄድ የተቀራረበ ስሜታዊ ትስስርን ይጨምራል። (ምሳሌ 31:11፤ ሚልክያስ 2:14, 15፤ ኤፌሶን 5:28, 33) እነዚህን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረግህ በአስተሳሰብም ሆነ በስሜት ለትዳር ጓደኛህ ታማኝ እንድትሆን የሚረዳህ ሲሆን ይህም ትዳርህን ከአደጋ ይጠብቀዋል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.11 ለመፋታት ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የሚሆነው የትዳር ጓደኛ ካልሆነ ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸም ብቻ እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባዋል።—ማቴዎስ 19:9

^ አን.14 ስሞቹ ተቀይረዋል።

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ ስለ ጾታ ግንኙነት ማውጠንጠን የጾታ ግንኙነት ወደ መፈጸም ሊመራ ይችላል?—ያዕቆብ 1:14, 15

▪ ከተቃራኒ ጾታ ጋር በጣም የተቀራረበ ወዳጅነት መመሥረት በትዳርህ ላይ ችግር ሊያስከትል ይችላል? —ኤርምያስ 17:9፤ ማቴዎስ 15:19

▪ የጋብቻ ጥምረታችሁን ለማጠናከር ምን ማድረግ ትችላለህ?—1 ቆሮንቶስ 7:4፤ 13:8፤ ኤፌሶን 5:28, 33

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የፆታ ስሜቱ እስኪቀሰቀስ ድረስ አንዲትን ሴት በምኞት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል።”—ማቴዎስ 5:28